ኢየሱስ ክርስቶስ—ታላቁ ሚስዮናዊ
‘እኔ ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱም ልኮኛል።’—ዮሐ. 7:29
1, 2. ሚስዮናዊ ማለት ምን ማለት ነው? ታላቁ ሚስዮናዊ ተብሎ ሊጠራ የሚችለውስ ማነው?
“ሚስዮናዊ” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንዶች፣ በሚያገለግሉባቸው አገሮች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትን የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ያስባሉ። አንተ ግን የይሖዋ ምሥክር እንደ መሆንህ መጠን በተለያዩ የምድር ክፍሎች ምሥራቹን እንዲሰብኩ የበላይ አካሉ የሚልካቸውን ሚስዮናውያንን ታስታውስ ይሆናል። (ማቴ. 24:14) እነዚህ ሚስዮናውያን፣ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡና ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና እንዲመሠርቱ ለመርዳት በሚያስችላቸው ክቡር የሆነ ሥራ በመካፈል ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ይጠቀሙበታል።—ያዕ. 4:8
2 “ሚስዮናዊ” እና “ሚስዮናውያን” የሚሉት ቃላት በአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ በግርጌ ማስታወሻው ላይ እንጂ በጥቅሶቹ ውስጥ አይገኙም። በባለ ማጣቀሻው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ላይ የኤፌሶን 4:11 የግርጌ ማስታወሻ “ወንጌላውያን” የሚለው የግሪክኛ ቃል “ሚስዮናውያን” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ይገልጻል። ይሖዋ ከሁሉም የላቀ ወንጌላዊ ነው፤ ሆኖም በማንም ስላልተላከ ታላቁ ሚስዮናዊ ተብሎ ሊጠራ አይችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰማይ የሚገኘውን አባቱን በተመለከተ ‘እኔ ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱም ልኮኛል’ ብሏል። (ዮሐ. 7:29) ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር ያለውን ታላቅ ፍቅር ለማሳየት አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኳል። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከበት አንዱ ምክንያት “ስለ እውነት ለመመስከር” በመሆኑ ታላቁ ሚስዮናዊ እንዲሁም ከሁሉ የላቀ ሚስዮናዊ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። (ዮሐ. 18:37) ኢየሱስ፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ ረገድ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነበር፤ እሱ ባከናወነው አገልግሎት አሁንም ድረስ እየተጠቀምን ነው። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ለማስተማር የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ሚስዮናዊ ሆንም አልሆንን በአገልግሎታችን ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን።
3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?
3 ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ ሆኖ የተጫወተው ሚና እንደሚከተሉት ያሉት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል:- ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ምን አጋጥሞት ነበር? እሱ የተጠቀመበት የማስተማሪያ ዘዴ ውጤታማ የነበረው ለምንድን ነው? በአገልግሎቱ ስኬታማ እንዲሆን የረዳውስ ምንድን ነው?
በአዲስ አካባቢ ለማገልገል የፈቃደኝነት መንፈስ አሳይቷል
4-6. ኢየሱስ ወደ ምድር ሲላክ ካጋጠሙት ለውጦች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
4 በዘመናችን የሚገኙ ሚስዮናውያን እንዲሁም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታዎች ሄደው የሚያገለግሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይኖሩበት ከነበረው ሁኔታ ያነሰ አኗኗር መልመድ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በሰማይ ትቶት የመጣውን ሁኔታ (ይሖዋን በንጹሕ ልብ ከሚያገለግሉ መላእክት ጋር ሆኖ በአባቱ ዘንድ መኖርን) በምድር ላይ ከነበረው ሁኔታ ጋር ስናወዳድር ያለው ልዩነት ለማሰብ እንኳ ያዳግታል። (ኢዮብ 1:6፤ 2:1) በሰማይ ይኖርበት የነበረው ሁኔታ፣ ምግባረ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ ኃጢአተኛ ከሆኑ የሰው ልጆች ጋር ከመኖር ምንኛ የተለየ ነው! (ማር. 7:20-23) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ በቅርብ ደቀ መዛሙርቱ መካከል የነበረውን ፉክክር እንኳ መቻል ነበረበት። (ሉቃስ 20:46፤ 22:24) እርግጥ ነው፣ በምድር ላይ ያጋጠመውን ማንኛውንም ሁኔታ ፍጹም በሆነ መንገድ ተወጥቶታል።
5 ኢየሱስ፣ የሰው ልጆችን ቋንቋ መናገር የቻለው በተአምር አይደለም፤ ከልጅነቱ ጀምሮ መማር ነበረበት። ይህ ሁኔታ፣ በሰማይ ለሚገኙት መላእክት መመሪያ ከመስጠት ምንኛ የተለየ ነው! ኢየሱስ በምድር ሳለ ‘ከሰዎች ልሳን’ ቢያንስ በአንዱ ተናግሯል። ይህ ደግሞ “በመላእክት ልሳን” ከመናገር ፍጹም የተለየ ነው። (1 ቆሮ. 13:1) ይሁን እንጂ ከአንደበቱ በሚወጣው የጸጋ ቃል ወይም ማራኪ በሆነው ንግግሩ ከሰው ልጆች መካከል ኢየሱስን የሚተካከለው አልነበረም።—ሉቃስ 4:22
6 የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ሲመጣ በከፍተኛ ሁኔታ የተለወጡበትን ሌሎች ነገሮች ደግሞ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ ምንም እንኳ ከአዳም የወረሰው ኃጢአት ባይኖርም ወደፊት “ወንድሞቹ” ወይም የተቀቡ ተከታዮቹ እንደሚሆኑት ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እሱም ሰው ነበር። (ዕብራውያን 2:17, 18ን አንብብ።) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ በሰማይ ያለውን አባቱን “ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት” እንዲልክለት አልጠየቀም። ሆኖም የመላእክት አለቃ ሚካኤል በነበረበት ጊዜ በእሱ ሥልጣን ሥር የነበሩትን መላእክት አስብ! (ማቴ. 26:53፤ ይሁዳ 9) ኢየሱስ ተአምራት ቢፈጽምም በምድር እያለ ያደረገው ነገር በሰማይ ሆኖ ሊያከናውነው ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር በጣም ውስን ነበር።
7. አይሁዳውያን ከሕጉ ጋር በተያያዘ ምን አድርገዋል?
7 ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” በነበረበት ጊዜ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸው የአምላክ ቃል አቀባይ እሱ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 1:1፤ ዘፀ. 23:20-23) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ‘በመላእክት አማካይነት የተሰጣቸውን ሕግ ተቀበሉ እንጂ አልጠበቁትም።’ (ሥራ 7:53፤ ዕብ. 2:2, 3) እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሕጉን እውነተኛ ትርጉም ለማስተዋል አልቻሉም ነበር። እስቲ የሰንበትን ሕግ እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ማርቆስ 3:4-6ን አንብብ።) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን” ንቀው ነበር። (ማቴ. 23:23) ያም ሆኖ ኢየሱስ እነሱን ሊረዳቸው እንደማይችል ተሰምቶት እውነትን ከማወጅ ወደኋላ አላለም።
8. ኢየሱስ እኛን ሊረዳን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?
8 ኢየሱስ የፈቃደኝነት መንፈስ አሳይቷል። ሰዎችን ከመውደዱም በላይ እነሱን የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ምንጊዜም የወንጌላዊነት መንፈስ ነበረው። ኢየሱስ በምድር እያለ ለይሖዋ ታማኝ በመሆኑ “ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት [ሆኖላቸዋል]።” ከዚህም በላይ “እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል።”—ዕብ. 2:18፤ 5:8, 9
አስተማሪ ለመሆን በሚገባ ሠልጥኗል
9, 10. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመላኩ በፊት ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝቶ ነበር?
9 በዘመናችን ያሉ ሚስዮናውያን ከመላካቸው በፊት ሥልጠና እንዲያገኙ የበላይ አካሉ ዝግጅት ያደርጋል። ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጠና አግኝቶ ነበር? አዎን አግኝቷል፤ ሆኖም መሲሕ ሆኖ ከመቀባቱ በፊት የረቢዎች ትምህርት ቤት አልገባም። ወይም ደግሞ በታወቁ የሃይማኖት መሪዎች እግር ሥር ተቀምጦ አልተማረም። (ዮሐ. 7:15፤ ከሐዋርያት ሥራ 22:3 ጋር አወዳድር።) ታዲያ ኢየሱስ ይህን ያህል የማስተማር ብቃት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ ከእናቱ ከማርያምና ከአሳዳጊ አባቱ ከዮሴፍ የተማረው ነገር ሊኖር ቢችልም ለአገልግሎቱ የሚሆነውን ሥልጠና በዋነኝነት ያገኘው ከሁሉ ከላቀ አካል ነው። ይህን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ።” (ዮሐ. 12:49) ኢየሱስ ስለሚያስተምረው ነገር ዝርዝር መመሪያ እንደተሰጠው ልብ በል። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለረጅም ዘመናት የአባቱን መመሪያ እንዳዳመጠ ጥርጥር የለውም። ከዚህ የተሻለ ምን ሥልጠና ሊያገኝ ይችል ነበር?
11. ኢየሱስ፣ አባቱ ለሰው ልጆች ያለውን አመለካከት ምን ያህል አንጸባርቋል?
11 ኢየሱስ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ከአባቱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ነበረው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት በመመልከት አምላክ ለሰው ዘሮች ያለውን አመለካከት ማስተዋል ችሎ ነበር። አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ኢየሱስ ያንጸባረቀ ሲሆን እሱም በጥበብ ተመስሎ “በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር” በማለት ለመናገር ችሏል።—ምሳሌ 8:22, 31
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ፣ አባቱ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት በመመልከት ትምህርት ያገኘው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሱስ ከአባቱ ያገኘውን ሥልጠና ተግባራዊ ያደረገው እንዴት ነበር?
12 ኢየሱስ፣ አባቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደተወጣ በመመልከትም ትምህርት ማግኘት ችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከዓመጸኞቹ እስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት እንመልከት። ነህምያ 9:28 እንዲህ ይላል:- “ነገር ግን ዕረፍት ባገኙ ጊዜ፣ በፊትህ [ማለትም በይሖዋ ፊት] ክፉውን ነገር እንደ ገና ፈጸሙ፤ ከዚያም ይገዟቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው እጅ ጣልሃቸው፤ እንደ ገና ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ፣ ከሰማይ ሰማህ፤ በርኅራኄህም በየጊዜው ታደግሃቸው።” ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር በመሥራቱና የሚያደርገውን በመመልከቱ በክልሉ ለነበሩት ሰዎች የአባቱን ዓይነት ርኅራኄ ማሳየት ችሏል።—ዮሐ. 5:19
13 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ርኅራኄ በማሳየት ያገኘውን ሥልጠና ተግባራዊ አድርጓል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ በጣም የሚወዳቸው ሐዋርያት በሙሉ “ጥለውት ሸሹ።” (ማቴ. 26:56፤ ዮሐ. 13:1) እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቶስን ሦስት ጊዜ ክዶታል! እንደዚያም ሆኖ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ ወደ እሱ እንዲመለሱ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ለጴጥሮስ “እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ” ብሎታል። (ሉቃስ 22:32) መንፈሳዊ እስራኤላውያን “በሐዋርያትና በነቢያት” መሠረት ላይ የታነጹ ሲሆን በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ቅጥር የመሠረት ድንጋዮች ላይ የበጉ የኢየሱስ ክርስቶስ 12 ታማኝ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ራሳቸውን ለአምላክ ከወሰኑት አጋሮቻቸው ይኸውም ‘ከሌሎች በጎች’ ጋር ሆነው በአምላክ ኃያል እጅና በተወደደው ልጁ አመራር ሥር በመሆን ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ በስፋት እየተካፈሉ ነው።—ኤፌ. 2:20፤ ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 21:14
ኢየሱስ ያስተማረው እንዴት ነበር?
14, 15. የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን የተለየ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
14 ኢየሱስ፣ ያገኘውን ሥልጠና ተከታዮቹን በሚያስተምርበት ጊዜ የተጠቀመበት እንዴት ነበር? ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ ከአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ስናወዳድር የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ በጣም የላቀ እንደነበረ በግልጽ እንመለከታለን። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ‘ስለ ወጋቸው ብለው የእግዚአብሔርን ቃል ሽረዋል።’ ከዚህ በተለየ መልኩ ግን ኢየሱስ ከራሱ ምንም አልተናገረም፤ ሁልጊዜም የአምላክን ቃል ወይም መልእክት ያስተምር ነበር። (ማቴ. 15:6፤ ዮሐ. 14:10) እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል።
15 ኢየሱስ በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሙሉ በሙሉ የተለየ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን በተመለከተ “የሚነግሯችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እንደሚናገሩት አያደርጉምና ተግባራቸውን አትከተሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 23:3) ኢየሱስ ግን ያስተማረውን በተግባር አሳይቷል። ይህ እውነት መሆኑን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
16. ኢየሱስ በማቴዎስ 6:19-21 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ሕይወቱን መርቷል የምትለው ለምንድን ነው?
16 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “በሰማይ . . . ሀብት አከማቹ” ብሎ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 6:19-21ን አንብብ።) ታዲያ የኢየሱስ አኗኗር ከሰጠው ማሳሰቢያ ጋር የሚስማማ ነበር? አዎን፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” በማለት በሐቀኝነት ስለ ራሱ መናገር ችሏል። (ሉቃስ 9:58) ኢየሱስ አኗኗሩን ቀላል አድርጎ ነበር። ሕይወቱ በዋነኝነት ያተኮረው የመንግሥቱን ምሥራች በማወጁ ሥራ ላይ ነበር፤ በምድር ላይ ሀብት ለማከማቸት መጣር ከሚያስከትላቸው ጭንቀቶች ራስን ነፃ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ በአኗኗሩ አሳይቷል። ኢየሱስ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት” በሰማይ ሀብት ማከማቸት ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ አሳይቷል። አንተስ፣ ኢየሱስ በሰማይ ሀብት ስለማከማቸት የሰጠውን ማሳሰቢያ እየተከተልክ ነው?
ኢየሱስን በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉት ባሕርያት
17. ኢየሱስ እጅግ የተዋጣለት ወንጌላዊ እንዲሆን ያደረጉት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?
17 ኢየሱስ እጅግ የተዋጣለት ወንጌላዊ እንዲሆን ያደረጉት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? አንደኛው፣ ይረዳቸው ለነበሩ ሰዎች ያለው አመለካከት ነው። ከይሖዋ ግሩም ባሕርያት መካከል ኢየሱስ ትሕትናን፣ ፍቅርንና ርኅራኄን አንጸባርቋል። እነዚህ ባሕርያት፣ ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ እንዲቀርቡ ያደረጓቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
18. ኢየሱስ ትሑት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ ወደ ምድር የመምጣት ተልእኮውን ሲቀበል “የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵ. 2:7) ይህ ደግሞ ትሕትና የተንጸባረቀበት ተግባር ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተም። ‘ከሰማይ ስለመጣሁ ልትሰሙኝ ይገባል’ የሚል አመለካከት አልነበረውም። ራሳቸውን የሾሙ ሐሰተኛ መሲሖች ከሚያደርጉት በተቃራኒ ኢየሱስ እውነተኛ መሲሕ መሆኑን በጉራ ለማወጅ አልሞከረም። አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች ስለ ማንነቱም ሆነ ስላደረጋቸው ነገሮች ለሌሎች እንዳይገልጡ ይነግራቸው ነበር። (ማቴ. 12:15-21) ኢየሱስ፣ ሰዎች ከተመለከቱት ነገር በመነሳት እሱን ለመከተል ራሳቸው ውሳኔ እንዲያደርጉ ይፈልግ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ጌታቸው በሰማይ እያለ አብረውት እንደነበሩት ፍጹም መላእክት እንዲሆኑ የማይጠብቅባቸው መሆኑ ምንኛ አበረታቷቸው ይሆን!
19, 20. ኢየሱስ በፍቅርና በርኅራኄ ተነሳስቶ ሰዎችን የረዳው እንዴት ነበር?
19 ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ያለው አባቱ ዋነኛ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርንም አሳይቷል። (1 ዮሐ. 4:8) ኢየሱስ ሰዎችን ያስተማረው በፍቅር ተነሳስቶ ነበር። ለአብነት ያህል፣ ለአንድ ወጣት አለቃ የነበረውን ስሜት እንመልከት። (ማርቆስ 10:17-22ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ወጣት ‘ስለ ወደደው’ ሊረዳው ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ወጣቱ አለቃ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ሲል ያለውን ብዙ ሀብት ለመተው ፈቃደኛ አልነበረም።
20 ኢየሱስ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን ካደረጉት ባሕርያት መካከል ርኅራኄ ይገኝበታል። እንደማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው ሁሉ፣ ለትምህርቱ ምላሽ ይሰጡ የነበሩ ሰዎችም የተለያዩ ችግሮች ነበሯቸው። ኢየሱስ ይህንን ያውቅ ስለነበር በርኅራኄና በሐዘኔታ አስተምሯቸዋል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ በጣም በሥራ ከመወጠራቸው የተነሳ ምግብ ለመብላት እንኳ ጊዜ አልነበራቸውም። ሆኖም ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ እንደተሰበሰበ በተመለከተ ጊዜ ምን አደረገ? “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” (ማር. 6:34) ኢየሱስ በክልሉ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ በመመልከት አስተምሯቸዋል እንዲሁም ተአምራትን ፈጽሟል። አንዳንዶች ግሩም በሆኑት ባሕርያቱና ንግግሩ በመማረካቸው ደቀ መዛሙርቱ ሆነዋል።
21. በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?
21 የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው ከኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት መማር የምንችለው ከዚህ የበለጠ ብዙ ነገር አለ። ታላቁ ሚስዮናዊ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ልንመስለው የምንችለው በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች ነው?
መልስህ ምንድን ነው?
• ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ሥልጠና አግኝቷል?
• የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን የላቀ የሆነው እንዴት ነበር?
• ኢየሱስን በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሕዝቡን ያስተማረው እንዴት ነበር?