የጥናት ርዕስ 38
ከመንፈሳዊ ቤተሰብህ ጋር ተቀራረብ
“ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ . . . ላርግ ነው።”—ዮሐ. 20:17
መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን
ማስተዋወቂያa
1. ታማኝ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ሊኖራቸው ይችላል?
የይሖዋን አምላኪዎች ያቀፈው ቤተሰብ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” የሆነውን ኢየሱስን እና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መላእክት ያካትታል። (ቆላ. 1:15፤ መዝ. 103:20) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ታማኝ ሰዎች ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው መመልከት እንደሚችሉ ጠቁሟል። ለደቀ መዛሙርቱ በላከው መልእክት ላይ ይሖዋን ‘አባቴና አባታችሁ’ በማለት ጠርቶታል። (ዮሐ. 20:17) በተጨማሪም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ቤተሰብ ክፍል እንሆናለን።—ማር. 10:29, 30
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 አንዳንዶች ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባታቸው መመልከት ይከብዳቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ፍቅራቸውን እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ ግራ ይገባቸው ይሆናል። ይሖዋን፣ የሚወደንና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚፈልግ አፍቃሪ አባታችን አድርገን እንድንመለከተው ኢየሱስ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በምንይዝበት መንገድ ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችልባቸውን መንገዶች እንማራለን።
ይሖዋ ወደ እሱ እንድትቀርብ ይፈልጋል
3. ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?
3 ይሖዋ አፍቃሪ አባት ነው። ኢየሱስ፣ እሱ ለይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል፤ በሌላ አባባል ይሖዋን እንደ አስፈሪ ገዢ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ ልናነጋግረው እንደምንችል አፍቃሪ አባታችን አድርገን እንድንመለከተው ይፈልጋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማራቸው ጸሎት ይህን ማየት እንችላለን። በጸሎቱ ናሙና ላይ ይሖዋን “አባታችን” ብለው እንዲጠሩት ነግሯቸዋል። (ማቴ. 6:9) ኢየሱስ ይሖዋን “ሁሉን ቻይ፣” “ፈጣሪ” ወይም ‘የዘላለም ንጉሥ’ ብለን እንድንጠራው ሊነግረን ይችል ነበር፤ ምክንያቱም ሁሉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ የማዕረግ ስሞች ናቸው። (ዘፍ. 49:25፤ ኢሳ. 40:28፤ 1 ጢሞ. 1:17) ሆኖም ኢየሱስ “አባታችን” የሚለውን ፍቅር የሚንጸባረቅበት መጠሪያ እንድንጠቀም አስተምሮናል።
4. ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?
4 ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት መመልከት ይከብድሃል? አንዳንዶቻችን ይከብደናል። የአባት ፍቅር ሳናገኝ በማደጋችን የተነሳ አባትን አፍቃሪ አድርጎ ማሰብ ይከብደን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ስሜታችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን ማወቃችን በጣም ያጽናናናል። ይሖዋ ወደ እኛ መቅረብ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት የሚያበረታታን ለዚህ ነው። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ ይወደናል፤ እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ አባት እንደሚሆንልን ቃል ገብቶልናል።
5. በሉቃስ 10:22 መሠረት ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ ይሖዋን በደንብ ያውቀዋል፤ እንዲሁም ባሕርያቱን ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ያለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ አባታችንን ማክበርና መታዘዝ፣ እሱን ከማሳዘን መቆጠብ እንዲሁም የእሱን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ልክ እንደ ታላቅ ወንድም አስተምሮናል። ከሁሉ በላይ ግን ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምን ያህል ደግና አፍቃሪ እንደሆነ በሕይወቱ አሳይቶናል። (ሉቃስ 10:22ን አንብብ።) ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
6. ይሖዋ ኢየሱስን የሰማው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
6 ይሖዋ ልጆቹ ሲያነጋግሩት ይሰማቸዋል። ይሖዋ የበኩር ልጁን እንደሰማው የሚያሳዩ ምሳሌዎችን እንመልከት። ይሖዋ ልጁ ምድር ላይ ሳለ ያቀረባቸውን በርካታ ጸሎቶች እንደሰማ ምንም ጥያቄ የለውም። (ሉቃስ 5:16) ኢየሱስ ከባድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ለምሳሌ 12ቱን ሐዋርያቱን ሲመርጥ ያቀረበውን ጸሎት ሰምቶታል። (ሉቃስ 6:12, 13) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኢየሱስ በጭንቀት በተዋጠበት ጊዜ ያቀረበውን ጸሎት ሰምቶታል። ኢየሱስ ልክ አልፎ ከመሰጠቱ በፊት፣ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከባድ ፈተና በተመለከተ ወደ አባቱ አጥብቆ ጸልዮ ነበር። ይሖዋ የኢየሱስን ጸሎት ከመስማት ባለፈ ውድ ልጁን ለማበረታታት መልአክ ልኮለታል።—ሉቃስ 22:41-44
7. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ማወቃችን ምን እንዲሰማን ያደርጋል?
7 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል፤ እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜና ከሁሉ በተሻለው መንገድ መልስ ይሰጣቸዋል። (መዝ. 116:1, 2) በሕንድ የምትኖር አንዲት እህት በሕይወቷ ውስጥ ይህን ያየችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ይህች እህት በከባድ ጭንቀት ትዋጥ ነበር፤ እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቃ ጸልያ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ጭንቀትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ የሚናገረው የግንቦት 2019 JW ብሮድካስቲንግ ልክ የሚያስፈልገኝን እርዳታ ሰጥቶኛል። ይህ ቪዲዮ የጸሎቴ መልስ ነበር።”
8. ይሖዋ ለኢየሱስ ፍቅሩን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
8 ይሖዋ፣ ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ፍቅር እንዳሳየውና እንደተንከባከበው ሁሉ ለእኛም ፍቅር ያሳየናል እንዲሁም ይንከባከበናል። (ዮሐ. 5:20) ይሖዋ የኢየሱስን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ሥጋዊ ፍላጎት በሙሉ አሟልቶለታል። በተጨማሪም ይሖዋ ልጁን እንደሚወደውና እንደሚደሰትበት ከመግለጽ ወደኋላ አላለም። (ማቴ. 3:16, 17) ኢየሱስም የሚወደው ሰማያዊ አባቱ ከጎኑ እንደሆነ ስለሚያውቅ መቼም ቢሆን ብቻውን እንደሆነ ተሰምቶት አያውቅም።—ዮሐ. 8:16
9. ይሖዋ እንደሚወደን እንዴት እናውቃለን?
9 ሁላችንም ልክ እንደ ኢየሱስ የይሖዋን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች አይተናል። እስቲ አስበው፤ ይሖዋ ወደ ራሱ ስቦናል፤ እንዲሁም ደስተኛ እንድንሆንና የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እንድናገኝ ሲል አፍቃሪ የሆነና አንድነት ያለው መንፈሳዊ ቤተሰብ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 6:44) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ ያቀርብልናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለኑሮ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች እንድናገኝ ይረዳናል። (ማቴ. 6:31, 32) ይሖዋ ስላሳየን ፍቅር ስናስብ እኛም ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል።
መንፈሳዊ ቤተሰብህን በምትይዝበት መንገድ ይሖዋን ምሰል
10. ይሖዋ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከሚይዝበት መንገድ ምን እንማራለን?
10 ይሖዋ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይወዳቸዋል። እኛ ግን የመንፈሳዊ ቤተሰባችንን አባላት መውደድና ለእነሱ ፍቅራችንን መግለጽ አንዳንድ ጊዜ ሊከብደን ይችላል። ምክንያቱም ሁላችንም ባሕላችንና አስተዳደጋችን የተለያየ ነው። በተጨማሪም ሁላችንም ስህተት ስለምንሠራ ሌሎችን ማበሳጨታችን ወይም ማሳዘናችን አይቀርም። ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ቤተሰባችን መካከል ያለው ፍቅር እንዲጠናከር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። እንዴት? ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር በማሳየት ረገድ አባታችንን በመምሰል ነው። (ኤፌ. 5:1, 2፤ 1 ዮሐ. 4:19) ከይሖዋ ምሳሌ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት።
11. ኢየሱስ ‘ከአንጀት በመራራት’ ረገድ የይሖዋን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ‘ከአንጀት ይራራልናል።’ (ሉቃስ 1:78) ሩኅሩኅ የሆነ ሰው ሌሎች ሲሠቃዩ ሲያይ ያዝናል፤ እንዲሁም እነሱን ለመርዳትና ለማጽናናት የሚያስችል መንገድ ይፈልጋል። ኢየሱስ የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። (ዮሐ. 5:19) በአንድ ወቅት ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) የኢየሱስ ርኅራኄ ከስሜት ባለፈ በተግባርም ተገልጿል። የታመሙትን ፈውሷል፤ እንዲሁም ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው’ ሰዎች እረፍት ሰጥቷል።—ማቴ. 11:28-30፤ 14:14
12. ርኅራኄ ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ።
12 ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ርኅራኄ ማሳየት እንድንችል በመጀመሪያ፣ ስላጋጠማቸው ችግር ማሰብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት ከባድ የጤና ችግር ይኖርባት ይሆናል። ስላለባት ችግር ብዙ ጊዜ ባታወራም በአንዳንድ መንገዶች እርዳታ ቢደረግላት ደስ እንደሚላት ጥያቄ የለውም። ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት ተቸግራ ይሆን? ምግብ በማዘጋጀት ወይም ቤት በማጽዳት ልንረዳት እንችል ይሆን? አሊያም ደግሞ አንድ ወንድም ከሥራው ተፈናቅሎ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ማንነታችንን ሳናሳውቅ የተወሰነ ገንዘብ ብንሰጠው ሌላ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ሊረዳው ይችላል።
13-14. እንደ ይሖዋ ልግስና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ለጋስ አምላክ ነው። (ማቴ. 5:45) ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ርኅራኄ ለማሳየት እነሱ እስኪጠይቁን መጠበቅ አያስፈልገንም። ልክ እንደ ይሖዋ ቅድሚያውን ወስደን ልንረዳቸው እንችላለን። ይሖዋ በየቀኑ ፀሐይ ያወጣልናል፤ እንዲህ እንዲያደርግልን መጠየቅ እንኳ አያስፈልገንም። ደግሞም የፀሐይ ሙቀት የሚጠቅመው አመስጋኝ የሆኑ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው ነው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ማሟላቱ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው ቢባል አትስማማም? ይሖዋ በጣም ደግና ለጋስ በመሆኑ በእጅጉ እንወደዋለን!
14 በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሰማያዊ አባታቸውን ምሳሌ በመከተል ቅድሚያውን ወስደው ልግስና ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ2013 ሃያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ በፊሊፒንስ ከፍተኛ ውድመት አስከትሎ ነበር። ብዙ ወንድሞችና እህቶች ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። ሆኖም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ተረባርበው ረድተዋቸዋል። ብዙዎች የገንዘብ መዋጮ በማድረግ አሊያም መጠነ ሰፊ በሆነው የግንባታ ሥራ በመካፈል እገዛ አበርክተዋል፤ በዚህም ምክንያት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ 750 የሚጠጉ ቤቶችን ማደስ ወይም መልሶ መገንባት ተችሏል! በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመደገፍ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል። ለመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት በአፋጣኝ ስንደርስላቸው እንደምንወዳቸው እናሳያለን።
15-16. በሉቃስ 6:36 መሠረት የሰማዩን አባታችንን መምሰል የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ምንድን ነው?
15 ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ ነው። (ሉቃስ 6:36ን አንብብ።) የሰማዩ አባታችን በየዕለቱ ምሕረት ያደርግልናል። (መዝ. 103:10-14) ኢየሱስም ተከታዮቹ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ምሕረትና ይቅር ባይነት አሳይቷቸዋል። ኢየሱስ ለኃጢአታችን ይቅርታ እንድናገኝ ሲል ሕይወቱን እንኳ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) ይሖዋና ኢየሱስ መሐሪና ይቅር ባይ መሆናቸውን ማወቅህ ወደ እነሱ ይበልጥ ለመቅረብ አያነሳሳህም?
16 እኛም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ‘በነፃ ይቅር በማለት’ በመንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ ያለው ፍቅር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። (ኤፌ. 4:32) እርግጥ ነው፣ ሌሎችን ይቅር ማለት አንዳንድ ጊዜ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። አንዲት እህት “እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ” የሚለው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ይህን ለማድረግ እንደረዳት ተናግራለች።b እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ይህን ርዕስ ማጥናቴ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ እንዳየው፣ ይኸውም ይቅር ማለት የሚያስገኘውን ጥቅም እንዳስተውል ረድቶኛል። ርዕሱ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ሲባል መጥፎ ባሕርያቸውን ትክክል እንደሆነ አድርጎ መቀበል ወይም ያደረሱትን ጉዳት አቅልሎ መመልከት ማለት እንዳልሆነ ይገልጻል። ከዚህ ይልቅ፣ ይቅር እንላለን ሲባል በተፈጸመብን በደል ምክንያት ቅሬታ እንዳያድርብንና ሰላማችንን እንዳናጣ ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው።” ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በነፃ ይቅር በማለት እንደምንወዳቸው እናሳያለን፤ የሰማዩን አባታችንን ይሖዋንም እንመስላለን።
በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ያለህን ቦታ ከፍ አድርገህ ተመልከተው
17. በማቴዎስ 5:16 መሠረት የሰማዩን አባታችንን ማስከበር የምንችለው እንዴት ነው?
17 አፍቃሪ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል መሆን ትልቅ መብት ነው። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች አብረውን ይሖዋን እንዲያመልኩ እንፈልጋለን። በመሆኑም የይሖዋንም ሆነ የሕዝቦቹን ስም የሚያጎድፍ ምንም ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሰዎች ስለ ይሖዋ ለመማርና እሱን ለማገልገል እንዲነሳሱ የሚያደርግ ምግባር ሊኖረን ይገባል።—ማቴዎስ 5:16ን አንብብ።
18. በድፍረት ምሥክርነት ለመስጠት ምን ሊረዳን ይችላል?
18 አንዳንዶች የሰማዩን አባታችንን በመታዘዛችን ምክንያት ያቃልሉን ወይም ያሳድዱን ይሆናል። በዚህ የተነሳ ስለ እምነታችን ለሌሎች መናገር የሚያስፈራን ቢሆንስ? የይሖዋና የልጁ እርዳታ እንደማይለየን መተማመን እንችላለን። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት ወይም ምን ብለው መናገር እንዳለባቸው ሊጨነቁ እንደማይገባ ነግሯቸዋል። ሊጨነቁ የማይገባው ለምንድን ነው? ኢየሱስ መልሱን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።”—ማቴ. 10:19, 20
19. ሮበርት በድፍረት ምሥክርነት የሰጠው እንዴት ነው?
19 የሮበርትን ምሳሌ እንመልከት። ሮበርት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ ነበር፤ በወቅቱ ሮበርት የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ውስን ነበር። ሮበርት የገለልተኝነት አቋም የያዘው ለክርስቲያን ወንድሞቹ ባለው ፍቅር ምክንያት እንደሆነ በፍርድ ቤቱ ፊት በድፍረት ተናገረ። በመንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ ያለውን ቦታ ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። ዳኛው “ወንድሞችህ እነማን ናቸው?” ብለው በድንገት ጠየቁት። ሮበርት እንዲህ ያለ ጥያቄ ይቀርብልኛል ብሎ አልጠበቀም ነበር፤ ሆኖም በዚያ ቀን ያነበበው የዕለት ጥቅስ ወዲያውኑ ትዝ አለው። የዕለቱ ጥቅስ ማቴዎስ 12:50 ነበር፤ ጥቅሱ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው” ይላል። ሮበርት አዲስ ጥናት ቢሆንም የይሖዋ መንፈስ ይህን ጥያቄ ጨምሮ በርካታ ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን እንዲመልስ ረድቶታል። ይሖዋ በሮበርት በጣም ኮርቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በእሱ ታምነን በድፍረት ምሥክርነት ስንሰጥ ይኮራብናል።
20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? (ዮሐንስ 17:11, 15)
20 አፍቃሪ የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል የመሆን መብታችንን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል። ከሁሉ የተሻለ አባት እንዲሁም የሚወዱን ወንድሞችና እህቶች አሉን። ለዚህ ስጦታ ያለን አድናቆት እንዳይቀንስ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሰይጣንና ክፉ የሆኑት ተከታዮቹ የሰማዩ አባታችን ለእኛ ያለውን ፍቅር እንድንጠራጠር ለማድረግ እንዲሁም በመካከላችን ያለውን አንድነት ለማደፍረስ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁንና ኢየሱስ የቤተሰባችን አንድነት እንዳይደፈርስ የሰማዩ አባታችን እንዲጠብቀን ልመና አቅርቦልናል። (ዮሐንስ 17:11, 15ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን ጸሎት እየመለሰው እንደሆነ ማየት እንችላለን። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የሰማዩ አባታችን እንደሚወደንና እንደሚደግፈን መቼም ቢሆን አንጠራጠር። ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ጥረት ማድረጋችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች
a አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን የያዘ ቤተሰብ ውስጥ የመታቀፍ ልዩ መብት አግኝተናል። ሁላችንም በመካከላችን ያለውን ፍቅር ማጠናከር እንፈልጋለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ እኛን በሚይዝበት መንገድ ሌሎችን በመያዝ እንዲሁም የኢየሱስን ብሎም የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ምሳሌ በመከተል ነው።
b የኅዳር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-30ን ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ይሖዋ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስን ለማበረታታት መልአክ ልኮለታል።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ብዙዎች ምግብ ለማዘጋጀትና ለማከፋፈል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ልጅ፣ እናቷ እያገዘቻት እስር ቤት ላለ አንድ ወንድም የሚያበረታታ ደብዳቤ ስታዘጋጅ።