123ኛው የጊልያድ ምረቃ
የጊልያድ ምሩቃን “መቆፈር እንዲጀምሩ” ማበረታቻ ተሰጣቸው
ቅዳሜ መስከረም 8, 2007 በተካሄደው የ123ኛው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ41 አገሮች የመጡ 6,352 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። የበላይ አካል አባልና የዕለቱ ፕሮግራም ሊቀ መንበር የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ከጠዋቱ 4:00 ላይ ተሰብሳቢዎቹን ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ በማለት ፕሮግራሙን ጀመረ። ወንድም ሞሪስ የመክፈቻውን ንግግር ካቀረበ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነውን ወንድም ጋሪ ብሮን የመጀመሪያውን ንግግር እንዲያቀርብ ጋበዘው።
ወንድም ብሮ፣ ተማሪዎቹ መልክና ቁመናቸው ምንም ይሁን ምን የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉ ሁሉ በፊቱ ክቡር ወይም ውብ እንደሆኑ ተናገረ። (ኤር. 13:11) ተመራቂዎቹ ይህን ዓይነቱን ውበት ይዘው እንዲቀጥሉም አሳሰባቸው። ቀጥሎም የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ፣ ይሖዋን ስናገለግል ዋጋ ወይም ሽልማት እንደምናገኝ ተስፋ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ተናገረ። (ዕብ. 11:6) ይሁን እንጂ ይሖዋን እንድናገለግል የሚያነሳሳን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መሆን እንዳለበት ገልጿል።
ቀጥሎም ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተል ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ዊልያም ሳሙኤልሰን፣ ተመራቂዎቹ በመግዛት ላይ ስላለው ንጉሥ የማወጁን ክቡር ሥራ አጥብቀው እንዲይዙት እንዲሁም በመልካም ምግባራቸው ሥራቸው ክቡር መሆኑን እንዲያሳዩ አሳሰበ።a ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተል ክፍል ረዳት የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ሳም ሮበርሰን ደግሞ ተመራቂዎቹ ምንጊዜም የሌሎችን መልካም ባሕርያት እንዲመለከቱ አበረታታቸው። ተመራቂዎቹ እንዲህ ካደረጉ ሁሉንም ‘ወንድሞች መውደድ’ እንደሚችሉ ገለጸ።—1 ጴጥ. 2:17
እነዚህ ለተግባር የሚያነሳሱ ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር ለበርካታ ተመራቂዎች ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ሲሆን እነሱም በጊልያድ ሲሠለጥኑ በመስክ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች ተናግረዋል። ተመራቂዎቹ ለአገልግሎት ፍቅር እንዳላቸውና ሌሎችን ለመርዳት እንደሚፈልጉ በግልጽ መመልከት ይቻል ነበር። በፓተርሰን የቤቴል ቢሮ የሚያገለግለው ወንድም ኬንት ፊሸር፣ ሚስዮናውያን ከተላኩባቸው አገሮች መካከል ለሦስቱ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ቃለ መጠይቅ አደረገላቸው። እነዚህ ግሩም ወንድሞች የሰጧቸው ሐሳቦች፣ አዲስ ሚስዮናውያን በተመደቡባቸው ቦታዎች ያሉት ወንድሞች እንደሚንከባከቧቸው የተመራቂዎቹ ወላጆችም ሆኑ እዚያ የነበሩት ተሰብሳቢዎች በሙሉ እንዲገነዘቡ አድርገዋል። በትርጉም አገልግሎት ክፍል የሚሠራው ወንድም ኢሳክ መሬ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉ ሚስዮናውያን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ተመራቂዎቹ ወደፊት ምን ዓይነት አስደሳች ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው እንዲመለከቱ አድርጓል።
የዕለቱን ዋና ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሲሆን የንግግሩም ጭብጥ “ይህን ሁሉ ከሰማችሁ በኋላ ምን ታደርጋላችሁ?” የሚል ነበር። ወደ 25 ለሚጠጉ ዓመታት በደቡብ ፓስፊክ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጃክሰን በተራራው ስብከት መጨረሻ ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች አብራራ። ኢየሱስ ቤቶችን ስለሠሩ ብልኅና ሞኝ ሰዎች ተናግሮ ነበር። ወንድም ጃክሰን፣ ሁለቱም ቤቶች የተሠሩት በአንድ አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ገለጸ። ሆኖም ሞኙ ሰው ቤቱን የሠራው ከላይ በአሸዋው ላይ ሲሆን ብልኅ የሆነው ሰው ግን ቤቱን ለመገንባት መሠረት የሚሆነው ዐለት እስኪያገኝ ድረስ በጥልቀት ቆፍሮ ነበር። ኃይለኛ ነፋስ ሲመጣ ዐለት ላይ የተገነባው ቤት ምንም አልሆነም፤ በአሸዋ ላይ የተሠራው ግን ወደቀ።—ማቴ. 7:24-27፤ ሉቃስ 6:48
ኢየሱስ እንደገለጸው ሞኙ ሰው፣ የእሱን ትምህርቶች የሚሰሙ ሆኖም በተግባር የማያውሉ ሰዎችን የሚያመለክት ሲሆን ብልኁ ሰው ደግሞ ትምህርቶቹን ከመስማትም አልፈው በተግባር የሚያውሉትን ሰዎች ያመለክታል። ወንድም ጃክሰን ተመራቂዎቹን እንዲህ አላቸው:- “ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያገኛችሁትን ትምህርት በሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁ ተግባራዊ ስታደርጉት ብልኁን ሰው ትመስላላችሁ።” ወንድም ጃክሰን ንግግሩን ሲደመድም ተመራቂዎቹ በሚስዮናዊነት ምድባቸው “መቆፈር እንዲጀምሩ” አበረታታቸው።
በመጨረሻም ተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉና ምድባቸው ከተነገራቸው በኋላ ወንድም ሞሪስ የመደምደሚያ ምክር ሰጣቸው። ተመራቂዎቹ ሁልጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉና ብርታት ለማግኘት ምንጊዜም በይሖዋ እንዲታመኑ አበረታታቸው። የምረቃ ፕሮግራሙ በዚህ ሁኔታ ተጠናቀቀ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተል ክፍል፣ በትምህርት ኮሚቴ ሥር ሲሆን የጊልያድ ትምህርት ቤትን፣ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ትምህርት ቤትንና የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ትምህርት ቤትን በኃላፊነት ይቆጣጠራል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 10
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 24
የተማሪዎቹ ብዛት:- 56
አማካይ ዕድሜ:- 33.5
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 17.9
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.8
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 123ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ኤስተር ኤስፓርሳ፣ ሣራ ፓፓይ፣ አኒታ ቢላል፣ ሚሪያም ስዋሬስ፣ ኢለዊዝ ኤቨርስ፣ ካቲ ዲሚቺኖ (2) ማድሌን ሮዛ፣ ርዮኮ ፉጂ፣ ኦልጊታ ሬቲ፣ ጆና ሌቨተን፣ ሚኬ ቫን ሊምፑተን (3) አና ቦስካይኖ፣ ክርስቲን ቤክ፣ ሃይኬ ቡዳኖፍ፣ ካትሪን ብራዝ፣ ክርስቲ ፔልትስ፣ አፍዋ ሲያው (4) ስካት ሌቨተን፣ ሃና ሳንቲኮ፣ ሣራ ኮንቲ፣ ጄኒፈር ዊልሰን፣ ጂኒ ራይሌት፣ ሾና ፒርስ፣ ኩኒሂሮ ፉጂ (5) ዴቪድ ሮዛ፣ ሚካኤል ቦስካይኖ፣ ቫኔሳ ኦስቲን፣ ፓትሪሻ ሮድየል፣ ፖል ቢላል፣ ፖል ዲሚቺኖ (6) ባራክ ሬቲ፣ ዴቭ ቺዚክ፣ ካሚል ክላርክ፣ አንዬ ሪደል፣ ፋውስቶ ኤስፓርሳ፣ ፕሪንስ ሲያው፣ ቶም ቫን ሊምፑተን (7) ሆሴ ሮድየል፣ ጆን ኤቨርስ፣ ጃኪ ግሪን፣ ጁሊ ቺዚክ፣ ሚካ ሳንቲኮ፣ ማት ራይሌት (8) ላዝሎ ፔልትስ፣ ዳንየል ኦስቲን፣ ቶቢያስ ሪደል፣ ማርክ ቤክ፣ ዊልያም ፒርስ፣ ስቲቭ ኮንቲ፣ ስቲቭ ግሪን (9) ጆሴ ስዋሬስ፣ ጄረሚ ክላርክ፣ ሴብ ፓፓይ፣ ሚሻ ቡዳኖፍ፣ ሬይ ዊልሰን፣ ሪክ ብራዝ