“ምን እንበላለን?”
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሰዎች ስለ መብልና መጠጥ አዘውትረው ያወሩ ነበር። ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያው ተአምር ውኃን ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ነበር፤ እንዲሁም በሌሎች ሁለት ጊዜያት በጥቂት ዳቦና ዓሣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል። (ማቴዎስ 16:7-10፤ ዮሐንስ 2:3-11) ኢየሱስ በሌሎች ዘንድ ይታወቅ የነበረው ከድሆች ጋር አብሮ በመብላቱ ብቻ ሳይሆን ሀብታሞች በሚያዘጋጁት ግብዣ ላይ በመገኘቱ ጭምር ነበር። እንዲያውም ጠላቶቹ እንኳ ‘ሆዳምና ጠጪ’ በማለት ከሰውታል። (ማቴዎስ 11:18, 19) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ ምግብና መጠጥ ለሰዎች አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን ስለሚያውቅ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማስረዳት እነዚህን ነገሮች በምሳሌነት ተጠቅሞባቸዋል።—ሉቃስ 22:14-20፤ ዮሐንስ 6:35-40
በኢየሱስ ዘመን ሰዎች የሚያዘወትሯቸው ምግቦችና መጠጦች የትኞቹ ነበሩ? ምግብ ይዘጋጅ የነበረው እንዴት ነው? ምግቡን ማዘጋጀትስ ምን ጥረት ይጠይቅ ነበር? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘትህ በወንጌል ውስጥ ተዘግበው የሚገኙ አንዳንድ ክንውኖችንና አባባሎችን በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችልሃል።
“የዕለቱን ምግባችንን” ስጠን
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባስተማራቸው ጊዜ አምላክ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማለትም ‘የዕለቱን ምግባቸውን’ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ተገቢ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። (ማቴዎስ 6:11) መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ጥቅስ ላይ “ምግብ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ዳቦ” የሚል ነው። በኢየሱስ ዘመን ዳቦ በዕብራውያንም ሆነ በግሪካውያን ዘንድ ዋነኛ ምግብ ሆኖ ያገለግል የነበረ ከመሆኑ የተነሳ “ምግብ ብላ” የሚለው አባባል “ዳቦ ብላ” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን በአብዛኛው የሚመገቡት ዳቦን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉትን እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ አጃና ማሽላ ያሉ እህሎች ነበር። አንድ ሰው በዓመት ውስጥ ወደ 200 ኪሎ ግራም የሚጠጋ የአዝርዕት እህል ይመገብ እንደነበር ምሑራን ገምተዋል፤ ይህ ደግሞ ግለሰቡ በዓመት ከሚያስፈልገው የካሎሪ መጠን ግማሽ ያህሉን የሚያገኘው ከእነዚህ እህሎች እንደነበር ያሳያል።
በወቅቱ አንድ ሰው ገበያ ወጥቶ ዳቦ መግዛት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ለቤተሰባቸው የሚሆን ዳቦ ራሳቸው ያዘጋጁ ነበር። ዳቦ፣ ወይን፣ ቅጥሮች እና ጥቅልሎች የተሰኘው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) “ዱቄትን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ስለሆነ አንዲት የቤት እመቤት በየቀኑ [የዳቦ እህል] ትፈጭ ነበር” ብሏል። ታዲያ እንዲህ ለማድረግ ምን ያህል ሰዓት ይፈጅባታል? የመጽሐፉ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “በእጅ ወፍጮ ተጠቅማ ለአንድ ሰዓት ያህል ብትፈጭ ከ1 ኪሎ ግራም ስንዴ ማግኘት የምትችለው ከ0.8 ኪሎ ግራም ያነስ ዱቄት ነበር። አንድ ሰው በቀን ውስጥ በአማካይ ይመገብ የነበረው ስንዴ ግማሽ ኪሎ ግራም ያህል ስለነበር አንዲት የቤት እመቤት አምስት ወይም ስድስት አባላት ላሉት ቤተሰብ [ዳቦ] ለማዘጋጀት ለሦስት ሰዓት ያህል መፍጨት ይኖርባታል።”
እስቲ የኢየሱስ እናት ስለሆነችው ስለ ማርያም ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። ማርያም ካሉባት በርካታ የቤት ውስጥ ሥራዎች በተጨማሪ ለባሏ እንዲሁም ለአምስት ወንድና ሁለት ሴት ልጆቿ የሚበቃ ዳቦ ማዘጋጀት ነበረባት። (ማቴዎስ 13:55, 56) እንደ ሌሎቹ አይሁዳውያን ሴቶች ሁሉ ማርያምም የቤተሰቡን ‘የዕለት ምግብ’ ለማዘጋጀት ጠንክራ ትሠራ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
“ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ”
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ለተወሰኑት ደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ ለማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ ቢደክሙም አልተሳካላቸውም ነበር። ኢየሱስ በጣም ለደከሙት ጓደኞቹ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” አላቸው። ከዚያም ትኩስ ዓሣና ዳቦ አቀረበላቸው። (ዮሐንስ 21:9-13) ምንም እንኳ ቁርስ ስለመብላት በወንጌሎች ውስጥ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ቢሆንም ሰዎች ጠዋት ላይ ዳቦ፣ ለውዝና ዘቢብ ወይም የወይራ ፍሬ የመብላት ልማድ ነበራቸው።
ምሳን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ሠራተኛው ኅብረተሰብ ይመገብ የነበረው ምንድን ነው? ላይፍ ኢን ቢብሊካል ኢዝሪኤል የተሰኘው መጽሐፍ “ምሳቸው ቀለል ያለ ሲሆን ዳቦ፣ ጥራጥሬ፣ የወይራ ፍሬና በለስ ይቀርብ ነበር” ብሏል። ኢየሱስ በሲካር በሚገኘው የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር እየተነጋገረ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ገዝተውት የመጡት እነዚህን ነገሮች ሳይሆን አይቀርም። “ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ” ይኸውም እኩለ ቀን የነበረ ሲሆን “ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማይቱ ሄደው ነበር።”—ዮሐንስ 4:5-8
ማታ ቤተሰቡ ሁሉ የዕለቱን ዋና ምግብ ለመመገብ አንድ ላይ ይሰበሰባል። ፖቨርቲ ኤንድ ቻሪቲ ኢን ሮማን ፓለስታይን፣ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ ሲ.ኢ. የተባለው መጽሐፍ ራት ላይ ይቀርብ የነበረውን ምግብ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ ሰዎች ከገብስ፣ ከተለያዩ የእህል ዓይነቶችና ከጥራጥሬዎች አልፎ አልፎም ከስንዴ የተዘጋጀ ዳቦ ወይም ገንፎ ይበሉ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ምግቦች በጨውና በዘይት ይቀምሟቸው ወይም የወይራ ፍሬ ይጨምሩባቸው ነበር፤ አንዳንዴም በደንብ ከተቀመመ ስጎ፣ ከማር ወይም ጣፋጭ ከሆኑ ፍራፍሬዎች ጭማቂ ጋር ይመገቧቸው ነበር።” ከዚህም በላይ ወተት፣ አይብና አትክልት እንዲሁም ደርቀው የሚቀርቡትን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎች በማዕድ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። በዚያን ወቅት እንደ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ጎመን ያሉትን ጨምሮ ወደ 30 የሚጠጉ የአትክልት ዓይነቶች ማግኘት ይቻል ነበር። በተጨማሪም (1) በለስ፣ (2) ቴምር እና (3) ሮማን በአካባቢው ይበቅሉ ከነበሩት ከ25 በላይ የሚሆኑ ፍራፍሬዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ኢየሱስ ከአልዓዛር እንዲሁም ማርታና ማርያም ከተባሉት ከአልዓዛር እህቶች ጋር ራት በበላበት ጊዜ እነዚህ ምግቦች በጠረጴዛው ላይ ተደርድረው በዓይነ ሕሊናህ መሳል ትችላለህ? አሁን ደግሞ ማርያም የኢየሱስን እግር “ንጹሕ [በሆነ] የናርዶስ ሽቶ” በቀባች ጊዜ ቤቱ ምን ምን ሊል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር፤ የምግቡ መዓዛና ውድ የሆነው ሽቶ ቤቱን አውዶት ነበር።—ዮሐንስ 12:1-3
“ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ”
ኢየሱስ “ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ” በዚያ ለሚገኙት ሰዎች ጠቃሚ ትምህርት ሰጣቸው። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ አካለ ስንኩላንን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውሮችን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ። ምክንያቱም በጻድቃን ትንሣኤ ብድራት ይመለስልሃል።” (ሉቃስ 14:1-14) ፈሪሳዊው የኢየሱስን ምክር ቢከተል በሚያዘጋጀው ግብዣ ላይ ምን ዓይነት ምግብ ይቀርብ ነበር?
አንድ ሀብታም ሰው ወይን፣ ማር፣ ወተትና ቅመማ ቅመሞች የተጨመሩበት በተለያየ ቅርጽ የተጋገረ ምርጥ ዳቦ ሊያቀርብ ይችላል። ቅቤና ፎርማጆ የሚቀርቡበት ጊዜም አለ። ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ የተቀመጡም ሆኑ ገና የተቆረጡ የወይራ ፍሬዎች አሊያም የወይራ ዘይት ከገበታ አይጠፉም ነበር። ፉድ ኢን አንቲክዊቲ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “እያንዳንዱ ሰው በዓመት ውስጥ ሃያ ኪሎ ግራም የሚሆን የወይራ ዘይት ለምግብነት ይጠቀማል፤ ከዚህም በተጨማሪ የወይራ ዘይት ለመዋቢያነት እና ለመብራት ያገለግል ነበር።”
ፈሪሳዊው የሚኖረው በባሕር አቅራቢያ ከሆነ ከተጠመደ ብዙም ያልቆየ ዓሣ ለእንግዶቹ ሊያቀርብ ይችላል። ከባሕሩ ርቀው የሚኖሩት ደግሞ ዓሣ ለመብላት ከፈለጉ አብዛኛውን ጊዜ የሚያገኙት በሆምጣጤ ወይም በጨው የተዘፈዘፈ አሊያም በጨው የታሸ ዓሣ ነው። ጋባዡ ሥጋም ያቀርብ ይሆናል፤ ይሁንና እንዲህ ያለው መስተንግዶ ለድሆች አይደረግም ነበር ማለት ይቻላል። በገበታ ላይ ከእንቁላል የተዘጋጁ ምግቦችን ማየት የተለመደ ነበር። (ሉቃስ 11:12) ገበታ ላይ የሚቀርቡትን ምግቦች ለማጣፈጥ እንደ ኮሰረት፣ እንስላል፣ ከሙን እና ሰናፍጭ ያሉ ቅመማ ቅመሞች ይጨመሩ ነበር። (ማቴዎስ 13:31፤ 23:23፤ ሉቃስ 11:42) እንግዶቹ ዋናውን ምግብ በልተው ከጨረሱ በኋላ ለውዝ፣ ማርና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች የተጨመሩበት የስንዴ ቆሎ ሊቀርብላቸው ይችላል።
በግብዣው ላይ ላሉት እንግዶች የወይን ዘለላ፣ ዘቢብ አሊያም የወይን ጠጅ ይቀርብላቸው ይሆናል። በፓለስቲና ምድር በሺዎች የሚቆጠሩ የወይን መጭመቂያዎች መገኘታቸው ብዙ ሰዎች ወይን ይጠጡ እንደነበር ያሳያል። ገባዖን በሚገኝ አንድ ቦታ ላይ አርኪኦሎጂስቶች 100,000 ሊትር ወይን መያዝ የሚችሉ ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ 63 መጋዘኖች አግኝተዋል።
“ፈጽሞ አትጨነቁ”
የወንጌል ዘገባዎችን በምታነብበት ጊዜ ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ላይ ስለ ምግብና ስለ መጠጥ የጠቀሰው ምን ያህል እንደሆነ ወይም በገበታ ላይ እያለ አንዳንድ አስፈላጊ ትምህርቶችን ያስተማረው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በተለይ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር መብላትና መጠጣት ያስደስታቸው ነበር፤ ያም ሆኖ ምግብና መጠጥ በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የሚይዝ ነገር አልነበረም።
ኢየሱስ ለምግብና ለመጠጥ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ ደቀ መዛሙርቱን ለመርዳት ሲል እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር፦ “‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።” (ማቴዎስ 6:31, 32) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ምክር የተከተሉ ሲሆን አምላክም የሚያስፈልጋቸውን ነገር አሟልቶላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 9:8) አንተ የምትመገበው ምግብ በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከሚመገቡት የተለየ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በሕይወትህ ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት ቅድሚያ የምትሰጥ ከሆነ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያሟላልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ማቴዎስ 6:33, 34