ቁሳዊ ነገሮችን ሳይሆን የአምላክን መንግሥት ፈልጉ
“ዘወትር [የአምላክን መንግሥት] ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል።”—ሉቃስ 12:31
1. በሚያስፈልገንና በምንፈልገው ነገር መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
‘የሰው ልጅ፣ በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉት ነገሮች ጥቂት ሲሆኑ የሚፈልጋቸው ነገሮች ግን ስፍር ቁጥር የላቸውም’ ሲባል እንሰማለን። ብዙዎች፣ በሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮችና እነሱ በሚፈልጓቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስተውሉ አይመስልም። ይሁንና ልዩነቱ ምንድን ነው? “የሚያስፈልገን ነገር” የሚባለው በሕይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። “የምንፈልገው ነገር” የሚባለው ግን ቢኖረን ደስ የሚለን ሆኖም ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የግድ አስፈላጊ ያልሆነ ነገር ነው።
2. ሰዎች የሚፈልጓቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
2 ሰዎች የሚፈልጉት ነገር፣ እንደሚኖሩበት አካባቢ ሊለያይ ይችላል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የሚፈልጉት ሞባይል ስልክ፣ ሞተር ብስክሌት ወይም አነስ ያለ መሬት መግዛት ሊሆን ይችላል። በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ውድ የሆኑ ልብሶች፣ ትልቅ ቤት ወይም ውድ መኪና መግዛት ይፈልጋሉ። የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ አደገኛ በሆነው የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ልንወድቅ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ የመግዛት አቅሙ ቢኖረንም ባይኖረንም፣ የምንገዛው ነገር ቢያስፈልገንም ባያስፈልገንም ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የመመኘት አባዜ እንዲጠናወተን ሊያደርግ ይችላል።
ከፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ተጠበቁ
3. ፍቅረ ንዋይ ምንድን ነው?
3 ፍቅረ ንዋይ ምንድን ነው? ከመንፈሳዊ ሀብት ይልቅ ለቁሳዊ ሀብት ትልቅ ትኩረት የመስጠት አዝማሚያ ነው። ፍቅረ ንዋይ አንድ ሰው ከሚመኛቸው፣ ቅድሚያ ከሚሰጣቸውና ትኩረት ከሚያደርግባቸው ነገሮች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ይህ ዝንባሌ፣ ቁሳዊ ነገሮችን የማካበት ከፍተኛ ምኞት በውስጣችን እንዲፈጠር ያደርጋል። ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ሰው፣ ብዙ ገንዘብ ላይኖረው ወይም ውድ የሆኑ ነገሮችን ላይገዛ ይችላል። ድሃ የሆኑ ሰዎችም እንኳ ፍቅረ ንዋይ ሊጠናወታቸውና የአምላክን መንግሥት የማስቀደሙን ጉዳይ ችላ ሊሉ ይችላሉ።—ዕብ. 13:5
4. ሰይጣን ‘የዓይን አምሮትን’ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
4 ሰይጣን፣ በሕይወታችን ደስተኛ መሆን ከፈለግን መሠረታዊ ከሆኑት ቁሳዊ ነገሮች ባሻገር ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች እንደሚያስፈልጉን ሊያሳምነን ይሞክራል፤ ይህን ለማድረግም የንግዱን ዓለም ይጠቀማል። “የዓይን አምሮት” እንዲያድርብን በማድረግ ረገድ የተካነ ነው። (1 ዮሐ. 2:15-17፤ ዘፍ. 3:6፤ ምሳሌ 27:20) ይህ ዓለም፣ ምርጥ ከሚባሉት አንስቶ እርባና ቢስ እስከሆኑት ነገሮች ድረስ በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን ያቀርባል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ በጣም የሚያጓጉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድን ዕቃ በማስታወቂያ ስላየኸው ወይም ሱቅ ውስጥ የተቀመጠበት መንገድ ቀልብህን ስለሳበው ብቻ ገዝተህ ታውቃለህ? በኋላ ላይ ስታስበው ግን የገዛኸው ነገር ጨርሶ እንደማያስፈልግህ ተገንዝበህ ይሆናል። እንዲህ ያሉት አላስፈላጊ ነገሮች ሕይወታችንን ከማወሳሰብና ጫና ከመፍጠር ባለፈ የሚፈይዱልን ነገር አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናት፣ ለስብሰባዎች እንደ መዘጋጀትና በስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት እንዲሁም በአገልግሎት ላይ አዘውትሮ እንደ መካፈል የመሳሰሉ መንፈሳዊ ልማዶቻችንን ሊያስተጓጉሉብንና ወጥመድ ሊሆኑብን ይችላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማስታወሳችን ተገቢ ነው።
5. ጉልበታቸውን ሁሉ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት የሚያውሉ ሰዎች ምን ሊደርስባቸው ይችላል?
5 ሰይጣን ከይሖዋ ይልቅ ለሀብት ባሪያ እንድንሆን ይፈልጋል። (ማቴ. 6:24) ጉልበታቸውን ሁሉ ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት የሚያውሉ ሰዎች፣ የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ስለሚያተኩሩ ውሎ አድሮ ሕይወታቸው ትርጉም አልባ ይሆናል፤ ከዚያ የከፋው ደግሞ በመንፈሳዊ ባዶ መሆናቸው እንዲሁም ለሐዘንና ለብስጭት መዳረጋቸው ነው። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ ራእይ 3:17) ይህ ሁኔታ ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደገለጸው ነው። የመንግሥቱ መልእክት “በእሾህ መካከል” ሲዘራ “የሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት . . . ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።”—ማር. 4:14, 18, 19
6. ከባሮክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
6 እስቲ የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረውን ባሮክን እንደ ምሳሌ እንመልከት። አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ኢየሩሳሌም ልትጠፋ ተቃርባ በነበረበት ጊዜ፣ ባሮክ ለራሱ “ታላላቅ ነገሮችን” ይኸውም ዘላቂ ጥቅም የሌላቸውን ነገሮች መፈለግ ጀምሮ ነበር። ይሁንና ባሮክ፣ “ሕይወትህ እንዲተርፍ አደርጋለሁ” በማለት ይሖዋ የገባለትን ቃል ብቻ በተስፋ መጠባበቅ ነበረበት። (ኤር. 45:1-5 ግርጌ) አምላክ፣ ከተማዋ ስትጠፋ የማንንም ሰው ንብረት እንደማያተርፍ የተረጋገጠ ነው። (ኤር. 20:5) እኛም የምንኖረው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በቀረበበት ጊዜ ላይ እንደመሆኑ መጠን አሁን ለራሳችን ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የምናከማችበት ወቅት አይደለም። የቱንም ያህል ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ወይም ውድ የሆኑ ቁሳዊ ንብረቶቻችን ከታላቁ መከራ ይተርፉልናል ብለን መጠበቅ አይኖርብንም።—ምሳሌ 11:4 ግርጌ፤ ማቴ. 24:21, 22፤ ሉቃስ 12:15
7. ከዚህ ቀጥሎ ስለ ምን ጉዳይ እንመረምራለን? ለምንስ?
7 ኢየሱስ ትኩረታችን ሳይከፋፈል፣ በፍቅረ ንዋይ ሳንጠመድ እንዲሁም በራሳችን ላይ አላስፈላጊ ጭንቀት ሳንጨምር ለሕይወት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ማግኘት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ግሩም ምክር ሰጥቷል። ይህ ምክር በተራራ ስብከቱ ላይ ይገኛል። (ማቴ. 6:19-21) እስቲ በማቴዎስ 6:25-34 ላይ የሚገኘውን ዘገባ አንብበን እንወያይበት። እንዲህ ማድረጋችን ቁሳዊ ነገሮችን ሳይሆን ‘ዘወትር መንግሥቱን እንድንፈልግ’ ያነሳሳናል።—ሉቃስ 12:31
ይሖዋ ቁሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል
8, 9. (ሀ) ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለ ሰዎችም ሆነ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ምን የሚያውቀው ነገር አለ?
8 ማቴዎስ 6:25ን አንብብ። ኢየሱስ አድማጮቹን ‘ስለ ሕይወታችሁ መጨነቃችሁን ተዉ’ [ግርጌ] ብሏቸው ነበር። አድማጮቹ፣ ሊያስጨንቃቸው ስለማይገባ ነገር ይጨነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መጨነቃቸውን እንዲተዉ እያሳሰባቸው ነው፤ ይህን ያለው ያለ ምክንያት አይደለም። ሊያሳስቡን ስለሚገቡ ነገሮችም እንኳ ከልክ በላይ መጨነቅ፣ ትኩረታችን እንዲሰረቅና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከልብ ስለሚያስብ፣ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህን አደገኛ ዝንባሌ በተመለከተ አራት ጊዜ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 6:27, 28, 31, 34
9 ኢየሱስ ስለምንበላው፣ ስለምንጠጣው ወይም ስለምንለብሰው ነገር እንዳንጨነቅ ያሳሰበን ለምንድን ነው? እነዚህ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች አይደሉም? ደግሞስ እነዚህን ነገሮች የምናገኝበት መንገድ ከሌለ መጨነቃችን ይቀራል? መጨነቃችን አይቀርም፤ ኢየሱስም ይህን ያውቃል። ሰዎች በየዕለቱ ምን እንደሚያስፈልጋቸው በሚገባ ያውቃል። ከዚህም በላይ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባለው በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ የሚኖሩ ተከታዮቹ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ይረዳል። (2 ጢሞ. 3:1) ብዙዎች ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች መካከል እንደ ሥራ ማጣት፣ የኑሮ ውድነት፣ የምግብ እጥረትና የከፋ ድህነት ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገኙበታል። ያም ሆኖ ኢየሱስ ‘ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነት ከልብስ’ እንደሚበልጥ ተገንዝቦ ነበር።
10. ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ሲያስተምር በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ የጠቆመው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ፣ በተራራ ስብከቱ መጀመሪያ አካባቢ አድማጮቹ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች በተመለከተ “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን” በማለት የሰማዩ አባታቸውን መለመን እንደሚችሉ አስተምሮ ነበር። (ማቴ. 6:11) በሌላ ጊዜም “የዕለቱን ምግባችንን ለዕለቱ የሚያስፈልገንን ያህል ስጠን” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 11:3) ይህ ሲባል ግን ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ ማሰብ አለብን ማለት አይደለም። ኢየሱስ በዚሁ የጸሎት ናሙና ላይ በቅድሚያ ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት መጸለያችን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል። (ማቴ. 6:10፤ ሉቃስ 11:2) ከዚያም ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በማቅረብ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ መሆኑን ጎላ አድርጎ በመጥቀስ አድማጮቹ ጭንቀታቸው ቀለል እንዲልላቸው አድርጓል።
11, 12. ይሖዋ የሰማይ ወፎችን ከሚንከባከብበት መንገድ ምን እንማራለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
11 ማቴዎስ 6:26ን አንብብ። ‘የሰማይ ወፎችን ልብ ብለን’ መመልከት አለብን። እነዚህ ወፎች መጠናቸው ትንሽ ቢሆንም በጣም ብዙ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ ነፍሳት ወይም ትላትል ይመገባሉ። ወፎች፣ ከሰውነታቸው ክብደት አንጻር የሰው ልጆች ከሚመገቡት የበለጠ ይመገባሉ። ያም ሆኖ ለምግባቸው ሲሉ ማረስም ሆነ መዝራት አያስፈልጋቸውም። ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ ይሰጣቸዋል። (መዝ. 147:9) እርግጥ ነው፣ ምግቡን አፋቸው ውስጥ አይጨምረውም! ሄደው ምግባቸውን መፈለግ አለባቸው፤ ሆኖም የሚፈልጉትን እንደ ልብ ያገኛሉ።
12 ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ለወፎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እያሟላ የሰው ልጆችን መሠረታዊ ፍላጎት ችላ ይላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ ተሰምቶታል።[1] (1 ጴጥ. 5:6, 7) እርግጥ ነው፣ አምላክ ምግቡን አፋችን ላይ አያደርግልንም፤ ምግባችንን ለማግኘት ማረስ አሊያም እህሉን ለመግዛት የሚያስችለንን ገንዘብ ለማግኘት መሥራት ይኖርብናል፤ ይሖዋም የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። ከተቸገርን ደግሞ ሌሎች ያላቸውን እንዲያካፍሉን ሊያነሳሳቸው ይችላል። ኢየሱስ የሰማይ ወፎች መጠለያ ስለሚያገኙበት መንገድ ባይጠቅስም ይሖዋ፣ ጎጇቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ችሎታና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ፣ እኛም በተመሳሳይ ቤተሰባችንን የምናስጠልልበት ጎጆ እንድናገኝ ይረዳናል።
13. ከሰማይ ወፎች እንደምንበልጥ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
13 ኢየሱስ ለአድማጮቹ “ታዲያ እናንተ [ከሰማይ ወፎች] አትበልጡም?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል። ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕይወቱን ለሰው ልጆች አሳልፎ እንደሚሰጥ በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። (ከሉቃስ 12:6, 7 ጋር አወዳድር።) የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተዘጋጀው ለሌላ ለማንኛውም ፍጡር አይደለም። ኢየሱስ የሞተው ለሰማይ ወፎች ሳይሆን እኛ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ነው።—ማቴ. 20:28
14. አንድ ሰው ተጨንቆ ምን ማድረግ አይችልም?
14 ማቴዎስ 6:27ን አንብብ። ታዲያ ኢየሱስ፣ አንድ የሚጨነቅ ሰው በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ እንኳ መጨመር እንደማይችል የተናገረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በየዕለቱ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ ዕድሜያችንን አያረዝምልንም። ከዚህ ይልቅ ከልክ በላይ መጨነቅ ዕድሜያችንን ሊያሳጥረው ይችላል።
15, 16. (ሀ) ይሖዋ የሜዳ አበቦችን ከሚንከባከብበት መንገድ ምን እንማራለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን? ለምንስ?
15 ማቴዎስ 6:28-30ን አንብብ። ጥሩ ልብስ መልበስ የማይፈልግ ማን አለ? በተለይ ደግሞ አገልግሎት ስንወጣ አሊያም በጉባኤ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ጥሩ ለብሰን መታየት እንፈልጋለን። ያም ቢሆን ‘ስለ ልብስ መጨነቅ’ ይኖርብናል? ኢየሱስ አሁንም ትኩረታችንን በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ እንድናደርግ አበረታቶናል። በዚህ ረገድ “የሜዳ አበቦች” ካላቸው ውበት የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ምናልባትም ኢየሱስ፣ ‘መሸ ደህና እደሩ’ እንደሚባለው አበባ ያሉ የተለያዩ አበቦችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፤ ሁሉም የየራሳቸው ውበት አላቸው። እነዚህ ፍጥረታት ራሳቸውን ለማልበስ መፍተል፣ መስፋት ወይም መሸመን አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አብበው ሲታዩ በጣም ውብ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም” ይላል።
16 ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ልብ በሉ፤ “አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?” ያለ ምንም ጥርጥር ያለብሳቸዋል! ይሁንና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እምነት ጎድሏቸው ነበር። (ማቴ. 8:26፤ 14:31፤ 16:8፤ 17:20) ጠንካራ እምነት ማዳበርና በይሖዋ መታመን ያስፈልጋቸው ነበር። እኛስ? ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ሙሉ እምነት አለን?
17. ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን የሚችለው ምንድን ነው?
17 ማቴዎስ 6:31, 32ን አንብብ። አፍቃሪ የሆነው በሰማይ የሚገኘው አባት፣ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ለሚያስቀድሙ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው “አሕዛብ” እምነት የላቸውም፤ እኛ ግን እንደ እነሱ መሆን የለብንም። “አሕዛብ አጥብቀው [የሚፈልጓቸውን]” ነገሮች በሙሉ ለማከማቸት መሞከር ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል። ከዚህ ይልቅ የሚጠበቅብንን ነገር የምናደርግ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን የምናስቀድም ከሆነ ይሖዋ ጥሩ የሆነውን ነገር እንደማይነፍገን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “ለአምላክ ያደርን መሆናችን” የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ይኸውም “ምግብና ልብስ” እንዲሁም “መጠለያ” በማግኘታችን ረክተን እንድንኖር ሊያደርገን ይገባል።—1 ጢሞ. 6:6-8 ግርጌ
በሕይወታችሁ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እያስቀደማችሁ ነው?
18. ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ምን ያውቃል? ምንስ ያደርግልናል?
18 ማቴዎስ 6:33ን አንብብ። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምንጊዜም መንግሥቱን ማስቀደም ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረግን ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ‘እነዚህ ነገሮች ሁሉ ይሰጡናል።’ ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ቀደም ባለው ቁጥር ላይ “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ [ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች] ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከራሳችን እንኳ አስቀድሞ ያውቃል። (ፊልጵ. 4:19) የትኛው ልብሳችን እያለቀ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ምግብ እንደሚያስፈልገን እንዲሁም ለቤተሰባችን የሚበቃው ምን ዓይነት መጠለያ እንደሆነ ያውቃል። ደግሞም የሚያስፈልገንን ነገር ማግኘት አለማግኘታችንን በትኩረት ይከታተላል።
19. ወደፊት ስለሚሆነው ነገር በማሰብ መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው?
19 ማቴዎስ 6:34ን አንብብ። ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ “ፈጽሞ አትጨነቁ” ማለቱን ልብ በሉ። ይህን ሲል የይሖዋ እርዳታ እንደማይለየን ሙሉ በሙሉ በመታመን፣ ለዕለት ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ መጨነቅ እንዳለብን መግለጹ ነው። አንድ ሰው ወደፊት ሊሆን ስለሚችለው ነገር ሳያስፈልግ የሚጨነቅ ከሆነ በአምላክ ከመታመን ይልቅ በራሱ እየታመነ ነው፤ ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ሊያበላሽበት ይችላል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵ. 4:6, 7
ከሁሉ አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ፤ የቀረውን ይሖዋ ያሟላላችኋል
20. (ሀ) ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል የትኞቹን ግቦች ማውጣት ትችላላችሁ? (ለ) ኑሯችሁን ለማቅለል ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
20 ሕይወታችን ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ምንኛ ሞኝነት ነው! ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ግቦችን መከታተል የተሻለ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ጉባኤ ሄዳችሁ ማገልገል ትችላላችሁ? አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆን? አቅኚ ከሆናችሁ ደግሞ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ገብታችሁ ለመማር አስባችሁ ታውቃላችሁ? ወደ ቤቴል ወይም ወደ አንድ የርቀት የትርጉም ቢሮ በተወሰኑ ቀናት እየሄዳችሁ ማገዝ ትችላላችሁ? በመንግሥት አዳራሽ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆናችሁ ማገልገል ትችላላችሁ? ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ራሳችሁን ይበልጥ ለማስጠመድ ኑሯችሁን ቀለል ማድረግ የምትችሉባቸውን አቅጣጫዎች ለማሰብ ሞክሩ። “ኑሯችሁን ማቅለል የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚለው ሣጥን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ይዟል። በዚህ ረገድ ትክክለኛውን ውሳኔ እንድታደርጉ ይሖዋ እንዲረዳችሁ በጸሎት ጠይቁት፤ ከዚያም ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚረዷችሁን እርምጃዎች ውሰዱ።
21. ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ምን ይረዳሃል?
21 በእርግጥም ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮችን ሳይሆን መንግሥቱን እንድንፈልግ ምክር መስጠቱ የተገባ ነው። ይህን ምክር የምንከተል ከሆነ ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ከሚገባው በላይ አንጨነቅም። በይሖዋ የምንታመን እንዲሁም የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ከማድረግና አቅማችን ቢፈቅድልንም እንኳ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች በሙሉ ከመግዛት የምንቆጠብ ከሆነ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን። በአሁኑ ጊዜ አኗኗራችንን ቀላል ካደረግን ከፊታችን የሚጠብቀንን ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀን መያዝ እንችላለን።’—1 ጢሞ. 6:19
^ [1] (አንቀጽ 12) ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን እንዲራብ ሊፈቅድ የሚችለው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የመስከረም 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።