ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?
“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።”—ሉቃስ 6:31
1, 2. (ሀ) የተራራው ስብከት ምንድን ነው? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?
ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ አስተማሪ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ እሱን እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን በላኩ ጊዜ ሰዎቹ ባዶ እጃቸውን የተመለሱ ሲሆን “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ብለዋል። (ዮሐ. 7:32, 45, 46) ግሩም ከሆኑት የኢየሱስ ንግግሮች አንዱ የተራራው ስብከት ሲሆን ይህም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ይገኛል፤ በሉቃስ 6:20-49 ላይም ተመሳሳይ ዘገባ ሰፍሯል።a
2 ኢየሱስ በዚህ ስብከት ላይ ከሰጣቸው ትምህርቶች ሁሉ በጣም ታዋቂ የሆነው በተለምዶ ወርቃማው ሕግ በመባል የሚጠራው ሳይሆን አይቀርም። ይህ ጥቅስ ከሌሎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ይገልጻል። ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል። (ሉቃስ 6:31) ደግሞም ኢየሱስ ለሰዎች መልካም ነገሮችን አድርጓል! የታመሙትን ፈውሷል፤ የሞቱትንም እንኳ አስነስቷል። ሰዎቹ ከሁሉ በላይ የተጠቀሙት ግን ኢየሱስ የሚያስተምረውን ምሥራች ሲቀበሉ ነበር። (ሉቃስ 7:20-22ን አንብብ።) ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ መካፈል ያስደስተናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ይህንን ሥራ አስመልክቶ ስለሰጠው ትምህርት እንዲሁም ከሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት በተራራው ስብከቱ ላይ የጠቀሳቸውን ሌሎች ነጥቦች እንመለከታለን።
የዋሆች ሁኑ
3. የዋህነት ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:5) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የዋህነት የድክመት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ አልተጠቀሰም። ከዚህ ይልቅ የዋህነት የአምላክን ብቃቶች ለማሟላት ስንል ገር መሆንን ያመለክታል። ይህ ዓይነቱ ባሕርይ ደግሞ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ይንጸባረቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ለማንም ክፉን በክፉ አንመልስም።’—ሮሜ 12:17-19
4. የዋህ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
4 የዋሆች ‘ምድርን ስለሚወርሱ’ ደስተኞች ናቸው። “የዋህና ትሑት” የሆነው ኢየሱስ ‘የሁሉ [ነገር] ወራሽ’ በመሆኑ በዋነኝነት ምድርን የሚወርሰው እሱ ነው፤ ይህም ሲባል ኢየሱስ ምድርን ይገዛል ማለት ነው። (ማቴ. 11:29፤ ዕብ. 1:2፤ መዝ. 2:8) ‘የሰው ልጅ’ ተብሎ የተጠራው መሲሕ በሰማይ በሚገኘው መንግሥቱ በሚገዛበት ወቅት አብረውት የሚነግሡ ሰዎች እንደሚኖሩ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ዳን. 7:13, 14, 21, 22, 27) የዋህ የሆኑት እነዚህ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ በመሆናቸው ከኢየሱስ ጋር ምድርን ይወርሳሉ። (ሮሜ 8:16, 17፤ ራእይ 14:1) የዋህ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ።—መዝ. 37:11
5. እንደ ክርስቶስ ዓይነት የዋህነት ማዳበራችን በባሕርያችን ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
5 አስቸጋሪ ባሕርይ ካለን ሌሎች እኛን መታገስ ስለሚከብዳቸው ሊርቁን ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ክርስቶስ ዓይነት የዋህነት የምናሳይ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ የምንወደድ እንዲሁም ሌሎችን በመንፈሳዊ የምናንጽ ሰዎች እንሆናለን። ከአምላክ መንፈስ ፍሬ አንዱ ገርነት ወይም የዋህነት ነው፤ ‘በመንፈስ የምንኖርና የምንመላለስ’ ከሆነ ደግሞ የአምላክ መንፈስ ይህንን ፍሬ እንድናፈራ ይረዳናል። (ገላትያ 5:22-25ን አንብብ።) ሁላችንም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ከሚመሩት የዋህ ሰዎች መካከል መሆን እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም!
ምሕረትን የሚያደርጉ ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
6. “ምሕረት የሚያደርጉ” ሰዎች ምን ግሩም ባሕርያት አሏቸው?
6 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 5:7) “ምሕረት የሚያደርጉ” ሰዎች ርኅሩኆች ከመሆናቸውም ባሻገር ለተቸገሩት ደግነት ያሳያሉ፤ ከዚያም አልፈው እንደዚህ ላሉት ሰዎች ያዝናሉ። ኢየሱስ ለሰዎች ‘ይራራላቸው’ ስለነበር በተአምራዊ መንገድ ሥቃያቸውን አስወግዶላቸዋል። (ማቴ. 14:14፤ 20:34) እኛም ለሰዎች ያለን አዘኔታና አሳቢነት ምሕረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።—ያዕ. 2:13
7. ኢየሱስ ለሰዎች ማዘኑ ምን እንዲያደርግላቸው አነሳስቶታል?
7 ኢየሱስ ጥቂት እረፍት ለማድረግ ፈልጎ በነበረበት ወቅት ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” (ማር. 6:34) እኛም በተመሳሳይ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ለሰዎች ስናካፍልና ስለ ይሖዋ ታላቅ ምሕረት ስንናገር ምንኛ እንደሰታለን!
8. ምሕረት የሚያደርጉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
8 ምሕረት የሚያደርጉ ሰዎች ‘ምሕረትን ስለሚያገኙ’ ደስተኞች ናቸው። ለሰዎች ምሕረት ስናደርግ አብዛኛውን ጊዜ እነሱም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉልናል። (ሉቃስ 6:38) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል” ብሏል። (ማቴ. 6:14) የሌሎችን በደል ይቅር ማለት እንዲሁም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚያመጣውን ደስታ የሚያጣጥሙት ምሕረት የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ ናቸው።
“ሰላምን የሚያወርዱ” ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?
9. ሰላማዊ ሰዎች ከሆንን ምን እናደርጋለን?
9 ኢየሱስ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ሌላም ነጥብ ሲጠቅስ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” ብሏል። (ማቴ. 5:9) “ሰላምን የሚያወርዱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ሰላም ፈጣሪዎች” የሚል ፍቺ አለው። ሰላም ፈጣሪዎች ከሆንን እንደ ሐሜት ያሉ ‘የቅርብ ወዳጆችን የሚለያዩ’ ድርጊቶችን በቸልታ አንመለከትም፤ እንዲሁም እንዲህ ባሉት ድርጊቶች አንካፈልም። (ምሳሌ 16:28) በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥና ከጉባኤው ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (ዕብ. 12:14) በተለይም ደግሞ በይሖዋ አምላክ ፊት ሰላማውያን ሆነን ለመገኘት እንጥራለን።—1 ጴጥሮስ 3:10-12ን አንብብ።
10. “ሰላምን የሚያወርዱ” ሰዎች ደስተኞች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስ “ሰላምን የሚያወርዱ” ሰዎች “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው [ስለሚጠሩ]” ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አምነው ስለተቀበሉ “የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት” አግኝተዋል። (ዮሐ. 1:12፤ 1 ጴጥ. 2:24) “ሌሎች በጎች” ተብለው ስለተጠሩት የኢየሱስ ሰላማዊ ተከታዮችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ ከተባባሪ ገዢዎቹ ጋር በሰማይ ለአንድ ሺህ ዓመት በሚገዛበት ወቅት ለእነሱም “የዘላለም አባት” ይሆንላቸዋል። (ዮሐ. 10:14, 16፤ ኢሳ. 9:6፤ ራእይ 20:6) ሰላም ፈጣሪ የሆኑት እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ሙሉ በሙሉ የአምላክ ምድራዊ ልጆች ወደ መሆን ደረጃ ይደርሳሉ።—1 ቆሮ. 15:27, 28
11. ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ የምንመራ ከሆነ ከሌሎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረናል?
11 “የሰላም አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖረን ሰላማዊ መሆንን ጨምሮ የእሱን ሌሎች ባሕርያት መኮረጅ ይኖርብናል። (ፊልጵ. 4:9) “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ” እንድትመራን ፈቃደኞች ከሆንን ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ሰላማዊ እንሆናለን። (ያዕ. 3:17) አዎን፣ ሰላም ፈጣሪዎች በመሆን ደስታ እናገኛለን።
‘ብርሃናችሁ ይብራ’
12. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መንፈሳዊ ብርሃን ምን ብሏል? (ለ) ብርሃናችንን ማብራት የምንችለው እንዴት ነው?
12 ሰዎች ከአምላክ የሚገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን እንዲያገኙ ስንረዳቸው ከሁሉ የላቀ መልካም ነገር እያደረግንላቸው ነው። (መዝ. 43:3) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “የዓለም ብርሃን” እንደሆኑ የነገራቸው ሲሆን ሰዎች ‘መልካም ሥራቸውን’ ማለትም ለሌሎች የሚያደርጉትን መልካም ነገር ማየት እንዲችሉ ብርሃናቸውን እንዲያበሩ አበረታቷቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው “በሰዎች ፊት” መንፈሳዊ ብርሃን ለማብራት የሚያስችላቸው ሲሆን ይህም ለመላው የሰው ዘር ጥቅም ያስገኛል። (ማቴዎስ 5:14-16ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ለሌሎች መልካም በማድረግና ምሥራቹን “በዓለም ዙሪያ” ማለትም “ለሕዝብ ሁሉ” በመስበኩ ሥራ በመካፈል ብርሃናችንን ማብራት እንችላለን። (ማቴ. 26:13፤ ማር. 13:10) ይህ እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!
13. ሰዎች የትኞቹን ነገሮች ያስተውላሉ?
13 ኢየሱስ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም” ብሏል። በተራራ ላይ የምትገኝን ከተማ በቀላሉ ማየት ይቻላል። በተመሳሳይ እኛም የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የምናከናውነውን መልካም ሥራ እንዲሁም የምናሳያቸውን እንደ ጭምትነት ወይም ልከኝነት ያሉ ባሕርያትና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ሰዎች ያስተውላሉ።—ቲቶ 2:1-14
14. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኩራዝ የሚሠራው እንዴት ነበር? (ለ) መንፈሳዊውን ብርሃን “ከዕንቅብ ሥር” ማስቀመጥ የለብንም ሲባል ምን ማለት ነው?
14 ኢየሱስ፣ አንድ ሰው መብራት አብርቶ ከዕንቅብ ሥር እንደማያስቀምጠው ከዚህ ይልቅ ብርሃኑ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ እንደሚያደርገው ተናግሯል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረው ኩራዝ የሚሠራው ከሸክላ ሲሆን ነዳጅ (አብዛኛውን ጊዜ የወይራ ዘይት) ይጨመርበት ነበር፤ ከዚያም በውስጡ የሚገኘው ክር ጫፉ ሲቀጣጠል ብርሃን ይሰጣል። ይህ ኩራዝ ‘በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ’ አብዛኛውን ጊዜ ከእንጨት ወይም ከብረት በተሠራ መቅረዝ ላይ እንጂ ‘ከዕንቅብ ሥር አይቀመጥም’፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች የሚጠቀሙበት ዕንቅብ 9 ኪሎ ያህል የሚይዝ ትልቅ መሥፈሪያ ነበር። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ ብርሃናቸውን በምሳሌያዊ ሁኔታ ከዕንቅብ ሥር እንዳያስቀምጡት አሳስቧቸዋል። እኛም፣ ተቃውሞም ሆነ ስደት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች እንድንደብቅ ወይም ለሌሎች ከመናገር ወደኋላ እንድንል እንዲያደርጉን ባለመፍቀድ ብርሃናችንን ማብራት ይኖርብናል።
15. የምናከናውናቸው መልካም ‘ሥራዎች’ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሷቸው ይችላሉ?
15 ኢየሱስ ብርሃን ስለማብራት ከተናገረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” ብሏቸዋል። መልካም ‘ሥራችንን’ የተመለከቱ አንዳንዶች የአምላክ አገልጋዮች በመሆን እሱን ‘አክብረዋል።’ ይህን ማወቃችን “እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ [ማብራታችንን]” እንድንቀጥል የሚያበረታታ ነው!—ፊልጵ. 2:15
16. “የዓለም ብርሃን” ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 “የዓለም ብርሃን” ለመሆን ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ይኖርብናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጉ ብቻ አይበቃም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 5:8, 9) ላቅ ካሉት የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ምንጊዜም ተስማምተን በመኖር ምሳሌ መሆን ይኖርብናል። “ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ” የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:12) ይሁን እንጂ በሁለት ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ምን መደረግ ይኖርበታል?
“ከወንድምህ ጋር ተስማማ”
17-19. (ሀ) በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ የተገለጸው ‘መባ’ ምን ያመለክታል? (ለ) አንድ ሰው ከወንድሙ ጋር እርቅ መፍጠሩ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ኢየሱስ የዚህን አስፈላጊነት ያጎላው እንዴት ነበር?
17 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ፣ ደቀ መዛሙርቱ በወንድማቸው ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ተቆጥተው መቆየት ወይም ወንድማቸውን በንቀት መመልከት እንደሌለባቸው አስጠንቅቋል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ቅር ከተሰኘባቸው ወንድም ጋር ጊዜ ሳያጠፉ መስማማት ነበረባቸው። (ማቴዎስ 5:21-25ን አንብብ።) ኢየሱስ የሰጠውን ይህንን ምክር ልብ ልንለው ይገባል። መባህን በመሠዊያው ላይ ለማቅረብ ተዘጋጅተህ እያለ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር እንዳለ ብታስታውስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? መባህን በዚያው በመሠውያው ፊት ትተህ በመሄድ ከወንድምህ ጋር መስማማት ይጠበቅብሃል። ይህን ካደረግህ በኋላ ተመልሰህ መባህን ማቅረብ ትችላለህ።
18 አብዛኛውን ጊዜ ‘መባ’ አንድ ሰው በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ያመለክታል። አምላክ፣ እስራኤላውያን ለእሱ የሚያቀርቡትን አምልኮ በተመለከተ በሙሴ ሕግ አማካኝነት የሰጣቸው ትእዛዝ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብን ይጨምራል። በመሆኑም ይህ ዓይነቱ መሥዋዕት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ያም ሆኖ ግን ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩን ብታስታውስ፣ መባህን ከማቅረብ የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።” ከወንድምህ ጋር መስማማት በሕጉ ላይ የሰፈረውን ነገር ከመፈጸም መቅደም ነበረበት።
19 እዚህ ላይ ኢየሱስ የተወሰነ መሥዋዕትንና መተላለፍን ለይቶ አልጠቀሰም። በመሆኑም አንድ ሰው፣ ወንድሙ የተቀየመበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለው የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕት ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ይኖርበታል። መሥዋዕቱ እንስሳ ከሆነ፣ እንስሳውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በካህናት አደባባይ ላይ በሚገኘው ‘መሠዊያ ፊት’ ከነሕይወቱ ትቶ መሄድ ነበረበት። ጥፋተኛ የሆነው ሰው አለመግባባቱን ካስወገደ በኋላ ተመልሶ በመምጣት መሥዋዕቱን ማቅረብ ይችላል።
20. በወንድማችን ላይ ተቆጥተን ከሆነ ሁኔታውን ወዲያውኑ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
20 አምላክ፣ ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ነገር አድርጎ ይመለከተዋል። የእንስሳት መሥዋዕት የሚያቀርበው ሰው ከወንድሙ ጋር ጥሩ ግንኙነት ከሌለው መሥዋዕቱ በይሖዋ ፊት ዋጋ አይኖረውም። (ሚክ. 6:6-8) በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከወንድሞቻቸው ጋር ‘ፈጥነው እንዲስማሙ’ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 5:25) ጳውሎስም እንደሚከተለው በማለት ከዚህ ጋር የሚስማማ ሐሳብ ጽፏል:- “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።” (ኤፌ. 4:26, 27) እንድንቆጣ የሚያደርገን ነገር ቢያጋጥመን ሳንውል ሳናድር ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ አለብን፤ እንዲህ ሳናደርግ ቀርተን እንደተቆጣን የምንቆይ ከሆነ ለዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንሰጠዋለን።—ሉቃስ 17:3, 4
ምንጊዜም ለሌሎች አክብሮት ይኑራችሁ
21, 22. (ሀ) እስካሁን የተመለከትናቸውን የኢየሱስ ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለየትኛው ጉዳይ እንመለከታለን?
21 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ከሰጣቸው ትምህርቶች አንዳንዶቹን መከለሳችን ሌሎችን በደግነትና በአክብሮት እንድንይዝ ሊረዳን ይገባል። ማንኛችንም ፍጹም ባንሆንም ኢየሱስም ሆነ በሰማይ ያለው አባታችን ከአቅማችን በላይ ስለማይጠብቁብን እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። ወደ አምላክ በመጸለይ፣ ልባዊ ጥረት በማድረግና ይሖዋ በሚሰጠን እርዳታ በመታገዝ የዋሆች መሆንና ምሕረት ማድረግ እንዲሁም ሰላምን ማውረድ እንችላለን። ከዚህም በላይ ይሖዋን የሚያስከብር መንፈሳዊ ብርሃን ማብራት እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር አለመግባባት በሚኖርበት ጊዜ ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ እንችላለን።
22 አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። (ማር. 12:31) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለሌሎች መልካም ማድረጋችንን እንድንቀጥል የሚረዱንን በተራራው ስብከት ላይ የተገለጹ አንዳንድ ሐሳቦች እንመለከታለን። ግሩም ከሆነው የኢየሱስ ንግግር ላይ በተወሰዱት በእነዚህ ነጥቦች ላይ ካሰላሰልን በኋላ ‘ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ምን ይመስላል?’ በማለት ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህንንና የሚቀጥለውን ርዕስ ከመዘጋጀትህ በፊት እነዚህን ጥቅሶች በግልህ ብታነባቸው ጠቃሚ ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የዋህ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
• “ምሕረት የሚያደርጉ” ሰዎች ደስተኞች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
• ብርሃናችን እንዲበራ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• ሳንዘገይ ‘ከወንድማችን ጋር መስማማት’ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብርሃናችን እንዲበራ ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች ውስጥ ዋነኛው ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ማወጅ ነው
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ላቅ ካሉት የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው በመኖር ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከወንድምህ ጋር ለመስማማት የተቻለህን ሁሉ አድርግ