ዮናስ ስለ ይሖዋ ምሕረት ትምህርት አገኘ
ይሖዋ ለነቢዩ ዮናስ አንድ ሥራ ሰጥቶት ነበር። ይህ የሆነው በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በሚገዛበት ጊዜ ነበር። ዮናስ ጋትሔፌር ተብላ የምትጠራ የዛብሎን ከተማ ነዋሪ ነው። (ኢያሱ 19:10, 13፤ 2 ነገሥት 14:25) ዮናስ ከሚኖርበት ከተማ በሰሜን ምሥራቅ ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ወደምትገኘው ነነዌ ተብላ ወደምትጠራ የአሦራውያን ዋና ከተማ እንዲሄድ አምላክ ላከው። የነነዌ ሰዎችን አምላክ ሊያጠፋቸው እንደሆነ ማስጠንቀቅ ነበረበት።
ዮናስ እንደሚከተለው አስቦ ሊሆን ይችላል፦ ‘ወደዚያ ከተማ ሕዝብ የምሄደው ለምንድን ነው? ሕዝቡ እንደሆነ ለአምላክ ያደሩ አይደሉም። ደም የተጠሙት አሦራውያን እንደ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን አልገቡም። እንዲያውም በዚያ መጥፎ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያዬን እንደ ዛቻ ቆጥረው እስራኤልን ድል አድርገው ይይዟታል! እኔ አልሄድም። ወደ ኢዮጴ ሄጄ በመርከብ ከተሳፈርኩ በኋላ ታላቁን ባሕር አቋርጬ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደምትገኘው ተርሴስ እኮበልላለሁ። አዎን፣ ያለኝ አማራጭ ይህ ነው!’—ዮናስ 1:1-3
በባሕር ላይ ያጋጠመው አደጋ!
ዮናስ ብዙም ሳይቆይ በሜዲትራኒያን ዳርቻ ወደምትገኘው ኢዮጴ ደረሰ። ሒሳቡን ከፈለና ወደ ተርሴስ በምትሄድ መርከብ ተሳፈረ። ከስፔይን ጋር የተያያዘችው ተርሴስ ከነነዌ በስተምዕራብ ከ3,500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ትገኛለች። መርከቡ ጉዞውን ሲጀምር ደክሞት የነበረው ነቢይ ወደ መርከቡ ታችኛ ክፍል ገባና ተኛ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ከባድ ነፋስ በባሕሩ ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ በዚህ ጊዜ በፍርሃት የተዋጡት መርከበኞች እርዳታ ለማግኘት እያንዳንዳቸው ወደየአምላካቸው ይጮሁ ጀመር። መርከቡ በጣም ሲዋልልና ሲናወጥ ክብደቱን ለመቀነስ ጭነቱን ውኃ ውስጥ ጣሉት። ሆኖም መርከቧ መስጠሟ እንደማይቀር ሆኖ ተሰማቸው። በጣም የተረበሸው የመርከቧ አዛዥ ዮናስን “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አለው። ዮናስ ከተኛበት ተነስቶ ወደ ላይኛው የመርከቡ ክፍል ወጣ።—ዮናስ 1:4-6
መርከበኞቹ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ፣ ዕጣ እንጣጣል” አሉ። ዕጣው ዮናስ ላይ ወደቀ። መርከበኞቹ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ?” ሲሉት ምን ያህል እንደተሸበረ ገምት። ዮናስ “ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን” የሚያመልክና ለእርሱ አክብሮታዊ ፍርሃት ያለው ዕብራዊ እንደሆነ ነገራቸው። ማዕበሉ ያጋጠማቸው ዮናስ አምላክ የላከውን መልእክት በታዛዥነት ለነነዌ ሰዎች ከማድረስ ይልቅ ከይሖዋ ፊት ስለሸሸ ነው።—ዮናስ 1:7-10
መርከበኞቹ “ባሕሩ ከእኛ ዘንድ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?” ብለው ጠየቁት። ማዕበሉ እየጨመረ ስለመጣ ዮናስ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፣ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው። የይሖዋን አገልጋይ ባሕር ውስጥ ጥለው እንዲሞት ማድረግ ስላልፈለጉ ወደ የብስ ለመቅዘፍ ሞከሩ። መርከበኞቹ ሙከራቸው ሳይሳካ ሲቀር “አቤቱ፣ እንደ ወደድህ አድርገሃልና እንለምንሃለን፤ አቤቱ፣ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን” በማለት ጮኹ።—ዮናስ 1:11-14
ባሕር ውስጥ!
ከዚያም መርከበኞቹ ዮናስን ባሕር ውስጥ ጣሉት። ዮናስ የሚናወጠው ባሕር ውስጥ እየሰጠመ ሲሄድ ባሕሩ ፀጥ ማለት ጀመረ። ሰዎቹ ይህን ሲመለከቱ “እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፣ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን አቀረቡ፣ ስእለትንም ተሳሉ።”—ዮናስ 1:15, 16
ዮናስ ውኃ ውስጥ እየሰጠመ ሲሄድ እንደ ጸለየ አያጠራጥርም። ከዚያም ወደ አንድ ትልቅ ክፍት ቦታ ሲገባ በአንድ ለስላሳ ቱቦ ውስጥ እያለፈ እንዳለ ሆኖ ተሰማው። ይህ ሁሉ ሲሆን መተንፈስ መቻሉ ያስገርማል! ራሱ ላይ የተጠመጠመውን የባሕር ተክል ከላዩ ላይ ሲያነሳ ለየት ያለ ቦታ ውስጥ እንዳለ ተገነዘበ። ይህ የሆነው ‘እግዚአብሔር ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናድቶ ዮናስ ለሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ዓሣው ሆድ ውስጥ እንዲቆይ ስላደረገ ነው።’—ዮናስ 2:1
ዮናስ ያቀረበው ልባዊ ጸሎት
ዮናስ ግዙፍ በሆነው ዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ ጸልዮአል። በጸሎቱ ውስጥ ከጠቀሳቸው ቃላት መካከል ጥቂቶቹ ከአንዳንድ መዝሙሮች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። ዮናስ ተስፋው ጨልሞበት እንደነበረና ጸጸት እንደተሰማው በመግለጽ ከጊዜ በኋላ ጸሎቱን መዝግቦታል። ለምሳሌ የዓሣው ሆድ ለእርሱ ሲኦል ማለትም መቃብሩ የሚሆን መስሎት ነበር። ስለዚህ “በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፣ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፣ ቃሌንም አዳመጥህ” በማለት ጸልዮአል። (ዮናስ 2:2, 3) እስራኤላውያን በየዓመቱ ለሚከበሩ በዓላት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ የሚዘምሯቸው መዝሙሮች ናቸው ተብለው ከሚገመቱት የመዓርግ መዝሙሮች መካከል ሁለቱ ከዮናስ ጸሎት ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ይዘዋል።—መዝሙር 120:1፤ 130:1, 2
ዮናስ ባሕር ውስጥ መስመጡን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ “ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፣ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ።”—ዮናስ 2:4፤ ከመዝሙር 42:7፤ 69:2 ጋር አወዳድር።
ዮናስ አለመታዘዙ መለኮታዊ ሞገስ የሚያሳጣውና የይሖዋን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ የማያይ መስሎት ተጨንቆ ነበር። “እኔም ‘ከዓይንህ ፊት ተጣልኩ! እንደገና ወደ ቅዱስ መቅደስህ እንዴት እመለከታለሁ?’ አልሁ” በማለት ጸልዮአል። (ዮናስ 2:4 አዓት፤ ከመዝሙር 31:22 ጋር አወዳድር።) ዮናስ የነበረበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ስለነበር እንዲህ ብሏል፦ “ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ [ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥለውት ነበር]፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር።” (ዮናስ 2:6፤ ከመዝሙር 69:1 ጋር አወዳድር።) ዮናስ የሚከተለውን አክሎ ሲናገር የነበረበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስብ፦ “ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ [በዓሣው ሆድ ውስጥ]፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ [ልክ እንደ መቃብር መዝጊያ ባሉ] ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፣ አቤቱ አምላኬ፣ [በሦስተኛው ቀን] ሕይወቴን ከጉድጓዱ አወጣህ።”—ዮናስ 2:7፤ ከመዝሙር 30:3 ጋር አወዳድር።
ዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ‘በጣም ስለተጨነቅሁ መጸለይ አልችልም’ ብሎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ “ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ [ለሞት ተቃርቦ ሳለ] እግዚአብሔርን አሰብሁት [ወደር የሌለው ኃይልና ምሕረት እንዳለው በማመን]፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች” በማለት ጸልዮአል። (ዮናስ 2:8) አምላክ በሰማያዊ መቅደሱ ሆኖ ዮናስን በመስማት አድኖታል።
ዮናስ እንዲህ በማለት ጸሎቱን ደመደመ፦ “[በድን በሆኑ የሐሰት አማልክት ምስሎች በመታመን] የሐሰት አማልክትን የተከተሉ ሁሉ፣ ለአንተ ያላቸውን ታማኝነት ትተዋል [ይህንን ጠባይ የሚያሳየውን አምላክ በመተው]። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ ከምስጋና ጋር መሥዋዕት ለአንተ [ለይሖዋ አምላክ] አቀርባለሁ፤ የተሳልሁትንም [በዚህ ጊዜም ሆነ በሌላ ወቅት] እሰጣለሁ።” (ዮናስ 2:8, 9 የ1980 ትርጉም፤ ከመዝሙር 31:6፤ 50:14 ጋር አወዳድር።) ይህ ንስሐ የገባ ነቢይ ከሞት ሊያድነው የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ (ከእርሱ በፊት እንደኖሩት ንጉሥ ዳዊትና ሰሎሞን) መዳን የሚገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ተናግሯል።—መዝሙር 3:8፤ ምሳሌ 21:31 አዓት
ዮናስ የታዘዘውን አደረገ
ዮናስ ብዙ ካሰበና ከልቡ ከጸለየ በኋላ ገብቶበት በነበረው ቱቦ መሳይ ነገር ውስጥ እየተገፋ ሲወጣ ተሰማው። በመጨረሻ ዓሣው የብስ ላይ ተፋው። (ዮናስ 2:11) ዮናስ ከሞት ስለተረፈ በመደሰት “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፣ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት” የሚለውን የአምላክ ቃል ታዘዘ። (ዮናስ 3:1, 2) ዮናስ ወደ አሦር ዋና ከተማ አመራ። ቀኑ ምን እንደሆነ ሲያውቅ በዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን እንዳሳለፈ ተገነዘበ። ነቢዩ የኤፍራጥስ ወንዝ ወደ ምዕራብ በሚታጠፍበት ቦታ ላይ ወንዙን ተሻገረና ሰሜናዊ መስጴጦምያን አቋርጦ ወደ ምሥራቅ ከተጓዘ በኋላ በጤግሮስ ወንዝ አድርጎ ታላቋ ከተማ ደረሰ።—ዮናስ 3:3
ዮናስ ትልቅ ከተማ ወደ ሆነችው ነነዌ ገባ። በከተማዋ ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች!” ብሎ አወጀ። ዮናስ በተአምራዊ ሁኔታ የአሦራውያንን ቋንቋ የመናገር ችሎታ ተሰጥቶት ነበርን? ስለዚህ ጉዳይ የምናውቀው ነገር የለም። ሆኖም በዕብራይስጥ ተናግሮ አንድ ሰው አስተርጉሞለት ቢሆንም እንኳ የተናገረው ማስጠንቀቂያ ፍሬ አፍርቷል። የነነዌ ሰዎች በአምላክ አመኑ። ጾም ከመታወጁም በተጨማሪ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። የነነዌ ንጉሥ መልእክቱ ሲደርሰው ከዙፋኑ ተነሳ፣ ልብሰ መንግሥቱን አወለቀ፣ ማቅ ለበሰና አመድ ላይ ተቀመጠ።—ዮናስ 3:4-6 የ1980 ትርጉም
ዮናስ እንዴት ተገርሞ ይሆን! የአሦር ንጉሥ እንዲህ የሚል አዋጅ አስነገረ፦ “ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፣ ከጽኑ ቁጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”—ዮናስ 3:7-9
የነነዌ ሰዎች የንጉሣቸውን ድንጋጌ አከበሩ። አምላክ ከመጥፎ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሲመለከት እንደሚያመጣባቸው በተናገረው ጥፋት ስለ ተጸጸተ አላጠፋቸውም። (ዮናስ 3:10) የነነዌ ሰዎች ባሳዩት የንስሐ መንፈስ፣ በትሕትናቸውና በእምነታቸው የተነሳ ይሖዋ የወሰነባቸውን ቅጣት አላመጣባቸውም።
ሆደ ባሻው ነቢይ
አርባ ቀናት ቢያልፉም በነነዌ ላይ ምንም ነገር አልደረሰም። (ዮናስ 3:4 የ1980 ትርጉም) ዮናስ የነነዌ ሰዎች እንደማይጠፉ ሲገነዘብ በጣም አዝኖና ተበሳጭቶ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ “አቤቱ፣ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምሕረትህም የበዛ፣ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ፈጥኜ ነበር። አሁንም፣ አቤቱ፣ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፣ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ።” አምላክ “በውኑ ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን?” በማለት በጥያቄ መለሰለት።—ዮናስ 4:1-4
ዮናስ ብስጭት ብሎ ከተማዋን ለቅቆ ወጣ። ወደ ምሥራቅ ሄደና አንድ ዳስ ሠርቶ በከተማዋ ላይ የሚመጣውን ነገር እየተጠባበቀ በጥላው ሥር ተቀመጠ። ይሖዋም በርኅራኄ ተነሳስቶ ‘ከጭንቀቱ ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን ቅል አዘጋጀና በራሱ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት።’ ዮናስ ቅሏ በማደግዋ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ሆኖም አምላክ በነጋታው ጠዋት ቅሏ በትል እንድትበላ ሲያደርግ መጠውለግ ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። በተጨማሪም አምላክ የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ። በዚህ ጊዜ ፀሐዩ ራሱን ስላቃጠለው ነቢዩ በጣም ዛለ። እንዲሞት አጥብቆ መማጸኑን ቀጠለ። አዎን፣ ዮናስ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” በማለት ደጋግሞ ተናግሯል።—ዮናስ 4:5-8
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ተናገረ። “በውኑ ስለዚች ቅል ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን?” በማለት ዮናስን ጠየቀው። ዮናስም “እስከ ሞት ድረስ እቆጣ ዘንድ ይገባኛል” በማለት መለሰ። ይሖዋ “ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፣ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል” በማለት መሠረታዊውን ነጥብ ለነቢዩ ገልጾለታል። በመቀጠልም አምላክ “እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” በማለት አሳማኝ ምክንያት አቀረበለት። (ዮናስ 4:9-11) ትክክለኛው መልስ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው።
ዮናስ ንስሐ የገባ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በስሙ የሚጠራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነ መጽሐፍ ጽፏል። መርከበኞቹ ይሖዋን እንደፈሩ፣ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዳቀረቡና እንደተሳሉ እንዴት አወቀ? በመለኮታዊ መንፈስ አማካኝነት ወይም ምናልባት ከመርከበኞቹ አለዚያም ከተሳፋሪዎቹ አንዱን በቤተ መቅደስ አግኝቶ ሊሆን ይችላል።—ዮናስ 1:16፤ 2:5
‘የዮናስ ምልክት’
ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ክርስቶስ ምልክት እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” አላቸው። ኢየሱስ በመቀጠል “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል” አላቸው። (ማቴዎስ 12:38-40) የአይሁዳውያን ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። ክርስቶስ የሞተው ኒሳን 14, 33 እዘአ ዐርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው። የተቀበረው በዚያኑ ዕለት ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ነበር። ከዚያን ዕለት ምሽት ጀምሮ ሰባተኛውና የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን በሆነው ቅዳሜ ዕለት ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ የነበረው ጊዜ ኒሳን 15 ነው። ኒሳን 16 ደግሞ ከዚህ ጊዜ አንስቶ እሑድ ብለን በምንጠራው ቀን ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ስለዚህ ኢየሱስ የሞተው ኒሳን 14 ሲሆን ከዚሁ ቀን ውስጥ የተወሰነውን ጊዜ፣ ከዚያም ኒሳን አሥራ አምስትን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ኒሳን 16 የሌሊቱን ክፍል መቃብር ውስጥ አሳልፏል። እሑድ ጠዋት ሴቶች ወደ መቃብሩ ሲሄዱ ከሞት ተነስቶ ነበር።—ማቴዎስ 27:57-61፤ 28:1-7
ኢየሱስ ሦስቱን ቀን በተወሰነ መጠን መቃብር ውስጥ አሳልፏል። ስለዚህ ጠላቶቹ ‘የዮናስን ምልክት’ አይተዋል። ሆኖም ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም፣ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።” (ማቴዎስ 12:41) ትክክለኛ አባባል ነው! ከዮናስ በጣም የሚበልጠው ነቢይ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዶች መካከል ይገኝ ነበር። ምንም እንኳ ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ጥሩ ምልክት ሆኖላቸው የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከነቢዩ በበለጠ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ከመስበኩም በተጨማሪ ከእርሱ የበለጠ የድጋፍ ማስረጃዎች አቅርቧል። ሆኖም በጥቅሉ ሲታይ አይሁዶች አላመኑም።—ዮሐንስ 4:48
በብሔር ደረጃ አይሁዶች ከዮናስ የሚበልጠውን ነቢይ በትሕትና አልተቀበሉም፤ እንዲሁም አላመኑበትም። የቀድሞ አባቶቻቸውስ? እነርሱም እምነትና ትሕትና የላቸውም ነበር። እንዲያውም ይሖዋ ዮናስን ወደ ነነዌ የላከው የንስሐ መንፈስ ባላቸው የነነዌ ሰዎችና ምንም ዓይነት እምነትና ትሕትና በሌላቸው አንገተ ደንዳናዎቹ እስራኤላውያን መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ነው።—ከዘዳግም 9:6, 13 ጋር አወዳድር።
ስለ ዮናስስ ምን ለማለት ይቻላል? የአምላክ ምሕረት ታላቅ መሆኑን ተምሯል። በተጨማሪም ዮናስ ንስሐ ለገቡት የነነዌ ሰዎች ይቅርታ በመደረጉ የተነሳ ሲያጉረመርም ይሖዋ የሰጠው ምላሽ ሰማያዊ አባታችን በጊዜያችን ለሚገኙ ሰዎች ምሕረት ሲያደርግ ቅሬታ ከማሳየት እንድንታቀብ ያደርገናል። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እምነትና ትሕትና በማሳየት ወደ ይሖዋ ሲመለሱ መደሰት ይኖርብናል።