የጥናት ርዕስ 46
አትፍራ፣ ይሖዋ ረዳትህ ነው
“ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።”—ዕብ. 13:5
መዝሙር 55 አትፍሯቸው!
ማስተዋወቂያa
1. ብቻችንን እንደሆንን ወይም ችግሮቻችን ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ ሲሰማን ምን ያጽናናናል? (መዝሙር 118:5-7)
ብቻህን እንደሆንክና በችግርህ ከጎንህ የሚቆም እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችን ጨምሮ ብዙዎች እንደዚያ ተሰምቷቸው ያውቃል። (1 ነገ. 19:14) እንዲህ ከተሰማህ ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባውን ቃል አስታውስ። እንግዲያው “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” ብለን በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን። (ዕብ. 13:5, 6) ይህ ሐሳብ ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ ላሉ የእምነት ባልንጀሮቹ በ61 ዓ.ም. ከጻፈው ደብዳቤ ላይ የተወሰደ ነው። ጥቅሱ በመዝሙር 118:5-7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያስታውሰናል።—ጥቅሱን አንብብ።
2. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን? ለምንስ?
2 እንደ መዝሙራዊው ሁሉ ጳውሎስም ይሖዋ ረዳቱ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ለምሳሌ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ከመጻፉ ከሁለት ዓመት በፊት፣ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ አደገኛ ጉዞ አድርጎ ነበር። (ሥራ 27:4, 15, 20) ይህን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ባለው ጊዜም ሆነ በጉዞው ወቅት ይሖዋ ጳውሎስን ለመርዳት በተለያዩ መንገዶች ተጠቅሟል። በዚህ ርዕስ ላይ ሦስቱን መንገዶች እንመለከታለን። ይሖዋ በኢየሱስና በመላእክቱ፣ በሥልጣን ላይ ባሉ ሰዎች እንዲሁም በእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት ጳውሎስን ረድቶታል። ጳውሎስ ያጋጠሙትን እነዚህን ሁኔታዎች መመርመራችን፣ አምላክ ለእርዳታ የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማ በገባው ቃል ላይ ይበልጥ እንድንተማመን ያደርጋል።
ከኢየሱስና ከመላእክት የሚገኝ እርዳታ
3. ጳውሎስ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል? ለምንስ?
3 ጳውሎስ እርዳታ ያስፈልገው ነበር። በ56 ዓ.ም. ገደማ ተቃዋሚዎቹ በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መቅደስ እየጎተቱ ካወጡት በኋላ ሊገድሉት ሞክረው ነበር። በቀጣዩ ቀን ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረበበት ወቅት ጠላቶቹ ሊገነጣጥሉት ደርሰው ነበር። (ሥራ 21:30-32፤ 22:30፤ 23:6-10) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘በዚህ ሁኔታ የምዘልቀው እስከ መቼ ድረስ ነው?’ የሚል ስሜት ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል።
4. ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው?
4 ጳውሎስ ምን እርዳታ አግኝቷል? ጳውሎስ ከተያዘ በኋላ ሌሊት ላይ “ጌታ” ማለትም ኢየሱስ አጠገቡ ቆሞ እንዲህ አለው፦ “አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።” (ሥራ 23:11) ጳውሎስ ይህን ሲሰማ እንዴት ተበረታቶ ይሆን! ኢየሱስ ጳውሎስን በኢየሩሳሌም ለሰጠው ምሥክርነት አመስግኖታል። ከዚያም በሰላም ሮም እንደሚደርስና በዚያ ተጨማሪ ምሥክርነት እንደሚሰጥ አረጋግጦለታል። ጳውሎስ ይህን ማረጋገጫ መስማቱ በአባቱ እቅፍ እንዳለ ልጅ የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርበት አድርጎ መሆን አለበት።
5. ይሖዋ በመልአክ ተጠቅሞ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)
5 ጳውሎስ ምን ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል? በኢየሩሳሌም ሁከት ከገጠመው ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በመርከብ ወደ ጣሊያን መጓዝ ጀመረ፤ ሆኖም በጉዞ ላይ ሳሉ ከባድ ማዕበል ስለገጠማቸው የመርከቡ ሠራተኞችም ሆኑ ተሳፋሪዎቹ በሕይወት የመትረፍ ተስፋቸው ተሟጥጦ ነበር። ጳውሎስ ግን አልፈራም። ለምን? በመርከብ አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትና ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል።” ይሖዋ ቀደም ሲል በኢየሱስ ተጠቅሞ ለጳውሎስ የሰጠውን ማረጋገጫ በዚህ ወቅት በመልአኩ አማካኝነት ደገመለት። ይሖዋ እንዳለውም ጳውሎስ በሰላም ሮም ደርሷል።—ሥራ 27:20-25፤ 28:16
6. ብርታት የሚሰጠን ኢየሱስ የገባው የትኛው ቃል ነው? ለምንስ?
6 እኛስ ምን እርዳታ እናገኛለን? ኢየሱስ ጳውሎስን እንደረዳው ሁሉ እኛንም ይደግፈናል። ለምሳሌ ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሙሉ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:20) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ የብርታት ምንጭ ይሆነናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለመቋቋም የሚከብድ ችግር የሚገጥመን ጊዜ አለ። ለምሳሌ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ሐዘኑ ለጥቂት ቀናት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት ሊቀጥል ይችላል። አንዳንዶች በእርጅና የተነሳ ከባድ ሁኔታ የሚገጥማቸው ጊዜ አለ። ሌሎች ደግሞ በመንፈስ ጭንቀት የሚዋጡበት ጊዜ ይኖራል። ሆኖም ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስጨናቂ ሁኔታ የገጠመንን ጊዜ ጨምሮ “ሁልጊዜ” አብሮን እንደሆነ እናውቃለን፤ ይህ ደግሞ ለመጽናት ብርታት ይሰጠናል።—ማቴ. 11:28-30
7. በራእይ 14:6 መሠረት ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት እንደሚረዳን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል። (ዕብ. 1:7, 14) ለምሳሌ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ’ ስንሰብክ መላእክት ይደግፉናል እንዲሁም ይመሩናል።—ማቴ. 24:13, 14፤ ራእይ 14:6ን አንብብ።
በሥልጣን ላይ ካሉ ሰዎች የሚገኝ እርዳታ
8. ይሖዋ በአንድ ሻለቃ አማካኝነት ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ ምን እርዳታ አግኝቷል? በ56 ዓ.ም. ኢየሱስ፣ በሰላም ሮም እንደሚደርስ ለጳውሎስ አረጋግጦለት ነበር። ሆኖም በኢየሩሳሌም ያሉ አንዳንድ አይሁዳውያን አድብተው በጳውሎስ ላይ ጥቃት ለመሰንዘርና እሱን ለመግደል አሲረው ነበር። የሮም ሠራዊት ሻለቃ የሆነው ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ሴራቸውን ሲሰማ ጳውሎስን ለማዳን እርምጃ ወሰደ። ቀላውዴዎስ ወዲያውኑ ጳውሎስን ከኢየሩሳሌም ወደ ቂሳርያ ላከው፤ እሱን እንዲጠብቁትም ብዙ ወታደሮች አብረውት እንዲሄዱ አደረገ (የተከተሉት መንገድ ከኢየሩሳሌም 105 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል)። እዚያም አገረ ገዢው ፊሊክስ፣ ጳውሎስ “[በሄሮድስ] ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ አዘዘ።” በዚህ መንገድ ጳውሎስ ሊገድሉት ከሚፈልጉት ሰዎች አመለጠ።—ሥራ 23:12-35
9. አገረ ገዢው ፊስጦስ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው?
9 ከሁለት ዓመት በኋላም ጳውሎስ ቂሳርያ ውስጥ እንደታሰረ ነበር። አገረ ገዢው ፊሊክስ በፊስጦስ ተተካ። አይሁዳውያኑ፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ችሎት ፊት እንዲቀርብ ፊስጦስን ለመኑት፤ ፊስጦስ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። አገረ ገዢው አይሁዳውያኑ “መንገድ ላይ አድፍጠው ጳውሎስን ሊገድሉት [እንዳሰቡ]” አውቆ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 24:27 እስከ 25:5
10. አገረ ገዢው ፊስጦስ፣ ጳውሎስ በቄሳር ለመዳኘት ላቀረበው ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጠ?
10 በኋላ ላይ ጳውሎስ ቂሳርያ ውስጥ ችሎት ፊት ቀረበ። ፊስጦስ “በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ ጳውሎስን ‘ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?’ ሲል ጠየቀው።” ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ቢሄድ ሊገደል እንደሚችል ያውቃል። በተጨማሪም ሕይወቱን ለማትረፍ፣ ሮም በሰላም ለመድረስና አገልግሎቱን ለመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ስለዚህ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አለ። “በዚህ ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ ‘ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ’ ሲል መለሰለት።” የፊስጦስ ውሳኔ ጳውሎስ በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ሮም ይደርሳል፤ በመሆኑም ሊገድሉት የሚፈልጉት አይሁዳውያን ሊያገኙት አይችሉም።—ሥራ 25:6-12
11. ጳውሎስ ኢሳይያስ የተናገረውን የትኛውን የሚያበረታታ ሐሳብ አስታውሶ ሊሆን ይችላል?
11 ጳውሎስ ወደ ጣሊያን ጉዞ የሚጀምርበትን ጊዜ በሚጠባበቅበት ወቅት፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋን ለሚቃወሙ ሰዎች በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዕቅድ አውጡ፤ ይሁንና ይጨናገፋል! የፈለጋችሁትን ተናገሩ፤ ሆኖም አይሳካም፤ አምላክ ከእኛ ጋር ነውና!” (ኢሳ. 8:10) ጳውሎስ አምላክ እንደሚረዳው ያውቅ ነበር። ይህም ከፊቱ የሚጠብቁትን ፈተናዎች ለመቋቋም ብርታት ሰጥቶት መሆን አለበት።
12. ዩልዮስ ጳውሎስን የያዘው እንዴት ነው? ጳውሎስስ ምን አስተውሎ መሆን አለበት?
12 በ58 ዓ.ም. ጳውሎስ ወደ ጣሊያን ጉዞ ጀመረ። እስረኛ ስለነበር ዩልዮስ ለተባለ ሮማዊ የጦር መኮንን አስረከቡት። ከዚያ በኋላ በእሱ ሥልጣን ሥር ስለሚሆን ዩልዮስ የጳውሎስን ሕይወት መራራ ሊያደርግበት ወይም እሱን በደግነት ሊይዘው ይችል ነበር። ታዲያ ዩልዮስ ሥልጣኑን እንዴት ይጠቀምበት ይሆን? በማግሥቱ አንድ ወደብ ጋ ሲደርሱ ዩልዮስ “ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ [ፈቀደለት]።” እንዲያውም በኋላ ላይ ዩልዮስ የጳውሎስን ሕይወት አትርፎለታል። እንዴት? ወታደሮቹ በመርከቡ ላይ የነበሩትን እስረኞች በሙሉ ለመግደል አስበው ነበር፤ ዩልዮስ ግን ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው። ለምን? “ጳውሎስን ለማዳን ቆርጦ ስለነበር” ነው። ጳውሎስ፣ ይሖዋ እሱን ለመርዳትና ለማዳን በዚህ ደግ የጦር መኮንን እንደተጠቀመ አስተውሎ መሆን አለበት።—ሥራ 27:1-3, 42-44
13. ይሖዋ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን የሚጠቀመው እንዴት ሊሆን ይችላል?
13 እኛስ ምን እርዳታ እናገኛለን? ይሖዋ ከዓላማው ጋር የሚስማማ በሚሆንበት ወቅት፣ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የእሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህን የሚያደርገው ኃያል ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ ነው። ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የንጉሥ ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው። እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል።” (ምሳሌ 21:1) ይህ ምን ማለት ነው? ሰዎች አንድ ጅረት ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲፈስ ለማድረግ ቦይ ይቆፍራሉ። በተመሳሳይም ይሖዋ መንፈሱን ተጠቅሞ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ሐሳብ ሊመራ ይችላል፤ ይህን የሚያደርገው ከእሱ ዓላማ ጋር የሚስማማ ነገር እንዲያከናውኑ ሲል ነው። ይሖዋ ይህን በሚያደርግበት ወቅት ባለሥልጣናቱ የአምላክን ሕዝቦች የሚጠቅም ውሳኔ ለማድረግ ይነሳሳሉ።—ከዕዝራ 7:21, 25, 26 ጋር አወዳድር።
14. በሐዋርያት ሥራ 12:5 መሠረት እነማንን በተመለከተ ልንጸልይ እንችላለን?
14 ምን ማድረግ እንችላለን? ‘ነገሥታትና በሥልጣን ላይ ያሉ’ ሰዎች፣ አምልኳችንን እና አገልግሎታችንን የሚነካ ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት እነሱን በተመለከተ ልንጸልይ እንችላለን። (1 ጢሞ. 2:1, 2፤ ነህ. 1:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በእስር ላይ ስላሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ወደ አምላክ አጥብቀን እንጸልያለን። (የሐዋርያት ሥራ 12:5ን አንብብ፤ ዕብ. 13:3) በተጨማሪም በእስር ላይ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጠብቁ የእስር ቤት ጠባቂዎችን በተመለከተ መጸለይ እንችላለን። እነዚህ የእስር ቤት ጠባቂዎች እንደ ዩልዮስ፣ ለታሰሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን “ሰብዓዊ ደግነት” ለማሳየት እንዲነሳሱ ይሖዋ ሐሳባቸውን እንዲመራ ልንለምነው እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 27:3 ግርጌ
ከእምነት ባልንጀሮች የሚገኝ እርዳታ
15-16. ይሖዋ ሉቃስንና አርስጥሮኮስን ተጠቅሞ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው?
15 ጳውሎስ ምን እርዳታ አግኝቷል? ጳውሎስ ወደ ሮም ሲጓዝ ይሖዋ በእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት በተደጋጋሚ ረድቶታል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
16 ጳውሎስ ወደ ሮም ሲጓዝ፣ ታማኝ ወዳጆቹ የሆኑት ሉቃስና አርስጥሮኮስ አብረውት ለመሄድ ወሰኑ።b እነዚህ ክርስቲያኖች ሮም በሰላም እንደሚደርሱ ከኢየሱስ ማረጋገጫ ያገኙ አይመስልም፤ ስለዚህ ከጳውሎስ ጋር ለመሄድ የወሰኑት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ሕይወታቸው እንደሚተርፍ ያወቁት አስቸጋሪውን ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ነበር። እንግዲያው ሉቃስና አርስጥሮኮስ ከቂሳርያ አብረውት በመርከብ ሲሳፈሩ ጳውሎስ ይሖዋን በእጅጉ አመስግኖት መሆን አለበት፤ በእነዚህ ሁለት ደፋር የእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት ላደረገለት እርዳታ ይሖዋን እንዳመሰገነው ጥርጥር የለውም።—ሥራ 27:1, 2, 20-25
17. ይሖዋ ጳውሎስን በእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት የረዳው እንዴት ነው?
17 ጳውሎስ በጉዞው ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከእምነት ባልንጀሮቹ እርዳታ አግኝቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሲዶና ወደተባለች የወደብ ከተማ ሲደርሱ ጳውሎስ “ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት” ዩልዮስ ፈቅዶለት ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ፑቲዮሉስ የተባለችው ከተማ ሲደርሱ ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ‘ወንድሞችን አገኙ፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረዋቸው እንዲቆዩ ለመኗቸው።’ ጳውሎስና ጓደኞቹ በእነዚህ ቦታዎች ያሉ ክርስቲያኖች ካደረጉላቸው እንክብካቤ ተጠቅመዋል፤ ያስተናገዷቸው ወንድሞች ደግሞ የጳውሎስን የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች በመስማት በእጅጉ ተደስተው መሆን አለበት። (ከሐዋርያት ሥራ 15:2, 3 ጋር አወዳድር።) የሚያበረታታ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ ጉዟቸውን ቀጠሉ።—ሥራ 27:3፤ 28:13, 14
18. ጳውሎስ የተበረታታውና አምላክን ያመሰገነው ለምንድን ነው?
18 ጳውሎስ ወደ ሮም በሚወስደው ጎዳና ላይ በእግሩ ሲጓዝ፣ በዚያ ከተማ ለሚገኘው ጉባኤ ከሦስት ዓመታት በፊት የጻፈውን ሐሳብ አስታውሶ መሆን አለበት፤ ጳውሎስ “ለብዙ ዓመታት ወደ እናንተ ለመምጣት ስጓጓ ቆይቻለሁ” ብሏቸው ነበር። (ሮም 15:23) በእርግጥ እስረኛ ሆኖ እንደሚመጣ አልጠበቀም። እሱን ለመቀበል የተወሰነ መንገድ የመጡትን በሮም የሚኖሩ ወንድሞች ሲያይ ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ወንድሞችን “ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።” (ሥራ 28:15) ጳውሎስ ወንድሞች በመምጣታቸው አምላክን እንዳመሰገነ ልብ በል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? አሁንም በእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት ይሖዋ እየረዳው እንደሆነ ስላስተዋለ ነው።
19. በ1 ጴጥሮስ 4:10 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በእኛ ተጠቅሞ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
19 ምን ማድረግ እንችላለን? በሕመም ወይም በሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተነሳ የተጨነቁ ወንድሞችና እህቶች በጉባኤ ውስጥ አሉ? ወይም ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ይኖሩ ይሆናል። እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው እንዳለ ካወቅን ግለሰቡን የሚጠቅም ነገር መናገር ወይም ማድረግ እንድንችል የይሖዋን እርዳታ እንጠይቅ። የምንናገረው ወይም የምናደርገው ነገር የእምነት ባልንጀራችን በዚያ ወቅት የሚያስፈልገውን ማበረታቻ እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 4:10ን አንብብ።)c የእምነት ባልንጀራችንን ስንረዳው፣ ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት በገባው ቃል ላይ ያለው እምነት ይበልጥ ይጠናከራል። ይህ ደግሞ በጣም እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው።
20. “ይሖዋ ረዳቴ ነው” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
20 ጳውሎስና ጓደኞቹ በጉዟቸው ላይ እንደገጠማቸው ሁሉ እኛም በሕይወት ጉዞ ላይ እንደ ማዕበል ያሉ ችግሮች ያጋጥሙናል። ያም ቢሆን ይሖዋ አብሮን እንደሆነ ስለምናውቅ አንፈራም። በኢየሱስና በመላእክቱ አማካኝነት ይረዳናል። በተጨማሪም ከዓላማው ጋር የሚስማማ በሚሆንበት ወቅት ይሖዋ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ተጠቅሞ ይረዳናል። እንዲሁም ብዙዎቻችን በሕይወታችን እንዳየነው ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ የአገልጋዮቹን ልብ በማነሳሳት ለክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዲደርሱላቸው ያደርጋል። በእርግጥም እንደ ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።—ዕብ. 13:6
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
a ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ የገጠሙትን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲወጣ ይሖዋ በየትኞቹ ሦስት መንገዶች እንደረዳው በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩ አገልጋዮቹ ረዳት የሆነው እንዴት እንደሆነ መመልከታችን ይጠቅመናል፤ በዛሬው ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ እንደ ማዕበል ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንደሚረዳን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።
b ሉቃስና አርስጥሮኮስ ከዚህ በፊትም ከጳውሎስ ጋር አብረው ይጓዙ ነበር። እነዚህ ታማኝ ሰዎች ጳውሎስ ሮም ውስጥ በታሰረበት ወቅትም አብረውት ነበሩ።—ሥራ 16:10-12፤ 20:4፤ ቆላ. 4:10, 14