የአምላክ መንግሥት—ከሁሉ የላቀ መስተዳድር
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን’” በማለት አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:9, 10) አብዛኛውን ጊዜ አባታችን ሆይ ወይም የጌታ ጸሎት ተብሎ የሚጠራው ይህ ጸሎት የአምላክን መንግሥት ዓላማ ያብራራል።
በዚህ መንግሥት አማካኝነት የአምላክ ስም ይቀደሳል። የይሖዋ ስም በሰይጣንም ሆነ በሰው ልጆች ዓመጽ ምክንያት ከተሰነዘረበት ነቀፋ ነጻ ይሆናል። ይህ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ ደስታቸው የተመካው የአምላክን ስም ቅዱስ አድርገው በመመልከታቸውና የመግዛት መብቱን በፈቃደኝነት በመቀበላቸው ላይ ነው።—ራእይ 4:11
ከዚህም በተጨማሪ ይህ መንግሥት የተቋቋመው የአምላክ ‘ፈቃድ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር እንድትሆን’ ነው። ሆኖም ይህ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው? አዳም ያጣውን ነገር ማለትም አምላክ ከሰዎች ጋር ያለውን ዝምድና መመለስ ነው። ይህ መንግሥት የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሆነው ይሖዋ፣ ጥሩ ሰዎች ለዘላለም በምድር ላይ ተደስተው የሚኖሩበትን ገነት ለማቋቋም ያለውን ዓላማም ያስፈጽማል። አዎን፣ የአምላክ መንግሥት የመጀመሪያው ኃጢአት ያስከተላቸውን ችግሮች በሙሉ አስወግዶ አፍቃሪ የሆነው አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ እውን ያደርጋል። (1 ዮሐንስ 3:8) እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት በዚህ መንግሥትና በሚያከናውናቸው ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።
የአምላክ መንግሥት ከሁሉ የላቀ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
የአምላክ መንግሥት ታላቅ ኃይል ያለው እውን የሆነ መስተዳድር ነው። ነቢዩ ዳንኤል ይህ መንግሥት ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል። ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር:- “የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ . . . [ሰብዓዊ መንግሥታትን] ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል።” ከዚህም በተጨማሪ በታሪክ ውስጥ እየተነሱ ከወደቁት ሰብዓዊ መንግሥታት በተለየ የአምላክ መንግሥት “ፈጽሞ የማይፈርስ” ነው። (ዳንኤል 2:44) ይሁን እንጂ ከሁሉ የላቀ መስተዳድር የሆነበት ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም። ይህ መንግሥት በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን ከማንኛውም ሰብዓዊ አገዛዝ እጅግ የላቀ ነው።
የአምላክ መንግሥት ከሁሉ የላቀ ንጉሥ አለው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ማን መሆኑን እንመልከት። ዳንኤል ባየው ‘ሕልምና ራእይ’ ላይ የአምላክ መንግሥት ገዢ ‘የሰውን ልጅ እንደሚመስልና’ ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ቀርቦ ዘላቂ “ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል” እንደተሰጠው ተመልክቷል። (ዳንኤል 7:1, 13, 14) የሰው ልጅ የተባለው ከመሲሑ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ማቴዎስ 16:13-17) ይሖዋ አምላክ ልጁን፣ ኢየሱስን የመንግሥቱ ንጉሥ እንዲሆን መርጦታል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ለክፉዎቹ ፈሪሳውያን “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ሲል የተናገረው የመንግሥቱ የወደፊት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ራሱ ከእነርሱ ጋር በምድር ላይ መሆኑን ለማመልከት ነበር።—ሉቃስ 17:21
ከሰው ልጆች መካከል መሪ ለመሆን ባለው ብቃት ረገድ ኢየሱስን ሊተካከለው የሚችል ማን አለ? ኢየሱስ ቀደም ሲል ባደረጋቸው ነገሮች ጻድቅ፣ እምነት የሚጣልበትና ርኅሩኅ መሆኑን አስመስክሯል። ወንጌሎች ኢየሱስ የተግባር ሰው እንደሆነ እንዲሁም ጥልቅ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት እንዳለው ይገልጻሉ። (ማቴዎስ 4:23፤ ማርቆስ 1:40, 41፤ 6:31-34፤ ሉቃስ 7:11-17) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ሞትም ሆነ ሰዎች ያሏቸው ሌሎች የአቅም ገደቦች በእርሱ ላይ ሥልጣን የላቸውም።—ኢሳይያስ 9:6, 7
ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ ከፍ ባለ ቦታ ሆነው ይገዛሉ። ዳንኤል ‘መንግሥትና ሥልጣን ለቅዱሳኑ ሲሰጥ’ በራእይ ተመልክቷል። (ዳንኤል 7:27) ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አይደለም። ከእርሱ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙና ካህናት ሆነው የሚያገለግሉ ሌሎች ሰዎችም አሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) እነዚህን በተመለከተ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር . . . [ከምድር የተዋጁ] መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ።”—ራእይ 14:1-3
በጉ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐንስ 1:29፤ ራእይ 22:3) የጽዮን ተራራ ደግሞ ሰማይን ያመለክታል።a (ዕብራውያን 12:22) ኢየሱስና 144,000 ተባባሪ ገዢዎቹ ከፍ ባለ ቦታ ይኸውም በሰማይ ሆነው እየገዙ ነው። በሰማይ በመሆናቸው ሁሉንም ነገር ለማየት ይችላሉ። ‘የእግዚአብሔር መንግሥት’ መቀመጫው ሰማይ በመሆኑ “መንግሥተ ሰማይ” በመባልም ተጠርቷል። (ሉቃስ 8:10፤ ማቴዎስ 13:11) ማንኛውም የጦር መሣሪያም ሆነ የኑክሌር ጥቃት በሰማይ ያለውን መንግሥት ሊያሰጋውም ሆነ ሊያጠፋው አይችልም። ፈጽሞ የማይናወጥ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ዓላማ ዳር ያደርሳል።—ዕብራውያን 12:28
የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ እምነት የሚጣልባቸው ወኪሎች አሉት። ይህንን እንዴት እናውቃለን? መዝሙር 45:16 (የ1980 ትርጉም) “አንተም በምድር ሁሉ ላይ ትሾማቸዋለህ” ይላል። በዚህ ትንቢት ላይ “አንተ” የተባለው የአምላክ ልጅ ነው። (መዝሙር 45:6, 7፤ ዕብራውያን 1:7, 8) በመሆኑም እርሱን የሚወክሉ ገዢዎችን የሚሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እነርሱም መመሪያውን በመታዘዝ ረገድ ታማኞች እንደሚሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በዛሬው ጊዜም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ብቃት ያላቸው ወንዶች በእምነት ባልንጀሮቻቸው ላይ “ጌቶች” እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ እንዲጠብቋቸው፣ እንዲያነቃቋቸውና እንዲያበረታቷቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል።—ማቴዎስ 20:25-28፤ ኢሳይያስ 32:2
የመንግሥቱ ተገዢዎች ጻድቅ ናቸው። በአምላክ ዓይን ነቀፋ የሌለባቸውና ቅኖች ናቸው። (ምሳሌ 2:21, 22) መጽሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል። (መዝሙር 37:11) የመንግሥቱ ዜጎች ገሮች ማለትም ትሑቶች፣ የዋሆች፣ ደጎችና ለመማር ፈቃደኞች ናቸው። ለመንፈሳዊ ነገሮችም ቅድሚያ ይሰጣሉ። (ማቴዎስ 5:3 NW) ትክክለኛውን ነገር ለማድረግና መለኮታዊ መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው።
የአምላክ መንግሥት የሚተዳደረው በላቁ ሕግጋት ነው። የአምላክ መንግሥት የሚመራባቸው ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንጭ ይሖዋ ነው። እነዚህ ሕግጋት መፈናፈኛ የሚያሳጡን ሳይሆኑ የሚጠቅሙን ናቸው። (መዝሙር 19:7-11) ብዙ ሰዎች ይሖዋ ካወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው በመኖራቸው አሁንም እየተጠቀሙ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች፣ ለሚስቶችና ለልጆች የሚሰጠውን ምክር መከተል የቤተሰብ ሕይወታችን የተሻለ እንዲሆን ይረዳናል። (ኤፌሶን 5:33 እስከ 6:3) ‘ፍቅርን እንድንለብስ’ የተሰጠንን መመሪያ በምንታዘዝበት ጊዜ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ይሻሻላል። (ቈላስይስ 3:13, 14) የቅዱሳን ጽሑፎችን መመሪያ ተከትለን ስንኖር ጥሩ የሥራ ልማድ የምናዳብር ከመሆኑም በላይ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኖረናል። (ምሳሌ 13:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከስካር፣ ከጾታ ብልግና፣ ትንባሆ ከማጨስና ሱስ ከሚያስይዙ ዕፆች መራቅ ጤንነታችንን በመጠበቅ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ምሳሌ 7:21-23፤ 23:29, 30፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
የአምላክ መንግሥት በይሖዋ የተቋቋመ መስተዳድር ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነው መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ተባባሪ ገዢዎቹ ፍትሐዊ የሆኑትን የአምላክ ሕግጋትና ፍቅር የተንጸባረቀባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ምድራዊ ወኪሎቹን ጨምሮ የመንግሥቱ ተገዢዎች በሙሉ የአምላክን ሕግጋት በመታዘዝ ይደሰታሉ። የመንግሥቱ ገዢዎችም ሆኑ ተገዢዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት ለአምላክ ነው። በመሆኑም ይህ መንግሥት ቲኦክራሲያዊ ማለትም በአምላክ የሚመራ ነው። ይህ መንግሥት የተቋቋመበትን ዓላማ እንደሚያስፈጽም ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም መሲሐዊው መንግሥት በመባልም የሚታወቀው የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?
መንግሥቱ መግዛት ጀምሯል
ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት መንግሥቱ መግዛት የጀመረው መቼ እንደሆነ ለማወቅ ይረዱናል። ኢየሱስ “ኢየሩሳሌምም የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ፣ በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:24) በመላው ምድር ላይ ከሚገኙት ከተሞች መካከል ይሖዋ ስሙን ያኖረው በኢየሩሳሌም ብቻ ነበር። (1 ነገሥት 11:36፤ ማቴዎስ 5:35) ይህች ከተማ የአምላክ ድጋፍ የነበረው ምድራዊ መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። ከተማዋ በአሕዛብ የምትረገጠው አምላክ ሕዝቦቹን የሚገዛበት ጊዜ አብቅቶ የዓለም መንግሥታት ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሯት ነው። ታዲያ ይህ ጊዜ የጀመረው መቼ ነው?
በኢየሩሳሌም በነበረው የይሖዋ ዙፋን ላይ ለተቀመጠው የመጨረሻ ንጉሥ እንዲህ ተብሎ ነበር:- “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ . . . የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” (ሕዝቅኤል 21:25-27) ንጉሡ ዘውዱን እንዲያወልቅ ይደረጋል፤ አምላክ በሕዝቦቹ ላይ የሚገዛበት ጊዜም ያበቃል። ይህ ደግሞ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባጠፏት ጊዜ ተፈጽሟል። ከዚያ በኋላ በሚኖረው “የአሕዛብ ዘመን” ውስጥ የአምላክን አገዛዝ የሚወክል መንግሥት በምድር ላይ አይኖርም። ይሖዋ “የሚገባው ባለ መብት” ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ የመግዛት ሥልጣን የሚሰጠው እነዚህ ዘመናት ሲያበቁ ነው። ሆኖም እነዚህ ዘመናት ምን ያህል ርዝማኔ ይኖራቸዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ትንቢት እንዲህ ይላል:- “ዛፉን ቍረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጕቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ . . . ሰባት ዓመትም [“ዘመናትም፣” የ1954 ትርጉም] ይለፍበት።” (ዳንኤል 4:23) ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው እዚህ ላይ የተጠቀሱት “ሰባት ዘመናት” ‘ከአሕዛብ ዘመን’ ጋር እኩል የሆነ የጊዜ ርዝማኔ አላቸው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች፣ ገዢዎችና መንግሥታት በዛፍ ተመስለዋል። (መዝሙር 1:3፤ ኤርምያስ 17:7, 8፤ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 31) በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ምሳሌያዊ ዛፍ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።” (ዳንኤል 4:11) በመሆኑም በሚቆረጠውና ረዘም ላለ ጊዜ በሚታሰረው ዛፍ የተመሰለው ግዛት “እስከ ምድር ዳርቻ” ድረስ የሚደርስ አገዛዝ ሲሆን ይህም የሰው ልጆችን መንግሥታት በሙሉ የሚጠቀልል ነው። (ዳንኤል 4:17, 20, 22) ስለዚህ ይህ ዛፍ የአምላክን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊ አገዛዝ በተለይ ደግሞ ከምድር ጋር በተያያዘ የሚጫወተውን ሚና ያመለክታል። ይሖዋ በእስራኤል ብሔር ላይ ባቋቋመው መንግሥት አማካኝነት ለተወሰነ ጊዜ በምድር ላይ ይገዛ ነበር። በትንቢቱ ላይ በተገለጸው መሠረት ምሳሌያዊው ዛፍ ተቆረጠ፣ እድገቱን ለመግታትም ጉቶው በብረትና በናስ ታሰረ። ይህም ሲባል በምድር ላይ አምላክን የሚወክለው አገዛዝ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሥራውን ያቆማል ማለት ነው፤ ሆኖም እንዲህ ሲባል አገዛዙ ለዘላለም ይቋረጣል ማለት አይደለም። ዛፉ “ሰባት ዘመናት” እስኪያልፉ ድረስ የታሰረ ሆኖ ይቆያል። በእነዚህ ዘመናት ፍጻሜ ላይ ይሖዋ ሕጋዊ ወራሽ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ግዛቱን ይሰጠዋል። እነዚህ “ሰባት ዘመናት” እና “የአሕዛብ ዘመን” ተመሳሳይ የሆነ ወቅትን እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የእነዚህን “ሰባት ዘመናት” ርዝማኔ እንድናውቅ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 1,260 ቀናት ‘ከአንድ ዘመን፣ ከዘመናትና [ሁለት ዘመናት] ከዘመን እኩሌታ’ ጋር እኩል እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል፤ ይህ ደግሞ በአጠቃላይ ሦስት ተኩል “ዘመናት” ይሆናል። (ራእይ 12:6, 14) የእነዚህ ቁጥሮች እጥፍ ወይም ሰባት ዘመናት፣ 2,520 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው።
ከ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምረን 2,520 ቀናትን ብንቆጥር 600 ከክርስቶስ ልደት በፊት ላይ ያደርሰናል። ሆኖም ሰባቱ ዘመናት ከዚህ የሚበልጥ የጊዜ ርዝማኔ አላቸው። ኢየሱስ ስለ “አሕዛብ ዘመን” ሲናገር ሰባቱ ዘመናት ገና አላበቁም ነበር። ስለዚህ እነዚህ ሰባት ዘመናት ትንቢታዊ ናቸው። በመሆኑም “እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ደንብ መከተል ይኖርብናል። (ዘኍልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6) በዚህ መንገድ፣ አምላክ ጣልቃ ሳይገባ የዓለም መንግሥታት የገዙባቸው ሰባቱ ዘመናት 2,520 ዓመታት ይሆናሉ። ከ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምረን 2,520 ዓመታትን ብንቆጥር ወደ 1914 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያመጣናል። “የአሕዛብ ዘመን” ወይም ሰባቱ ዘመናት ያበቁት በዚህ ዓመት ነው። ስለዚህ በ1914 ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል ማለት ነው።
“መንግሥትህ ትምጣ”
መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ በመሆኑ ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ባስተማረው መሠረት መንግሥቱ እንዲመጣ መጸለያችንን መቀጠል ይኖርብናል? (ማቴዎስ 6:9, 10) አዎን። አሁንም የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መለመናችን ተገቢና ትርጉም ያለው ነው። ወደፊት የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል።
ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ ታማኝ የሰው ልጆች አስደናቂ በረከት ያገኛሉ! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) አምላክን የሚያስደስቱ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዮሐንስ 17:3) እነዚህና ሌሎች አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ‘ከሁሉ አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥትና የአምላክን ጽድቅ እንሻ።’—ማቴዎስ 6:33
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ኢያቡሳውያንን ድል አድርጎ ምድራዊውን የጽዮን ተራራ በመያዝ ዋና ከተማው አድርጓታል። (2 ሳሙኤል 5:6, 7, 9) ቅዱሱንም ታቦት ወደ ጽዮን አዛውሮታል። (2 ሳሙኤል 6:17) ታቦቱ የይሖዋን መገኘት ያመለክት ስለነበር ጽዮን የአምላክ ማደሪያ እንደሆነች ተደርጋ ተገልጻለች፤ ይህም ለሰማይ ተስማሚ ምሳሌ እንድትሆን አድርጓታል።—ዘፀአት 25:22፤ ዘሌዋውያን 16:2፤ መዝሙር 9:11፤ ራእይ 11:19
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስን መርጧል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]
2,520 ዓመታት
ጥቅምት 607 ◀ ከክ.ል.በፊት ከክ.ል.በኋላ ▸ ጥቅምት 1914
606 ዓመታትና 3 ወራት 1,913 ዓመታትና 9 ወራት
“የአሕዛብ ዘመን” በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በ1914 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አብቅቷል