እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማን ናቸው?
“ክርስትና የሚገኘው በቃልም ሆነ በድርጊት ክርስቶስ በሚታወስበት ቦታ ብቻ ነው።” (ኦን ቢንግ ኤ ክርስቺያን) ሃንስ ኩንግ የተባሉ ስዊዘርላንዳዊ የሃይማኖት ምሑር የተናገሯቸው እነዚህ ቃላት ‘እውነተኛው ክርስትና የሚገኘው የኢየሱስን ትምህርቶች በተግባር ላይ በሚያውሉ ቅን ሰዎች ዘንድ ብቻ ነው’ የሚለውን ተጨባጭ ሐቅ ያስተጋባሉ።
ታዲያ የክርስቶስ ተከታዮች ነን እያሉ ኢየሱስ ያስተማረውን በተግባር ስለማያውሉ ግለሰቦች አሊያም ድርጅቶች ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ራሱ ብዙ ሰዎች ክርስቲያን ነን እንደሚሉ ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች “በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?” እያሉ ያደረጓቸውን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመጥቀስ እርሱን ያገለግሉ እንደነበር ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚሰጣቸው መልስ ምን ይሆን? “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ!” የሚሉት አስደንጋጭ ቃላት ምን ፍርድ እንደሚሰጣቸው ያሳያሉ።—ማቴዎስ 7:22, 23
ኢየሱስን እንከተላለን ለሚሉ “ክፉዎች” እንዴት ያለ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው! ኢየሱስ እንደ ክፉ አድራጊዎች ሳይሆን እንደ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲመለከታቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ሁለት መሠረታዊ ብቃቶች አሉ። እስቲ ኢየሱስ ያስቀመጣቸውን እነዚህን ብቃቶች እንመልከት።
“እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ”
ኢየሱስ ያስቀመጠው አንደኛው ብቃት ይህ ነው:- “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35
ኢየሱስ የእርሱ ተከታዮች አንዳቸው ለሌላውም ሆነ ለቀረው የሰው ዘር እውነተኛ ፍቅር እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በምድር ላይ ከተመላለሰበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት መቶ ዘመናት ይህንን ብቃት በግለሰብ ደረጃ ሲያሟሉ ቆይተዋል። ይሁንና ክርስቶስን እንወክላለን ስለሚሉት አብዛኞቹ የሃይማኖት ድርጅቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ያሳለፉት ታሪክ ፍቅር እንዳላቸው የሚያንጸባርቅ ነው? እንዳልሆነ እሙን ነው። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የንጹሐን ሰዎች ደም በፈሰሱባቸው ስፍር ቁጥር በሌላቸው ጦርነቶችና ግጭቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተካፍለዋል።—ራእይ 18:24
በዘመናችንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብሔራት በሃያኛው መቶ ዘመን በተደረጉት አሰቃቂ እልቂት በታየባቸው ሁለት የዓለም ጦርነቶች ውስጥ ዋና ተዋናዮች ነበሩ። በቅርብ ጊዜ ደግሞ ክርስቲያን ነን የሚሉ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን፣ በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ በተፈጸመው አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ሙከራ ላይ በግንባር ቀደምትነት ተሳትፈዋል። የቀድሞው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ “እነዚህ ደም የተፋሰሱ ሰዎች አንድ እምነት ነበራቸው። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ነበሩ” በማለት ጽፈዋል።
“በትምህርቴ ብትጸኑ”
እውነተኛ ክርስትና ሊያሟላው የሚገባው ሁለተኛው መሠረታዊ ብቃት ኢየሱስ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ ውስጥ ይገኛል:- “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:31, 32
ኢየሱስ ተከታዮቹ በትምህርቶቹ እንዲጸኑ ማለትም ትምህርቶቹን በጥብቅ እንዲከተሉ ይጠብቅባቸዋል። ክርስቶስን እንከተላለን የሚሉት የሃይማኖት አስተማሪዎች እንዲህ ከማድረግ ፈንታ የሃይማኖት ምሑር የሆኑት ኩንግ እንደተናገሩት “ከጊዜ ወደ ጊዜ የግሪክ ጽንሰ ሐሳቦችን እየተቀበሉ መጥተዋል።” የሃይማኖት አስተማሪዎቹ የኢየሱስን ትምህርቶች ነፍስ አትሞትም፣ መንጽሔ፣ የማርያም አምልኮ፣ የቀሳውስት መደብ እንደሚሉት ባሉ ጽንሰ ሐሳቦች ተክተዋቸዋል። እነዚህ ትምህርቶች ከአረማውያን ሃይማኖቶችና ከፈላስፎች የተወሰዱ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 1:19-21፤ 3:18-20
ከዚህም በተጨማሪ የሃይማኖት አስተማሪዎች ለኢየሱስ የሌለውን ቦታ በመስጠት ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነውን የሥላሴ ትምህርት ፈልስፈዋል። ኢየሱስ ምድር ሳለ ሁልጊዜ የሰዎችን ትኩረት ወደ አባቱ ይመራ ነበር፤ የሥላሴ ትምህርት ግን ሰዎች አባቱን ይሖዋን ከማምለክ ዞር እንዲሉ አድርጓቸዋል። (ማቴዎስ 5:16፤ 6:9፤ ዮሐንስ 14:28፤ 20:17) ሃንስ ኩንግ “ኢየሱስ፣ አምላክ ሲል የጥንቱን የፓትርያርኮቹን የአብርሃምን፣ የይስሐቅንና የያዕቆብን አምላክ ያህዌህን መጥቀሱ ነበር። . . . ለእርሱ ያህዌህ አንዱና ብቸኛው አምላክ ነው” በማለት ጽፈዋል። በዛሬው ጊዜ የኢየሱስ አምላክና አባት ሲባል ወዲያውኑ ያህዌህ አሊያም ይሖዋ (በአማርኛ በጣም የተለመደው አጻጻፍ ይህ ነው) የሚመጣላቸው ስንቶቹ ናቸው?
የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ ስለመሆን ከሰጠው ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ ርቀዋል። ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ገሊላ “የብሔርተኝነት እምብርት ነበረች” በማለት ትሬቨር ማሮ የተባሉ ጸሐፊ ገልጸዋል። ብዙ አይሁዳውያን አርበኞች ፖለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ነጻነት ለማግኘት የትጥቅ ትግል ውስጥ ገብተዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲካፈሉ ነግሯቸዋል? በፍጹም። ከዚህ በተቃራኒ “የዓለም አይደላችሁም” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14) ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ገለልተኛ ሆነው ከመቀጠል ይልቅ ህዩበርት በትለር የተባሉ አየርላንዳዊ ጸሐፊ እንደገለጹት “ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስብከት” ጀምረዋል። እኚህ ሰው “ፖለቲካ አራማጅ የሆነችው ክርስትና ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ወታደራዊም ነች። የፖለቲካ ባለ ሥልጣናትና የሃይማኖት መሪዎች ሲደራደሩ ቤተ ክርስቲያን ለምታገኛቸው ጥቅሞች በበኩሏ የአገሪቱን ጦር ትባርካለች” ሲሉ ጽፈዋል።
ሐሰተኛ አስተማሪዎች ኢየሱስን ይክዱታል
ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛውን ክርስትና የሚክዱ ሰዎች እንደሚኖሩ አስጠንቅቆ ነበር። እርሱ ከሞተ በኋላ ክርስቲያን ነን ከሚሉት መካከል “ነጣቂ ተኵላዎች” እንደሚነሱና ‘የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን እንደሚያጣምሙ’ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ‘እግዚአብሔርን እናውቃለን እያሉ’ በይፋ ቢናገሩም እንኳ እውነታው እንደሚያሳየን “በተግባራቸው ይክዱታል።” (ቲቶ 1:16) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች “የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ” ሲል አስጠንቅቋል። እርሱ እንደተናገረው በሚፈጽሙት መጥፎ ድርጊት አማካኝነት “የእውነት መንገድ ይሰደባል።” (2 ጴጥሮስ 2:1, 2) ዊልያም ኢ ቫይን የተባሉ ግሪካዊ ምሑር በዚህ መንገድ ክርስቶስን መካድ ሲባል “ከዳተኛ በመሆንና ጠንቀኛ ትምህርቶችን በማስፋፋት አብንም ሆነ ወልድን መተው” ማለት እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች ‘በትምህርቱ ባይጸኑና’ እርሱ ያስቀመጣቸውን ሌሎች ብቃቶች ባያሟሉ ምን ይሰማዋል? “በሰው ፊት የሚክደኝን፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 10:33) ኢየሱስ፣ ታማኝ ለመሆን ልባዊ ጥረት እያደረገ ስህተት የሚፈጽምን ሰው እንደማይክድ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ቢክደውም እንኳ ንስሐ በመግባቱ ይቅርታ አግኝቷል። (ማቴዎስ 26:69-75) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ የበግ ለምድ እንደለበሱ ተኩላዎች የእርሱ ተከታዮች እንደሆኑ የሚያስመስሉ ዳሩ ግን ነጋ ጠባ ሆን ብለው ትምህርቱን የሚክዱ ግለሰቦችንም ይሁን ድርጅቶችን አይቀበላቸውም። እንደነዚህ ስላሉት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሲናገር “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል።—ማቴዎስ 7:15-20
ከሐዋርያት ሞት በኋላ ክህደት ተስፋፋ
ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መካድ የጀመሩት መቼ ነው? ኢየሱስ በሞተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ኢየሱስ ራሱ ሰይጣን ዲያብሎስ ‘በጥሩ ዘር’ ላይ ማለትም ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ባፈራቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል “እንክርዳድ” ወይም ሐሰተኛ ክርስቲያኖችን በፍጥነት እንደሚዘራ አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 13:24, 25, 37-39) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ በዚያን ጊዜም እንኳ አሳሳች አስተማሪዎች እንደነበሩ አስታውቋል። እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት እንዲያፈነግጡ ያደረጋቸው መሠረታዊ ምክንያት ‘እውነትን አለመውደዳቸው’ እንደሆነም ተናግሯል።—2 ተሰሎንቄ 2:10
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት በሕይወት እስካሉ ድረስ ይህ ክህደት እንዳይስፋፋ ሲከላከሉ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ ከሞቱ በኋላ ብዙዎችን ለማሳት የቆረጡ የሃይማኖት መሪዎች ‘በሐሰተኛ ታምራት፣ በምልክቶችና በድንቅ ነገሮች ሁሉ እንዲሁም በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ’ መጠቀም ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች ኢየሱስና ሐዋርያቱ ላስተማሯቸው እውነቶች ጀርባቸውን ሰጥተዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 6-12) በርትራንድ ራስል የተባለ እንግሊዛዊ ፈላስፋ እንደተናገረው የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ ተለውጦ “ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን ጳውሎስንም ጭምር የሚያስገርም” ሃይማኖታዊ ድርጅት ሆኗል።
እውነተኛው ክርስትና ዳግመኛ ተቋቋመ
ነጥቡ ግልጽ ነው። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የክርስቶስ ትምህርቶች በእርሱ ስም በሚንቀሳቀሱት በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ውስጥ አልተንጸባረቁም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ” ከተከታዮቹ ጋር እንደሚሆን የገባውን ቃል ጠብቋል። (ማቴዎስ 28:20) እነዚህን ቃላት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ‘በቃልም ሆነ በድርጊት ክርስቶስን የሚያስታውሱ’ ታማኝ ሰዎች እንደነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅርን ለማንጸባረቅና እርሱ ያስተማራቸውን እውነቶች በታማኝነት ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርጉትን ሰዎች ለመደገፍ የገባውን ቃል ጠብቋል።
ከዚህም በላይ ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን፣ ፈቃዱን ለማስፈጸም ወደሚጠቀምበትና በቀላሉ ተለይቶ ሊታወቅ ወደሚችለው የክርስቲያን ጉባኤ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚሰበስባቸው ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 24:14, 45-47) ደግሞም ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ጉባኤ በመጠቀም “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚገኙበትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየሰበሰበ ነው። ይህንን ሕዝብ በእርሱ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆኖ ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ “አንድ መንጋ” አድርጎታል።—ራእይ 7:9, 14-17፤ ዮሐንስ 10:16፤ ኤፌሶን 4:11-16
እንግዲያው ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ የክርስቶስን ስም ካጠፋና ክርስትናን ካሰደበ የትኛውም ዓይነት ድርጅት አሊያም ተቋም ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት አይኑርህ። አለበለዚያ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ዮሐንስ እንደተናገረው አምላክ በቅርብ ጊዜ ፍርዱን ሲያስፈጽም ከሚያመጣባቸው ‘መቅሰፍት ትካፈላለህ።’ (ራእይ 1:1፤ 18:4, 5) ነቢዩ ሚክያስ “በመጨረሻው ዘመን” የአምላክን መመሪያ እንደሚሰሙና ‘በመንገዱ እንደሚሄዱ’ ከተናገረላቸው እውነተኛ አምላኪዎች ማለትም እውነተኛውን ክርስትና ከሚደግፉት ሰዎች መካከል ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። (ሚክያስ 4:1-4) የዚህ መጽሔት አዘጋጆች እውነተኛ አምላኪዎችን ለይተህ እንድታውቅ ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?
[ምንጭ]
በስተ ግራ፣ ወታደሮች:- U.S. National Archives photo; በስተ ቀኝ፣ እሳት የሚተፋ መሣሪያ የያዘ ወታደር:- U.S. Army Photo
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ እንዲሁም ‘በትምህርቴ ጽኑ’ የሚሉትን ብቃቶች እንዲያሟሉ ይጠብቅባቸዋል