ምዕራፍ 35
ታዋቂው የተራራ ስብከት
የተራራው ስብከት
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል 12ቱን ሐዋርያት አድርጎ ለመምረጥ ሲል ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል፤ በዚህ ወቅት ደክሞት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ጠዋት ላይ፣ ሰዎችን ለመርዳት ብርታቱም ሆነ ፍላጎቱ አለው። ኢየሱስ የሚገኘው በገሊላ ባለ ተራራ ምናልባትም የአገልግሎቱ ማዕከል ከሆነችው ከቅፍርናሆም ብዙም ሳይርቅ መሆን አለበት።
ብዙ ሕዝብ፣ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ኢየሱስ መጥተዋል። አንዳንዶቹ ከደቡብ ይኸውም ከኢየሩሳሌምና ከሌሎች የይሁዳ ከተሞች የመጡ ናቸው። ሌሎቹ የመጡት ደግሞ በስተ ሰሜን ምዕራብ ከሚገኙት ጢሮስና ሲዶና የተባሉ በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ከተሞች ነው። ሰዎቹ፣ ኢየሱስን ማግኘት የፈለጉት ለምንድን ነው? “እሱን ለመስማትና ከበሽታቸው ለመፈወስ” ነው። ኢየሱስም ‘ሁሉንም ስለፈወሰ’ የፈለጉትን አድርጎላቸዋል። እስቲ አስበው! የታመሙት ሰዎች ሁሉ ተፈወሱ። ኢየሱስ “በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩ” ይኸውም የሰይጣን ግብረ አበሮች በሆኑት ክፉ መላእክት የተያዙ ሰዎችንም ጭምር አድኗል።—ሉቃስ 6:17-19
ከዚያም ኢየሱስ ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ። ደቀ መዛሙርቱ በተለይም 12ቱ ሐዋርያት አጠገቡ ሳይሆኑ አይቀሩም። ሰዎቹ በሙሉ፣ እነዚህን አስደናቂ ተአምራት የፈጸመው አስተማሪ የሚናገረውን ለመስማት ጓጉተዋል። የኢየሱስ ስብከት አድማጮቹን የሚጠቅም እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚያ ጊዜ በኋላ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከዚህ ንግግር ጥቅም አግኝተዋል። የኢየሱስ ስብከት ጥልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ብሎም ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ በመቅረቡ እኛንም ይጠቅመናል። ኢየሱስ የጠቀሳቸው ነገሮች የተለመዱና ሰዎች በሚገባ የሚያውቋቸው ናቸው። እንዲህ ማድረጉ የአምላክን መመሪያ በመከተል የተሻለ ሕይወት መምራት የሚፈልጉ ሁሉ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲረዱ አስችሏቸዋል። የኢየሱስ ስብከት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንዲሆን የሚያደርጉት ጉልህ ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?
እውነተኛ ደስታ ያላቸው እነማን ናቸው?
ሁሉም ሰው ደስተኛ መሆን ይፈልጋል። ኢየሱስ ይህን በመገንዘብ የተራራውን ስብከት የጀመረው እውነተኛ ደስታ ያላቸው እነማን እንደሆኑ በመግለጽ ነው። ይህ የአድማጮቹን ትኩረት እንደሚስብ መገመት እንችላለን። ሆኖም ከተናገራቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ግራ ሳያጋቧቸው አልቀሩም።
እንዲህ አለ፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና። የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና። . . . ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ ይጠግባሉና። . . . ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና። በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁ . . . ደስተኞች ናችሁ። . . . ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ።”—ማቴዎስ 5:3-12
ኢየሱስ “ደስተኞች” ሲል ምን ማለቱ ነው? አንድ ሰው ጥሩ ጊዜ ሲያሳልፍ የሚኖረውን ዓይነት ዘና የማለት ስሜት መግለጹ አይደለም። እውነተኛ ደስታ ከዚህ የበለጠ ጥልቀት አለው። እንዲህ ያለው ደስታ፣ እውነተኛ እርካታን እንዲሁም በሕይወት ስኬታማ መሆን የሚፈጥረውን ስሜት ያመለክታል።
ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ የሚኖራቸው መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው የሚታወቃቸው፣ ኃጢአተኛ በመሆናቸው ያዘኑ እንዲሁም አምላክን አውቀው እሱን ማገልገል የጀመሩ ሰዎች እንደሆኑ አመልክቷል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው ቢጠሉ ወይም ቢሰደዱም እንኳ አምላክን እንደሚያስደስቱና እሱ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚሰጣቸው ስለሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።
ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች፣ አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ብልጽግናና ተድላ እንደሆነ ያስባሉ። ኢየሱስ ግን ደስታ የሚገኘው ከእነዚህ ነገሮች እንዳልሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹን የሚያስገርም ንጽጽር በመጠቀም እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናኛችሁን በሙሉ አግኝታችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁና፤ እንዲሁም ታለቅሳላችሁ። ሰዎች ስለ እናንተ መልካም ነገር በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኛ ነቢያት እንዲህ ያለ ነገር አድርገው ነበርና።”—ሉቃስ 6:24-26
ሀብት ማግኘት፣ በደስታ ስሜት መሳቅና ከሰዎች ውዳሴ ማግኘት ወዮታ የሚያስከትለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች ሲያገኝና ትልቅ ቦታ ሲሰጣቸው ለአምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት ችላ ሊል ይችላል፤ ይህ ደግሞ እውነተኛ ደስታ እንዳያገኝ ያደርገዋል። ኢየሱስ፣ ድሃ መሆን ወይም መራብ በራሱ አንድን ሰው ደስተኛ ያደርገዋል ማለቱም አይደለም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የኢየሱስን ትምህርት የሚቀበሉትና እውነተኛ ደስታ በማግኘት የሚባረኩት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው።
በመቀጠልም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” አላቸው። (ማቴዎስ 5:13) እርግጥ ቃል በቃል ጨው ናቸው ማለቱ አይደለም። ጨው ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ ይረዳል። በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያው አጠገብ ትልቅ የጨው ክምር የነበረ ሲሆን መሥዋዕቱን ለመቀመም ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ከዚህም ሌላ ጨው አንድ ነገር፣ ከብክለት የጸዳ ወይም ያልተበላሸ መሆኑን ያመለክታል። (ዘሌዋውያን 2:13፤ ሕዝቅኤል 43:23, 24) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ ሰዎች በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ እንዳይበከሉ ስለሚከላከል “የምድር ጨው” ሊባሉ ይችላሉ። በእርግጥም ደቀ መዛሙርቱ የያዙት መልእክት፣ የሚሰሟቸውን ሰዎች ሕይወት ይጠብቃል!
በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸዋል። ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ ብርሃኑ እንዲታይ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል። በመሆኑም ኢየሱስ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 5:14-16
ተከታዮቹ እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው የላቀ መሥፈርት
የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስ የአምላክን ሕግ እንደሚጥስ ስለተሰማቸው እሱን ለመግደል ከጥቂት ጊዜ በፊት አሲረው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም” በማለት በግልጽ ተናገረ።—ማቴዎስ 5:17
ኢየሱስ የአምላክን ሕግ እጅግ ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አበረታቷል። እንዲያውም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ ይባላል።” ይህን ሲል እንዲህ ዓይነቱ ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ጨርሶ እንደማይገባ መግለጹ ነው። አክሎም “እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል” አለ።—ማቴዎስ 5:19
ኢየሱስ፣ የአምላክን ሕግ እንድንጥስ የሚገፋፋ አስተሳሰብንም ጭምር አውግዟል። ሕጉ “አትግደል” እንደሚል ከገለጸ በኋላ “በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል” አለ። (ማቴዎስ 5:21, 22) አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት ከሆነ ይህ ነፍስ ወደማጥፋት ሊመራ ስለሚችል ከባድ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ አንድ ሰው እርቅ ለመፍጠር ምን ያህል ጥረት ማድረግ እንዳለበት ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:23, 24
በሕጉ ውስጥ የተካተተው ሌላው ትእዛዝ ደግሞ ምንዝርን ይከለክላል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ማቴዎስ 5:27, 28) ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ለቅጽበት ወደ አእምሮ ስለሚመጣ የብልግና ሐሳብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ‘መመልከቱን’ ሲቀጥል የሚፈጠረውን ሁኔታ ማጉላቱ ነው። ግለሰቡ መመልከቱን መቀጠሉ ብዙውን ጊዜ የፍትወት ስሜቱ እንዲቀሰቀስ ያደርጋል። ከዚያም አጋጣሚውን ካገኘ ምንዝር ሊፈጽም ይችላል። አንድ ሰው ይህ እንዳይሆን መከላከል የሚችለው እንዴት ነው? ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገው ይሆናል። ኢየሱስ “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። . . . ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው” ብሏል።—ማቴዎስ 5:29, 30
አንዳንድ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ የታመመ እጃቸው ወይም እግራቸው እንዲቆረጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። ከዚህ አንጻር፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነን አስተሳሰብና ይህ የሚያስከትለውን ድርጊት ለማስወገድ ሲባል ማንኛውንም ነገር ሌላው ቀርቶ የዓይንን ወይም የእጅን ያህል በጣም ውድ የሆነ ነገርን እንኳ ‘መጣል’ ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ይህን ሲያብራራ “መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል” ብሏል፤ ገሃነም፣ ከኢየሩሳሌም ግንብ ውጭ ለነበረው ሁልጊዜ የሚቃጠል የቆሻሻ ክምር የተሰጠ ስም ሲሆን ዘላለማዊ ጥፋትን ያመለክታል።
በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሰዎች ቢጎዱን ወይም ቅር ቢያሰኙን ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ሰጥቷል። “ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት” ብሏል። (ማቴዎስ 5:39) ይህ ሲባል አንድ ሰው በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ ጥቃት ቢሰነዘር መከላከል የለበትም ማለት አይደለም። ኢየሱስ የጠቀሰው ጥፊ መሆኑን ልብ በል፤ ጥፊ የሚሰነዘረው በአንድ ሰው ላይ ከባድ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ ወይም ለመግደል ሳይሆን ግለሰቡን ለማዋረድ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ለመግለጽ የፈለገው፣ አንድ ሰው ቃል በቃል በጥፊ በመማታትም ሆነ የስድብ ቃላት በመሰንዘር ጠብ ወይም ክርክር ለማነሳሳት ቢሞክር የአጸፋ እርምጃ መውሰድ እንደሌለብን ነው።
ይህ ምክር ባልንጀራችንን እንድንወድ ከሚያዝዘው የአምላክ ሕግ ጋር ይስማማል። በመሆኑም ኢየሱስ ለአድማጮቹ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ” የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል። እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን አሳማኝ ምክንያት ሲገልጽ “ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና” ብሏል።—ማቴዎስ 5:44, 45
ኢየሱስ ይሄኛውን የስብከቱን ክፍል ያጠቃለለው “በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” በማለት ነው። (ማቴዎስ 5:48) ሰዎች ሙሉ በሙሉ ፍጹም መሆን ይችላሉ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና አምላክን በመምሰል ጠላቶቻችንን እንኳ መውደድ እንችላለን። በሌላ አባባል “አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ” ማለቱ ነው።—ሉቃስ 6:36
ጸሎት እና በአምላክ መተማመን
ኢየሱስ ስብከቱን በመቀጠል አድማጮቹን “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ” በማለት አሳሰባቸው። አክሎም አንዳንዶች ለአምላክ ያደሩ መስለው ለመታየት የሚፈጽሙትን የግብዝነት ድርጊት በማውገዝ እንዲህ አለ፦ “ምጽዋት በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ።” (ማቴዎስ 6:1, 2) ትኩረት በማይስብ መንገድ ምጽዋት መስጠት የተሻለ ነው።
ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና።” ከዚህ በተቃራኒ ምን ማድረግ እንደሚገባን ሲገልጽ “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:5, 6) ኢየሱስ በሕዝብ ፊት መጸለይ ሁልጊዜ ስህተት እንደሆነ መግለጹ አይደለም፤ እሱ ራሱም በሕዝብ ፊት ጸልዮአል። ኢየሱስ ያወገዘው፣ አድማጮችን ለማስደመምና አድናቆት ለማትረፍ ተብለው የሚቀርቡ ጸሎቶችን ነው።
ኢየሱስ “በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” በማለት ሕዝቡን መከራቸው። (ማቴዎስ 6:7) እንዲህ ሲል ስለ አንድ ጉዳይ ደጋግሞ መጸለይ ስህተት እንደሆነ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተሸመደዱ ሐሳቦችን ‘ደጋግሞ’ በማነብነብ የሚቀርብ ጸሎትን ማውገዙ ነው። ቀጥሎም ኢየሱስ ሰባት ልመናዎችን ያካተተ የጸሎት ናሙና ሰጠ። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ከአምላክ የመግዛት መብትና ከዓላማዎቹ ጋር የተያያዙ ናቸው፤ ይኸውም በአምላክ ስም መቀደስ፣ በመንግሥቱ መምጣትና በፈቃዱ መፈጸም ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህን ነጥቦች ከጠቀስን በኋላ ስለ ራሳችን ጉዳይ ይኸውም ስለ ዕለታዊ ምግባችንና የኃጢአት ይቅርታ ስለ ማግኘት እንዲሁም አምላክ ከአቅማችን በላይ እንድንፈተን እንዳይፈቅድና ከክፉው እንዲያድነን መጸለይ እንችላለን።
ለቁሳዊ ንብረት ምን ያህል ቦታ ልንሰጥ ይገባል? ኢየሱስ ሕዝቡን “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ” በማለት አሳስቧቸዋል። ይህ እንዴት ያለ ምክንያታዊ ምክር ነው! ቁሳዊ ሀብት መጥፋቱ አይቀርም፤ እንዲህ ዓይነት ንብረት ማከማቸታችንም በአምላክ ዘንድ የሚያስገኝልን ዋጋ የለም። በመሆኑም ኢየሱስ ቀጥሎ “በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ” ብሏል። ይህን ማድረግ የምንችለው በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ ለምናቀርበው አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት ነው። በአምላክ ፊት ያለንን ጥሩ አቋም ወይም ይህ የሚያስገኝልንን የዘላለም ሕይወት ሽልማት ማንም ሊወስድብን አይችልም። በእርግጥም ኢየሱስ “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል” ማለቱ ምንኛ ትክክል ነው።—ማቴዎስ 6:19-21
ኢየሱስ ይህን ነጥብ ለማጉላት አንድ ምሳሌ ተናገረ፦ “የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዓይንህ ምቀኛ ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል።” (ማቴዎስ 6:22, 23) በትክክል የሚያይ ዓይን ለሰውነታችን እንደ መብራት ነው። ሆኖም ዓይናችን በትክክል ማየት እንዲችል በአንድ ነገር ላይ ማተኮር አለበት፤ ይህ ካልሆነ ስለ ሕይወት የተዛባ አመለካከት ልናዳብር እንችላለን። አምላክን ከማገልገል ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን በመሰብሰብ ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ ‘መላ ሰውነታችን ጨለማ ይሆናል’፤ ምናልባትም ጨለማ ወደሆነ ወይም ሐቀኝነት ወደጎደለው ነገር ልንሳብ እንችላለን።
ቀጥሎም ኢየሱስ ኃይለኛ መልእክት ያዘለ ምሳሌ ተናገረ፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።”—ማቴዎስ 6:24
ከኢየሱስ አድማጮች አንዳንዶቹ ስለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ የአምላክን አገልግሎት ካስቀደሙ ስለ ቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ እንደሌለባቸው አረጋገጠላቸው። “የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል።”—ማቴዎስ 6:26
በተራራው ላይ ስላሉት የሜዳ አበቦችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ “ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም” አለ። ይህ ምን ያሳያል? ኢየሱስ “አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?” ብሏል። (ማቴዎስ 6:29, 30) ከዚያም ኢየሱስ የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ማሳሰቢያ ሰጠ፦ “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። . . . በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴዎስ 6:31-33
ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
ሐዋርያትም ሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሌሎቹ ሰዎች ሕይወታቸውን አምላክን በሚያስደስት መንገድ መምራት ቢፈልጉም ካሉበት ሁኔታ አንጻር ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ ፈሪሳውያን ነቃፊዎች ከመሆናቸውም ሌላ በሌሎች ላይ ያላንዳች ርኅራኄ ይፈርዳሉ። በመሆኑም ኢየሱስ አድማጮቹን “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል” በማለት አሳሰባቸው።—ማቴዎስ 7:1, 2
ኢየሱስ፣ ከሚገባው በላይ ነቃፊ የነበሩትን ፈሪሳውያን አካሄድ መከተል አደገኛ መሆኑን ለማሳየት “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላል? ሁለቱም ተያይዘው ጉድጓድ ውስጥ አይወድቁም?” አላቸው። ታዲያ የኢየሱስ አድማጮች ለሌሎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ነቃፊዎች መሆን አይኖርባቸውም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ከባድ በደል ነው። ኢየሱስ የሚከተለውን ጥያቄ አቅርቧል፦ “በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።”—ሉቃስ 6:39-42
ይህ ሲባል ግን ደቀ መዛሙርቱ የሌሎችን ሁኔታ መገምገም የለባቸውም ማለት አይደለም። ኢየሱስ “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 7:6) በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉት እውነቶች እንደ ዕንቁ ውድ ናቸው። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ለእነዚህ ውድ እውነቶች ምንም ዓይነት አድናቆት ባለማሳየት በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ እንስሳት ሊሆኑ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ እነዚህን ሰዎች ትተው እውነትን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑትን መፈለግ አለባቸው።
ኢየሱስ እንደገና ስለ ጸሎት በማንሳት በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ሲገልጽ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል” ብሏል። አምላክ ለጸሎት ምላሽ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ለማጉላት የሚከተለውን ጥያቄ አነሳ፦ “ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? . . . ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!”—ማቴዎስ 7:7-11
ኢየሱስ በመቀጠል ታዋቂ የሆነውን የሥነ ምግባር ደንብ ሰጠ፦ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።” ታዲያ ማንኛችንም ብንሆን ይህን መልካም ምክር ልብ ልንለውና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ተግባራዊ ልናደርገው አይገባም? ይሁንና ኢየሱስ በመቀጠል የተናገረው ሐሳብ እንደሚያሳየው ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:12-14
አንዳንዶች፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ መጓዛቸውን እንዳይቀጥሉ ለማሳት ይጥራሉ፤ በመሆኑም ኢየሱስ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 7:15) ኢየሱስ ጥሩ ዛፎችና መጥፎ ዛፎች በፍሬያቸው ተለይተው ሊታወቁ እንደሚችሉ ተናገረ። ከሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሐሰተኛ ነቢያትን በትምህርታቸውና በምግባራቸው ለይተን ማወቅ እንችላለን። በእርግጥም ኢየሱስ እንደገለጸው አንድን ሰው የእሱ ደቀ መዝሙር የሚያሰኘው ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱ ጭምር ነው። ጌታቸው ኢየሱስ እንደሆነ እየተናገሩ የአባቱን ፈቃድ የማያደርጉ ሰዎችስ? “‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ” ብሏል።—ማቴዎስ 7:23
ኢየሱስ ስብከቱን ሲደመድም እንዲህ አለ፦ “ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም።” (ማቴዎስ 7:24, 25) ቤቱ ጸንቶ መቆም የቻለው ለምንድን ነው? ሰውየው “በጥልቀት ቆፍሮ በዓለት ላይ” መሠረቱን ስለጣለ ነው። (ሉቃስ 6:48) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተናገረውን ከመስማት ያለፈ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። የተማርነውን ‘በተግባር ለማዋል’ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
አንድ ሰው፣ የኢየሱስን ቃል “ሰምቶ በተግባር የማያውል” ከሆነስ? ይህ ሰው “ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።” (ማቴዎስ 7:26) እንዲህ ያለው ቤት፣ ዶፍና ነፋስ ሲመታው እንዲሁም ጎርፍ ሲመጣበት ይደረመሳል።
ሕዝቡ በኢየሱስ ትምህርት አሰጣጥ እጅግ ተደነቁ። የሚያስተምራቸው እንደ ሃይማኖት መሪዎች ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነው። ከአድማጮቹ ብዙዎቹ የእሱ ደቀ መዛሙርት ሳይሆኑ አልቀሩም።