ምዕራፍ 13
ሰላማዊው የአምላክ መንግሥት
1. ሰብዓዊ መንግሥታት ምን ማድረግ ተስኗቸዋል?
ሰብዓዊ መንግሥታት፣ ቅን አስተሳሰብ ያላቸውም ጭምር፣ የሰዎችን ፍላጎቶች ሳያሟሉ እንደቀሩ ተመልክተሃልን? ለወንጀልና ለዘር ጥላቻ ችግሮች መፍትሔ የሰጠ ወይም ለሕዝቦቹ ሁሉ ተስማሚውን ምግብና ቤት ያስገኘ አንድም መንግሥት የለም። ዜጎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ከበሽታ ነፃ አላደረጉም። የትኛውም መንግሥት ቢሆን እርጅናን ወይም ሞትን ለማስቀረት ወይም የሞቱትን እንደገና ሕያው ለማድረግ አልቻለም። ለዜጎቹ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ያመጣ አንድም መንግሥት የለም። ባጭሩ ሰብዓዊ መንግሥታት ሰዎች ለገጠሙአቸው ትልልቅ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት አልቻሉም።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት ምንድን ነው?
2 ፈጣሪያችን ሁሉም ሰዎች የተሟላና አስደሳች ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችል የጽድቅ መንግሥት ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ አመራር ስር አንድ መንግሥት እንደሚቋቋም የሚናገረውም በዚህ ምክንያት ነው። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት ይህ አምላክ አመጣዋለሁ ብሎ ቃል የገባለት መንግሥት ነው።
3. ኢሳይያስ 9:6, 7 ስለ አምላክ መንግሥት ምን ይላል?
3 ይሁን እንጂ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው የት ላይ ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በኢሳይያስ 9:6, 7 ላይ ስለዚያ መንግሥት ይናገራል። በኪንግ ጄምስ ቨርሽን መሠረት ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ መንግሥቱም በትከሻው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት የሰላም መስፍን ተብሎ ይጠራል። ለመንግሥቱና ለሰላሙ ብዛት ፍጸሜ አይኖረውም።”
4. የአምላክ መንግሥት ገዥ የሚሆነው ልጅ ማን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ የሚናገረው ስለ አንድ ልጅ፣ ስለ አንድ መስፍን መወለድ ነው። ከጊዜ በኋላም ይህ ‘የንጉሥ ልጅ’ ታላቅ ገዥ “የሰላም መስፍን” የሚሆን ነበር። እርሱም በእርግጥ አስደናቂ የሆነ የአንድ መንግሥት የበላይ ኃላፊ ይሆናል። ይህ መንግሥት ለጠቅላላው ምድር ሰላምን ያመጣል፤ ሰላሙም ለዘላለም ይቀጥላል። በኢሳይያስ 9:6, 7 ላይ እንደሚወለድ ትንቢት የተነገረለት ይህ ልጅ ኢየሱስ ነበር። መልአኩ ገብርኤል ድንግል ለነበረችው ለማርያም ስለዚህ ሕፃን መወለድ ሲያበሥራት ኢየሱስ “ለዘላለም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” አላት።— ሉቃስ 1:30-33
የመንግሥቱን አስፈላጊነት አጥብቆ መግለጽ
5. (ሀ) የመንግሥቱ አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎልቶ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ምንስ ነገር ያከናውናል?
5 ኢየሱስ ክርስቶስና ደጋፊዎቹ በምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ ዋናው ሥራቸው ስለ መጪው የአምላክ መንግሥት መስበክና ማስተማር ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ 8:1) እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ መንግሥት 140 ጊዜ ያህል ጠቅሰዋል። እንዲያውም ኢየሱስ ለተከታዮቹ ወደ አምላክ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10) ይህ ክርስቲያኖች የሚጸልዩለት መንግሥት በእርግጥ ሰዎችን የሚያስተዳድር መንግሥት ማለት ነውን? ምናልባት እንደዚያ አድርገህ አታስበው ይሆናል፤ ነገሩ ግን እንደዚያው ነው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ሲሆን ጠቅላላው ምድር እርሱ የሚያስተዳድረው ግዛቱ ይሆናል። የምድር ሕዝቦች ተቀናቃኝ በሆኑ ብዙ መንግሥታት በመከፋፈል ፋንታ ሁሉም ሰዎች በአምላክ ንጉሣዊ መንግሥት ስር ሰላም አግኝተው እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ሲኖሩ ምንኛ መልካም ይሆናል!
6. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ መንግሥቲቱ “ቀርባለች” እንዲሁም “በመካከላችሁ ናት” የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው?
6 መጥምቁ ዮሐንስ ለሕዝቡ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ስለዚህ መንግሥት መስበክ ጀመረ። (ማቴዎስ 3:1, 2) ዮሐንስ እንደዚህ ለማለት የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ገዥ የሚሆነው ኢየሱስ በእርሱ በቅርቡ ሊጠመቅና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊቀባ ስለነበረ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ቆየት ብሎ ለፈሪሳውያን:- “እነሆ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ሊል የቻለው ለምን እንደሆነ ሊገባህ ይችላል። (ሉቃስ 17:21) አምላክ እንደ ንጉሥ አድርጎ የቀባው ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በዚያ ስለ ነበረ ነው። ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በሰበከበትና ባስተማረበት ወቅት ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ባሳየው ታማኝነት ንጉሥ ለመሆን ያለውን መብት አረጋግጧል።
7. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ መንግሥቲቱ ከፍተኛ አወዛጋቢ ጉዳይ እንደነበረች የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 በክርስቶስ አገልግሎት ወቅት የአምላክ መንግሥት ከፍተኛው አወዛጋቢ ጉዳይ እንደ ነበረ ለማሳየት ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ቀን ምን እንደተፈጸመ እስቲ እንመርምር። ሰዎች ኢየሱስን:- “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሳርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም:- እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው” በማለት እንደከሰሱት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህን ነገሮች ሲሰማ ሮማዊው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ኢየሱስን “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።— ሉቃስ 23:1-3
8. (ሀ) ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ ሲጠየቅ የመለሰው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
8 ኢየሱስ ለጲላጦስ ጥያቄ በቀጥታ መልስ አልሰጠም፤ ነገር ግን:- “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው።” ኢየሱስ በዚህ መንገድ የመለሰው መንግሥቱ ምድራዊት ስለማትሆን ነው። ወደፊት የሚገዛው እንደ አንድ ሰው በመሆን በምድራዊ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳይሆን ከሰማይ ሆኖ ነው። አወዛጋቢው ጉዳይ ኢየሱስ እንደ ንጉሥ ሆኖ የመግዛት መብት አለው ወይስ የለውም የሚል ስለነበረ ጲላጦስ እንደገና ኢየሱስን “እንግዲያ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።
9. (ሀ) ኢየሱስ የትኛውን አስደናቂ እውነት አስታወቀ? (ለ) በዛሬው ጊዜ ትልልቆቹ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
9 በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስ ስለ አንድ አዲስ መንግሥት ስለሰበከና ስላስተማረ በሞት እንዲቀጣ ለፍርድ ቀርቦ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ ለጲላጦስ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጄአለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቼአለሁ” ብሎ መለሰለት። (ዮሐንስ 18:36, 37) አዎ፤ ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ሕይወቱን ስለ አምላክ ንጉሣዊ መንግሥት አስደናቂ እውነት ለሰዎች በመናገር አሳልፎታል። የእርሱ ዋነኛ መልእክት ይህ ነበር። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ከፍተኛው ጥያቄ ይህ መንግሥት ነው። ይሁን እንጂ የሚከተሉት ጥያቄዎች ይቀራሉ:- ‘በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው መንግሥት የትኛው ነው? አንድ ዓይነት የሰዎች መንግሥት ነው ወይስ ክርስቶስ ገዥው የሆነለት የአምላክ መንግሥት ነው?’
ለአዲሱ የምድር መንግሥት ዝግጅት ማድረግ
10. (ሀ) አምላክ የአዲስ መንግሥትን አስፈላጊነት የተመለከተው መቼ ነበር? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መንግሥት በመጀመሪያ የተጠቀሰው የት ላይ ነው? (ሐ) እባቡ ማንን ያመለክታል?
10 ይሖዋ በሰው ዘር ላይ የሚገዛ አዲስ መንግሥት የማቋቋሙን አስፈላጊነት የተመለከተው ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን በዐመፁ እንዲተባበሩት ባደረጋቸው ጊዜ ነበር። ስለዚህ ወዲያው አምላክ እንደዚህ ያለ መንግሥት ለማቋቋም ስላለው ዓላማ ተናገረ። ይህንን መንግሥት የጠቀሰው ለእባቡ ማለትም ለሰይጣን ዲያብሎስ እንዲህ ብሎ ፍርዱን በነገረው ጊዜ ነበር:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”— ዘፍጥረት 3:14, 15
11. ጥላቻ የሚፈጠረው በእነማን መካከል ነው?
11 ይሁን እንጂ ‘እዚህ ውስጥ ስለ መንግሥት የሚገልጽ ነገር የት አለ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እስቲ ይህንን ዐረፍተ ነገር በጥንቃቄ እንመልከተውና እንደዚያ የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ጥቅሱ በሰይጣንና “በሴቲቱ” መካከል ጠላትነት ወይም ጥላቻ እንደሚኖር ይናገራል። በተጨማሪም በሰይጣን “ዘር” ወይም በልጆቹና በሴቲቱ “ዘር” ወይም በልጆቿ መካከል ጥላቻ ይኖራል። ከሁሉ በፊት “ሴቲቱ” ማን እንደሆነች ማወቅ ያስፈልገናል።
12. በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ ስለ “ሴቲቱ” ምን ተብሏል?
12 እርስዋ ምድራዊት ሴት አይደለችም። ሰይጣን ለአንዲት ሰብዓዊት ፍጡር ልዩ የሆነ ጥላቻ የለውም። ከዚያ ይልቅ ይህች ምሳሌያዊ ሴት ናት። ይህም ለአንድ ለሌላ ነገር የቆመች ነች ማለት ነው። ይህ ነገር ስለ እርስዋ ሰፊ አሳብ በተሰጠበት በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማለትም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል። በዚያ ውስጥ “ሴቲቱ” ‘ፀሐይን እንደተጎናጸፈች፣ በጨረቃ ላይ እንደቆመችና በራስዋ ላይ አሥራ ሁለት ከዋክብት እንዳሉባት’ ሆና ተገልጻለች። ይህች “ሴት” ማንን እንደምታመለክት ለማወቅ እንዲረዳን የራእይ መጽሐፍ ስለ ልጅዋ ምን እንደሚል አስተውል:- “አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች ፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።”— ራእይ 12:1-5
13. ‘ወንዱ ልጅ’ እና ‘ሴቲቱ’ የሚያመለክቱት ማንን ወይም ምንን ነው?
13 ‘ወንዱ ልጅ’ ማን ወይም ምን እንደሆነ ማወቁ “ሴቲቱ” ማንን ወይም ምንን እንደምታመለክት ለማወቅ ይረዳናል። ሴቲቱ ቃል በቃል ሰብዓዊት ፍጡር እንዳልሆነች ሁሉ ልጅዋም ቃል በቃል ሰው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ “ወንድ ልጅ” ‘አሕዛብን ሁሉ እንደሚገዛ’ ያሳያል። ስለዚህም ‘ልጁ’ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በመሆን የሚገዛበትን የአምላክን መንግሥት ያመለክታል። ስለዚህም ሴቲቱ የአምላክን ታማኝ ሰማያዊ ፍጥረታት ያቀፈውን ድርጅት ታመለክታለች። ‘ወንዱ ልጅ’ ‘ከሴቲቱ’ አካል እንደወጣ ሁሉ ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስም የመጣው የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም በሰማይ ውስጥ በአንድነት ከሚሠሩት የታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት አካል ማለትም ከሰማያዊ ድርጅት ነው። ገላትያ 4:26 ይህንን ድርጅት “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” በማለት ይጠራዋል። ስለዚህ አዳምና ሔዋን በመጀመሪያ በአምላክ አገዛዝ ላይ ባመፁበት ጊዜ ይሖዋ ጽድቅ ወዳድ ለሆኑት ሰዎች ተስፋ የሚሆን አንድ መንግሥታዊ አገዛዝ ለማቋቋም ዝግጅት አድርጓል።
ይሖዋ የገባውን ቃል ያስታውሳል
14. (ሀ) ይሖዋ ሰይጣንን ስለሚቀጠቅጠው “ዘር” የገባውን ቃል እንዳስታወሰ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ተስፋ የተደረገበት “ዘር” ማን ነው?
14 የአምላክ መንግሥት ገዥ የሚሆነውን “ዘር” እንደሚልክ የገባውን ቃል ይሖዋ አልረሳም። ይህ ገዥ የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ ያጠፋዋል። (ሮሜ 16:20፤ ዕብራውያን 2:14) ከዚያ ቆየት ብሎ ይሖዋ ተስፋ የተሰጠበት ዘር በታማኙ አብርሃም በኩል እንደሚመጣ ተናገረ። ይሖዋ ለአብርሃም:- “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” ብሎ ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ይህ በአብርሃም መስመር በኩል እንደሚመጣ ተስፋ የተሰጠበት “ዘር” ማን ነው? ከዚያ አያሌ ዘመናት ቆይቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር:- ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።” (ገላትያ 3:16) በተጨማሪም ይሖዋ ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅና ለልጅ ልጁ ለያዕቆብ ከአምላክ “ሴት” የሚወጣው “ዘር” በእነርሱ የትውልድ መስመር በኩል እንደሚመጣ ነግሯቸዋል።— ዘፍጥት 26:1-5፤ 28:10-14
15, 16. ‘ዘሩ’ ሕዝብን የሚገዛ ንጉሥ እንደሚሆን ምን ያረጋግጣል?
15 ያዕቆብ ለልጁ ለይሁዳ የሚከተለውን በመናገር ይህ “ዘር” ሕዝብን የሚገዛ ንጉሥ እንደሚሆን ግልጽ አድርጎታል:- “በትረ መንግሥት (ወይም የመግዛት ሥልጣን) ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው (ሻይሎ) እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብም መታዘዝ ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍጥረት 49:10) ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ከይሁዳ ነገድ ነው። እርሱም “የአሕዛብ መታዘዝ ለእርሱ ይሆናል” የተባለለት “ሻይሎ” ሆኖ ተገኘ።— ዕብራውያን 7:14
16 ይህ ነገር ለይሁዳ ከተነገረው ከ700 ዓመታት አካባቢ በኋላ ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ዳዊትን በሚመለከት እንዲህ አለ:- “ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት . . . ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ።” (መዝሙር 89:20, 29) አምላክ የዳዊት ዘር” “ለዘላለም” ይኖራል፤ “ዙፋኑም እንደ ሰማይ ዘመን” ይቆያል ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይሖዋ አምላክ እርሱ በሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው ንጉሣዊ መንግሥቱ ለሁልጊዜ እንደሚቀጥል መጥቀሱ ነበር። እንዴት እናውቃለን?
17. ቃል የተገባለት ገዥ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
17 የይሖዋ መልአክ ገብርኤል ከእርስዋ ስለሚወለደው ልጅ ለማርያም የነገራትን አስታውስ። እርሱ “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ብሏት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ ሕፃን ልጅ፣ ወይም ሰው ብቻ ሆኖ የሚቀር አልነበረም። ገብርኤል ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ [ይሖዋ (አዓት)] አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:31-33) ይሖዋ እርሱን ለሚወዱትና ለሚተማመኑበት ዘላለማዊ ጥቅም ሲል የጽድቅ መንግሥት ለማቋቋም ዝግጅት ማድረጉ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነገር አይደለምን?
18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የምድራዊ መንግሥታትን ፍጻሜ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት ለሰዎች ምን ያደርግላቸዋል?
18 የአምላክ ንጉሣዊ መንግሥት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ለማጥፋት ርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ቀርቧል። ያን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ በመሆን ርምጃ መውሰድ ይጀምራል። ይህንን ጦርነት ሲያብራራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 19:11-16) ሌሎች መንግሥታት ሁሉ ከተወገዱ በኋላ የአምላክ መንግሥት የሰዎችን እውነተኛ ፍላጎት ያሟላል። ገዥው ኢየሱስ ክርስቶስ ከታማኝ ተገዥዎቹ መካከል አንዱም ቢሆን እንዳይታመም፣ እንዳያረጅ፣ ወይም እንዳይሞት ያደርጋል። ወንጀል፣ የቤት እጦት፣ ረሃብና ይህንን የመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ። በመላው ምድር ላይ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ይመጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3-5) ሆኖም በዚህ የአምላክ ንጉሣዊ መንግሥት ውስጥ ገዥዎች ስለሚሆኑት ሰዎች የበለጠ መማር ያስፈልገናል።
[በገጽ 112, 113 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥት የስብከት ሥራ እንዲያከናውኑ ደቀ መዛሙርቱን ላካቸው
[በገጽ 114 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሞት እንዲቀጣ ለፍርድ በቀረበበትም ጊዜ የአምላክን መንግሥት መስበኩን ቀጥሏል
[በገጽ 119 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስን የምትመለከተው እንዴት አድርገህ ነው?— እንደ አንድ ድል አድራጊ ንጉሥ ወይስ አቅም እንደሌለው ሕፃን?