‘የሚድኑት’ እነማን ናቸው?
“የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።”—ሥራ 2:21
1. በ33 እዘአ የዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በዓለም ታሪክ ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የነበረው ለምንድን ነው?
በ33 እዘአ የዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን በዓለም ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዕለት ነበር። ለምን? በዚህ ዕለት አንድ አዲስ ብሔር ተወልዷል። ይህ ብሔር በመጀመሪያ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ደርብ ውስጥ የነበሩትን 120 የሚያክሉትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብቻ ያቀፈ ስለነበር ትልቅ ብሔር አልነበረም። ዛሬ በዚያ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ብሔሮች ፈጽመው ሲረሱ ይህ በዚያ ደርብ ውስጥ የተወለደው ብሔር ግን አሁንም በመካከላችን ይገኛል። ይህ ሐቅ ለሁላችንም ትልቅ ትርጉም አለው። ምክንያቱም አምላክ በመላው የሰው ልጅ ፊት ምሥክር እንዲሆን የሾመው ይህ ብሔር ነው።
2. አዲሱ ብሔር ወደ ሕልውና በመጣበት ጊዜ ምን ተዓምራዊ ክንውኖች ተፈጽመዋል?
2 ይህ አዲስ ብሔር ወደ ሕልውና በመጣበት ጊዜ ለኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ የሚሆኑ አስፈላጊ የሆኑ ክንውኖች ተፈጽመዋል። ስለ እነዚህ ክንውኖች ሥራ 2:2-4 ላይ እንደሚከተለው እናነባለን:- “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” በዚህ መንገድ እነዚህ 120 የሚያክሉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች መንፈሳዊ ብሔር፣ ማለትም ቆየት ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር እስራኤል” ሲል የጠራው ሕዝብ የመጀመሪያ አባላት ሆኑ።— ገላትያ 6:16
3. በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን የተፈጸመው የትኛው የኢዩኤል ትንቢት ነው?
3 ‘የዓውሎ ነፋሱ ድምፅ’ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሲሉ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ሐዋርያው ጴጥሮስም ከኢዩኤል ትንቢቶች አንዱ መፈጸም መጀመሩ እንደሆነ ገለጸላቸው። የትኛው ትንቢት? ጴጥሮስ የተናገረውን አዳምጥ:- “እግዚአብሔር ይላል:- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፣ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፣ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።” (ሥራ 2:17-21) እነዚህ ጴጥሮስ የጠቀሳቸው ቃላት ኢዩኤል 2:28-32 ላይ የሚገኙ ሲሆን ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በአይሁድ ሕዝብ ላይ ጥፋት በጣም የቀረበ መሆኑን ያመለክታል። የታመኑ ሆነው ያልተገኙ እስራኤላውያን የሚቀጡበት ‘ታላቁና የተሰማው የይሖዋ ቀን’ ቀርቦ ነበር። ታዲያ ከጥፋቱ የሚድኑት እነማን ናቸው? ይህስ በዘመናችን ለሚፈጸም ለየትኛው ነገር ጥላ ሆኗል?
የትንቢቱ ሁለት ፍጻሜዎች
4, 5. መጪዎቹን ክንውኖች ግምት ውስጥ በማስገባት ጴጥሮስ ምን ምክር ሰጥቷል? ይህ ምክሩ ከእሱ ዘመን በኋላ የሚሠራውስ ለምንድን ነው?
4 ከ33 እዘአ በኋላ ባሉት ዓመታት የአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል እየበዛ ሲሄድ ሥጋዊው የእስራኤል ብሔር ግን እየመነመነ መጣ። በ66 እዘአ ሥጋዊው እስራኤል ከሮም መንግሥት ጋር ውጊያ ገጠመ። በ70 እዘአ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ባትጠፋም ኢየሩሳሌም ግን ከነቤተ መቅደስዋ ተቃጥላ ትቢያ ሆናለች። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጴጥሮስ ይህን አሳዛኝ ክንውን አስመልክቶ ጥሩ ምክር ሰጥቶ ነበር። ኢዩኤልን ደግሞ በመጥቀስ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል” አላቸው። እያንዳንዱ ግለሰብ አይሁዳዊ የይሖዋን ስም ለመጥራት የግል ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። ይህም የጴጥሮስን ተጨማሪ መመሪያ መፈጸምን የሚጨምር ነበር:- “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ።” (ሥራ 2:38) የጴጥሮስ አድማጮች የእስራኤል ሕዝብ በብሔር ደረጃ የካደውን ኢየሱስን መሲሕ እንደሆነ መቀበል ነበረባቸው።
5 እነዚህ የኢዩኤል ትንቢታዊ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ላይ ትልቅ ውጤት አስከትለዋል። በዛሬው ጊዜ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ውጤት አላቸው። ምክንያቱም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ክንውኖች እንደሚያመለክቱት የኢዩኤል ትንቢት ሁለተኛ ፍጻሜ አለው። እንዴት እንደተፈጸመ እስቲ እንመልከት።
6. የአምላክ እስራኤል ማንነት 1914 እየተቃረበ በመጣ ጊዜ ግልጽ ሆኖ የታየው እንዴት ነው?
6 ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ የአምላክ እስራኤል በሐሰት ክርስትና እንክርዳድ ተሸፈነ። በ1914 በጀመረው የመጨረሻ ቀን ግን የዚህ መንፈሳዊ ብሔር ማንነት እንደገና ግልጽ ሆኖ ታየ። ይህ ሁሉ የተፈጸመው ኢየሱስ ስለ ስንዴና እንክርዳድ በተናገረው ምሳሌ መሠረት ነው። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) ቅቡዓን ክርስቲያኖች 1914 እየቀረበ ሲመጣ የሕዝበ ክርስትናን የሐሰት ትምህርቶች በድፍረት በማስወገድና ‘የተወሰነው የአሕዛብ ዘመን’ ሊፈጸም የተቃረበ መሆኑን በመስበክ ራሳቸውን ከከዳተኛይቱ ሕዝበ ክርስትና መለየት ጀመሩ። (ሉቃስ 21:24) ይሁን እንጂ በ1914 የፈነዳው የመጀመሪያ ዓለም ጦርነት ገና ያልተዘጋጁባቸው ጥያቄዎች አስነሳባቸው። በደረሰባቸው ከባድ ተጽእኖ ምክንያት ብዙዎች እንቅስቃሴያቸውን የቀነሱ ሲሆን አንዳንዶቹ አቋማቸውን እስከማላላት ደርሰዋል። በ1918 የስብከት እንቅስቃሴያቸው ፈጽሞ አቆመ ከሚባልበት ደረጃ ላይ ደረሰ።
7. (ሀ) በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጋር የሚመሳሰል በ1919 የተፈጸመ ምን ሁኔታ አለ? (ለ) ከ1919 ጀምሮ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የአምላክ መንፈስ መውረዱ ምን ውጤት አስገኝቷል?
7 ቢሆንም በዚህ ሁኔታቸው ብዙ አልቆዩም። ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መንፈሱን በሕዝቡ ላይ ማፍሰስ ጀመረ። እርግጥ፣ በ1919 በተለያዩ ልሳናት መናገርም ሆነ ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ አልነበረም። በ1 ቆሮንቶስ 13:8 ላይ ከተጻፉት ቃላት እንደምንረዳው ተአምራት የሚደረጉበት ዘመን ካበቃ ረዥም ጊዜ ሆኗል። ይሁን እንጂ በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ታማኝ ክርስቲያኖች ባገኙት ማነቃቂያ አንሰራርተው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ በጀመሩ ጊዜ የአምላክ መንፈስ እንደፈሰሰላቸው ግልጽ ሆኖ ነበር። በ1922 ደግሞ ወደ ሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ተመልሰው “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” በሚለው ጥሪ አማካኝነት ተጠናክረው ለሥራ ተነሳሱ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ በዚህም ወቅት ዓለም የአምላክ መንፈስ መፍሰስ ያስከተለውን ውጤት ለማስተዋል ተገድዶ ነበር። እያንዳንዱ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን፣ ወንድም ሆነ ሴት፣ ሽማግሌም ሆነ ወጣት ‘የአምላክን ድንቅ ነገሮች’ በማወጅ ትንቢት መናገር ጀመረ። (ሥራ 2:11) እንደ ጴጥሮስ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” እያሉ መማጸን ጀመሩ። (ሥራ 2:40) ታዲያ ይህን ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ይህን ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? በኢዩኤል 2:32 ላይ የሚገኙትን “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚሉትን የኢዩኤል ቃላት በመፈጸም ነው።
8. ከአምላክ እስራኤል ጋር የተያያዙት ጉዳዮች ከ1919 ጀምሮ እድገት ያሳዩት እንዴት ነው?
8 ከአምላክ እስራኤል ጋር የተያያዙት ጉዳዮች ከነዚህ ቀደምት ዓመታት ጀምሮ ወደፊት በመግፋት ላይ ናቸው። የመጨረሻዎቹ ቅቡዓን የታተሙ ሲሆን ከ1930ዎቹ ጀምሮ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ቅን ሰዎች ብቅ ብለዋል። (ራእይ 7:3, 9) ሁሉም ቢሆኑ ከፍተኛ የሆነ የጥድፊያ ስሜት ይሰማቸዋል። ምክንያቱም የኢዩኤል 2:28, 29 ሁለተኛ ፍጻሜ ምድር አቀፉ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የንግድ ሥርዓት ድምጥማጡ ወደሚጠፋበት ታላቅና አስፈሪ የይሖዋ ቀን እንደቀረብን ያመለክታል። ከጥፋቱ እንደሚያድነን ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘የይሖዋን ስም የምንጠራበት’ በቂ ምክንያት አለን!
የይሖዋን ስም የምንጠራው እንዴት ነው?
9. የይሖዋን ስም መጥራት የትኞቹን ነገሮች ያጠቃልላል?
9 የይሖዋን ስም መጥራት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? የኢዩኤል 2:28, 29 አገባብ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ እርሱን ለሚጠራ ለሁሉም ጆሮውን አይሰጥም። ኢሳይያስ በሚባል ሌላ ነቢይ አማካኝነት ይሖዋ ለእስራኤላውያን “እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም” ብሏል። ይሖዋ ሕዝቡን ለመስማት እምቢተኛ የሆነው ለምንድን ነው? “እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” ሲል ራሱ ገልጿል። (ኢሳይያስ 1:15) ይሖዋ ደም አፍሳሽ የሆነን ወይም ልማደኛ ኃጢአተኛ የሆነን ሰው አይሰማም። ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ቀን አይሁዳውያን ንስሐ ግቡ ያለው በዚህ ምክንያት ነበር። ኢዩኤልም ንስሐ መግባት በጣም አስፈላጊ መሆኑን በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል በኢዩኤል 2:12, 13 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “አሁንስ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ በፍጹም ልባችሁ፣ በጾምም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፣ ቁጣው የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።” ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1919 ጀምረው ከእነዚህ ቃላት ጋር የሚስማማ ሥራ ሠርተዋል። ከስህተቶቻቸው ንስሐ የገቡ ሲሆን ዳግመኛ ከአቋማቸው ፍንክች ላለማለት ወይም ላለመቀዝቀዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይህም የአምላክ መንፈስ የሚፈስበትን መንገድ ክፍት አድርጎላቸዋል። የይሖዋን ስም ለመጥራትና ይሖዋም እንዲሰማው የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ይህንኑ አካሄድ መከተል ይኖርበታል።
10. (ሀ) እውነተኛ ንስሐ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለእውነተኛ ንስሐ ምን ምላሽ ይሰጣል?
10 እውነተኛ ንስሐ “አዝናለሁ” በማለት ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ አስታውሱ። እስራኤላውያን የሐዘናቸውን ክብደት ለማሳየት ልብሳቸውን ይቀዱ ነበር። ይሖዋ ግን “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” ብሏል። እውነተኛ ንስሐ የሚመነጨው ከውስጣችን ማለትም ከልባችን ነው። ኢሳይያስ 55:7 ላይ እንደምናነበው ለክፉ ድርጊቶች ጀርባችንን መስጠትን ይጨምራል:- “ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም አሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ።” ኢየሱስ እንዳደረገው ኃጢአትን መጥላትን ይጨምራል። (ዕብራውያን 1:9) እንዲህ ካደረግን ይሖዋ “ቸርና መሐሪ፣ ቁጣው የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ” ስለሆነ በቤዛዊው መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር እንደሚለን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አምልኮታችንን ማለትም መንፈሳዊውን የእህልና የመጠጥ ቁርባናችንን ይቀበለናል። ስሙን ስንጠራ ያዳምጠናል።—ኢዩኤል 2:14
11. በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ አምልኮ ምን ቦታ ሊኖረው ይገባል?
11 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” በማለት ልናስብበት የሚገባንን ሌላ ነገር ጠቅሷል። (ማቴዎስ 6:33) አምልኮታችንን ለይስሙላ ብቻ ወይም የሕሊናችንን ወቀሳ ጋብ ለማድረግ ብቻ የምንፈጽመው ነገር አድርገን መመልከት አይኖርብንም። አምላክን ማገልገል በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መያዝ ይኖርበታል። በመሆኑም ይሖዋ በኢዩኤል አማካኝነት እንደሚከተለው በማለት ይቀጥላል:- “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ . . . ሕዝቡንም አከማቹ፣ ማኀበሩንም ቀድሱ፣ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፣ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፣ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ።” (ኢዩኤል 2:15, 16) አዲስ የተጋቡ ባልና ሚስት ትኩረታቸው ከምንም ነገር በላይ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት እንደሚያዝ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ለእነርሱም እንኳን ቢሆን ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የበለጠ ቅድሚያ ይሰጠዋል። ወደ አምላካችን ከመሰብሰብና ስሙን ከመጥራት የሚበልጥብን ምንም ዓይነት ጉዳይ ሊኖር አይገባም።
12. ባለፈው ዓመት ከተከበረው የመታሰቢያው በዓል የተገኘው ሪፖርት የማደግ አቅም እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 ይህንን በአእምሮአችን እንያዝና በ1997 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ላይ የተገለጹ አሐዛዊ መረጃዎችን እንመልከት። ባለፈው ዓመት 5,599,931 ከፍተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ነበረን። በእርግጥም ይሖዋን የሚያወድሱ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ! በመታሰቢያው በዓል ላይ 14,322,226 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ከጠቅላላዎቹ አስፋፊዎች በስምንት ተኩል ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ተገኝተው ነበር ማለት ነው። ይህ አኃዝ ራሱ ገና ብዙ የማደግ አቅም እንዳለን ያመለክታል። ከእነዚህ ስምንት ተኩል ሚልዮን ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ያሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ወይም የተጠመቁ ወላጆች ያሏቸው ልጆች ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ የተገኙ በርካታ ሰዎችም ነበሩ። ስብሰባ ላይ መገኘታቸው የይሖዋ ምሥክሮች ከእነርሱ ጋር እንዲተዋወቁና ተጨማሪ ዕድገት እንዲያደርጉ እንዲረዷቸው የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አስገኝቶላቸዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ በየዓመቱ በመታሰቢያ በዓልና ምናልባትም በአንዳንድ ሌሎች ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ፣ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ ምንም ዓይነት እድገት የማያሳዩ ሰዎች አሉ። እርግጥ፣ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አብረውን መሰብሰባቸው ያስደስተናል። ይሁን እንጂ የኢዩኤልን ትንቢታዊ ቃላት በጥንቃቄ እንዲያሰላስሉና የይሖዋን ስም ሲጠሩ እንደሚሰማቸው እርግጠኞች ለመሆን መውሰድ ስለሚኖርባቸው ተጨማሪ እርምጃዎች በጥሞና እንዲያስቡ ከልብ እንመክራቸዋለን።
13. የይሖዋን ስም የምንጠራ ሁሉ ለሌሎች ምን የማድረግ ኃላፊነት አለብን?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ስም መጥራት ያለውን ሌላ ገጽታ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚለውን የኢዩኤል ትንቢት ጠቅሷል። ከዚያም “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” ብሏል። (ሮሜ 10:13, 14) አዎን፣ ይሖዋን እስከ አሁን የማያውቁ ሌሎች ሰዎችም የአምላክን ስም እንዲጠሩ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። እኛ ይሖዋን የምናውቅ ሰዎች የመስበክ ብቻ ሳይሆን ወደነዚህ ሰዎች የመሄድና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ የመስጠት ኃላፊነት አለብን።
መንፈሳዊ ገነት
14, 15. የይሖዋ ሕዝቦች እሱን በሚያስደስተው መንገድ ስሙን ስለሚጠሩ የትኞቹን ገነታዊ በረከቶች አግኝተው ይደሰታሉ?
14 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች በጎች ያላቸው አመለካከት ይህን የመሰለ ነው። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ይባርካቸዋል። “እግዚአብሔርም ስለ ምድሩ ቀና፣ ለሕዝቡም ራራለት።” (ኢዩኤል 2:18) ይሖዋ በ1919 ሕዝቦቹን መልሶ ባቋቋመና ወደ መንፈሳዊ ገነት ባገባ ጊዜ ቅንዓትና ርህራሄ አሳይቷቸዋል። ኢዩኤል በሚከተሉት ቃላት በገለጸው መሠረት ይህ ገነት እውነተኛ መንፈሳዊ ገነት ነው:- “ምድር ሆይ፣ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፣ ደስም ይበልሽ፣ እልልም በይ። እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፣ የምድረ በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፣ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፣ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ። እናንተ የጽዮን ልጆች፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር የፊተኛውን ዝናብ በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፣ እንደ ቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፣ ለእርሱም እልል በሉ። አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፣ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ።”—ኢዩኤል 2:21-24
15 እንዴት ያለ አስደሳች ሥዕላዊ መግለጫ ነው! በእስራኤል ምድር ለዕለታዊ ቀለብነት የሚያገለግሉት ሦስት ነገሮች ማለትም እህል፣ የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅ ከመንጋዎች ጋር ሊትረፈረፉ ነው። በእኛ ዘመን እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት የተፈጸሙት በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በሙሉ ይሰጠናል። አምላክ ይህን ሁሉ ዝግጅት አትረፍርፎ በመስጠቱ አትደሰቱም? በእርግጥ ሚልክያስ እንደተነበየው አምላካችን ‘የሰማይን መስኮቶች ከፍቶ ምንም የሚቸግረን ነገር እስከማይኖር ድረስ በረከቱን አዝንቦልናል።’— ሚልክያስ 3:10
የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ
16. (ሀ) የይሖዋ መንፈስ መፍሰሱ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው? (ለ) የወደፊቱ ጊዜ ምን ነገር ይዞልናል?
16 ኢዩኤል ስለ ይሖዋ መንፈስ መፍሰስ የተነበየው የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩበትን ገነታዊ ሁኔታ ከተነበየ በኋላ ነበር። ጴጥሮስ ይህን ትንቢት በጰንጠቆስጤ ዕለት በጠቀሰ ጊዜ ትንቢቱ የተፈጸመው “በመጨረሻው ቀን” እንደሆነ አመልክቷል። (ሥራ 2:17) የአምላክ መንፈስ በዚያ ዘመን መፍሰሱ የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት በመጨረሻ ቀን ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አመልክቷል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የአምላክ መንፈስ በአምላክ እስራኤል ላይ መፍሰሱ ደግሞ በዓለም አቀፉ ሥርዓት መጨረሻ ቀን ውስጥ መኖራችንን ያመለክታል። ታዲያ የወደፊቱ ጊዜ ምን ነገር ይዞልናል? የኢዩኤል ትንቢት እንደሚከተለው ይለናል:- “በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፣ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።”—ኢዩኤል 2:30, 31
17, 18. (ሀ) በኢየሩሳሌም ላይ የመጣው የይሖዋ አስፈሪ ቀን ምንድን ነው? (ለ) ወደፊት የይሖዋ አስፈሪ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆናችን ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
17 እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ሁኔታዎች በ70 እዘአ ወደተከናወነው የይሖዋ የሚያስፈራ ቀን መቋጫ መገስገስ በጀመሩበት በ66 እዘአ መፈጸም ጀምረዋል። በዚያ ጊዜ የይሖዋን ስም ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አለመሆን ምን ያህል የሚያስፈራ ሆኖ ይሆን! ዛሬም የዚህኑ ያህል የሚያስፈሩ ክንውኖች ከፊታችን ይጠብቁናል። የመላው ዓለም ሥርዓት በይሖዋ እጅ ተንኮታኩቶ ይወድማል። ሆኖም ከዚህ ጥፋት መዳን ይቻላል። ትንቢቱ በመቀጠል “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፣ የምስራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ” ይላል። (ኢዩኤል 2:32) በእርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን ስም ለማወቅ በመቻላቸው በጣም አመስጋኞች ናቸው። ስሙን በሚጠሩበት ጊዜም እንደሚያድናቸው እርግጠኞች ናቸው።
18 ይሁን እንጂ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን በዚህ ዓለም ላይ መዓቱን በሚያወርድበት ጊዜ ምን ይሆናል? ይህ ጉዳይ በመጨረሻው የጥናት ርዕስ ላይ ይብራራል።
ታስታውሳለህን?
◻ ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ በመጀመሪያ መንፈሱን ያፈሰሰው መቼ ነበር?
◻ የይሖዋን ስም መጥራት የሚያጠቃልላቸው አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
◻ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን በሥጋውያን እስራኤል ላይ የመጣው መቼ ነበር?
◻ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ስሙን የሚጠሩትን የሚባርከው እንዴት ነው?
[ገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን አንድ አዲስ ብሔር ተወልዷል
[ገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢዩኤል 2:28, 29 ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በዚህ መቶ ዘመን ቀደምት ዓመታት ላይ ይሖዋ በድጋሚ በሕዝቡ ላይ መንፈሱን አፍስሷል
[ገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች የይሖዋን ስም እንዲጠሩ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል