የዓለም መንፈስ እየመረዛችሁ ነውን?
በመስከረም 12, 1990 ካዛክስታን በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ላይ ፍንዳታ ተከሰተ። አደገኛ የሆኑ የራዲዮ አክቲቭ ጨረሮች ወደ ከባቢው አየር ተረጩ። በአካባቢው የሚኖሩ ከ120,000 የሚበልጡ ሰዎችን ጤንነት አደጋ ላይ በመጣሉ በርካታ ሰዎች ገዳይ የሆነውን መርዝ በመቃወም በመንገዶች ላይ ትዕይንተ ሕዝብ አደረጉ።
ይሁን እንጂ ተጨማሪ መረጃዎች በተገኙ ጊዜ ለአሥርተ ዓመታት መርዛማ በሆነ አካባቢ ይኖሩ እንደነበር አወቁ። ለበርካታ ዓመታት 100,000 ቶን የራዲዮ አክቲቭ ዝቃጭ ባልታጠረ፣ ክፍት ሜዳ ላይ ተከማችቶ ነበር። አደጋው ደጃፋቸው ላይ የነበረ ቢሆንም እንኳን ማንም ሰው ጉዳዩን ከመጤፍ አልቆጠረውም። ለምን?
ባለ ሥልጣናት የሚወጣውን ጨረር መጠን የሚገልጽ ማስታወቂያ በአካባቢው በሚገኝ በአንድ ስታዲዮም ውስጥ በየዕለቱ ይለጥፉ ስለነበር ማስታወቂያው ምንም ዓይነት አደጋ አይደርስም የሚል አመለካከት አሳድሮ ነበር። አኃዙ ትክክል ነበር። ይሁን እንጂ ያመለክት የነበረው የጋማ ጨረርን ብቻ ነበር። መጠኑ ያልተገለጸው የአልፋ ጨረር ብናኝም ቢሆን የዚያኑ ያህል ገዳይ ሊሆን የሚችል ነው። ብዙ እናቶች ልጆቻቸው ያን ያህል ለምን ታማሚ እንደሆኑባቸው ቀስ በቀስ መረዳት ጀመሩ።
በመንፈሳዊ ሁኔታም በማይታዩ በካይ ነገሮች እየተመረዝን ሊሆን ይችላል። እንዲሁም በካዛክስታን ይኖሩ እንደነበሩት ያልታደሉ ሰዎች ሕይወትን አስጊ ሁኔታ ላይ ስለሚጥለው ስለዚህ አደጋ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያውቁት ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ብክለት ‘የዓለም መንፈስ’ በማለት ይገልጸዋል። ይህንንም በበላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 2:12) የአምላክ ባላጋራ ይህን የዓለም መንፈስ ወይም በብዙዎች ዘንድ ተስፋፍቶ የሚገኘውን አመለካከት ለአምላክ ያለንን የጠለቀ ፍቅር ለማዳከም በተንኮል መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።
የዓለም መንፈስ መንፈሳዊ ኃይላችንን ሊያሟጥጥብን የሚችለው እንዴት ነው? የዓይን አምሮትን በመቀስቀስና በዘር የወረስነውን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በመጠቀም ነው። (ኤፌሶን 2:1-3፤ 1 ዮሐንስ 2:16) ዓለማዊ አስተሳሰብ መንፈሳዊነታችንን ቀስ በቀስ ሊመርዝ የሚችልበትን ሦስት የተለያዩ መንገዶችን እንደ ምሳሌ አድርገን እንመለከታለን።
አስቀድሞ መንግሥቱን መፈለግ
ኢየሱስ ‘አስቀድመው መንግሥቱንና የአምላክን ጽድቅ እንዲፈልጉ’ ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም መንፈስ ለራሳችን ፍላጎቶችና ምቾት ከተገቢው በላይ ትኩረት እንድንሰጥ ሊያደርገን ይችላል። የመጀመሪያው አደጋ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ጨርሶ መተዉ ሳይሆን እነሱን በሁለተኛ ደረጃ ማስቀመጡ ነው። በካዛክስታን ይኖሩ እንደነበሩት ሰዎች ተታልለን ደህንነት እንደተሰማን አድርገን በማሰብ አደጋውን ችላ ልንል እንችላለን። ለዓመታት በታማኝነት ማገልገላችንና ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለን አድናቆት የእውነትን መንገድ ፈጽሞ ልንተው እንደማንችል አድርገን እንድናስብ ሊያደርጉን ይችላሉ። በኤፌሶን ጉባኤ ይኖሩ የነበሩ ብዙዎቹ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ሳያድርባቸው አልቀረም።
በ96 እዘአ አካባቢ ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷቸው ነበር:- “ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና።” (ራእይ 2:4) ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት እነዚህ ክርስቲያኖች ብዙ ችግሮችን አሸንፈዋል። (ራእይ 2:2, 3) ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ ታማኝ ከሆኑ ሽማግሌዎች ተምረው ነበር። (ሥራ 20:17-21, 27) ይሁን እንጂ ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ለይሖዋ የነበራቸው ፍቅር እየተዳከመ ሄዷል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ግለታቸውን አጥተዋል።—ራእይ 2:5
በኤፌሶን ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከተማው ውስጥ በነበረው ንግድና ብልጥግና ሳይነኩ አልቀረም። የሚያሳዝነው ደግሞ ቁሳዊ ሃብት በማሳደዱ የሚታወቀው የዛሬው ኅብረተሰብ በተመሳሳይ መንገድ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ጠልፎ ወስዷል። የተንደላቀቀ የአኗኗር መንገድ ለመከተል ቆርጦ መነሳት ከመንፈሳዊ ግቦቻችን ዞር እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም።—ከማቴዎስ 6:24 ጋር አወዳድር።
ኢየሱስ ስለዚህ አደጋ ሲያስጠነቅቅ “የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ [“ቀና፣” NW] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ [“ክፉ፣” NW፤ “ቀናተኛ፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:22, 23) “ቀና” ዓይን መንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩር ዓይን ነው፤ በአምላክ መንግሥት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ዓይን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ “ክፉ” ወይም “ቀናተኛ” ዓይን በቅርብ ብቻ የሚመለከት፣ አሁን በሚገኙ ሥጋዊ ፍላጎቶች ላይ ብቻ ማትኮር የሚችል ዓይን ማለት ነው። መንፈሳዊ ግቦችና የወደፊት ሽልማቶች ግን እንዲህ ካለው ዓይን እይታ ውጭ ናቸው።
ኢየሱስ በፊተኛው ቁጥር ላይ “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:21) ልባችን ያተኮረው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ወይም በቁሳዊ ነገሮች ላይ መሆኑን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ‘አፍ የሚናገረው ከልብ ሞልቶ የተረፈውን’ በመሆኑ ከሁሉ የተሻለው መመዘኛ አነጋገራችን ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 6:45) ስለ ቁሳዊ ነገሮች ወይም ስለ ዓለማዊ የሥራ ክንውኖች አዘውትረን እንደምናወራ ከተገነዘብን ይህ ልባችን የተከፋፈለና መንፈሳዊ እይታችን የተዛባ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።
የስፔይን ተወላጅ የሆነችው ካርሜንa የተባለች እህት ይህን ችግር ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል አድርጋለች። እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ያደግሁት በእውነት ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን 18 ዓመት ሲሆነኝ የራሴን የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ከፈትኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ አራት ሠራተኞች ቀጠርኩ፤ ሥራውም አመርቂ እየሆነ መጣ፤ ብዙ ገንዘብ አገኝ ጀመር። ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝ ግን በገንዘብ በኩል ራሴን መቻሌና ‘የተሳካልኝ’ መሆኔ ሳይሆን አይቀርም። እውነት ለመናገር ልቤ ሥራዬ ላይ ነበር፤ ለሥራዬም ከፍተኛ ፍቅር ነበረኝ።
“አብዛኛውን ጊዜዬን ለሥራ ጉዳዮች ብሰዋም ምሥክር ሆኜ መቀጠል እንደምችል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋን ለማገልገል የበለጠ መሥራት እንደምችል ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። በመጨረሻ የመንግሥቱን ጉዳዮች በአንደኛ ቦታ እንዳስቀምጥ የገፋፋኝ ነገር የሁለት አቅኚ ጓደኞቼ ምሳሌነት ነው። አንደኛዋ ማለትም ሁሊያና እኔ ባለሁበት ጉባኤ ነበረች። አቅኚ እንድሆን አልተጫነችኝም፣ ነገር ግን የምታወራው ነገርና ከአገልግሎቷ ታገኘው የነበረው በግልጽ የሚታየው ደስታዋ ለመንፈሳዊ ነገሮች የምሰጠውን ቦታ በድጋሚ እንዳጤን ረድቶኛል።
“ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለእረፍት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄድኩና ግሎሪያ የምትባል አቅኚ እህት ቤት አረፍኩ። በዚያን ጊዜ ባሏ ከሞተ ብዙም አልቆየም ነበር፤ እንዲሁም የአምስት ዓመት ሴት ልጅዋን እያሳደገች የካንሰር በሽተኛ የሆኑትን እናቷን ታስታምማለች። ሆኖም አቅኚ ነበረች። የሷ ምሳሌነትና ለአገልግሎቱ ያላት ልባዊ አድናቆት ልቤን ነካው። በእርሷ ቤት የቆየሁባቸው አራት ቀናት ለይሖዋ የተቻለኝን ለማድረግ እንድወስን አድርገውኛል። በመጀመሪያ የዘወትር አቅኚ ሆንሁ፤ ከዛም ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔና ባለቤቴ በቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። ለመንፈሳዊ እድገቴ ደንቃራ የሆነብኝን ሥራዬን አቆምኩ፤ ባሁኑ ጊዜ በይሖዋ ፊት የተስተካከለ አቋም እንዳለኝ ይሰማኛል፤ ደግሞም ዋናው ነገር ይህ ነው።”—ሉቃስ 14:33
ካርሜን እንዳደረገችው ‘የሚሻለውን ነገር ፈትኖ ማወቅን’ መማር ስለ ሥራችን፣ ስለ ትምህርታችን፣ ስለ ቤታችንና ስለ አኗኗራችን ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ነገር ግን ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ሁኔታም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር እናስቀድማለንን? የዓለም መንፈስ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድርበት ሌላው መስክ ይህ ነው።
መዝናኛን በተገቢው ቦታ አስቀምጡት
የዓለም መንፈስ ሰዎች ለእረፍትና ለመዝናኛ ያላቸውን የተፈጥሮ ፍላጎት መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል። ብዙ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውን የሆነ ተስፋ ስለሌላቸው፣ የአሁኑ ጊዜያቸውን በጨዋታና በመዝናኛ ማስያዝ እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። (ከኢሳይያስ 22:13ና ከ1 ቆሮንቶስ 15:32 ጋር አወዳድር።) ለመዝናኛ የምንሰጠው ትኩረት እየጨመረ ሄዷልን? ይህ የዓለም አስተሳሰብ አመለካከታችንን እየቀረጸው መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ “ተድላ [“መዝናኛ፣” ላምሳ] የሚወድ ድሀ ይሆናል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 21:17) መጫወት ስህተት አይደለም፤ ነገር ግን ጨዋታን የምንወድ ወይም ተቀዳሚውን ቦታ የምንሰጠው ከሆነ መንፈሳዊ ድህነት ያስከትልብናል። በመጨረሻም የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎታችን መጥፋቱ አይቀርም፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለመስበክ የሚኖረን ጊዜ ጥቂት ይሆናል።
በዚህም ምክንያት የአምላክ ቃል “ሙሉ በሙሉ ራሳችሁን በመግዛት ልቦናችሁን አንቅታችሁ ለሥራ ተዘጋጁ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 1:13 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) የመዝናኛ ጊዜያችን ከልክ እንዳያልፍ ራስን መግዛት አስፈላጊ ነው። ለሥራ የታጠቁ መሆን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይኸውም ለግል ጥናት፣ ለስብሰባ ወይም ለመስክ አገልግሎት ዝግጁ መሆን ማለት ነው።
አስፈላጊ ስለሆነ እረፍትስ ምን ለማለት ይቻላል? ለመዝናናት የእረፍት ጊዜ ስንወስድ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን ይገባል? በምንም ዓይነት። በተለይ በዛሬው በውጥረት በተሞላ ዓለም እረፍት በጣም አስፈላጊ ነው። የሆነ ሆኖ ራሳችንን የወሰን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችን መዝናኛ ላይ እንዲያተኩር መፍቀድ የለብንም። ከልክ በላይ በመዝናኛ መጠመድ ትርጉም ያላቸውን እንቅስቃሴዎች ለማከናወን የምናውለውን ጊዜ እንድንቀንስ ሊያደርገን ይችላል። ያለንን የጥድፊያ ስሜት ሊቀንስብንና ከልክ በላይ ለራሳችን ተድላ ትኩረት እንድንሰጥም ሊያበረታታን ይችላል። ታዲያ ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገባው በላይ ከመሥራት ይልቅ መጠነኛ እረፍት መውሰድን ያበረታታል፤ በተለይ ደግሞ የምንሠራው ሰብዓዊ ሥራ አላስፈላጊ ከሆነ ይህን ማድረጋችን ተገቢ ነው። (መክብብ 4:6) ምንም እንኳን እረፍት ሰውነታችን ብርታት እንዲያገኝ የሚረዳ ቢሆንም የመንፈሳዊ ብርታት ምንጭ የአምላክ ፈጣን ኃይል ነው። (ኢሳይያስ 40:29-31) መንፈስ ቅዱስንም የምናገኘው ከክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻችን ጋር በተያያዘ መንገድ ነው። የግል ጥናት ልባችንን ይመግባል እንዲሁም ትክክለኛ ፍላጎቶችን ይቀሰቅሳል። በስብሰባዎች መገኘት ለፈጣሪያችን ያለንን አድናቆት ያሳድግልናል። በክርስቲያናዊ አገልግሎት መሳተፍ ለሌሎች ያለንን ስሜት ያነቃቃል። (1 ቆሮንቶስ 9:22, 23) ጳውሎስ በሐቀኝነት እንደገለጸው “የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።”—2 ቆሮንቶስ 4:16
የስድስት ልጆች እናት የሆነችውና የማያምን ባል ያላት ኢሌና ሕይወቷ በሥራ የተወጠረ ነው። የራስዋን ቤተሰብና ሌሎች ብዙ ዘመዶችዋን የመርዳት ኃላፊነት አለባት፤ ይህም ሕይወቷ በሩጫ የተሞላ እንዲሆን አድርጓታል። ያም ሆኖ ግን በስብከቱ ሥራ በምታደርገው ተሳትፎና ለስብሰባ በመዘጋጀት ረገድ የምትደነቅ ምሳሌ ነች። ይህን ሁሉ ሥራ በሚገባ ማከናወን የቻለችው እንዴት ነው?
“ስብሰባዎችና የመስክ አገልግሎት ሌሎች ኃላፊነቶቼን በሚገባ እንድወጣ ረድተውኛል” በማለት ኢሌና ትገልጻለች። “ለምሳሌ ያህል ከአገልግሎት በኋላ የቤት ሥራዬን በምሠራበት ጊዜ ብዙ የማሰላስልባቸው ነገሮች ይኖሩኛል። አብዛኛውን ጊዜ ሥራዬን እየሠራሁ እዘምራለሁ። በሌላ በኩል ግን ስብሰባ ከቀረሁ ወይም በመስክ አገልግሎት የማደርገው ተሳትፎ ከቀነሰ የቤት ውስጥ ሥራው በጣም አድካሚ ይሆንብኛል።”
ይህ ለመዝናኛ ከሚሰጠው ከመጠን ያለፈ ትኩረት እንዴት የተለየ ነው!
መንፈሳዊ ውበት ይሖዋን ያስደስታል
የምንኖረው ለውጫዊ መልክ እየጨመረ የሚሄድ ትኩረት በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ነው። ሰዎች መልካቸውን ለማስዋብና በእርጅና ምክንያት የሚከሰቱትን ጉድለቶች ለመቀነስ ለታቀዱ ሕክምናዎች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ያፈስሳሉ። ይህም ፀጉር ማስተከልንና ማቅለምን፣ በቀዶ ሕክምና ጡትንና ፊትን ማስተካከልን ይጨምራል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክብደት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ሚደረጉባቸው የስፖርት ማዕከሎች ወይም ጅምናዝየሞች ይሄዳሉ፤ አለዚያም ደግሞ የሰውነት ማጠናከሪያ ልምምድ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችንና ስለ ጥሩ የአመጋገብ ልማድ የሚያብራሩ መጽሐፎችን ይከታተላሉ። ዓለም ወደ ደስታ የሚያሸጋግረው የይለፍ ወረቀት ውጫዊ መልክ መሆኑንና ከሁሉም የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር “መልካችን” እንደሆነ ሊያሳምነን ይሞክራል።
ኒውስ ዊክ መጽሔት አንድን ጥናት ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ ነጭ አሜሪካውያን “ውጫዊ መልካቸው እንደማያስደስታቸው” ገልጸዋል። ጥሩ ቁመና ለማግኘት የሚደረገው ብርቱ ትንቅንቅ መንፈሳዊነታችንን ሊጎዳ ይችላል። ዶራ የተባለችው ወጣት የይሖዋ ምሥክር ወፍራም መሆንዋ ያሳፍራት ነበር። “ገበያ በምወጣበት ጊዜ፣ ለኔ የሚሆን ተስማሚ ልብስ ለማግኘት እቸገር ነበር” በማለት ትገልጻለች። “የሚያምሩ ልብሶች ሸንቃጣ ለሆኑ ወጣቶች ብቻ የተዘጋጁ ይመስላል። ይባስ ብሎም ሰዎች፣ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ በውፍረቴ ሲቀልዱ በጣም እናደድ ነበር።
“በዚህም ምክንያት፣ በሕይወቴ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች የምሰጠው ቦታ ሁለተኛ ደረጃ እስኪይዝ ድረስ ለቁመናዬ ይበልጥ ትኩረት እሰጥ ጀመር። ደስታዬ በወገቤ ቅጥነት ላይ የተመካ ይመስል ነበር። ይህ ከሆነ በርካታ ዓመታት አልፈዋል፣ ባሁኑ ጊዜ በዕድሜ የበሰልኩ ጎልማሳ ክርስቲያን በመሆኔ አመለካከቴ ተለውጧል። ለውጫዊ ቁመናዬ የምጠነቀቅ ቢሆንም እንኳ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ መንፈሳዊ ውበት መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፤ ታላቅ እርካታ የሚሰጠኝ ነገር እሱ ነው። ይህን አንዴ ከተረዳሁ በኋላ የመንግሥቱን ፍላጎቶች በትክክለኛ ቦታቸው ላይ ማስቀመጥ ችያለሁ።”
ሣራ ይህን የመሰለ ሚዛናዊ አመለካከት የነበራት ታማኝ የጥንት ሴት ነች። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ከ60 ዓመት በላይ በነበረችበት ጊዜ ስለነበራት አካላዊ ውበት ቢናገርም በይበልጥ ትኩረት የሚያደርገው በነበራት መልካም ባሕርያት ማለትም በውስጣዊ ስብዕናዋ ላይ ነው። (ዘፍጥረት 12:11፤ 1 ጴጥሮስ 3:4-6) የደግነትና የገርነት መንፈስ አሳይታለች እንዲሁም ባሏን በእሺ ባይነት ታዝዛዋለች። ሣራ ሌሎች ለሷ ስላላቸው አመለካከት ከልክ በላይ አትጨነቅም ነበር። ምንም እንኳን ከባለጸጋ ቤተሰብ የተወለደች ብትሆንም በፈቃደኝነት ከ60 ዓመታት በላይ በድንኳን ኖራለች። በየዋህነትና ራስ ወዳድነት በሌለበት መንገድ ባልዋን የደገፈች የእምነት ሴት ነበረች። እውነተኛ ውበት የሰጣት ይህ አቋሟ ነበር።—ምሳሌ 31:30፤ ዕብራውያን 11:11
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መንፈሳዊ ውበታችንን ለማሻሻል እንፈልጋለን። ይህ ውበት ዘወትር ከተኮተኮተ የሚያድግና ለዘለቄታው የሚኖር ነው። (ቆላስይስ 1:9, 10) መንፈሳዊ መልካችንን በሁለት ዓበይት መንገዶች ይበልጥ ውብ ማድረግ እንችላለን።
ሕይወት አድን በሆነው አገልግሎታችን ስንሳተፍ በይሖዋ ዓይኖች ይበልጥ ውብ እንሆናለን። (ኢሳይያስ 52:7፤ 2 ቆሮንቶስ 3:18–4:2) ከዚህም በላይ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እያንጸባረቅን በሄድን መጠን ውበታችን ይጨምራል። መንፈሳዊ ውበታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ:- “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ . . . በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ . . . እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። . . . ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” (ሮሜ 12:10-18) እነዚህን የመሰሉ ጠባዮች መኮትኮታችን በአምላክም ዘንድ ሆነ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል፤ እንዲሁም በውርስ ያገኘነውን የኃጢአተኝነት ዝንባሌ አስቀያሚ መልክ ያደበዝዘዋል።—ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-8
የዓለምን መንፈስ መዋጋት እንችላለን!
የዓለም መርዛማ መንፈስ በብዙ መሰሪ መንገዶች የአቋም ጽናታችንን ሊያዳክም ይችላል። ባለን ነገሮች እንዳንረካና የአምላክን ሳይሆን የራሳችንን ፍላጎቶችና ጥቅሞች እንድናስቀድም ግፊት ሊያሳድርብን ይችላል። ወይም በአምላክ አስተሳሰብ ምትክ የሰዎች አስተሳሰብ በመያዝ ለመዝናኛና ለአካላዊ ውበታችን ተገቢ ያልሆነ ትኩረት እንድንሰጥ ሊያደርገን ይችላል።—ከማቴዎስ 16:21-23 ጋር አወዳድር።
ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ሊያበላሽብን ቆርጦ ተነስቷል፤ ለዚህም የዓለም መንፈስ የእርሱ ዋነኛ መሳሪያ ነው። ዲያብሎስ እንደሚያገሳ አንበሳ ብቻ ሳይሆን እንደ ብልህ እባብም በመሆን የማጥቂያ ዘዴዎቹን ሊቀያይር እንደሚችል አስታውሱ። (ዘፍጥረት 3:1፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) አልፎ አልፎ ዓለም አንድን ክርስቲያን ከባድ ስደት በማድረስ ሊያሸንፈው ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን ይህን ዓላማውን የሚያሳካው ቀስ በቀስ በመመረዝ ነው። ጳውሎስ ይበልጥ ያሳሰበው ይሄኛው አደጋ ነበር:- “ነገር ግን እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።”—2 ቆሮንቶስ 11:3
ከእባቡ ማታለያዎች ራሳችንን ለመጠበቅ “ከዓለም” የሚመነጩትን ፕሮፓጋንዳዎች ለይተን ማወቅና አጥብቀን መቃወም ያስፈልገናል። (1 ዮሐንስ 2:16) የዓለም የአስተሳሰብ ዘይቤ ጎጂ አይደለም ብለን በማመን መታለል የለብንም። የሰይጣን ሥርዓት መርዛማ አየር አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል።—ኤፌሶን 2:2
የዓለምን አስተሳሰብ አንዴ ለይተን ካወቅን በኋላ አእምሯችንንና ልባችንን በይሖዋ የጠሩ ትምህርቶች በመሙላት መዋጋት እንችላለን። እኛም ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም” እንበል።—መዝሙር 25:4, 5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተንደላቀቀ የኑሮ ዘይቤ ለመከተል የሚደረግ ጥረት ከመንፈሳዊ ግቦች ዞር ሊያደርገን ይችላል