የኢየሱስ መወለድ ሰላም የሚያመጣው እንዴት ነው?
ከኢየሱስ መወለድ ጋር ተያይዞ የተነገረው ትንቢት “ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን” የሚለው ብቻ አይደለም። መላእክት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ስለ ሕፃኑ ኢየሱስ የተናገሩት ለእረኞቹ ብቻ ሳይሆን ለማርያምና ለባሏ ለዮሴፍም ጭምር ነው። እነዚህን መልእክቶች ትኩረት ሰጥተን መመርመራችን ስለ ኢየሱስ መወለድ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረንና መልአኩ በሰዎች መካከል ሰላም እንደሚሆን የተናገረውን ትንቢት ትርጉም እንድንረዳ ያስችለናል።
ማርያም ኢየሱስን ከመውለዷ በፊት፣ እንዲያውም ከማርገዟ ቀደም ብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገብርኤል ተብሎ የተጠራ አንድ መልአክ አነጋግሯት ነበር። መልአኩ ንግግሩን ሲጀምር “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” ብሏታል። በዚህ ጊዜ ማርያም በጣም ተረብሻ እንዲያውም ፈርታ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ። ታዲያ መልአኩ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
ገብርኤል እንዲህ በማለት ሁኔታውን አብራራላት:- “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያም ወንድ የማታውቅ ድንግል በመሆኗ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ጠየቀች። ገብርኤልም ሕፃኑ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደሚፀነስና ከሌሎች ልጆች የተለየ እንደሚሆን ነገራት።—ሉቃስ 1:28-35
አስቀድሞ የተነገረለት ንጉሥ
ገብርኤል የተናገራቸው ቃላት፣ ማርያም የምትወልደው ልጅ በጥንት ነቢያት አስቀድሞ የተነገረለት እንደሆነ እንድትገነዘብ ሳይረዳት አልቀረም። ይሖዋ፣ ማርያም ለምትወልደው ልጅ ‘የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እንደሚሰጠው’ መግለጹ እርሷም ሆነች ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚያውቅ ማንኛውም አይሁዳዊ፣ አምላክ ለእስራኤል ንጉሥ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን እንዲያስብ ያደርገዋል።
ይሖዋ በነቢዩ ናታን አማካኝነት ለዳዊት እንዲህ ብሎት ነበር:- “ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።” (2 ሳሙኤል 7:4, 16) ይሖዋ ስለ ዳዊት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የዘር ሐረጉን ለዘላለም፣ ዙፋኑንም በሰማያት ዕድሜ ልክ አጸናለሁ። የዘር ሐረጉ ለዘላለም፣ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል።” (መዝሙር 89:20, 29, 35, 36) በመሆኑም ማርያምም ሆነች ዮሴፍ በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል መምጣታቸው እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር አልነበረም።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ዳዊት ንጉሣዊ ልጅ የሚናገረው ትንቢት ይህ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ማርያም በኢሳይያስ ላይ የተነገረውን እንዲህ የሚል ትንቢት ሳታውቅ አትቀርም:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።”—ኢሳይያስ 9:6, 7
በመሆኑም ገብርኤል ለማርያም የነገራት መልእክት በተአምራዊ ሁኔታ ወንድ ልጅ እንደሚወለድ የሚጠቁም ብቻ አልነበረም። የምትወልደው ልጅ የንጉሥ ዳዊትን ዙፋን በመውረስ አምላክ ባቋቋመው መንግሥት ዘላለማዊ ንጉሥ ይሆናል። ኢየሱስ ወደፊት ምን ሚና እንደሚኖረው ገብርኤል የተናገረው ትንቢት ለሁላችንም ጥልቅ ትርጉም የያዘ ነው።
ዮሴፍ እጮኛው እርጉዝ መሆኗን ሲያውቅ ሊተዋት አሰበ። እርሱና እጮኛው የጾታ ግንኙነት አድርገው ስለማያውቁ የተረገዘው ልጅ የእርሱ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ማርያም እንዴት እንዳረገዘች ለዮሴፍ ስትነግረው ለማመን ምን ያህል እንደሚቸግረው ማሰብ አያዳግትም። የወንጌል ዘገባው እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ ‘የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ እጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።’”—ማቴዎስ 1:20, 21
ዮሴፍ፣ ልጁ ‘ሕዝቡን ከኀጢአታቸው እንደሚያድናቸው’ የተነገረውን ትንቢት ምን ያህል እንደተረዳው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም። ሆኖም ለዮሴፍ የተነገረው ይህ መልእክት ነፍሰ ጡሯ እናት ምንም መጥፎ ድርጊት እንዳልፈጸመች አረጋግጦለታል። በመሆኑም ዮሴፍ፣ መልአኩ ባዘዘው መሠረት ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ ይህን ማድረጉ እንደተጋቡ የሚያሳይ ነው።
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ሌሎች ሐሳቦች መልአኩ ምን ለማለት እንደፈለገ ለመረዳት ያስችሉናል። በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ ዓመጸኛ መልአክ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ክርክር አስነሳ። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ይህ ዓመጸኛ ከሰነዘራቸው ክሶች መካከል የአምላክ አገዛዝ ፍትሐዊ አይደለም፤ ማንም ሰው ፈተና ሲያጋጥመው ታማኝነቱን አይጠብቅም የሚሉት ይገኙበታል። (ዘፍጥረት 3:2-5፤ ኢዮብ 1:6-12) አዳም ታማኝነታቸውን ጠብቀው ካልተገኙት መካከል አንዱ ነው። ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ሁሉም የሰው ልጆች ኃጢአትን ወረሱ፤ የኃጢአት ውጤት ደግሞ ሞት ነው። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ሆኖም ኢየሱስ የተጸነሰው ከሰብዓዊ አባት ባለመሆኑ ከኃጢአት ነጻ ሆኖ ሊወለድ ችሏል። ኢየሱስ፣ አዳም ላጣው ሕይወት ተመጣጣኝ ቤዛ እንዲሆን ፍጹም ሰብዓዊ አካሉን በፈቃደኝነት በማቅረብ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ማዳን እንዲሁም ለእነርሱ የዘላለም ሕይወት ተስፋ መዘርጋት ችሏል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3-6፤ ቲቶ 3:6, 7፤ 1 ዮሐንስ 2:25
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የኃጢአት ውጤቶች መወገዳቸው ምን ትርጉም እንደሚኖረው አሳይቷል። ሰዎችን ከማንኛውም ዓይነት አካላዊ ሕመም ፈውሷቸዋል፤ የሞቱትን ሳይቀር ወደ ሕይወት አምጥቷል። (ማቴዎስ 4:23፤ ዮሐንስ 11:1-44) እነዚህ ተአምራቶች ወደፊት ምን እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ናቸው። ኢየሱስ ራሱ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ [ድምፄን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል . . . [እነርሱም] ይወጣሉ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29
ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር የሚናገረው ይህ ተስፋ ለኢየሱስ መወለድ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሞቱ ትልቅ ትኩረት የምንሰጥበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። ዮሐንስ 3:17 አምላክ ልጁን ወደ ምድር የላከው “ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው” በማለት ይናገራል። ይህ አስደሳች ምሥራች፣ ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት መንጎቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩት እረኞች የተነገራቸውን መልእክት ያስታውሰናል።
‘ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ የምሥራች’
መላእክቱ፣ ‘መድኅን እርሱም ጌታ ክርስቶስ’ መወለዱን ሲያበስሩ እውነትም ለሰው ልጆች ‘ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች’ መናገራቸው ነው። (ሉቃስ 2:10, 11) ይህ ልጅ የአምላክ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረው መሲሕ፣ ታላቅ ነቢይና ገዢ ነው። (ዘዳግም 18:18፤ ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረው ሕይወትም ሆነ ሞቱ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ በመሆኑም መላእክቱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም” ብለዋል።—ሉቃስ 2:14
መጽሐፍ ቅዱስ “የኋለኛው አዳም” ብሎ የሚጠራው ኢየሱስ ሰዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ አሳይቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) በዚህም ሰይጣን ክፉና ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ደግሞ በሰማይ የሚገኙት ታማኝ መላእክት እንዲደሰቱ አድርጓል።
ሆኖም ቀደም ሲል ወዳነሳነው ጥያቄ እንመለስ:- “ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት፣ የአምላክ መላእክት የተናገሩት መልእክት በእርግጥ ይፈጸማል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል?” በሚገባ! ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥን የሚጨምረው የአምላክ ዓላማ እንዲፈጸም ሰላም የግድ አስፈላጊ ነው። በምድር ዙሪያ ሰላም ሲሰፍን ሁሉም ሰዎች ለሌላው ፍቅር ያላቸው እንዲሁም ታማኞች ይሆናሉ። በመሆኑም የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም ሉዓላዊነቱን የሚቃወሙ ሁሉ መጥፋት ይኖርባቸዋል። የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች መጥፎ ናቸው ብለው ከሰይጣን ጎን ለተሰለፉ ሰዎች ግን ይህ አስደሳች ዜና አይደለም። እንዲያውም ለእነርሱ የጥፋት መልእክት ነው።—መዝሙር 37:11፤ ምሳሌ 2:21, 22
መላእክቱ፣ ለእረኞቹ ሁሉም ሰው ሰላም ይኖረዋል ብለው እንዳልነገሯቸው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ “ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች . . . ይሁን!” በማለት አውጀዋል። ይህን ሰላም የሚያገኙት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። በይሖዋ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ከመሆናቸውም በላይ እርሱን ለመምሰል ይጥራሉ። እነዚህ ወንዶችና ሴቶች በየዓመቱ ለጥቂት ቀናት ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ለሌሎች ደግነት ለማሳየትና ለጋስ ለመሆን ፈቃደኞች ናቸው።
የክርስትና መንፈስ ዓመቱን ሙሉ ይዘልቅ ይሆን?
ኢየሱስ የሰበከው ምሥራች ያለው ኃይል፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት ለመለወጥ ችሏል። በርካታ ሰዎች፣ የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመላ ሕይወታቸው ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል። በአንድ ወቅት ራስ ወዳድ የነበሩ ሰዎች፣ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ‘ኢየሱስ በእኔ ቦታ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ጀምረዋል። ሀብት በማካበትና ተድላን በማሳደድ ሕይወታቸውን ይመሩ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች መንፈሳዊ እሴቶች ያላቸውን ጠቀሜታና እነዚህንም ለጎረቤቶቻቸው ማካፈል ያለውን አስፈላጊነት እየተገነዘቡ መጥተዋል። እነዚህ ሰዎች ዓመቱን ሙሉ ለጋሶችና ደጎች ለመሆን ይጥራሉ። ታዲያ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች የምትጠብቀው ይሄን አይደለም?
ቅን የሆኑ ሰዎች ሁሉ መልአኩ ስለ ሰላም የተናገረውን መልእክት ትርጉምና አስፈላጊነት ቆም ብለው ቢያስቡና ከዚህ ጋር ተስማምተው ቢኖሩ ዓለማችን እጅግ በተሻለ ሁኔታ ላይ በተገኘች ነበር።
ስለ ኢየሱስ መወለድ የተነገሩት ትንቢቶች፣ አምላክ የሚወዳቸው ሰዎች ዘላቂና እውነተኛ ሰላም ማግኘት እንደሚችሉ ያረጋግጣሉ። አንተስ ብትሆን የምትፈልገው ይህን አይደለም? መላእክቱ፣ ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት የተናገሩት ታላቅ የሰላም ትንቢት አለምንም ጥርጥር እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ትንቢት በገና በዓል ወቅት የሚነገር ትርጉም አልባ አባባል ከመሆን አልፎ በምድር ላይ ለዘላለም ሰላም ሲሰፍን እውን ይሆናል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስትና መንፈስ ዓመቱን ሙሉ መታየት ያለበት ሲሆን ይህንንም ማድረግ ይቻላል