“ሽልማቱን እንድታገኙ . . . ሩጡ”
“ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።”—1 ቆሮ. 9:24
1, 2. (ሀ) ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ያበረታታቸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች ምን እንዲያደርጉ ምክር ተሰጥቷቸዋል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእምነት ባልንጀሮቹን ለማበረታታት ግሩም የሆነ ምሳሌ ተጠቅሟል። የሕይወትን ሩጫ የሚሮጡት እነሱ ብቻ እንዳልሆኑ አስታውሷቸዋል። ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቀ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” በዙሪያቸው እንዳለ ገልጾላቸዋል። የዕብራውያን ክርስቲያኖች ከእነሱ በፊት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በእምነት ያከናወኑትን ነገርና ያደረጉትን ብርቱ ጥረት ማሰባቸው ዝለው ውድድሩን ከማቋረጥ ይልቅ በሩጫው እንዲገፉ ብርታት ይሰጣቸዋል።
2 ቀደም ባለው የጥናት ርዕስ ላይ “የምሥክሮች ደመና” ከተባሉት መካከል ብዙዎቹ የተከተሉትን የሕይወት ጎዳና ተመልክተን ነበር። እነዚያ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ የማይናወጥ እምነት መያዛቸው በሩጫው እስከ መጨረሻው እንዲገፉ ይኸውም ለአምላክ ታማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ እንደረዳቸው አሳይተዋል። እኛም በተሳካ ሁኔታ ሩጫውን ካጠናቀቁት ከእነዚህ ሰዎች ትምህርት እናገኛለን። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ እኛን ጨምሮ ለእምነት ባልንጀሮቹ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።”—ዕብ. 12:1
3. ጳውሎስ፣ በግሪካውያን ስፖርታዊ ጨዋታዎች ከሚካፈሉት ሯጮች ጋር አያይዞ በሰጠው ምክር ላይ ሊያጎላው የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?
3 ባክግራውንድስ ኦቭ ኧርሊ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ፣ በጥንት ዘመን ታዋቂ ከነበሩት ስፖርታዊ ጨዋታዎች አንዱ ስለሆነው የሩጫ ውድድር ሲናገር “ግሪኮች ልምምድ የሚያደርጉትም ሆነ የሚወዳደሩት እርቃናቸውን ነበር” ይላል።a እንደዚህ ባሉት ወቅቶች ሯጮቹ ፍጥነታቸውን ሊቀንስባቸው የሚችል ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ያስወግዱ ነበር። እርቃናቸውን መሮጣቸው በዛሬው ጊዜ ስናስበው የሚያሳፍርና ተገቢ ያልሆነ ቢመስልም እንዲህ የሚያደርጉት ሽልማቱን ከማግኘት ምንም ነገር እንዲያግዳቸው ስለማይፈልጉ ነበር። ጳውሎስ እዚህ ላይ ሊያጎላው የፈለገው ነጥብ ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ላይ ሯጮቹ ሽልማቱን ለማግኘት ከፈለጉ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ማንኛውንም ነገር ማስወገዳቸው አስፈላጊ መሆኑን ነው። ይህ በዚያን ጊዜ ለነበሩትም ሆነ በዛሬው ጊዜ ላለነው ክርስቲያኖች ግሩም ምክር ነው። ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ላይ ሽልማቱን እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ሸክሞች ምንድን ናቸው?
‘ማንኛውንም ሸክም ከላያችሁ ጣሉ’
4. በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች በየትኞቹ ነገሮች ተጠምደው ነበር?
4 ጳውሎስ ‘ማንኛውንም ሸክም ከላያችን እንድንጥል’ ምክር ሰጥቷል። ይህም በሕይወት ሩጫ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳናተኩርና የምንችለውን ያህል ጥረት እንዳናደርግ እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ ማስወገድን ይጨምራል። ሸክም ከተባሉት መካከል አንዳንዶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ጳውሎስ እንደ ምሳሌ ከጠቀሳቸው የአምላክ አገልጋዮች አንዱ የሆነውን ኖኅን ስናስብ፣ ኢየሱስ “በኖኅ ዘመን እንደተከሰተው ሁሉ በሰው ልጅ ዘመንም እንዲሁ ይሆናል” ብሎ የተናገረውን ማስታወሳችን አይቀርም። (ሉቃስ 17:26) ኢየሱስ እዚህ ላይ በዋነኝነት ሊያጎላ የፈለገው ጥፋቱ ሳይታሰብ መምጣቱን ሳይሆን የሰዎቹን የአኗኗር ዘይቤ ነበር። (ማቴዎስ 24:37-39ን አንብብ።) በኖኅ ዘመን ከነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ አምላክን ለማስደሰት ጥረት ማድረግ ይቅርና ስለ እሱ ምንም ደንታ አልነበራቸውም። ትኩረታቸውን የሰረቀው ነገር ምን ነበር? እንደ መብላት፣ መጠጣትና ማግባት ያሉ የተለመዱ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። የእነዚህ ሰዎች ዋነኛ ችግር ኢየሱስ እንዳለው ‘አለማስተዋላቸው’ ነበር።—ማቴ. 24:37-39
5. ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንድንችል ምን ሊረዳን ይችላል?
5 እንደ ኖኅና ቤተሰቡ ሁሉ እኛም በየዕለቱ የምናከናውናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር መሥራት ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሊሻማብን ይችላል፤ የገንዘብ ችግር ካለብን ደግሞ በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት ጭንቀት ሊፈጥርብን ይችላል። በተለይም የኢኮኖሚ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች መጨነቃችን የማይቀር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች በመሆናችን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች አሉን። በአገልግሎት መካፈል፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር የግል ጥናትና የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ አለብን። ኖኅ አምላክን ሲያገለግል የሚያከናውናቸው ብዙ ነገሮች የነበሩት ቢሆንም ሁሉን ይሖዋ ‘እንዳዘዘው አድርጓል።’ (ዘፍ. 6:22) በሕይወት ሩጫ ላይ እስከ መጨረሻው ለመሮጥ ከፈለግን ያሉብንን ሸክሞች በተቻለ መጠን መቀነስና አላስፈላጊ ሸክም ከመጨመር መቆጠብ እንዳለብን ግልጽ ነው።
6, 7. ኢየሱስ የሰጠውን የትኛውን ምክር ልብ ልንል ይገባል?
6 ጳውሎስ “ማንኛውንም ሸክም” ከላያችን መጣል እንዳለብን ሲገልጽ ምን ማለቱ ነበር? ያሉብንን ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደማንችል የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ልብ ማለታችን ጠቃሚ ነው፦ “‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።” (ማቴ. 6:31, 32) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እንደ ምግብና ልብስ ያሉት መሠረታዊ ነገሮች እንኳ በሕይወታችን ውስጥ ከሚገባው በላይ ትኩረት ከሰጠናቸው ሸክም ወይም እንቅፋት ሊሆኑብን እንደሚችሉ ያሳያል።
7 ኢየሱስ “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” ማለቱን ልብ በል። ይህ ሐሳብ በሰማይ ያለው አባታችን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን ያሳያል። እርግጥ ነው፣ “እነዚህ [ነገሮች] ሁሉ” ይኖሩናል ሲባል የምንፈልገውን ወይም የምንመኘውን ነገር ሁሉ እናገኛለን ማለት አይደለም። ያም ሆኖ ‘አሕዛብ አጥብቀው ስለሚፈልጓቸው’ ነገሮች መጨነቅ እንደሌለብን ተመክረናል። እንዲህ የተባልነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ቆየት ብሎ ለአድማጮቹ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።”—ሉቃስ 21:34, 35
8. በተለይ በአሁኑ ጊዜ ‘ማንኛውንም ሸክም ከላያችን መጣል’ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
8 የመጨረሻው መስመር ላይ ለመድረስ የቀረን ጊዜ አጭር ነው። ወደ ውድድሩ መገባደጃ በጣም በቀረብንበት በአሁኑ ጊዜ ፍጥነታችንን እንድንቀንስ የሚያደርገን አላስፈላጊ ሸክም በራሳችን ላይ ብንጭን እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል” በማለት የሰጠው ምክር ምንኛ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው! (1 ጢሞ. 6:6) የጳውሎስን ምክር ልብ ማለታችን ሽልማቱን የማግኘት አጋጣሚያችን ሰፊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’
9, 10. (ሀ) ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (ለ) እኛስ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ ‘ከማንኛውም ሸክም’ በተጨማሪ “በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት” ከላያችን እንድንጥል ነግሮናል። ይህ ምን ሊሆን ይችላል? “በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው። አልበርት ባርንስ የተባሉት ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሯጭ በሚሮጥበት ጊዜ በቀላሉ በእግሩ ላይ ሊጠመጠምና ሊያደናቅፈው የሚችል ልብስ ላለመልበስ እንደሚጠነቀቅ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም እንዲሁ እንቅፋት የሚሆኑበትን ነገሮች በሙሉ ማስወገድ አለበት።” አንድ ክርስቲያን እንደነዚህ ባሉት ነገሮች ሊተበተብና እምነቱ ሊዳከም የሚችለው እንዴት ነው?
10 አንድ ክርስቲያን እምነቱን በአንድ ጀምበር ሊያጣ አይችልም። እምነቱ የሚጠፋው ቀስ በቀስ ምናልባትም ሳይታወቀው ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ቀደም ሲል በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንድ ሰው ‘ከእምነት ጎዳና ቀስ በቀስ እየራቀ የመሄድ’ እንዲሁም ‘እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ በውስጡ የማቆጥቆጥ’ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ዕብ. 2:1፤ 3:12) አንድ ሯጭ ልብሱ እግሩ ላይ ከተጠመጠመበት ተደናቅፎ መውደቁ የማይቀር ነው። በተለይ ደግሞ ሯጩ በሚሮጥበት ጊዜ አንዳንድ ልብሶችን መልበስ የሚያስከትለውን አደጋ አቅልሎ ከተመለከተው የመውደቁ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። ግለሰቡ እንዲህ ያለውን አደጋ አቅልሎ እንዲመለከት የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ቸልተኝነት፣ ከልክ በላይ በራስ መተማመን ወይም ትኩረት የሚሰርቁ ሌሎች ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ጳውሎስ ከሰጠው ምክር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
11. እምነታችን እንዲጠፋ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
11 አንድ ክርስቲያን እምነቱ እንዲጠፋ ምክንያት የሚሆነው ሲከተለው የቆየው አካሄድ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። አንድ ሌላ ምሑር “በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት” የሚለው አገላለጽ ‘ያለንበት ሁኔታ፣ የግል ድክመቶቻችን እንዲሁም አብረናቸው የምንሆናቸው ሰዎች በእኛ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ’ የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል። እነዚህ ሁኔታዎች እምነታችንን ሊያዳክሙብን አልፎ ተርፎም ሊያጠፉብን ይችላሉ።—ማቴ. 13:3-9
12. እምነታችን እንዳይጠፋ የትኞቹን ማሳሰቢያዎች ልብ ማለት ይኖርብናል?
12 ታማኝና ልባም ባሪያ፣ በምናየውና በምንሰማው ይኸውም ወደ ልባችንና አእምሯችን በምናስገባው ነገር ረገድ ጠንቃቆች እንድንሆን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠን ቆይቷል። ሀብት ንብረት ለማካበት የሚደረገው ሩጫ ተብትቦ እንዳይዘን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። የመዝናኛው ዓለም የሚያቀርባቸው ቀልብ የሚስቡና ብልጭልጭ የሆኑ ነገሮች ወይም በየጊዜው የሚወጡት ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ትኩረታችንን ሊሰርቁት ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ምክሮች ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆኑ ወይም በእኛ ላይ እንደማይሠሩ አሊያም እነዚህ አደጋዎች ሊያጋጥሙን እንደማይችሉ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። የሰይጣን ዓለም በመንገዳችን ላይ የሚያስቀምጣቸው ተብትበው ሊይዙን የሚችሉ ነገሮች ስውርና አታላይ ናቸው። ቸልተኝነት፣ ከልክ በላይ በራስ መተማመን ወይም ትኩረት የሚሰርቁ ነገሮች አንዳንዶችን ለውድቀት ዳርገዋቸዋል፤ እነዚህ ነገሮች እኛም የሕይወትን ሽልማት እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ።—1 ዮሐ. 2:15-17
13. ከጎጂ ተጽዕኖዎች ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
13 በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ የሚታየው ዓይነት ግብ፣ መሥፈርትና አስተሳሰብ እንዲኖረን የሚያበረታቱ ሰዎች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። (ኤፌሶን 2:1, 2ን አንብብ።) ያም ሆኖ እነዚህ ነገሮች በእኛ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በአብዛኛው የተመካው እኛ በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው። ጳውሎስ የጠቀሰው “አየር” ገዳይ ነው። በዚህ አየር ታፍነን ወይም መተንፈስ አቅቶን ሩጫውን እንዳናቆም ሁልጊዜ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ታዲያ በሩጫው ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል? ኢየሱስ ከፊታችን እየመራን እንዳለ ፍጹም የሆነ ሯጭ ነው። (ዕብ. 12:2) የጳውሎስንም ምሳሌ መከተል እንችላለን፤ ይህ ሐዋርያ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት ሩጫ ላይ እንዳለ አድርጎ ራሱን የገለጸ ሲሆን የእምነት ባልንጀሮቹ የእሱን አርዓያ እንዲከተሉ አበረታቷቸዋል።—1 ቆሮ. 11:1፤ ፊልጵ. 3:14
‘ሽልማቱን ማግኘት’ የሚቻለው እንዴት ነው?
14. ጳውሎስ ሩጫውን ስለማጠናቀቁ ምን አመለካከት ነበረው?
14 ጳውሎስ ሩጫውን ስለማጠናቀቁ ምን አመለካከት ነበረው? ለኤፌሶን ሽማግሌዎች በሰጠው የመጨረሻ ሐሳብ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም . . . ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ለነፍሴ ምንም አልሳሳም።” (ሥራ 20:24) ጳውሎስ ሩጫውን ለማጠናቀቅ ሲል ማንኛውንም ነገር ሌላው ቀርቶ ሕይወቱን እንኳ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ሩጫውን ሳያጠናቅቅ ቢቀር ምሥራቹን ከመስበክ ጋር በተያያዘ በትጋት ያከናወነው ሥራና ድካሙ ሁሉ ከንቱ እንደሚሆን ተሰምቶት ነበር። ይሁንና ከልክ በላይ በራሱ በመተማመን ሩጫውን እንደሚያጠናቅቅ በእርግጠኝነት አልተናገረም። (ፊልጵስዩስ 3:12, 13ን አንብብ።) ሐዋርያው “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄያለሁ” ብሎ የተናገረው በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ነበር።—2 ጢሞ. 4:7
15. ጳውሎስ አብረውት ለሚሮጡት ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል?
15 ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሩጫውን እንዲያጠናቅቁ እንጂ ውድድሩን አቋርጠው እንዲወጡ አይፈልግም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በፊልጵስዩስ የነበሩትን ክርስቲያኖች የራሳቸውን መዳን ለመፈጸም ተግተው እንዲሠሩ አሳስቧቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የሕይወትን ቃል አጥብቀው መያዝ’ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። አክሎም “ይህን ካደረጋችሁ ሩጫዬም ሆነ ድካሜ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይኖረኛል” ብሏል። (ፊልጵ. 2:16) በተመሳሳይም በቆሮንቶስ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ” በማለት አሳስቧቸዋል።—1 ቆሮ. 9:24
16. የመድረሻው መስመር ወይም ሽልማቱ እውን ሆኖ ሊታየን የሚገባው ለምንድን ነው?
16 እንደ ማራቶን ባለ የረጅም ርቀት ውድድር ላይ ተወዳዳሪው ሩጫውን ሲጀምር የመድረሻው መስመር አይታየው ይሆናል። ያም ሆኖ በሚሮጥበት ጊዜ ሁሉ ትኩረቱ የሚያርፈው በመድረሻው መስመር ላይ ነው። ወደ ውድድሩ መገባደጃ እየተቃረበ ሲሄድ ይህ መስመር ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታየዋል። እኛ በምናደርገው ሩጫ ላይም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የመድረሻው መስመር ወይም ሽልማቱ እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል። ይህ መሆኑ ሽልማቱን ማግኘት እንድንችል ይረዳናል።
17. እምነት በሽልማቱ ላይ ለማተኮር የሚረዳው እንዴት ነው?
17 ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ሲሆን እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” (ዕብ. 11:1) አብርሃምና ሣራ የተደላደለ ሕይወታቸውን ትተው “[በምድሩ] ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ሆነው ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ። ይህን ለማድረግ የረዳቸው ምንድን ነው? አምላክ የሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ “ከሩቅ አይተው” ስለነበር ነው። ሙሴ ‘በኃጢአት የሚገኝን ጊዜያዊ ደስታ’ ከማሳደድ የተቆጠበ ከመሆኑም ሌላ ‘በግብፅ የሚገኘውን ውድ ሀብት’ ለመተው መርጧል። ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው እምነትና ጥንካሬ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት በመመልከቱ” ነው። (ዕብ. 11:8-13, 24-26) በእርግጥም ጳውሎስ እያንዳንዳቸው ያከናወኑትን ነገር ከመዘርዘሩ በፊት ይህን ያደረጉት “በእምነት” ተነሳስተው እንደነበር የገለጸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። እምነት በወቅቱ በሚደርስባቸው መከራና ችግር ላይ ከማተኮር ይልቅ አምላክ ለእነሱ ያደረገላቸውንና ወደፊት የሚያደርግላቸውን ነገሮች አሻግረው እንዲመለከቱ ረድቷቸዋል።
18. “በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት” ከላያችን ለመጣል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?
18 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በተጠቀሱት የእምነት ሰዎች ምሳሌ ላይ በማሰላሰልና የእነሱን አርዓያ በመከተል እኛም እምነት ማዳበር እንዲሁም “በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት” ከላያችን መጣል እንችላለን። (ዕብ. 12:1) በተጨማሪም እንደ እኛ ዓይነት እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር በመሰብሰብ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት [መስጠት] እንችላለን።”—ዕብ. 10:24
19. በአሁኑ ጊዜ ሽልማታችንን በትኩረት መመልከታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ሩጫችንን ለመጨረስ ተቃርበናል። የመድረሻው መስመር በዓይናችን የምናየው ያህል ቅርብ ነው። እኛም እምነት በማዳበርና በይሖዋ እርዳታ በመታገዝ “ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን [መጣል]” እንችላለን። አዎ፣ ሽልማቱን ይኸውም አምላካችንና አባታችን ይሖዋ ቃል የገባልንን በረከቶች ለማግኘት በሚያስችል ሁኔታ መሮጥ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥንት ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ይህ በጣም አሳፋሪ ነገር ነበር። የአዋልድ መጽሐፍ የሆነው 2ኛ መቃብያን እንደሚገልጸው ከሃዲ የነበረው ሊቀ ካህኑ ጄሰን የግሪካውያንን ባሕል ለማስፋፋት ሲል በኢየሩሳሌም የስፖርት ማዕከል ለመገንባት ሐሳብ ማቅረቡ ታላቅ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።—2 መቃ. 4:7-17
ታስታውሳለህ?
• “ማንኛውንም ሸክም” ከላያችን መጣል ምን ማድረግን ይጨምራል?
• አንድ ክርስቲያን እምነቱ እንዲጠፋ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
• ሽልማታችንን በትኩረት መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ የተባለው ምንድን ነው? ተብትቦ ሊይዘን የሚችለውስ እንዴት ነው?