ልብህን ጠብቅ
“አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።”—ምሳሌ 4:23
1, 2. ልባችንን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
አንዲት የካሪቢያን ደሴት በከባድ አውሎ ነፋስ ከተመታች በኋላ አንድ አዛውንት ከመኖሪያቸው ወጥተው በአካባቢው የደረሰውን ጥፋት ሲመለከቱ ግቢያቸው ፊት ለፊት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የኖረ አንድ ግዙፍ ዛፍ ከቦታው አለመኖሩን ተገነዘቡ። ‘በአቅራቢያው ያሉት ሌሎች ትናንሽ ዛፎች ምንም ሳይሆኑ ያን የሚያክል ግዙፍ ዛፍ እንዴት ሊገነደስና ሊወሰድ ቻለ?’ በማለት ተደነቁ። ቀረብ ብለው ጉቶውን ሲመለከቱ ለጥያቄያቸው መልስ አገኙ። ምንም የማይበገር ይመስል የነበረው ዛፍ ለካስ ውስጡ በስብሶ ኖሯል፤ ዓውሎ ነፋሱ ዛፉ ውስጥ ውስጡን ተበልቶ ያለቀ መሆኑን አጋለጠ።
2 በክርስትና ሕይወት ሥር ሰድዶ እንደቆመ የሚመስል አንድ እውነተኛ አምላኪ በደረሰበት የእምነት ፈተና ተሸንፎ ሲወድቅ መመልከት ምንኛ የሚያሳዝን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። (ዘፍጥረት 8:21) ይህ ማለት ሁልጊዜ ንቁዎች ካልሆንን ጥሩ የሚባለው ልብ እንኳን ሳይቀር መጥፎ የሆነውን እንዲያደርግ ሊታለል ይችላል። የማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው ልብ በቀላሉ ሊበላሽ ስለሚችል “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” የሚለውን ምክር በቁም ነገር ልናስብበት ያስፈልገናል። (ምሳሌ 4:23) ታዲያ ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ዘወትር ምርመራ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው
3, 4. (ሀ) አካላዊውን ልብ በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ? (ለ) ምሳሌያዊ ልባችንን ለመመርመር ምን ይረዳናል?
3 የጤና ምርመራ ለማድረግ ወደ አንድ ሐኪም ብትሄድ ልብህን መመርመሩ የማይቀር ነው። ልብህን ጨምሮ አጠቃላይ የጤንነትህ ሁኔታ በቂ የተመጣጠነ ምግብ እንደምትመገብ ያሳያልን? የደም ግፊትህ እንዴት ነው? የልብ ምትህ የተስተካከለ ነው? በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ ታደርጋለህ? ልብህ ውጥረት ይበዛበታል?
4 አካላዊው ልብ ዘወትር ምርመራ ካስፈለገው ምሳሌያዊው ልብህስ? ይሖዋ ይመረምረዋል። (1 ዜና መዋዕል 29:17) እኛም በተመሳሳይ ልባችንን ልንመረምረው ይገባል። እንዴት? እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ልንጠይቅ እንችላለን:- ዘወትር በሚደረግ የግል ጥናትና በስብሰባ አማካኝነት ልቤን በቂ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እመግበዋለሁን? (መዝሙር 1:1, 2፤ ዕብራውያን 10:24, 25) የይሖዋ መልእክት በቁም ነገር የማስብበትና “በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት” በመንግሥቱ የስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድካፈል የሚገፋፋኝ ነውን? (ኤርምያስ 20:9፤ ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሮሜ 1:15, 16) የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ የአገልግሎት መስክ ለመካፈል እጋደላለሁን? (ሉቃስ 13:24) ምሳሌያዊውን ልቤን ለምን ዓይነት ሁኔታ እያጋለጥኩት ነው? ውሎዬ ልባቸውን በእውነተኛው አምልኮ አንድ ካላደረጉ ሰዎች ጋር ነውን? (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ያለብንን ማንኛውንም ዓይነት ጉድለት ለማወቅና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ፈጣኖች እንሁን።
5. የእምነት ፈተናዎች ለምን ጠቃሚ ዓላማ ሊያገለግሉ ይችላሉ?
5 ብዙውን ጊዜ የተለያዩ የእምነት ፈተናዎች ይገጥሙናል። እነዚህ ፈተናዎች ልባችን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ይከፍቱልናል። ሙሴ ተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ቆመው ለነበሩት እስራኤላውያን “አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፣ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ፣ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ መራህ” ብሏቸዋል። (ዘዳግም 8:2) አንድ ያልተጠበቀ ሁኔታ ወይም ፈተና በሚገጥመን ጊዜ በራሳችን ላይ የምናየው ስሜት፣ ምኞት ወይም የምንሰጠው ምላሽ ብዙውን ጊዜ አያስገርመንም? ይሖዋ እንዲደርሱብን የሚፈቅዳቸው ፈተናዎች ያሉብንን ጉድለቶች እንድናስተውል ያደርጉናል እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ እንድንችል አጋጣሚ ይከፍቱልናል። (ያዕቆብ 1:2-4) ለፈተናዎች ምን ዓይነት ምላሽ እንደምንሰጥ በጥንቃቄ ማሰብና መጸለይ አለብን!
የምንናገራቸው ነገሮች ስለ እኛ ምን ይገልጣሉ?
6. ማውራት የሚቀናን ነገር ስለ ልባችን ምን ሊገልጥ ይችላል?
6 በልባችን ውስጥ ያለው መዝገብ ምን ዓይነት እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፣ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።” (ሉቃስ 6:45) አዘውትረን የምንናገረው ነገር ልባችን በምን ነገር ላይ እንዳተኮረ ጥሩ ፍንጭ ይሰጣል። ስለ ቁሳዊ ነገሮችና በዓለም ውስጥ ስለሚገኝ ስኬት ማውራት ይቀናናል? ወይስ ጭውውታችን በመንፈሳዊ ነገሮችና በቲኦክራሲያዊ ግቦች ላይ ያተኮረ ነው? ሌሎች የሠሯቸውን ስህተቶች እየጠቀስን ከማውራት ይልቅ በፍቅር ለመሸፈን እንጥራለን? (ምሳሌ 10:11, 12) ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ከማውራት ይልቅ የሚቀናን ስለ ሰዎችና ስለ ድርጊቶቻቸው ማውራት ነው? ይህ ሁኔታ በሌሎች ሰዎች የግል ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንደምንገባ የሚያሳይ ምልክት ይሆን?—1 ጴጥሮስ 4:15
7. ልባችንን በመጠበቅ ረገድ ከዮሴፍ አሥር ወንድሞች ታሪክ ምን እንማራለን?
7 በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ምን እንደተከሰተ ተመልከት። አሥሩ የያዕቆብ ታላላቅ ልጆች ታናሽ ወንድማቸውን ዮሴፍን “በሰላም ይናገሩት ዘንድ አልቻሉም።” ለምን? አባታቸው ከእነርሱ አስበልጦ ይወድደው ስለነበር ቅናት አደረባቸው። ከጊዜ በኋላ አምላክ ሕልም በማሳየት ዮሴፍን እንደባረከውና ይህም የይሖዋን ሞገስ ማግኘቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን በተገነዘቡ ጊዜ ወንድሞቹ “በብዙ ጠሉት።” (ዘፍጥረት 37:4, 5, 11) በጭካኔ ወንድማቸውን አሳልፈው ለባርነት ሸጡት። ከዚያም መጥፎ ሥራቸውን ለመሸፈን አባታቸው ዮሴፍን የዱር አውሬ በልቶታል ብሎ እንዲያስብ በማድረግ አታለሉት። የዮሴፍ አሥር ወንድሞች በዚያን ወቅት ልባቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። እኛም ሌሎችን የመንቀፍ ዝንባሌ ካለብን እንዲህ የምናደርገው በልባችን ውስጥ አንድ ዓይነት የምቀኝነት ወይም የቅናት ስሜት ስላለብን ይሆን? ከአንደበታችን የሚወጣውን ለመመርመርና ተገቢ ያልሆኑ ዝንባሌዎችን ነቅለን ለመጣል ፈጣኖች መሆን ይኖርብናል።
8. ሳይታወቀን በድንገት ውሸት ብንናገር ልባችንን እንድንመረምር ምን ይረዳናል?
8 ምንም እንኳ ‘እግዚአብሔር ሊዋሽ ባይችልም’ ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች ሊዋሹ ይችላሉ። (ዕብራውያን 6:17, 18) መዝሙራዊው “ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው” በማለት አማርሯል። (መዝሙር 116:11) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንኳ ሳይቀር ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ በመዋሸት ሦስት ጊዜ ክዶታል። (ማቴዎስ 26:69-75) እንግዲያው ይሖዋ ‘ሐሰተኛ ምላስን’ ስለሚጠላ ውሸት እንዳንናገር መጠንቀቅ ይገባናል። (ምሳሌ 6:16-19) ሳይታወቀን በድንገት ውሸት ብንናገር እንኳ ምክንያቱን ለማጤን መሞከሩ ጥበብ ነው። ውሸት እንድናገር ያደረገኝ የሰው ፍርሃት ይሆን? ከቅጣት ለማምለጥ ብዬ ያደረግኩት ይሆን? ምናልባትም ስሜ እንዳይጎድፍ ብዬ ይሆን ወይስ ራስ ወዳድ ስለሆንኩ ነው? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ጉዳዩን ማጤናችን፣ ስህተቶቻችንን ማመናችንና ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመናችንን እንዲሁም ድክመታችንን ማሸነፍ እንችል ዘንድ እንዲረዳን መጠየቃችን ምንኛ ተገቢ ነው! እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ‘የጉባኤ ሽማግሌዎች’ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሊረዱን ይችላሉ።—ያዕቆብ 5:14
9. የምናቀርበው ጸሎት ስለ ልባችን ምን ሊገልጥ ይችላል?
9 ወጣቱ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብና እውቀት ለማግኘት ላቀረበው ጥያቄ ይሖዋ “ይህ በልብህ ነበረና፣ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርን . . . አልለመንህምና፣ ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ . . . ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው።” (2 ዜና መዋዕል 1:11, 12) ይሖዋ፣ ሰሎሞን ካቀረበው ጥያቄ በመነሳት ሰሎሞን ለምን ነገር ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ ለማወቅ ችሏል። ለአምላክ የምናቀርበው ጸሎት ስለ ልባችን ምን ነገር ይገልጣል? የምናቀርባቸው ጸሎቶች ለእውቀት፣ ለጥበብና ለማስተዋል ጥማት እንዳለን የሚያሳዩ ናቸው? (ምሳሌ 2:1-6፤ ማቴዎስ 5:3) የመንግሥቱ ፍላጎቶች ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ነገሮች ናቸው? (ማቴዎስ 6:9, 10) ጸሎታችን ተደጋጋሚና እንዲያው በዘልማድ የሚቀርቡ ከሆነ ይህ ሁኔታ ጊዜ መድበን በይሖዋ ሥራዎች ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 103:2) ሁሉም ክርስቲያኖች የሚያቀርቡት ጸሎት ምን ነገር እንደሚገልጥ ለመገንዘብ ንቁ መሆን አለባቸው።
ድርጊቶቻችን ምን ይናገራሉ?
10, 11. (ሀ) ዝሙትና ምንዝር የሚመነጩት ከየት ነው? (ለ) ‘በልባችን ዝሙት እንዳንፈጽም’ ምን ይረዳናል?
10 ከቃላት ይልቅ ድርጊት የጎላ ድምፅ አለው እየተባለ ይነገራል። ድርጊታችን ስለ ውስጣዊ ማንነታችን በግልጽ እንደሚናገር ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ሥነ ምግባርን በተመለከተ ልብን መጠበቅ ዝሙት ወይም ምንዝር ከመፈጸም መቆጠብ ማለት ብቻ አይደለም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:28) በልባችን እንኳ ሳይቀር ዝሙት ከመፈጸም መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
11 ታማኙ ፓትሪያርክ ኢዮብ ላገቡ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ምሳሌ ይሆናል። ኢዮብ ከወጣት ሴቶች ጋር የተለመደ ግንኙነት እንደነበረውና እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜም በደግነት ረድቷቸው መሆን እንዳለበት የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ጽኑ አቋም የነበረው ይህ ሰው እነዚህን ወጣት ሴቶች በፆታ ስሜት መመኘት ፈጽሞ የማያስበው ነገር ነበር። ለምን? ምክንያቱም ሴቶችን በምኞት ዓይን ላለማየት ቁርጥ አቋም ወስዶ ነበር። “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) እኛም ከዓይናችን ጋር ተመሳሳይ ቃል ኪዳን በመግባት ልባችንን እንጠብቅ።
12. ልብህን በመጠበቅ ረገድ ሉቃስ 16:10ን ሥራ ላይ የምታውለው እንዴት ነው?
12 የአምላክ ልጅ “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 16:10) አዎን፣ ቤታችን ውስጥ ለብቻችን በምንሆንበት ጊዜ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምናደርጋቸው ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮች እንኳ ሳይቀር ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። (መዝሙር 101:2) እቤታችን ቁጭ ብለን ቴሌቪዥን በምንመለከትበት ወይም ኢንተርኔት በምንጠቀምበት ጊዜ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ” ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ጋር ተስማምተን እንመላለሳለን? (ኤፌሶን 5:3, 4) የኃይል ድርጊት ሲፈጸም የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ወይም የቪዲዮ ፊልሞችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 11:5
13. ከልባችን የሚወጣውን በምንመረምርበት ጊዜ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?
13 ኤርምያስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (ኤርምያስ 17:9) ለሠራናቸው ስህተቶች ማመካኛ ስናቀርብ፣ የፈጸምነውን ስህተት ስናቃልል፣ ጉልህ የሆኑ የባሕርይ ድክመቶቻችንን በተመለከተ ሰበብ አስባብ ስናቀርብ ወይም ያገኘነውን ስኬት አጋንነን ስንናገር ልብ ምን ያህል አታላይ እንደሆነ በግልጽ ሊታይ ይችላል። ክፉ ልብ ሁለት ዓይነት መልክ ሊኖረውና የሚናገረው ሌላ ድርጊቱ ደግሞ ሌላ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 12:2፤ ምሳሌ 23:7) ከልባችን የሚወጣውን በምንመረምርበት ጊዜ ሃቀኞች መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ዓይናችን ቀና ነውን?
14, 15. (ሀ) “ቀና” ዓይን ምንድን ነው? (ለ) ዓይናችንን ቀና ማድረጋችን ልባችንን ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ “የሰውነት መብራት ዓይን ናት” በማለት ተናግሯል። “ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ [“ቀና፣” NW ] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:22) ቀና የሆነ ዓይን ዕይታው ሳይዛባ ወይም ወዲያ ወዲህ ሳይቅበዘበዝ ትኩረቱን በአንድ ግብ ወይም ዓላማ ላይ ያደርጋል። በእርግጥም ዓይናችን ‘የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ በመፈለጉ’ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 6:33) ዓይናችን ቀና ካልሆነ በምሳሌያዊው ልባችን ላይ ምን ሊደርስ ይችላል?
15 መተዳደሪያ ማግኘትን እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። ቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማቅረብ ልናሟላው የሚገባን አንዱ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ምግብን፣ ልብስን፣ ቤትንና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ እጅግ ዘመናዊ፣ ከሁሉ የተሻለና ሰው ያለው ሁሉ ካልኖረን የሚል ምኞት ቢጠናወተንስ? ልባችንንና አእምሯችንን ባሪያ በማድረግ አምልኮታችንን በግማሽ ልብ እንድናከናውን ሊያደርገን አይችልምን? (መዝሙር 119:113፤ ሮሜ 16:18) ሕይወታችን በሙሉ በቤተሰብ፣ በንግድና በቁሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን በማሟላት ብቻ መጠመድ ይኖርብናል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የሚከተለውን ምክር አስታውሱ:- “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።”—ሉቃስ 21:34, 35
16. ዓይንን በተመለከተ ኢየሱስ ምን ምክር ሰጥቷል? ለምንስ?
16 ለአእምሯችንና ለልባችን መልእክት በማቀበል ረገድ ዓይን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ዓይናችን በትኩረት የሚመለከተው ነገር በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በድርጊታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በዓይን የሚመጣ ፈተና ኃይል እንዳለው ሲገልጽ ኢየሱስ በምሳሌያዊ አነጋገር እንዲህ ብሏል:- “ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና።” (ማቴዎስ 5:29) ዓይን ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳይመለከት ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። ለምሳሌ ያህል የፆታ ስሜትን ወይም ምኞትን ለማነሳሳት ታስበው የተዘጋጁ የተለያዩ ነገሮችን እንዲመለከት ሊፈቀድለት አይገባም።
17. ቆላስይስ 3:5ን በሥራ ላይ ማዋል ልባችንን ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
17 ከውጭው ዓለም ጋር የሚያገናኘን የስሜት ሕዋስ ዓይን ብቻ አይደለም። እንደ መዳሰስና መስማት ያሉ ሌሎች የስሜት ሕዋሳትም የራሳቸው ድርሻ አላቸው። ለእነዚህም የስሜት ሕዋሳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው” በማለት ጥብቅ ምክር ሰጥቷል።—ቆላስይስ 3:5
18. ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችን በሚመለከት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይገባናል?
18 አእምሯችን ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ሊያመነጭ ይችላል። እንደዚህ ባሉ ነገሮች ላይ ማውጠንጠን መጥፎውን ምኞት ሊያባብስና ልባችንን ሊቆጣጠር ይችላል። “ከዚያ በኋላ . . . ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች።” (ያዕቆብ 1:14, 15) የማስተርቤሽን ልማድ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በዚህ መንገድ እንደሆነ ብዙዎች ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። አእምሯችንን መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች መሙላታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ፊልጵስዩስ 4:8) ተገቢ ያልሆነ ሐሳብ ወደ አእምሯችን ቢመጣ እንኳ በፍጥነት ከአእምሮአችን ለማውጣት መጣር ይኖርብናል።
‘ይሖዋን በሙሉ ልብ አገልግል’
19, 20. በሙሉ ልብ ይሖዋን በማገልገል ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?
19 ንጉሥ ዳዊት በእርጅና ዘመኑ ለልጁ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ልጄ ሰሎሞን ሆይ፣ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው።” (1 ዜና መዋዕል 28:9) ሰሎሞንም ቢሆን “ታዛዥ ልብ” እንዲኖረው ጸልዮአል። (1 ነገሥት 3:9 NW ) ያም ሆኖ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲህ ያለውን ልብ ይዞ በመቀጠል ረገድ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመውታል።
20 በዚህ ረገድ እኛም እንዲሳካልን ከፈለግን ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ይህን ልባችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ይህንንም ለማሳካት የአምላክን ቃል ማሳሰቢያዎች ወደ ልባችን ማቅረብ በሌላ አባባል በልባችን ውስጥ ‘ጠብቀን’ ማኖር ይገባናል። (ምሳሌ 4:20-22) ልባችንን መመርመርን፣ ቃላችንና ድርጊታችን ምን ነገር እንደሚገልጡ በጸሎት ማሰብን ልማድ ልናደርግ ይገባናል። ያገኘነውን ድክመት ማስተካከል እንድንችል የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ካልጣርን ይህን ማድረጋችን ብቻውን ምን ዋጋ አለው? በስሜት ሕዋሶቻችን አማካኝነት ስለምናስገባቸው ነገሮች ጠንቃቆች መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን ስናደርግ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” የሚል ማረጋገጫ አለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አዎን፣ ከሁሉም በላይ ልባችንን ለመጠበቅና በሙሉ ልብ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
ታስታውሳለህን?
• ልብን መጠበቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• የምንናገረውን ነገር ማጤናችን ልባችንን ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
• ዓይናችንን “ቀና” ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመስክ አገልግሎት፣ በስብሰባዎችና በቤታችን ብዙውን ጊዜ ማውራት የምንወድደው ስለምን ጉዳይ ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀና የሆነ ዓይን እይታው የተስተካከለ ነው