የአንባብያን ጥያቄዎች
አንዳንድ ጊዜ ወንድሞች የአምላክ መንግሥት ወደ ምድር እንዲመጣ ሲጸልዩ ወይም በንግግራቸው ሲጠቅሱ እንሰማለን። ይህ አነጋገር ትክክል ነውን?
እንደ እውነቱ ከሆነ የአምላክ መንግሥት የሚመጣው እንዴት እንደሆነ ዝርዝር ሐሳብ መስጠቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። የአምላክ መንግሥት ሰማያዊ ነው። በዚህ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን” በማለት ጽፏል።—2 ጢሞቴዎስ 4:18፤ ማቴዎስ 13:44፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50
መንግሥቱ በ1914 በሰማይ የተቋቋመ ሲሆን ተመልሶ ወደሚቋቋመው ምድራዊ ገነትም ሆነ ወደ ሌላ ቦታ አይዘዋወርም። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ነው። ኢየሱስ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በመላእክት ላይ ሥልጣን አለው። ስለዚህ መንበረ ሥልጣኑ ያለው በሰማያት በአምላክ በስተቀኝ ነው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነገሥታትና ካህናት በመሆን በሰማይ ከእርሱ ጋር ይገዛሉ።—ኤፌሶን 1:19-21፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6
ይህ ማለት “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በሚለው የጌታ ጸሎት ላይ የሚገኘውን ልመና ለአምላክ ማቅረብ የለብንም ማለት ነውን? (ማቴዎስ 6:10) እንደዚህ ማለት አይደለም፤ ይህ ጸሎት ተገቢና ትርጉም ያለው ነው።
ወደፊት የአምላክ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። ስንጸልይም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በጌታ ጸሎት ውስጥ ካሉት ጋር የሚመሳሰሉ አገላለጾች ስንጠቀም በአእምሯችን ያለው ይህ ነው። ለምሳሌ ዳንኤል 2:44 የአምላክ መንግሥት ሁሉንም ብሔራት ለማጥፋትና የዚህን ዓለም አገዛዝ ለመረከብ ‘እንደሚመጣ’ ይተነብያል። ራእይ 21:2 አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ እንደምትወርድ ይናገራል። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የክርስቶስ ሙሽራ በሚሆኑት 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተገነባች ናት። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብረው ይገዛሉ። ስለዚህ ራእይ 21:2 እነዚህ ሰዎች ትኩረታቸውን ወደ ምድር በማዞር ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ታላላቅ በረከቶች እንደሚያመጡ ይገልጻል።—ራእይ 21:3, 4
እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ድንቅ ትንቢቶች እስኪፈጸሙ ድረስ “መንግሥትህ ትምጣ” ከሚሉት የኢየሱስ ቃላት ጋር የሚስማማ ጸሎት ለይሖዋ አምላክ ማቅረቡ ተገቢ ሆኖ ይቀጥላል። ሆኖም የአምላክ መንግሥት ወደ ፕላኔቷ ምድራችን ቃል በቃል እንደማይመጣ በአእምሯችን መያዝ አለብን። የንጉሣዊው መንግሥት መቀመጫ ምድር ሳይሆን ሰማይ ነው።
[ምንጭ]
መሬት፦ Based on NASA photo