ከሁሉ አስቀድማችሁ ‘የአምላክን ጽድቅ’ መፈለጋችሁን ቀጥሉ
“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴ. 6:33
1, 2. የአምላክ ጽድቅ ምንድን ነው? በምንስ ላይ የተመሠረተ ነው?
“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . መፈለጋችሁን ቀጥሉ።” (ማቴ. 6:33) ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ላይ የሰጠው ይህ ምክር በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ አይደለም። በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ይህንን መንግሥት እንደምንወደውና ለዚህ መንግሥት ታማኝ መሆን እንደምንፈልግ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። ይሁንና የአምላክን “ጽድቅ” እንድንፈልግ የሚያበረታታውን የዚህን ጥቅስ ቀጣይ ክፍልም ልንረሳው አይገባም። ታዲያ የአምላክ ጽድቅ ምንድን ነው? ከሁሉ አስቀድሞ ጽድቁን መፈለግ ሲባልስ ምን ማለት ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ጽድቅን” የሚያመለክቱት ቃላት “ፍትሕ” ወይም “ቀናነት” ተብለው ሊተረጎሙም ይችላሉ። በመሆኑም የአምላክ ጽድቅ ሲባል ይሖዋ ካወጣቸው መሥፈርቶችና መመሪያዎች አንጻር ቀና የሆነውን ነገር ያመለክታል። ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን መልካምና ክፉ እንዲሁም ትክክልና ስህተት ለሆነው ነገር መሥፈርት የማውጣት መብት አለው። (ራእይ 4:11) ይሁንና የአምላክ ጽድቅ ሲባል ማለቂያ የሌላቸው ደንቦችንና መመሪያዎችን ወይም ውልፍት የማያደርጉ ስሜት አልባ ሕግጋትን አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ማንነት እንዲሁም ከዋነኛ ባሕርያቱ አንዱ በሆነው በፍትሑ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከሌሎቹ ዋነኛ ባሕርያቱ ይኸውም ከፍቅሩ፣ ከጥበቡና ከኃይሉ ጋር የሚስማማ ነው። በመሆኑም የአምላክ ጽድቅ ከፈቃዱና ከዓላማው ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቅባቸው ነገሮችም በአምላክ ጽድቅ ውስጥ ይካተታሉ።
3. (ሀ) ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን የምንኖረው ለምንድን ነው?
3 ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ሲባል ምን ማለት ነው? በቀላል አገላለጽ እሱን ለማስደሰት ስንል የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ማለት ነው። የአምላክን ጽድቅ መፈለግ፣ ከራሳችን መሥፈርት ሳይሆን እሱ ካወጣቸው መመሪያዎችና ፍጹም ከሆኑት መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር መጣርን ይጨምራል። (ሮም 12:2ን አንብብ።) በዚህ መንገድ መኖር ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይነካል። ይህ ግን ቅጣት እንዳይደርስብን በመፍራት ሕግጋቱን የመታዘዝ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ለአምላክ ያለን ፍቅር የራሳችንን መሥፈርት ከማውጣት ይልቅ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር እሱን ለማስደሰት እንድንጥር ያነሳሳናል። ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር ትክክለኛው አካሄድ እንደሆነና ከተፈጠርንበት ዓላማ ጋር እንደሚስማማ እንገነዘባለን። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም ጽድቅን መውደድ ይኖርብናል።—ዕብ. 1:8, 9
4. የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 የይሖዋን ጽድቅ መፈለጋችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? እስቲ ይህን አስብ፦ በኤደን ገነት ለአዳምና ለሔዋን የቀረበው የመጀመሪያው ፈተና ይሖዋ መሥፈርቶችን የማውጣት መብት እንዳለው ይቀበሉ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚመዝን ነበር። (ዘፍ. 2:17፤ 3:5) በፈተናው መውደቃቸው ዘሮቻቸው በሆንነው በእኛ ላይ መከራና ሞትን አምጥቷል። (ሮም 5:12) በሌላ በኩል ግን የአምላክ ቃል “ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል” ይላል። (ምሳሌ 21:21 የ1954 ትርጉም) ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያደርግ ሲሆን ይህ ደግሞ መዳን ያስገኝልናል።—ሮም 3:23, 24
ተመጻዳቂ መሆን ያለው አደጋ
5. የትኛውን ዝንባሌ ማስወገድ ይኖርብናል?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን ጽድቅ በመፈለግ ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን ሁላችንም ልናስወግደው የሚገባንን አንድ ዝንባሌ ጠቅሷል። ጳውሎስ ስለ አይሁዳውያን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁ፤ የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም።” (ሮም 10:2, 3) ጳውሎስ እንደገለጸው እነዚያ አይሁዳውያን የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ይጥሩ ስለነበር የአምላክን ጽድቅ መረዳት አልቻሉም።a
6. የትኛውን ዝንባሌ ማስወገድ አለብን? ለምንስ?
6 እንዲህ ባለው ወጥመድ ልንወድቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ የምናቀርበውን አገልግሎት ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድርበት የፉክክር መድረክ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ነው። እንዲህ ያለው አመለካከት በራሳችን ችሎታ ከመጠን በላይ እንድንተማመን ሊያደርገን ይችላል። በእርግጥ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የይሖዋን ጽድቅ ረስተናል ማለት ነው። (ገላ. 6:3, 4) መልካም ነገር እንድናደርግ ሊያነሳሳን የሚገባው ትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ለይሖዋ ያለን ፍቅር መሆን ይኖርበታል። ጻድቅ መስለን ለመታየት የምንጥር ከሆነ ይሖዋን እንደምንወደው መናገር አንችልም።—ሉቃስ 16:15ን አንብብ።
7. ኢየሱስ ራስን ስለ ማመጻደቅ ምን ብሏል?
7 ኢየሱስ ‘ጻድቃን ነን ብለው በማሰብ በራሳቸው የሚታመኑና ሌሎችን በንቀት ዓይን የሚመለከቱ’ ሰዎች ሁኔታ አሳስቦት ነበር። ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰዎችን በተመለከተ ቀጥሎ ያለውን ምሳሌ ተናግሯል፦ “ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንደኛው ፈሪሳዊ፣ ሌላኛው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር፦ ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላላደረግከኝ አመሰግንሃለሁ። በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት አወጣለሁ።’ ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ምሕረት አድርግልኝ’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” ኢየሱስ ንግግሩን ሲደመድም “እላችኋለሁ፣ ከዚያኛው ሰው ይልቅ ይኼኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይደረጋል” ብሏል።—ሉቃስ 18:9-14
“እጅግ ጻድቅ” መሆን የሚያስከትለው አደጋ
8, 9. “እጅግ ጻድቅ” መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ምን ዓይነት ስህተት እንድንፈጽም ሊያደርገን ይችላል?
8 ልናስወግደው የሚገባው ሌላው ዝንባሌ በመክብብ 7:16 ላይ ተጠቅሷል፦ “እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ?” ይህንን መጽሐፍ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ሰው እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ማስወገድ ያለብን ለምን እንደሆነ ሲገልጽ በቁጥር 20 ላይ “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ብሏል። “እጅግ ጻድቅ” የሆነ ሰው የራሱን የጽድቅ መሥፈርት የሚያወጣ ሲሆን ይህን መሠረት በማድረግ በሌሎች ላይ ይፈርዳል። ይህን ሲያደርግ ግን የራሱን መሥፈርቶች ከአምላክ መሥፈርቶች እያስበለጠ መሆኑን አይገነዘብም፤ ይህ ድርጊቱ ደግሞ በአምላክ ፊት ጻድቅ እንዳይሆን ያደርገዋል።
9 “እጅግ ጻድቅ” መሆን ወይም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዳስቀመጡት “ከልክ በላይ ጻድቅ” መሆን ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ እንኳ ጥያቄ ውስጥ እንድናስገባ ሊያደርገን ይችላል። ይሁንና የይሖዋ ውሳኔዎች ፍትሐዊ ወይም ትክክለኛ መሆናቸውን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት፣ የራሳችንን የጽድቅ መሥፈርቶች ከይሖዋ መሥፈርቶች የማስበለጥ ያህል እንደሚሆን ማስታወስ ይኖርብናል። በሌላ አባባል ይሖዋን ለፍርድ አቅርበን ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ራሳችን ባወጣናቸው መሥፈርቶች መሠረት በእሱ ላይ መፍረድ ይሆንብናል። ሆኖም የጽድቅ መሥፈርቶችን የማውጣት መብት ያለው ይሖዋ እንጂ እኛ አይደለንም!—ሮም 14:10
10. እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም በአምላክ ላይ እንድንፈርድ የሚያነሳሳን ምን ሊሆን ይችላል?
10 ማናችንም ብንሆን በአምላክ ላይ መፍረድ ባንፈልግም ፍጹማን ባለመሆናችን እንዲህ ያለውን ስህተት ልንፈጽም እንችላለን። ተገቢ እንዳልሆነ የሚሰማንን ሁኔታ ስንመለከት ወይም እኛ ራሳችን መከራ ሲደርስብን ሳናስበው በይሖዋ ላይ ልንፈርድ እንችላለን። ታማኝ የነበረው ኢዮብ እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት ሠርቷል። መጀመሪያ ላይ ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” ሰው እንደሆነ ተገልጾ ነበር። (ኢዮብ 1:1) ይሁንና ኢዮብ የተለያዩ መከራዎች ሲፈራረቁበት የደረሰበት ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ተሰማው። ይህም “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ” እንደሆነ አድርጎ እንዲቆጥር አነሳስቶታል። (ኢዮብ 32:1, 2) ኢዮብ አመለካከቱን ማስተካከል አስፈልጎት ነበር። እኛም አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥመን ልንገረም አይገባም። እንዲህ ያለ ዝንባሌ ማዳበር ብንጀምር አመለካከታችንን ለማስተካከል ምን ሊረዳን ይችላል?
የተሟላ መረጃ የማይኖረን ጊዜ አለ
11, 12. (ሀ) ተገቢ ያልሆነ ሁኔታ እንደተፈጸመ ከተሰማን ምን ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) ኢየሱስ በወይን እርሻ ቦታ ስለተቀጠሩት ሠራተኞች በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ኢፍትሐዊ የሚመስለው ለምን ሊሆን ይችላል?
11 ልናስታውሰው የሚገባው የመጀመሪያው ነገር አንዳንድ ጊዜ የተሟላ መረጃ እንደማይኖረን ነው። ኢዮብ ያጋጠመው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ኢዮብ፣ የአምላክ ልጆች የሆኑት መላእክት በሰማይ ስብሰባ እንዳደረጉና ሰይጣን እሱን በሐሰት እንደወነጀለው አላወቀም። (ኢዮብ 1:7-12፤ 2:1-6) የችግሮቹ መንስኤ ሰይጣን መሆኑን አልተገነዘበም። እንዲያውም ኢዮብ የሰይጣንን ማንነት በውል የተረዳ አይመስልም! በመሆኑም ‘መከራ ያመጣብኝ አምላክ ነው’ ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ደርሶ ነበር። በእርግጥም የተሟላ መረጃ በማይኖረን ጊዜ በቀላሉ ወደተሳሳተ ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን።
12 ኢየሱስ በወይን እርሻ ውስጥ ስለተቀጠሩት ሠራተኞች የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት። (ማቴዎስ 20:8-16ን አንብብ።) እዚህ ላይ ኢየሱስ የወይኑ እርሻ ባለቤት፣ ሙሉ ቀን ለሠሩትም ሆነ ለአንድ ሰዓት ብቻ ለሠሩት ተቀጣሪዎች በሙሉ እኩል ገንዘብ እንደከፈላቸው ተናግሯል። ይህን ታሪክ ስታነብ ምን ይሰማሃል? ድርጊቱ ተገቢ ነው? ምናልባትም ቀኑን ሙሉ በፀሐይ እየተቃጠሉ ሲሠሩ ለዋሉት ተቀጣሪዎች ታዝንላቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የበለጠ ሊከፈላቸው ይገባል ብለህ ታስብ ይሆናል። በዚህም ምክንያት የእርሻው ባለቤት ለሠራተኞቹ እንደማያስብና ድርጊቱም ኢፍትሐዊ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። በሁኔታው ቅር መሰኘታቸውን ለገለጹት ሠራተኞች የሰጠው መልስም እንኳ ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም ሰው ያስመስለው ይሆናል። ይሁንና ስለዚህ ጉዳይ የተሟላ መረጃ አለን?
13. ኢየሱስ በወይን እርሻ ቦታ ስለተቀጠሩት ሰዎች የተናገረውን ምሳሌ ከምን አንጻር ልንመለከተው እንችላለን?
13 እስቲ ይህን ምሳሌ ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አሠሪ ሠራተኞቹ በሙሉ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ እንዳለባቸው ሳይገነዘብ አልቀረም። በኢየሱስ ዘመን የቀን ሠራተኞች የሚከፈላቸው በየዕለቱ ነበር። ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በየዕለቱ በሚያገኙት ገቢ ነበር። ይህን በአእምሯችን በመያዝ የወይኑ እርሻ ባለቤት በቀኑ መገባደጃ አካባቢ ስላገኛቸውና ለአንድ ሰዓት ብቻ ስለሠሩት ሰዎች ለማሰብ እንሞክር። ምናልባት እነዚህ ሰዎች የአንድ ሰዓት ደሞዝ ብቻ ቢከፈላቸው ቤተሰባቸውን መመገብ አይችሉ ይሆናል። ግን እኮ እነዚህ ሰዎች የሚቀጥራቸው አለማግኘታቸው እንጂ ለመሥራት ፈቃደኞች ነበሩ፤ ምክንያቱም ሥራ ለማግኘት ቀኑን ሙሉ ሲጠብቁ ውለዋል። (ማቴ. 20:1-7) በመሆኑም መሥራት አለመቻላቸው የእነሱ ጥፋት አይደለም። ሆን ብለው ላለመሥራት እንደፈለጉ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። በቀኑ ውስጥ ሠርተህ በምታገኘው ገቢ የምታስተዳድራቸው ሰዎች ቢኖሩህና ሥራ ለማግኘት ሙሉ ቀን ብትጠብቅ ምን እንደሚሰማህ አስበው። ለተወሰነ ሰዓትም ቢሆን መሥራት ብትችል በጣም አትደሰትም? ቤተሰብህን ለመመገብ የሚበቃ ክፍያ ሲሰጥህ ደግሞ ደስታህ ወሰን አይኖረውም!
14. ከወይን እርሻ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
14 እስቲ የወይኑ እርሻ ባለቤት የወሰደውን እርምጃ እንደገና እንመልከተው። ለማንም ከሚገባው ያነሰ ክፍያ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ሠራተኞች ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስፈልጋቸውን ገቢ የማግኘት መብት እንዳላቸው አድርጎ ተመልክቷቸዋል። በወቅቱ መቀጠር የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ አሠሪው አጋጣሚውን በመጠቀም ሠራተኞችን በአነስተኛ ክፍያ መቅጠር ይችል ነበር፤ ሆኖም እንዲህ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ላሠራቸው ሰዎች በሙሉ በዕለቱ ቤተሰባቸውን ለመመገብ የሚበቃ ገንዘብ ሰጥቷቸዋል። እነዚህን ተጨማሪ ነጥቦች ከግምት ማስገባታችን የወይኑ እርሻ ባለቤት ስለወሰደው እርምጃ ያለንን አመለካከት ይለውጠው ይሆናል። ያደረገው ውሳኔ አሳቢ እንደሆነ እንጂ ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም ሰው እንደሆነ አያሳይም። ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ስለ አንድ ጉዳይ ያለን መረጃ የተወሰነ ከሆነ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ይህ ምሳሌ የአምላክ ጽድቅ የላቀ መሆኑን ያጎላል። የአምላክ ጽድቅ በሕግ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፤ እንዲሁም ሰዎች የሚገባቸው በመሆናቸው ወይም ባለመሆናቸው ላይ ብቻ የተመካ አይደለም።
አስተሳሰባችን የተዛባ፣ እውቀታችንም ውስን ሊሆን ይችላል
15. አስተሳሰባችን የተዛባ ወይም እውቀታችን ውስን ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
15 ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተፈጸመ ሲሰማን ልናስታውሰው የሚገባው ሁለተኛው ነገር አስተሳሰባችን የተዛባ ወይም እውቀታችን ውስን ሊሆን እንደሚችል ነው። አለፍጽምና፣ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ወይም ባሕል አስተሳሰባችንን ሊያዛቡብን ይችላሉ። በተጨማሪም የሰዎችን ዝንባሌ ማወቅም ሆነ ልባቸውን ማንበብ አንችልም። ከዚህ በተቃራኒ ግን ይሖዋና ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች አይገድቧቸውም።—ምሳሌ 24:12፤ ማቴ. 9:4፤ ሉቃስ 5:22
16, 17. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት በፈጸመበት ወቅት ይሖዋ ምንዝርን በተመለከተ ያወጣው ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ያላደረገው ለምን ሊሆን ይችላል?
16 ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ስለፈጸመው ምንዝር የሚናገረውን ዘገባ ደግሞ እንመልከት። (2 ሳሙ. 11:2-5) በሙሴ ሕግ መሠረት ሁለቱም መገደል ነበረባቸው። (ዘሌ. 20:10፤ ዘዳ. 22:22) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ቢቀጣቸውም እሱ ራሱ ያወጣው ሕግ እንዲፈጸምባቸው አላደረገም። ታዲያ ይሖዋ የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ አልነበረም ማለት ነው? ለዳዊት በማዳላት የራሱን የጽድቅ መሥፈርት ጥሷል? መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ተሰምቷቸዋል።
17 ይሁንና ይሖዋ ምንዝርን በተመለከተ ያወጣው ሕግ፣ ልብን ማንበብ ለማይችሉ ፍጽምና የጎደላቸው ዳኞች የተሰጠ መሆኑን ማስታወስ ይገባናል። እነዚህ ዳኞች ልብን ማወቅ ባይችሉም ይህ ሕግ መኖሩ የማይለዋወጥ ፍርድ ለመስጠት አስችሏቸዋል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ልብን ማንበብ ይችላል። (ዘፍ. 18:25፤ 1 ዜና 29:17) በመሆኑም ይሖዋ ፍጽምና ለጎደላቸው ዳኞች ብሎ ባወጣው ሕግ ሊገደብ እንደሚገባው መጠበቅ አይኖርብንም። እንዲህ ብሎ ማሰብ የዓይን ችግር ያለውን ሰው ለመርዳት የተዘጋጀውን መነጽር ጤናማ ዓይን ያለው ግለሰብ እንዲያደርግ የማስገደድ ያህል አይሆንም? ይሖዋ የዳዊትንና የቤርሳቤህን ልብ ማንበብና ከልባቸው ንስሐ እንደገቡ ማየት ይችል ነበር። የተመለከተውን ነገር ከግምት በማስገባት ምሕረትና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ፍርድ ሰጥቷቸዋል።
የይሖዋን ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ
18, 19. በራሳችን የጽድቅ መሥፈርት መሠረት ፈጽሞ በአምላክ ላይ ላለመፍረድ ምን ሊረዳን ይችላል?
18 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዘገባዎች ስናነብ አሊያም በግል ሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ነገሮች ስንመለከት አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ያደረገው ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ሊሰማን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ በራሳችን የጽድቅ መሥፈርት መሠረት ፈጽሞ በአምላክ ላይ ላለመፍረድ መጠንቀቅ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ የተሟላ መረጃ እንደማይኖረን እንዲሁም አስተሳሰባችን ሊዛባ ወይም እውቀታችን ውስን ሊሆን እንደሚችል እናስታውስ። “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም [እንደማያደርግ]” ፈጽሞ አንዘንጋ። (ያዕ. 1:19, 20) እንዲህ ካደረግን ምንጊዜም ቢሆን ልባችን በይሖዋ ላይ ‘አይቆጣም።’—ምሳሌ 19:3 የ1954 ትርጉም
19 ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ትክክለኛና ጽድቅ ለሆነው ነገር መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው ይሖዋ ብቻ መሆኑን ምንጊዜም አምነን እንቀበል። (ማር. 10:17, 18) ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች “ትክክለኛ እውቀት” ለማግኘት ጥረት እናድርግ። (ሮም 10:2፤ 2 ጢሞ. 3:7) እንዲህ በማድረግና ሕይወታችንን ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በመምራት ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን “ጽድቅ” እንደምንፈልግ እናሳያለን።—ማቴ. 6:33
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ምሑር እንደተናገሩት መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ለመመሥረት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ‘ሐውልት ማቆም’ የሚል ፍቺም ሊኖረው ይችላል። በመሆኑም እነዚያ አይሁዳውያን ለአምላክ ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ሲሉ ምሳሌያዊ ሐውልት ያቆሙ ያህል ነበር።
ታስታውሳለህ?
• የይሖዋን ጽድቅ መፈለጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• የትኞቹን ሁለት አደገኛ ዝንባሌዎች ማስወገድ ይኖርብናል?
• ከሁሉም አስቀድመን የአምላክን ጽድቅ መፈለግ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለጸለዩት ሁለት ሰዎች ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሥራ አንድ ሰዓት ለተቀጠሩት ሠራተኞች ሙሉ ቀን ከሠሩት እኩል መከፈሉ ፍትሐዊ ነበር?