ኢየሱስ በትሕትና ረገድ አርዓያ ትቷል
“እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።”—ዮሐ. 13:15
1, 2. ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለሐዋርያቱ ምን ተጨባጭ ትምህርት ሰጥቷቸዋል?
ጊዜው ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የመጨረሻው ምሽት ሲሆን በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ደርብ ላይ ከሐዋርያቱ ጋር ነበር። ራት እየበሉ ሳለ ኢየሱስ ተነስቶ መደረቢያዎቹን አስቀመጠ። ፎጣ ወስዶም አሸረጠ። ቀጥሎም በመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና በፎጣው ማድረቅ ጀመረ። ከዚያም መደረቢያዎቹን ለበሰ። ኢየሱስ ይህን ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ያከናወነው ለምንድን ነው?—ዮሐ. 13:3-5
2 ኢየሱስ እንዲህ የሚል ማብራሪያ ሰጥቷል፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? . . . እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።” (ዮሐ. 13:12-15) ኢየሱስ እንዲህ ያለ ዝቅተኛ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆን ከሐዋርያቱ አእምሮ ፈጽሞ የማይጠፋና በቀጣዮቹ ጊዜያት ትሕትና እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ተጨባጭ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።
3. (ሀ) ኢየሱስ በሁለት የተለያዩ ወቅቶች የትሕትናን አስፈላጊነት ያጎላው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚብራራው ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ የትሕትናን አስፈላጊነት ለሐዋርያቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸላቸው እግራቸውን ባጠበበት ወቅት አልነበረም። ከዚህ ቀደም ከሐዋርያቱ መካከል አንዳንዶቹ የፉክክር መንፈስ ባሳዩ ጊዜ አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ አጠገቡ ካቆመ በኋላ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ይህን ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝንም ይቀበላል። ምክንያቱም ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።” (ሉቃስ 9:46-48) ኢየሱስ በሌላ ወቅት አገልግሎቱን እያከናወነ ሳለ ፈሪሳውያን ራሳቸውን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ እንዳላቸው በማስተዋል “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” ሲል ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 14:11) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተከታዮቹ ትሑት እንዲሆኑ ይኸውም ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ እንዲሁም ከኩራትና ከእብሪት እንዲርቁ ይጠብቅባቸዋል። እስቲ የኢየሱስን አርዓያ የመከተል ግብ በመያዝ ትሕትና በማሳየት ረገድ የተወልንን ምሳሌ በጥንቃቄ እንመርምር። በተጨማሪም የትሕትና ባሕርይ ያለው ሰው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሊጠቅም የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
“ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም”
4. የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?
4 የአምላክ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ትሕትና አሳይቷል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር በውል የማይታወቁ ዓመታት አሳልፏል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢሳይያስ መጽሐፍ የአምላክ ልጅ ከአባቱ ጋር የነበረውን የጠበቀ ዝምድና አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል። ልዑል እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶታል፤ እኔም ዐመፀኛ አይደለሁም፤ ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም።” (ኢሳ. 50:4, 5) የአምላክ ልጅ የትሕትና ባሕርይ ያሳይ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት ይከታተል ነበር። ከእውነተኛው አምላክ የመማር ፈቃደኝነትም ሆነ ጉጉት ነበረው። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ምሕረት በማድረግ ያሳየውን የትሕትና ምሳሌ በቅርብ የመመልከት አጋጣሚ ነበረው።
5. የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሆነው ኢየሱስ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ በትሕትናና ቦታን በማወቅ ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
5 የአምላክ አንድያ ልጅ ያለው ዓይነት አመለካከት የነበራቸው በሰማይ የሚኖሩት ሁሉም መንፈሳዊ ፍጥረታት አይደሉም። ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው መልአክ ከይሖዋ የመማር ፍላጎት አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ የትሕትና ተቃራኒ የሆኑት ራስን የማዋደድና የኩራት ባሕርያት ተጽዕኖ እንዲያሳድሩበት የፈቀደ ከመሆኑም በላይ በይሖዋ ላይ ዓምጿል። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በሰማይ የነበረው ቦታ እንደሚያንሰው ሆኖ አልተሰማውም፤ ወይም ደግሞ በሥልጣኑ ያለ አግባብ ለመጠቀም አልተነሳሳም። ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ሆኖ “የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ” ሥልጣኑ ከሚፈቅድለት ውጭ አልፎ አልሄደም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ልጅ የትሕትና ባሕርይ አሳይቷል፤ ደግሞም ቦታውን ያውቅ ነበር። ኢየሱስ፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻው ፈራጅ የሆነው ይሖዋ፣ በራሱ መንገድና ጊዜ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ጉዳዩን ለእሱ መተው መርጧል።—ይሁዳ 9ን አንብብ።
6. ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ እንዲያገለግል የተሰጠውን ተልእኮ በመቀበል ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ከተማራቸው ነገሮች መካከል መሲሕ ሆኖ በምድር ላይ ስለሚያሳልፈው ሕይወት በዝርዝር የሚናገሩ ትንቢቶች እንደሚገኙበት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙት አስቀድሞ ሳያውቅ አይቀርም። ያም ሆኖ ኢየሱስ ምድር ላይ እንዲኖርና ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ሆኖ እንዲሞት የተሰጠውን ተልእኮ ተቀብሏል። ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ አንድያ ልጅ ያሳየውን ትሕትና ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እሱ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን ነጥቆ ሊወስደው እንደሚገባ ነገር አድርጎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ አደረገ፤ እንደ ባሪያ ሆኖም በሰው አምሳል መጣ።”—ፊልጵ. 2:6, 7
ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ ‘ራሱን ዝቅ አድርጓል’
7, 8. ኢየሱስ በልጅነት ዕድሜውና በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ትሕትና ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
7 ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “በሰው አምሳል በመጣ ጊዜ ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 2:8) ኢየሱስ ከልጅነት ዕድሜው አንስቶ ልንከተለው የሚገባ የትሕትና ምሳሌ ትቶልናል። አሳዳጊ ወላጆቹ ዮሴፍና ማርያም ፍጹም ባይሆኑም እንኳ በትሕትና “ይታዘዛቸው ነበር።” (ሉቃስ 2:51) ይህ ለልጆች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ልጆች ለወላጆቻቸው በፈቃደኝነት የሚገዙ ከሆነ አምላክ ይባርካቸዋል።
8 ኢየሱስ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ለይሖዋ ፈቃድ ቅድሚያ በመስጠት ትሕትና አሳይቷል። (ዮሐ. 4:34) ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሲያከናውን በአምላክ የግል ስም ይጠቀም ነበር፤ ከዚህም በላይ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ካስተማረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ከምንም ነገር በፊት የጠቀሰው ስሙን ነበር። (ማቴ. 6:9) በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ የይሖዋ ስም መቀደስ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ እንደሚገባ አስተምሯል። እሱ ራሱም ሕይወቱን የመራው በዚህ መንገድ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ለማጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ስምህን ለእነሱ [ለሐዋርያቱ] አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ” ማለት ችሏል። (ዮሐ. 17:26) ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ በምድር ላይ ለፈጸመው ሥራ መመስገን ያለበት ይሖዋ እንደሆነ ተናግሯል።—ዮሐ. 5:19
9. ዘካርያስ መሲሑን አስመልክቶ ምን ትንቢት ተናግሯል? ኢየሱስ ይህን ትንቢት የፈጸመውስ እንዴት ነው?
9 ዘካርያስ መሲሑን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ጽፏል፦ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻ[ድ]ቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል።” (ዘካ. 9:9) ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል ቀደም ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ወቅት ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። ሕዝቡ መደረቢያዎቻቸውንና የዛፍ ቅንጫፎችን መንገድ ላይ አነጠፉ። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ መላዋ ከተማ ተናወጠች። ሕዝቡ እንደ ንጉሥ ታላቅ አቀባበል ቢያደርግለትም እንኳ ኢየሱስ በትሕትና መመላለሱን ቀጥሏል።—ማቴ. 21:4-11
10. ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ መሆኑ ምን ነገር እንዲረጋገጥ አስችሏል?
10 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የተከተለው የታዛዥነትና የትሕትና ጎዳና በመከራ እንጨት ላይ ተሰቆሎ በሞተ ጊዜ ተደምድሟል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ሰዎች እጅግ ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው መኖር እንደሚችሉ በማያሻማ መልኩ አረጋግጧል። በተጨማሪም ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው የሚለው የሰይጣን ክስ ትክክል እንዳልሆነ አሳይቷል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) ደግሞም ክርስቶስ ፍጹም በሆነ መልኩ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክልና በጽድቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስመሥክሯል። ይሖዋ ትሑት የሆነው ልጁ ያሳየውን የማይናወጥ ታማኝነት ሲመለከት እንደተደሰተ ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 27:11ን አንብብ።
11. የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እምነት ላላቸው የሰው ልጆች ምን አጋጣሚ ከፍቷል?
11 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በመሞት ለሰው ልጆች ቤዛ ከፍሏል። (ማቴ. 20:28) ይህም በአንድ በኩል ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ የከፈተ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጽድቅ የሚጠይቀው መሥፈርት እንዲሟላ አድርጓል። ጳውሎስ “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊትም ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ተብለው በመጠራት ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል” በማለት ጽፏል። (ሮም 5:18) የኢየሱስ ሞት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሰማይ የማይሞት ሕይወት የማግኘት፣ “ሌሎች በጎች” ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል።—ዮሐ. 10:16፤ ሮም 8:16, 17
“በልቤ ትሑት ነኝ”
12. ኢየሱስ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ገርነትና ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ “የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ” የሚል ግብዣ አቅርቧል። አክሎም “ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል። (ማቴ. 11:28, 29) ኢየሱስ ትሑትና ገር መሆኑ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ደግና የማያዳላ እንዲሆን አነሳስቶታል። ከደቀ መዛሙርቱ በሚጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ነበር፤ ደግሞም ያመሰግናቸውና ያበረታታቸው ነበር። ብቃት እንደሚጎድላቸው ወይም ዋጋ እንደሌላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው አላደረገም። ኢየሱስ ጨካኝ ወይም ጨቋኝ ሰው አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ ተከታዮቹ ወደ እሱ በመቅረብና ያስተማረውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ እረፍት ማግኘት ችለዋል፤ ምክንያቱም ቀንበሩ ልዝብ፣ ሸክሙም ቀላል ነው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ አይከብዳቸውም ነበር።—ማቴ. 11:30
13. ኢየሱስ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ተራው የእስራኤል ሕዝብ ችግር ላይ ወድቆ ስለነበር ርኅራኄ ለማሳየት ተገፋፍቷል፤ ደግሞም በፍቅር ተነሳስቶ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አሟልቶላቸዋል። ለምሳሌ በርጤሜዎስ የተባለ ዓይነ ስውርና በስም ያልተጠቀሰ ሌላ ዓይነ ስውር በኢያሪኮ አጠገብ ተቀምጠው ይለምኑ ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንዲረዳቸው ደጋግመው ለመኑ፤ ሕዝቡ ግን ዝም እንዲሉ ገሠጻቸው። የዓይነ ስውሮቹን ልመና ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ በጣም ቀላል ነገር ነው! ይሁንና ኢየሱስ ስላዘነላቸው ወደ እሱ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ የዓይናቸውን ብርሃን መለሰላቸው። አዎ፣ ኢየሱስ ትሕትና በማንጸባረቅና ኃጢአተኛ ለሆኑ ምስኪን ሰዎች ምሕረት በማሳየት ይሖዋን መስሏል።—ማቴ. 20:29-34፤ ማር. 10:46-52
‘ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይደረጋል’
14. ኢየሱስ ያሳየው ትሕትና ምን ጥቅሞች አስገኝቷል?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው ትሕትና ለደስታ ምክንያት ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል። ይሖዋ የሚወደው ልጁ ለመለኮታዊው ፈቃድ በትሕትና መገዛቱን ሲመለከት ተደስቷል። ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ገርና በልቡ ትሑት መሆኑ እረፍት ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ የተወው ምሳሌ፣ ያስተማረው ትምህርትና ከልቡ ያመሰግናቸው የነበረ መሆኑ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ተራው ሕዝብ ኢየሱስ ካሳየው ትሕትና ተጠቅሟል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ከእሱ እርዳታና ማበረታቻ እንዲሁም ካስተማረው ትምህርት ጥቅም አግኝቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ከቤዛው ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዘላቂ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።
15. ኢየሱስ ትሑት መሆኑ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል?
15 ኢየሱስን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ትሑት መሆኑ ጥቅም አስገኝቶለታል? አዎ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” ማለቱ ይህን ያሳያል። (ማቴ. 23:12) የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ [ለኢየሱስ] የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤ ምላስም ሁሉ አባት ለሆነው አምላክ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በይፋ እውቅና እንዲሰጥ ነው።” ኢየሱስ በምድር ላይ የትሕትናና የታማኝነት ጎዳና በመከተሉ ይሖዋ አምላክ በሰማይም ሆነ በምድር ባሉ ፍጥረታት ላይ ሥልጣን በመስጠት ልጁን ከፍ ከፍ አድርጎታል።—ፊልጵ. 2:9-11
ኢየሱስ ‘ለእውነትና ለትሕትና ሲል ይገሠግሣል’
16. የአምላክ ልጅ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ትሕትና ማሳየቱን እንደሚቀጥል ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
16 የአምላክ ልጅ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ትሕትና ማሳየቱን ይቀጥላል። ኢየሱስ በሰማይ ካለው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ በጠላቶቹ ላይ የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ መዝሙራዊው “ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ፣ ሞገስን ተጐናጽፈህ በድል አድራጊነት ገሥግሥ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 45:4) ኢየሱስ ክርስቶስ ከእውነትና ከጽድቅ በተጨማሪ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ትሕትናን ለማስፈን ይገሠግሣል። መሲሐዊው ንጉሥ በሺህ ዓመት ግዛቱ ማብቂያ ላይ “መንግሥትን ሁሉ እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ” ሥራውን ሲያጠናቅቅ ምን ይከናወናል? በዚያን ጊዜስ ትሕትና ያሳያል? አዎ፣ ምክንያቱም “መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ [ያስረክባል]።”—1 ቆሮንቶስ 15:24-28ን አንብብ።
17, 18. (ሀ) የይሖዋ አገልጋዮች ኢየሱስ የተወውን የትሕትና ምሳሌ መከተላቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
17 በዚህ ረገድ እኛስ እንዴት ነን? ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ የተወውን ፈለግ በመከተል ትሕትና እናሳያለን? ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአርማጌዶን ጦርነት ፍርድ ለማስፈጸም በሚመጣበት ወቅት እንተርፍ ይሆን? ኢየሱስ እየገሠገሠ ያለበት ዓላማ በራሱ ትሑትና ጻድቅ የሆኑ ሰዎችን ብቻ እንዲያድን ያስገድደዋል። እንግዲያው ትሕትና ማዳበራችን ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና ጎዳና መከተሉ ለራሱም ሆነ ለሌሎች ጥቅም እንዳስገኘ ሁሉ እኛም ትሕትና ማሳየታችን በርካታ ጥቅሞች ያስገኛል።
18 ኢየሱስ የተወውን የትሕትና ምሳሌ ለመከተል ምን ሊረዳን ይችላል? ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ትሑት ለመሆን ጥረት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።