የመሲሑን መምጣት ይጠባበቁ ነበር
“ሕዝቡ ሁሉ የመሲሕን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ ስለዚህ ዮሐንስን ‘ይህ ሰው ምናልባት መሲሕ ይሆንን?’ እያሉ በልባቸው አሰቡ።”—ሉቃስ 3:15 የ1980 ትርጉም
1. አንድ መልአክ ለእረኞቹ ምን አላቸው?
ጊዜው መሽቷል። እረኞች ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን እየጠበቁ ነበር። በድንገት የይሖዋ መልአክ መጥቶ አጠገባቸው ሲቆምና የአምላክ ክብር በዙሪያቸው ሲያንጸባርቅ ምንኛ ተደናግጠው ይሆን! እስቲ ከዚያ ቀጥሎ የሆነውን ነገር እንመልከት። መልአኩ የሚከተለውን አስገራሚ ሐሳብ ተናገረ፦ “አትፍሩ፣ እነሆ ለሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ ምክንያቱም በዛሬው ዕለት . . . አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ [ማለትም መሲሕ] ነው።” መልአኩ፣ ሕፃኑን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ከተማ በግርግም ውስጥ ተኝቶ እንደሚያገኙት ለእረኞቹ ነገራቸው። ከዚያም በድንገት “ብዙ የሰማይ ሠራዊት” እንደሚከተለው በማለት ይሖዋን ማመስገን ጀመሩ፦ “በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።”—ሉቃስ 2:8-14
2. “መሲሕ” ሲባል ምን ማለት ነው? መሲሑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
2 አይሁዳውያኑ እረኞች “መሲሕ” ወይም “ክርስቶስ” የሚለው ቃል በአምላክ “የተቀባ” ማለት መሆኑን ያውቁ እንደነበር ግልጽ ነው። (ዘፀ. 29:5-7) ይሁንና መልአኩ የጠቀሰው ሕፃን ልጅ፣ ይሖዋ የቀባው መሲሕ እንደሆነ ይበልጥ ማወቅ እና ሌሎችን ማሳመን የሚችሉት እንዴት ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በመመርመር እንዲሁም ትንቢቶቹን ከዚህ ልጅ ሕይወትና ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጋር በማወዳደር መሲሑን ማወቅ ይችሉ ነበር።
ሕዝቡ ይጠባበቁ የነበረው ለምንድን ነው?
3, 4. ዳንኤል 9:24, 25ን እንዴት ልንረዳው ይገባል?
3 ከላይ የተገለጸው ሁኔታ ከተፈጸመ ከዓመታት በኋላ፣ አጥማቂው ዮሐንስ የሚናገራቸውንና የሚያደርጋቸውን ነገሮች የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች መሲሑ የመጣ መስሏቸው ነበር። (ሉቃስ 3:15ን አንብብ።) አንዳንዶች ስለ “ሰባ ሱባዔ” ወይም ሳምንታት የሚገልጸውን መሲሐዊ ትንቢት በትክክል ተረድተውት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ከሆነ መሲሑ የሚገለጥበትን ጊዜ ያውቁ ነበር ማለት ነው። ትንቢቱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል።” (ዳን. 9:24, 25) በርካታ ምሑራን እነዚህ ሱባዔዎች የዓመታት ሳምንታት እንደሆኑ ይስማማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን ይህን ጥቅስ “ሰባ የዓመታት ሳምንታት ታውጀዋል” በማለት ተርጉሞታል።
4 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች በዳንኤል 9:25 ላይ የተጠቀሱት 69 ሳምንታት ወይም 483 ዓመታት የጀመሩት በ455 ዓ.ዓ. እንደሆነ ያውቃሉ፤ በዚህ ጊዜ የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ፣ ነህምያ ኢየሩሳሌምን እንዲያድስና እንዲጠግን ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር። (ነህ. 2:1-8) እነዚህ ሳምንታት ያበቁት ከ483 ዓመታት በኋላ ይኸውም በ29 ዓ.ም. ሲሆን በዚህ ወቅት የናዝሬቱ ኢየሱስ ተጠምቆና በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ መሲሕ ሆነ።—ማቴ. 3:13-17a
5. የትኞቹን ትንቢቶች እንመረምራለን?
5 ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት፣ ከልጅነት ሕይወቱ ጋር በተያያዘ እንዲሁም አገልግሎቱን ሲያከናውን ፍጻሜያቸውን ካገኙት ስለ መሲሑ የሚናገሩ በርካታ ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹን እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያለንን እምነት እንደሚያጠናክርልን ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ እናገኛለን።
ከልጅነት ሕይወቱ ጋር የተያያዙ ትንቢቶች
6. ዘፍጥረት 49:10 የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
6 መሲሑ የሚወለደው ከይሁዳ ነገድ ነው። ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት ወንዶች ልጆቹን ሲባርካቸው እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው [“ሴሎ፣” የግርጌ ማስታወሻ] እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል።” (ዘፍ. 49:10) ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ የአይሁድ ምሑራን ይህ ሐሳብ መሲሑን እንደሚያመለክት ይናገሩ ነበር። ከይሁዳ ወገን የሆነው ንጉሥ ዳዊት መግዛት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በትረ መንግሥት (የንጉሡን ሉዓላዊነት ያመለክታል) እና የገዥነት ምርኩዝ (የመግዛት ሥልጣንን ያመለክታል) ከይሁዳ ነገድ እጅ አልወጣም። “ሴሎ” የሚለው ቃል “ባለቤት የሆነው፤ ባለመብት የሆነው” የሚል ትርጉም አለው። የይሁዳ ሥርወ መንግሥት የሚያበቃው ንጉሣዊ ወራሽ ሆኖ ለዘላለም የሚገዛው “ሴሎ” ሲነግሥ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከይሁዳ ነገድ ለሆነው ለመጨረሻው ንጉሥ ይኸውም ለሴዴቅያስ፣ ንግሥናው ባለ መብት ለሆነው እንደሚሰጥ ነግሮት ነበር። (ሕዝ. 21:26, 27) ከሴዴቅያስ በኋላ ከዳዊት ዘሮች መካከል ንጉሥ የመሆን መብት እንደሚኖረው ቃል የተገባለት ለኢየሱስ ብቻ ነበር። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት መልአኩ ገብርኤል ለማርያም እንዲህ ብሏታል፦ “ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) እንግዲያው ሴሎ የተባለው ከይሁዳ ነገድና ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለበት።—ማቴ. 1:1-3, 6፤ ሉቃስ 3:23, 31-34
7. መሲሑ የተወለደው የት ነው? ይህ በጣም የሚያስገርመው ለምንድን ነው?
7 መሲሑ የሚወለደው በቤተልሔም ነው። ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣ አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን የሆነ፣ የእስራኤል ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልኛል።” (ሚክ. 5:2) መሲሑ የሚወለደው በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም ሲሆን ይህች ከተማ በአንድ ወቅት ኤፍራታ ትባል ነበር። የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያምና አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ የሚኖሩት በናዝሬት ከተማ ቢሆንም የሮም መንግሥት ባወጣው አዋጅ የተነሳ ወደ ቤተልሔም ሄደው ነበር፤ በዚያም በ2 ዓ.ዓ. ኢየሱስ ተወለደ። (ማቴ. 2:1, 5, 6) ትንቢቱ የተፈጸመበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነው!
8, 9. ከመሲሑ መወለድና ከዚያ በኋላ ከተከናወኑት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የትኞቹ ትንቢቶች ተነግረው ነበር?
8 መሲሑ ከድንግል ይወለዳል። (ኢሳይያስ 7:14ን አንብብ።) በኢሳይያስ 7:14 ላይ ድንግል፣ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ትንቢት ተነግሮ ነበር። እዚህ ላይ ድንግል ተብሎ የተተረጎመው ቃል ርብቃ ከማግባቷ በፊት ከተጠራችበት ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዘፍ. 24:16, 43) ማቴዎስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ዘገባ ላይ ኢሳይያስ 7:14 ከኢየሱስ መወለድ ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ማግኘቱን ለማሳየት “ድንግል” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። የወንጌል ጸሐፊዎች የሆኑት ማቴዎስና ሉቃስ ድንግል የነበረችው ማርያም በአምላክ መንፈስ አማካኝነት እንደፀነሰች ጽፈዋል።—ማቴ. 1:18-25፤ ሉቃስ 1:26-35
9 መሲሑ ከተወለደ በኋላ ልጆች ይገደላሉ። ከብዙ ዘመን በፊት የግብፁ ፈርዖን የዕብራውያን ወንዶች ልጆች ዓባይ ወንዝ ውስጥ እንዲጣሉ ባዘዘበት ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሞ ነበር። (ዘፀ. 1:22) በተለይ ደግሞ ራሔል ልጆቿ ወደ ‘ጠላት ምድር’ በመወሰዳቸው እንዳለቀሰች የሚናገረው በኤርምያስ 31:15, 16 ላይ የሚገኘው ዘገባ ትኩረት የሚስብ ነው። የራሔል ዋይታ በኢየሩሳሌም ሰሜናዊ ክፍል ባለው በቢንያም ምድር ርቃ እስከምትገኘው እስከ ራማ ድረስ ተሰምቶ ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ በቤተልሔምና በአካባቢዋ የሚገኙት ወንዶች ልጆች እንዲገደሉ ትእዛዝ ባወጣበት ጊዜ የኤርምያስ ትንቢት እንደተፈጸመ ማቴዎስ ዘግቧል። (ማቴዎስ 2:16-18ን አንብብ።) በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምን ያህል አዝነው እንደነበር ማሰብ ትችላለህ!
10. ሆሴዕ 11:1 በኢየሱስ ላይ የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
10 ልክ እንደ እስራኤላውያን መሲሑም ከግብፅ ይጠራል። (ሆሴዕ 11:1) ሄሮድስ ሕፃናቱ እንዲገደሉ ትእዛዝ ከማስተላለፉ በፊት አንድ መልአክ ዮሴፍ፣ ማርያምና ኢየሱስ ወደ ግብፅ እንዲሸሹ ነገራቸው። “ይሖዋ ‘ልጄን ከግብፅ ጠራሁት’ ብሎ በነቢዩ [ሆሴዕ] አማካኝነት የተናገረው ይፈጸም ዘንድም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ እዚያው [ቆዩ]።” (ማቴ. 2:13-15) ኢየሱስ ራሱ፣ ከመወለዱና ከልጅነት ሕይወቱ ጋር በተያያዘ የተነገሩት ትንቢቶች በእሱ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ነገሮችን ማቀነባበር እንደማይችል ጥያቄ የለውም።
መሲሑ አገልግሎቱን ጀመረ
11. ይሖዋ የቀባው ከመምጣቱ በፊት መንገዱ የተዘጋጀው እንዴት ነበር?
11 አምላክ የቀባው ከመምጣቱ በፊት መንገዱ መዘጋጀት ነበረበት። “ነቢዩ ኤልያስ” ለመሲሑ መምጣት የሕዝቡን ልብ በማዘጋጀት ይህን ሥራ እንደሚያከናውን ሚልክያስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ሚልክያስ 4:5, 6ን አንብብ።) እዚህ ላይ “ኤልያስ” የተባለው አጥማቂው ዮሐንስ እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ተናግሯል። (ማቴ. 11:12-14) በተጨማሪም ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ዮሐንስ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት ፍጻሜውን እንዳገኘ ማርቆስ ጠቁሞ ነበር። (ኢሳ. 40:3፤ ማር. 1:1-4) ዮሐንስ ቀድሞ እንዲመጣና መንገዱን እንዲያዘጋጅ ያደረገው ኢየሱስ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘የኤልያስን’ ዓይነት ሥራ እንዲያከናውንና መሲሑን ለመቀበል ሕዝቡን እንዲያዘጋጅ ዮሐንስን የመረጠው አምላክ ነበር።
12. የመሲሑን ማንነት ለይቶ ለማወቅ የሚያስችለው የትኛው ተልእኮ ነው?
12 አምላክ የሰጠው ተልእኮ የመሲሑን ማንነት ለማወቅ ይረዳል። ኢየሱስ ባደገበት በናዝሬት ከተማ በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ የኢሳይያስን ጥቅልል ካነበበ በኋላ ጥቅሱ በእሱ ላይ እንደሚሠራ ተናግሯል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል፤ ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንድሰብክ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ እንዲሁም በይሖዋ ዘንድ የተወደደውን ዓመት እንድሰብክ ልኮኛል።” ኢየሱስ እውነተኛው መሲሕ ስለነበር “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ማለቱ ተገቢ ነው።—ሉቃስ 4:16-21
13. ኢየሱስ በገሊላ ምድር እንደሚሰብክ ምን ትንቢት ተነገሮ ነበር?
13 መሲሑ በገሊላ ምድር እንደሚሰብክ አስቀድሞ ተነግሯል። ኢሳይያስ “የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር” እንዲሁም “የአሕዛብን ገሊላ” በተመለከተ “በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ለኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው” በማለት ጽፏል። (ኢሳ. 9:1, 2) ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው በገሊላ በምትገኘው በቅፍርናሆም ሲሆን የዛብሎንና የንፍታሌም ነዋሪዎች የሆኑ በርካታ ሰዎች እሱ ከፈነጠቀው መንፈሳዊ ብርሃን መጠቀም ችለው ነበር። (ማቴ. 4:12-16) ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የሚነካውን የተራራ ስብከቱን ያቀረበው፣ ሐዋርያቱን የመረጠው፣ የመጀመሪያውን ተአምር የፈጸመው እንዲሁም ከሞት ከተነሳ በኋላ 500 ለሚያህሉ ደቀ መዛሙርቱ የተገለጠው በገሊላ ነበር። (ማቴ. 5:1 እስከ 7:27፤ 28:16-20፤ ማር. 3:13, 14፤ ዮሐ. 2:8-11፤ 1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ ‘በዛብሎንና በንፍታሌም ምድር’ በማገልገል የኢሳይያስን ትንቢት ፈጽሟል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በእስራኤል ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ቦታዎችም የመንግሥቱን መልእክት ሰብኳል።
መሲሑ ስለሚያከናውናቸው ሌሎች ተግባራት አስቀድሞ ተነግሯል
14. ኢየሱስ በመዝሙር 78:2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት የፈጸመው እንዴት ነው?
14 መሲሑ በምሳሌ እንደሚናገር ተተንብዮ ነበር። መዝሙራዊው አሳፍ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 78:2) ይህ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ እንዴት እናውቃለን? ማቴዎስ ይህን ያረጋግጥልናል። ማቴዎስ፣ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት እያደገች ከሄደች የሰናፍጭ ዘር እና ከእርሾ ጋር በማመሳሰል የተናገረውን ምሳሌ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “[ኢየሱስ] ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ይህም የሆነው ‘አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተሰወሩትን ነገሮች አሳውቃለሁ’ ተብሎ በነቢዩ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።” (ማቴ. 13:31-35) ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል ምሳሌዎች ይገኙበታል።
15. ኢሳይያስ 53:4 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
15 መሲሑ ሕመማችንን ይሸከማል። ኢሳይያስ “በእርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 53:4) ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት ከፈወሰ በኋላ ሌሎችንም እንደፈወሰ ማቴዎስ የገለጸ ሲሆን “ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ ‘እሱ ሕመማችንን ተቀበለ፣ ደዌያችንንም ተሸከመ’ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው” በማለት ዘግቧል። (ማቴ. 8:14-17) ኢየሱስ የታመሙትን እንደፈወሰ ከሚገልጹት በርካታ ዘገባዎች መካከል ይህ አንዱ ብቻ ነው።
16. ሐዋርያው ዮሐንስ በኢሳይያስ 53:1 ላይ ያለው ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ያሳየው እንዴት ነው?
16 መሲሑ መልካም ነገሮችን ቢያደርግም ብዙ ሰዎች በእሱ አያምኑም። (ኢሳይያስ 53:1ን አንብብ።) ይህ ትንቢት መፈጸሙን ለማሳየት ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ኢየሱስ] በፊታቸው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች ቢፈጽምም በእሱ አላመኑም፤ ስለሆነም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ እኛ የሰማነውን ነገር ማን አመነ? የይሖዋስ ክንድ ለማን ተገለጠ?’” (ዮሐ. 12:37, 38) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅትም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ በሚናገረው ምሥራች ላይ እምነት ያሳደሩ ሰዎች ጥቂት ነበሩ።—ሮም 10:16, 17
17. ዮሐንስ፣ መዝሙር 69:4 ፍጻሜውን ያገኘበትን መንገድ በተመለከተ ምን ብሏል?
17 መሲሑ ያለ ምክንያት ይጠላል። (መዝ. 69:4) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረ ጽፏል፦ “ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር [በሕዝቡ መካከል] ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን አይተዋል፤ እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል። ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።” (ዮሐ. 15:24, 25) ብዙውን ጊዜ ‘ሕግ’ የሚለው ቃል ቅዱሳን መጻሕፍትን በሙሉ ያመለክታል። (ዮሐ. 10:34፤ 12:34) የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ በተለይ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ይጠላ እንደነበር ያሳያሉ። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዓለም እናንተን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ እንደሆነ ስለምመሠክርበት ይጠላኛል።”—ዮሐ. 7:7
18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ጉዳይ መመርመራችን ኢየሱስ መሲሕ ስለ መሆኑ ያለንን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልናል?
18 በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች መሲሑ እሱ እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ። (ማቴ. 16:16) ቀደም ሲል እንዳየነው ስለ መሲሑ ከተነገሩት ትንቢቶች አንዳንዶቹ ከናዝሬቱ ኢየሱስ የልጅነት ሕይወትና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ መሲሑ የተነገሩ ሌሎች ትንቢቶችን እንመረምራለን። በእነዚህ ነገሮች ላይ በጸሎት ማሰላሰላችን፣ በሰማይ የሚገኘው አባታችን ይሖዋ የሾመው መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሆኑ ያለንን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ‘ሰባውን ሱባዔ’ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ከኢየሱስ መወለድ ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ያገኙት የትኞቹ ትንቢቶች ናቸው?
• መሲሑ ከመምጣቱ በፊት መንገዱ የተዘጋጀለት እንዴት ነበር?
• በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ የሚገኙት የትኞቹ ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ ተፈጽመዋል?