አምላክ ትኩረት ይሰጥሃል?
ከሰዎች አፈጣጠር ምን እንማራለን?
አንድ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ 60 ደቂቃዎች በሕፃኑ ሕይወት ውስጥ በጣም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ለምን? ምክንያቱም አንዲት እናት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከአራስ ልጇ ጋር ትስስር የምትፈጥር ከሆነ የልጇ እድገት በአስደናቂ ሁኔታ ይሻሻላል።a
አንዲት እናት ገና ለተወለደው ልጇ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንድታደርግ የሚያነሳሳት ምንድን ነው? ፕሮፌሰር ጀኔት ክሬንሾ ዘ ጆርናል ኦቭ ፐሪኔታል ኤጁኬሽን በተባለው መጽሔት ላይ እንደገለጹት ኦክሲቶሲን የተባለው ሆርሞን በከፍተኛ መጠን መመንጨቱ “አንዲት እናት አራስ ልጇን በምትደባብስበት፣ ትኩር ብላ በምትመለከትበትና ጡት በምታጠባበት ወቅት የእናትነት ስሜት በውስጧ እንዲቀሰቀስ ያደርጋል።” ከወሊድ በኋላ የሚመነጭ ሌላ ሆርሞን ደግሞ “እናቲቱ ለልጇ ፈጣን ምላሽ እንድትሰጥ” እንዲሁም ከልጇ ጋር ይበልጥ መግባባት እንድትችል ይረዳታል። ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
በአንዲት እናትና በልጇ መካከል የጠበቀ ትስስር እንዲኖር ያደረገው አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው።b ንጉሥ ዳዊት ‘ከማህፀን ያወጣው’ እንዲሁም በእናቱ እቅፍ ውስጥ ያለስጋት እንዲቀመጥ ያደረገው አምላክ እንደሆነ ተናግሯል። “ስወለድ ጀምሮ ለአንተ በአደራ ተሰጠሁ፤ ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ” በማለት ጸልዮአል።—መዝሙር 22:9, 10
እስቲ አስበው፦ አምላክ አንዲት እናት ለልጇ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንድታደርግና ለሚያስፈልጉት ነገሮች ፈጣን ምላሽ እንድትሰጥ የሚያደርግ ረቂቅ ሥርዓት ከፈጠረ ‘ልጆቹ’ ለሆንነው ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል ቢባል ምክንያታዊ አይሆንም?—የሐዋርያት ሥራ 17:29
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ትኩረት እንደሚሰጠን የሚያሳይ ምን ማስረጃ ይዟል?
ፈጣሪን ከማንም በላይ የሚያውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።”—ማቴዎስ 10:29-31
አንዲት ወፍ መሬት ላይ መውደቋን ማስተዋል ይቅርና በአጠቃላይ ወፎችን ትኩረት ሰጥተን የምናየው ስንቶቻችን ነን? በሰማይ ያለው አባታችን ግን እያንዳንዷን ወፍ ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታል! ሆኖም በእሱ ፊት ብዙ ወፎች አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳ የአንድ ሰው ያህል ዋጋ የላቸውም። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ አምላክ ትኩረት አይሰጠኝም ብለህ ‘መፍራት’ አይገባህም። እንዲያውም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!
አምላክ ለደህንነታችን ከልብ የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ ልዩ ትኩረት ይሰጠናል
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማረጋገጫ
“የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው፤ ክፉዎችንም ሆነ ጥሩ ሰዎችን ይመለከታሉ።”—ምሳሌ 15:3
“የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማሉ።”—መዝሙር 34:15
“በታማኝ ፍቅርህ እጅግ ሐሴት አደርጋለሁ፤ ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤ በጭንቀት መዋጤን ታውቃለህ።”—መዝሙር 31:7
“ይሖዋ እንደማይወደኝ ይሰማኝ ነበር”
አምላክ ለደህንነታችን ከልብ እንደሚያስብና ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠን ማወቃችን በሕይወታችን ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? እንዴታ! በኢንግላንድ የምትኖረው ሐናc እንዲህ በማለት ተናግራለች፦
“ለብዙ ጊዜያት፣ ይሖዋ እንደማይወደኝና ለጸሎቶቼ ምላሽ እንደማይሰጥ ይሰማኝ ነበር። ይህ የሆነው እምነት ስለጎደለኝ እንደሆነ አስብ ነበር። ይሖዋ እየቀጣኝ ያለው ወይም ችላ ያለኝ ከቁብ ስለማይቆጥረኝ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አምላክ ለእኔ ምንም ደንታ ያለው አይመስለኝም ነበር።”
በአሁኑ ጊዜ ግን ሐና ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጣትና እንደሚወዳት ምንም አትጠራጠርም። አመለካከቷን እንድትለውጥ የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ለውጡ የመጣው ቀስ በቀስ ነው። ከብዙ ዓመታት በፊት የቀረበ ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚገልጽ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በአመለካከቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ አስታውሳለሁ፤ ንግግሩ ይሖዋ እንደሚወደኝ እርግጠኛ እንድሆን ረድቶኛል። ይሖዋ ለጸሎቶቼ መልስ እንደሚሰጥ ማየቴ ደግሞ ‘ለካ ይሖዋ ይወደኛል’ ብዬ እንዳስብ ስለሚያደርገኝ እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኛል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ለእኛ ስላለው ስሜት ይበልጥ እንዳውቅ ረድቶኛል። አሁን ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደግፈንና እንደሚወደን እንዲሁም እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ የመንከባከብ ፍላጎት እንዳለው ማስተዋል ችያለሁ።”
ሐና የተናገረችው ነገር የሚያበረታታ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ስሜትህን እንደሚረዳና ለስሜትህ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል።
a ከወሊድ በኋላ በሚመጣ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ አንዳንድ እናቶች ከአራስ ልጃቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር ሊቸገሩ ይችላሉ። ሆኖም ይህ የእነሱ ጥፋት እንደሆነ ሊሰማቸው አይገባም። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤንነት ተቋም እንደገለጸው ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት “የአካላዊና የስሜታዊ መንስኤዎች ድምር ውጤት ሊሆን ይችላል። . . . እናቲቱ ባደረገችው ወይም ባላደረገችው ነገር ምክንያት የሚከሰት አይደለም።” ይህን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 8, 2003 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ከወሊድ በኋላ የሚመጣን ከባድ የመንፈስ ጭንቀት መረዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18
c በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።