ሌሎችን በይሖዋ ዓይን ለማየት ጣሩ
“ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና።”—1 ሳሙኤል 16:7
1, 2. ይሖዋና ሳሙኤል ለኤልያብ ምን የተለያየ አመለካከት ነበራቸው? ከዚህስ ምን እንማራለን?
በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ለነቢዩ ሳሙኤል አንድ ልዩ ተልእኮ ሰጠው። እሴይ ወደተባለ ሰው ቤት ሄዶ ከወንዶች ልጆቹ መካከል የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ የሚሆነውን እንዲቀባ አዘዘው። ሳሙኤል የእሴይን የበኩር ልጅ ኤልያብን ባየው ጊዜ አምላክ የመረጠው እርሱን እንደሆነ ምንም ጥርጣሬ አላደረበትም። ይሖዋ ግን “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። (1 ሳሙኤል 16:6, 7) ሳሙኤል ኤልያብን በይሖዋ ዓይን ማየት ተስኖት ነበር።a
2 ሰዎች ለሌሎች የሚኖራቸው ግምት ፈጽሞ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል! በአንድ በኩል ጥሩ መስለው በሚታዩ ሆኖም ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም በሌላቸው ሰዎች እንማረክ ይሆናል። በሌላ በኩል አንዳንድ ሰዎች ቅን ቢሆኑም ባሕርያቸው ደስ ስላላለን ብቻ በእነርሱ ላይ ጥብቅ በመሆን ፊት ልንነሳቸው እንችላለን።
3, 4. (ሀ) በሁለት ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ሁለቱም ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? (ለ) ከእምነት ባልንጀራችን ጋር ከባድ አለመግባባት ቢፈጠር ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
3 ለረጅም ዓመታት የምናውቃቸውን ጨምሮ በሌሎች ላይ ቸኩለን የምንፈርድ ከሆነ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። በአንድ ወቅት የቅርብ ወዳጅህ ከነበረ አንድ ክርስቲያን ጋር ከባድ ቅራኔ ውስጥ ገብታችኋል እንበል። ወዳጅነታችሁ እንዲታደስ ትፈልጋለህ? ለዚህ ምን ሊረዳህ ይችላል?
4 የክርስቲያን ወንድምህን ወይም እህትህን በጎ ጎን ለማየት ለምን ጥረት አታደርግም? ይህንን በምታደርግበት ጊዜ ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ሲል የተናገረውን አስብ። (ዮሐንስ 6:44) ከዚያም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይሖዋ ይህን ሰው ወደ ልጁ የሳበው ለምንድን ነው? ምን ጥሩ ባሕርያት አሉት? እነዚህን ባሕርያት ማየት ተስኖኝ ይሆን? በመጀመሪያ ወዳጅነት እንድንመሠርት ያስቻለን ምን ነበር? እርሱን እንድወደው ያደረገኝ ምንድን ነው?’ በተለይ ለተወሰነ ጊዜ ቅያሜ አድሮብህ ከነበረ መጀመሪያ ላይ የእርሱ መልካም ባሕርይ ላይታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድ ይህን የግድ ማድረግ ይኖርብሃል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በደካማ ጎናቸው የሚታወቁ ሆኖም መልካም ባሕርያት ያሏቸውን የሁለት ሰዎች ሁኔታ እንመልከት። እነርሱም ነቢዩ ዮናስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ናቸው።
የዮናስን መልካም ባሕርያት መመልከት
5. ዮናስ የተሰጠው ተልእኮ ምን ነበር? እርሱስ ምን አደረገ?
5 በዮአስ ልጅ በዳግማዊ ኢዮርብዓም የግዛት ዘመን ዮናስ በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ነቢይ ሆኖ አገልግሏል። (2 ነገሥት 14:23-25) በአንድ ወቅት ይሖዋ ዮናስን የኃያልዋ አሦር ግዛት ዋና ከተማ ወደ ነበረችው ወደ ነነዌ እንዲሄድ አዘዘው። ወደዚያ እንዲሄድ የታዘዘው ለምን ነበር? ታላቅዋ ከተማ ጥፋት እንደተፈረደባት ነዋሪዎቹን ለማስጠንቀቅ ነበር። (ዮናስ 1:1, 2) ዮናስ የአምላክን መመሪያ ከመታዘዝ ይልቅ ወደሌላ ቦታ ሸሽቶ ሄደ! በመርከብ ተሳፍሮ ከነነዌ በጣም ርቃ ወደምትገኘው ወደ ተርሴስ ኮበለለ።—ዮናስ 1:3
6. ይሖዋ ዮናስን ወደ ነነዌ ለመላክ የመረጠው ለምንድን ነው?
6 የዮናስ ስም ሲነሳ ምን ትዝ ይልሃል? የተሰጠውን ትእዛዝ የማያከብር ነቢይ እንደሆነ ይሰማሃል? ስለ ዮናስ በጥሞና ካላሰብን እምቢተኛ ነው ብለን እንደመድም ይሆናል። ሆኖም አምላክ ዮናስን ነቢይ አድርጎ የሾመው እምቢተኝነቱን አይቶ ነውን? እንዳልሆነ የታወቀ ነው! ዮናስ አንዳንድ ግሩም ባሕርያት ኖረውት መሆን አለበት። በነቢይነት ያሳለፈውን ሕይወት ተመልከት።
7. ዮናስ እስራኤል ውስጥ ይሖዋን ያገለገለው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ነው? ይህን ማወቅህ ስለ እርሱ ባለህ አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
7 ዮናስ ለመልእክቱ አዎንታዊ ምላሽ ባላገኘበት በእስራኤል ምድር በታማኝነት አገልግሏል። በእርሱ ዘመን የኖረው ነቢዩ አሞጽ በወቅቱ እስራኤላውያን ፍቅረ ነዋይ የተጠናወታቸው እንደነበሩ ተናግሯል።b በእስራኤል ክፋት ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም እስራኤላውያን ሁኔታውን በቸልታ ያልፉ ነበር። (አሞጽ 3:13–15፤ 4:4፤ 6:4-6) ሆኖም ዮናስ መልእክቱን እንዲያውጅ የተሰጠውን ተልእኮ ያለማሰለስ በታማኝነት ፈጽሟል። የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ ከሆንክ ደንታ ቢስና ግድ የለሽ ለሆኑ ሰዎች መልእክቱን ማድረስ ምን ያህል አዳጋች መሆኑን እንደምትገነዘብ የታወቀ ነው። እንግዲያው ዮናስ ደካማ ጎኖች እንደነበሩት የማይካድ ቢሆንም እምነት የለሽ ለሆኑት እስራኤላውያን በሚሰብክበት ጊዜ ያሳየውን ታማኝነትና ጽናት መዘንጋት አይኖርብንም።
8. አንድ እስራኤላዊ ነቢይ በነነዌ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ?
8 ዮናስ ወደ ነነዌ ሄዶ እንዲያከናውን የተሰጠው ተልእኮ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አስቸጋሪ ነበር። እዚያ ለመድረስ ወደ 800 ኪሎ ሜትር ገደማ በእግር መጓዝ ነበረበት። ይህ ደግሞ ወደ አንድ ወር ገደማ የሚፈጅ አድካሚ ጉዞ ነው። እዚያ ከደረሰ በኋላ በጭካኔያቸው ለሚታወቁት ለአሦራውያን መስበክ ይጠበቅበታል። አሦራውያን ጠላቶቻቸውን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የማሰቃየት ልማድ ነበራቸው። ይባስ ብሎም የጭካኔ ድርጊታቸውን በጉራ ይናገሩ ነበር። ነነዌ ‘የደም ከተማ’ ተብላ መጠራትዋ ምንም አያስደንቅም!—ናሆም 3:1, 7
9. መንገደኞቹን ከባድ ማዕበል ባስጨነቃቸው ወቅት የትኞቹ የዮናስ ባሕርያት በግልጽ ታይተዋል?
9 ዮናስ ይሖዋ ወዳዘዘው አካባቢ ለመሄድ ፈቃደኛ ስላልነበረ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመጓዝ ተነሳ። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእርሱ ተስፋ አልቆረጠም ወይም ሌላ ሰው እንዲተካው አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ዮናስ የተልእኮውን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ሊረዳው ፈለገ። አምላክ ባሕሩ ላይ ከባድ ማዕበል እንዲነሳ ሲያደርግ ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ በሞገዱ ትናወጥ ጀመር። በዮናስ ምክንያት ንጹሐን ሰዎች ጥፋት ሊደርስባቸው ነበር! (ዮናስ 1:4) ዮናስ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? በእርሱ ምክንያት ተሳፋሪዎቹ እንዲሞቱ ስላልፈለገ “አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፣ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው። (ዮናስ 1:12) በዚህ ጊዜ ዮናስን ወደ ባሕሩ የጣሉት ሲሆን እርሱም ይሖዋ ያድነኛል የሚል ግምት አልነበረውም። (ዮናስ 1:15) የሆነ ሆኖ መንገደኞቹ ከጥፋት እንዲድኑ ሲል ሕይወቱን ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። ዮናስ የወሰደው ይህ እርምጃ ደፋር፣ ትሑትና አፍቃሪ መሆኑን አያሳይም?
10. ዮናስ በነቢይነቱ እንዲቀጥል ከተፈቀደለት በኋላ የሆነው ነገር ምን ነበር?
10 በመጨረሻ ይሖዋ ዮናስን አዳነው። ዮናስ ለመኮብለል ያደረገው ጥረት ከዚያ በኋላ የአምላክ ነቢይ ሆኖ የማገልገል መብቱን እንዲያጣ አድርጎታልን? በጭራሽ። ይሖዋ ለዮናስ ምሕረትና ፍቅር በማሳየት ለነነዌ ሰዎች መልእክቱን እንዲያደርስ በድጋሚ ነገረው። ዮናስ ነነዌ ከደረሰ በኋላ አምላክ በዚያ የሚኖሩት ሰዎች በሚሠሩት ክፋት መቆጣቱንና ከተማዋን በ40 ቀናት ውስጥ እንደሚደመስሳት በድፍረት ነገራቸው። (ዮናስ 1:2፤ 3:4) የነነዌ ሰዎች ዮናስ የተናገረውን መልእክት ሰምተው ንስሐ በመግባታቸው ከተማዋ ከጥፋት ለመትረፍ በቃች።
11. ዮናስ ጠቃሚ ትምህርት መቅሰሙን የሚያሳየው ምንድን ነው?
11 ዮናስ አሁንም ቢሆን ትክክለኛ አመለካከት አልያዘም። ሆኖም ይሖዋ ተጨባጭ ምሳሌ በመጠቀም ዮናስን በትዕግሥት ረዳው። ይሖዋ የሰዎችን ልብ ይመረምራል። (ዮናስ 4:5-11) ዮናስ ይህን ዘገባ እንዳለ ማስፈሩ ጠቃሚ ትምህርት መቅሰሙን ያሳያል። ደካማ ጎኑን ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ ሁኔታ ከመጻፍ ወደኋላ አለማለቱ ትሕትናውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ስህተትን አምኖ መቀበል ድፍረት ይጠይቃል!
12. (ሀ) ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለሰዎች ያለውን አመለካከት እንደሚያንጸባርቅ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ምሥራቹን ለምንሰብክላቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
12 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮናስ ሕይወት ውስጥ ስለተፈጸመ አንድ ክንውን ገንቢ ሐሳብ ተናግሯል። “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል” ሲል ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 12:40) ዮናስ ወደፊት ትንሣኤ ሲያገኝ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ የሚያሳልፈውን ጊዜ እርሱ በዓሣ ሆድ ውስጥ ከቆየባቸው ቀናት ጋር እንዳመሳሰለው ማወቁ አይቀርም። አገልጋዮቹ ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ እርግፍ አድርጎ የማይተዋቸውን አምላክ ማገልገላችን አያስደስትም? መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” (መዝሙር 103:13, 14) ዛሬ ያሉትን ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ጨምሮ “አፈር” የሆኑት የሰው ዘሮች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ብዙ ነገር ማከናወን ይችላሉ!
ስለ ጴጥሮስ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
13. ስለ ጴጥሮስ ስታስብ የትኞቹ ባሕርያቱ ትዝ ይሉሃል? ይሁንና ኢየሱስ ሐዋርያ አድርጎ የመረጠው ለምንድን ነው?
13 አሁን ደግሞ የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ በአጭሩ እንመልከት። ጴጥሮስ ምን ዓይነት ሰው ነው ተብለህ ብትጠየቅ ችኩል፣ ትዕግሥት የለሽና ከልክ በላይ በራሱ የሚተማመን ሰው ነበር ብለህ ትመልሳለህን? ጴጥሮስ እነዚህን ባሕርያት ያንጸባረቀባቸው ወቅቶች እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በእርግጥ ችኩል፣ ትዕግሥት የለሽ ወይም ከልክ በላይ በራሱ የሚተማመን ሰው ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ አድርጎ ይመርጠው ነበርን? (ሉቃስ 6:12-14) እንደማይመርጠው የታወቀ ነው! ጴጥሮስ ደካማ ጎኖች ቢኖሩትም ኢየሱስ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ማየት አልተሳነውም።
14. (ሀ) ጴጥሮስ ለመናገር ችኩል የነበረው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ጴጥሮስ ብዙ ጊዜ ጥያቄ መጠየቁ እኛንም የጠቀመን እንዴት ነው?
14 ጴጥሮስ ሌሎቹን ሐዋርያት ወክሎ የተናገረባቸው ጊዜያት ነበሩ። አንዳንዶች ይህንን ራስን ከፍ ከፍ እንደማድረግ ይቆጥሩት ይሆናል። በእርግጥ ይህ ትክክል ነውን? አንዳንዶች ጴጥሮስ ከሌሎቹ ሐዋርያትም ሆነ ከኢየሱስም ጭምር በዕድሜ ሊበልጥ እንደሚችል ይገምታሉ። አባባላቸው ትክክል ከሆነ ጴጥሮስ አብዛኛውን ጊዜ ለመናገር ቀዳሚ የሆነበት ምክንያት ሊገባን ይችላል። (ማቴዎስ 16:22) ይሁን እንጂ ሌላም ልናየው የሚገባ ነጥብ አለ። ጴጥሮስ መንፈሳዊ ሰው በመሆኑ ለማወቅ ካለው ጉጉት የተነሳ ጥያቄዎች ይጠይቅ ነበር። ይህም እኛን ጠቅሞናል። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘሉ ሐሳቦችን የተናገረ ሲሆን እነዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ ‘ታማኙ መጋቢ’ የተናገረው ጴጥሮስ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ በሰጠበት ጊዜ ነው። (ሉቃስ 12:41-44) እንዲሁም ጴጥሮስ “እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?” በማለት ጠይቆ ነበር። ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ ቀጥሎ ያለውን እምነት የሚያጠነክር ተስፋ ሰጥቷል:- “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።”—ማቴዎስ 15:15፤ 18:21, 22፤ 19:27-29
15. ጴጥሮስ በእርግጥ ታማኝ ነበር እንድንል የሚያስችለን ምንድን ነው?
15 ከዚህም በላይ ጴጥሮስ ታማኝ ነበር። ኢየሱስ የሰጣቸውን ትምህርት በትክክል ያልተረዱ ብዙ ደቀ መዛሙርት እርሱን መከተል ባቆሙ ጊዜ 12ቱን ሐዋርያት ወክሎ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት የተናገረው ጴጥሮስ ነበር። (ዮሐንስ 6:66-68) ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ከጊዜ በኋላ ሰዎች ኢየሱስን ለመያዝ በመጡ ጊዜ ከሐዋርያቱ መካከል አብዛኞቹ ጥለውት ሸሹ። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ሰዎቹን በቅርብ ርቀት ይከተላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገብቶ ነበር። እዚያ ድረስ እንዲሄድ ያደረገው ድፍረት እንጂ ፍርሃት አልነበረም። ኢየሱስ ለጥያቄ በቀረበ ጊዜ ጴጥሮስ ተሰብስበው እሳት ከሚሞቁ አይሁዳውያን ጋር ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ማንነቱን በማወቁ ከኢየሱስ ጋር ነበር ብሎ አጋለጠው። እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ ጌታውን ክዷል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሐዋርያት ፈርተው ሲሸሹ ጴጥሮስ እንዲህ ባለ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ የቻለው ለኢየሱስ ከነበረው ታማኝነትና አሳቢነት የተነሳ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም።—ዮሐንስ 18:15-27
16. የዮናስንና የጴጥሮስን መልካም ባሕርያት በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል?
16 ጴጥሮስ ከደካማ ጎኑ ይበልጥ ጎልተው የሚታዩ ግሩም ባሕርያት ነበሩት። የዮናስም ሁኔታ ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። ዮናስና ጴጥሮስ ስላላቸው በጎ ጎን ከወትሮው የተሻለ ግንዛቤ እንዳገኘን ሁሉ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሚኖረን ግምት ረገድ ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ራሳችንን ማስለመድ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ከእነርሱ ጋር የተሻለ ዝምድና እንድንመሠርት ያስችለናል። አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ መጣራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ትምህርቱን በሥራ ላይ ማዋል
17, 18. (ሀ) በክርስቲያኖች መካከል ቅራኔ የሚፈጠረው በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል? (ለ) ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሔ ለማግኘት የሚያስችለን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ከተለያየ የኑሮና የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ብሔር የተውጣጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ይሖዋን በአንድነት እያገለገሉ ነው። (ራእይ 7:9, 10) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለያየ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች አሉ! እርስ በርስ ተቀራርበን አምላክን የምናገለግል በመሆናችን አንዳንድ ጊዜ በመካከላችን አለመግባባት መፈጠሩ የማይቀር ነው።—ሮሜ 12:10፤ ፊልጵስዩስ 2:3
18 የወንድሞቻችን ደካማ ጎኖች በግልጽ የሚታዩን ቢሆንም በእነዚህ ላይ አናተኩርም። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” በማለት ሲዘምር የገለጸውን የይሖዋን ባሕርይ ለመኮረጅ እንጣጣራለን። (መዝሙር 130:3) በመካከላችን መከፋፈል እንዲፈጠር በሚያደርጉ ባሕርያት ላይ ከማተኮር ይልቅ ‘ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተላለን።’ (ሮሜ 14:19) ሌሎችን በይሖዋ ዓይን ለማየትና ደካማ ጎናቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ባሕርያቶቻቸው ላይ ለማተኮር ጥረት እናደርጋለን። ይህን ማድረጋችን ‘እርስ በርሳችን ይቅር እንድንባባል’ ይረዳናል።—ቆላስይስ 3:13
19. አንድ ክርስቲያን ከባድ አለመግባባት ሲያጋጥመው ሊወስዳቸው የሚገቡት እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?
19 በቀላሉ ልንረሳው የማንችለው አለመግባባት ቢፈጠርስ? (መዝሙር 4:4) አንተስ ከመንፈሳዊ ወንድምህ ጋር እንዲህ ያለ ቅራኔ አጋጥሞህ ያውቃል? ቅራኔውን ለመፍታት ለምን ጥረት አታደርግም? (ዘፍጥረት 32:13-15) በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው። ከዚያም ግለሰቡ ያሉትን መልካም ባሕርያት በአእምሮህ ይዘህ ‘ጥበብ በተሞላበት የዋህነት’ ቀርበህ አነጋግረው። (ያዕቆብ 3:13) ከእርሱ ጋር የነበራችሁ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመለስ ፍላጎት እንዳለህ ግለጽለት። “ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቊጣም የዘገየ ይሁን” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ተከተል። (ያዕቆብ 1:19) “ለቁጣ የዘገየ ይሁን” የሚለው ምክር ሌላው ወገን ሊያስቆጣህ የሚችል ነገር ሊያደርግ ወይም ሊናገር እንደሚችል ያመለክታል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ከተፈጠረ ይሖዋ ራስን መግዛት እንዲሰጥህ ለምነው። (ገላትያ 5:22, 23) ወንድምህ የተሰማውን ቅሬታ እንዲናገር ፍቀድለት፤ አንተም በጥሞና አዳምጠው። የማትቀበላቸውን ነገሮች ቢናገርም እንኳ ንግግሩን አስጨርሰው። የተሳሳተ አመለካከት ይዞ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም አመለካከቱን ልታከብርለት ይገባል። ችግሩን በእርሱ ቦታ ሆነህ ለማየት ሞክር። ይህም እርሱ ለአንተ ያለውን አመለካከት መረዳትን ይጨምራል።—ምሳሌ 18:17
20. የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በምትሞክሩበት ጊዜ ሐሳብህን ከመናገርህ በፊት ሌላው ወገን የሚናገረውን በጥሞና ማዳመጥህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
20 ሐሳብህን የምትገልጽበትን አጋጣሚ ስታገኝ ደግነት በተሞላበት መንገድ ተናገር። (ቆላስይስ 4:6) ደስ የሚሉህን የእርሱን ጎኖች ጥቀስለት። አለመግባባቱ እንዲፈጠር ያደረግኸው ነገር ካለ አምነህ ተቀብለህ ይቅርታ ጠይቅ። ከእርሱ ጋር ሰላማዊ ዝምድና ለመመሥረት በትህትና ያደረግኸው ጥረት ከሰመረልህ ይሖዋን አመስግን። ካልሆነ ደግሞ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችሉ ሌሎች አጋጣሚዎችን በተስፋ በመጠባበቅ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጥህ መለመንህን አታቋርጥ።—ሮሜ 12:18
21. ይህ ትምህርት ሌሎችን በይሖዋ ዓይን መመልከት እንድትችል የረዳህ እንዴት ነው?
21 ይሖዋ አገልጋዮቹን ሁሉ ያፈቅራል። ፍጹማን ባንሆንም ሁላችንም እርሱን እንድናገለግለው ይፈልጋል። ሌሎችን እንዴት እንደሚመለከት ባወቅን መጠን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ያድጋል። ለመንፈሳዊ ወንድማችን ያለን ፍቅር ከቀዘቀዘ መልሶ እንዲቀጣጠል ማድረግ ይቻላል። ወንድሞቻችንን ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ይኸውም መልካም ጎናቸውን ለማየት ብርቱ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ከፍተኛ በረከት እናገኛለን!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መልከ መልካም የሆነው ኤልያብ የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን ብቃት እንዳልነበረው ከጊዜ በኋላ በግልጽ ታይቷል። ግዙፍ የነበረው የፍልስጤም ተዋጊ ጎልያድ እስራኤላውያንን ለፍልሚያ በጠራቸው ጊዜ ኤልያብም ሆነ ሌሎቹ የእስራኤል ተዋጊዎች በፍርሃት ተርበድብደው ነበር።—1 ሳሙኤል 17:11, 28-30
b ዳግማዊ ኢዮርብዓም አንዳንድ ወሳኝ ድሎችን በመቀዳጀቱና ቀድሞ በእስራኤል ግዛት ሥር የነበሩ ክልሎችን በማስመለሱ ምክንያት ይሰበሰብለት የነበረው ግብር በመጨመሩ ሰሜናዊው መንግሥት ከፍተኛ ብልጽግና እንዲያገኝ አስችሎታል።—2 ሳሙኤል 8:6፤ 2 ነገሥት 14:23-28፤ 2 ዜና መዋዕል 8:3, 4፤ አሞጽ 6:2
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ የታማኝ አገልጋዮቹን ደካማ ጎን የሚመለከተው እንዴት ነው?
• ዮናስና ጴጥሮስ የነበሯቸው አንዳንድ መልካም ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
• ለክርስቲያን ወንድሞችህ ምን ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ትፈልጋለህ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አምላክ ለሰዎች ያለውን አመለካከት አስብ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዮናስ በሚናገረው ታሪክ ላይ ስታሰላስል ምሥራቹን ለምትሰብክላቸው ሰዎች ያለህን አመለካከት መለወጥ እንዳለብህ አልተገነዘብክምን? እነርሱም ልክ እንደ እስራኤላውያን ደንታ ቢሶች ወይም ግዴለሾች ይባስ ብሎም ተቃዋሚዎች መስለው ይታዩ ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ አምላክ ለእነርሱ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? በዮናስ ስብከት አማካኝነት የነነዌ ንጉሥ ንስሐ እንደገባው ሁሉ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው አንዳንድ ሰዎችም በሆነ ወቅት ወደ ይሖዋ ሊመጡ ይችላሉ።—ዮናስ 3:6, 7
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
ሰዎችን የምታየው በይሖዋ ዓይን ነውን?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
ኢየሱስ ስለ ዮናስ መልካም ጎን ተናግሯል