መልካሙን ዓመልህን ማንም አያበላሽብህ
“አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል።” — 1 ቆሮንቶስ 15:33
1, 2. (ሀ) ጳውሎስ በቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች ምን ተሰምቶት ነበር? ለምንስ? (ለ) በተለይ የትኛውን ምክሩን እንመረምራለን?
የወላጅ ፍቅር እንዴት ያለ ኃይለኛ ስሜት ያለው ነው! ወላጆችን ለልጆቻቸው ሲሉ ብዙ መሥዋዕትን እንዲከፍሉ፣ እንዲያስተምሯቸውና እንዲመክሯቸው ይገፋፋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሥጋዊ አባት ባይሆንም በቆሮንቶስ ይገኙ ለነበሩት ክርስቲያኖች “በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጃችኋለሁና” በማለት ጽፎላቸዋል። — 1 ቆሮንቶስ 4:15
2 ቀደም ሲል ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ ለአይሁዶችና ለግሪኮች ሰብኮላቸው ነበር። በቆሮንቶስ ከተማ ጉባኤ እንዲቋቋም ረድቷል። ያሳየውን እንክብካቤ ከሞግዚት ጋር አመሳስሎ በሌላው ደብዳቤ ላይ ቢጽፍም ለቆሮንቶስ ጉባኤ ግን እንደ አባት ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:7) አንድ አፍቃሪ ሥጋዊ አባት እንደሚያደርገው ጳውሎስ መንፈሳዊ ልጆቹን መክሯቸዋል። “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል” በማለት በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ከሰጣቸው አባታዊ ምክር አንተም ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ለምን ነበር? እኛስ ምክሩን እንዴት ልንሠራበት እንችላለን?
ለእነርሱና ለእኛ የሚሆን ምክር
3, 4. ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን የቆሮንቶስ ከተማና ስለ ሕዝቧ ብዛት ምን የምናውቀው ነገር አለ?
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ስትራቦ የተባለው ግሪካዊው የመልክዓ ምድር ተመራማሪ “የቆሮንቶስ ከተማ ‘ሀብታም’ ናት የተባለችው በንግዷ ምክንያት ነው። በልሳነ ምድር ላይ የተቆረቆረች በመሆኗና አንዱ ወደ እስያ በቀጥታ የሚወስድ ሌላው ደግሞ ወደ ጣልያን የሚያመራ የሁለት ወደቦች ባለቤት ከመሆኗ የተነሣ የሁለቱም አገሮች የንግድ እንቅስቃሴ ልውውጥ አግዟታል” በማለት ጽፏል። በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው የታወቀው የኢዝሚያን የስፖርት ጨዋታ በጣም ብዙ ሕዝብ ወደ ቆሮንቶስ ከተማ እንዲጎርፍ ያደርጋል።
4 የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችና የፍትወት አምልኮ የሚቀርብላት አፍሮዳይት የተባለችው ጣዖት ማዕከል በሆነችው በዚህች ከተማ ስለሚኖሩት ሰዎችስ ምን ሊባል ይቻላል? ፕሮፌሰር ቲ ኤስ ኢቫንስ “የከተማው ሕዝብ ብዛት ወደ 400,000 ይጠጋል። ኅብረተሰቡ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም በስነ ምግባር ግን ልቅ የሆነና ከመጠን በላይ የሚባልግ ነበር። . . . በአካይያ የሚኖሩ ግሪካውያን እውቀት ለማግኘትና አዳዲስ ነገሮችን ለመስማትና ለማወቅ ባላቸው ኃይለኛ ጉጉት የተነሣ አርፈው የማይቀመጡ ሰዎች ነበሩ። . . . የራስህን መንገድ ራስህ ተከተል የሚለው መሠረተ ትምህርታቸው የመናፍቅነትን ችቦ ለማቀጣጠል የሚረዳ ተጨማሪ ነዳጅ ነበር” በማለት ገልጸዋል።
5. በቆሮንቶስ ይገኙ የነበሩት ወንድሞች ምን አደገኛ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር?
5 ከጊዜ በኋላም ኩራት የተሞላው የግምት አስተሳሰብ ባጠቃቸው አንዳንድ ሰዎች ምክንያት ጉባኤው ተከፋፈለ። (1 ቆሮንቶስ 1:10–31፤ 3:2–9) አንዱ ካባድ ችግር አንዳንዶች “ትንሣኤ ሙታን የለም” ማለታቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16–18) በትክክል የሚያምኑት (ወይም የማያምኑት) ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ክርስቶስ “ከሙታን ተነሥቷል” በማለት ጉልህ ማስረጃ አቅርቦ እነሱን ማረሙ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች አምላክ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል መንሣትን” ሊሰጣቸው እንደሚችል ሊተማመኑ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:20, 51–57) በዚያ ተገኝተህ ቢሆን ኖሮ ጉባኤውን በሚከፋፍለው በዚህ መንፈስ ትወሰድ ነበርን?
6. ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሰጠው ምክር በተለይ የሚመለከተው እነማንን ነበር?
6 ሙታን የሚነሡ ለመሆናችው ጠንካራ ማስረጃ በሚያቀርብበት ጊዜ ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል” በማለት ተናገረ። የዚህ ምክር ፍሬ ሐሳብ የሚመለከተው በትንሣኤ መሠረተ ትምህርት ያልተስማሙትን ከጉባኤው ጋር የተቀራረቡትን ሰዎች ነበር። አንድ ነጥብ ስላልገባቸው ብቻ የተጠራጠሩ ሰዎች ነበሩን? (ከሉቃስ 24:38 ጋር አወዳድር።) ተጠራጣሪዎች ብቻ አልነበሩም። ጳውሎስ “ከእናንተ አንዳንዶቹ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ” በማለት ስለጻፈ ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ክህደት በማዘንበል አለመስማማታቸውን የገለጹ ናቸው። ጳውሎስ የሌሎቹን ጥሩ ዓመልና አስተሳሰብ ሊያበላሹ እንደሚችሉ በሚገባ ተረድቶ ነበር። — ሥራ 20:30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1
7. 1 ቆሮንቶስ 15:33ን በሥራ ላይ ልናውልበት የምንችለው አንዱ ሁኔታ ምንድን ነው?
7 ስለ ባልንጀርነት ጳውሎስ የሰጠውን ምክር እንዴት ልንሠራበት እንችላለን? በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ትምህርት አልገባ ቢለው እሱን ከመርዳት መቆጠብ አለብን ማለቱ አይደለም። እንደዚህ ያለ ጥርጣሬ ያለባቸውን ቅን ሰዎች አዘኔታ የተሞላበት እርዳታ እንድናደርግላቸው ይሁዳ 22, 23 ያሳስበናል። (ያዕቆብ 5:19, 20) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከምናውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለየት ያለ ወይም የተጠራጣሪነት ወይም አፍራሽ የሆነ ሐሳብ መሰንዘሩን ቢቀጥል የጳውሎስን አባታዊ ምክር ልንሠራበት ይገባል። እንደዚህ ከመሰለው ሰው ጋር ስለምናደርገው ቅርርብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። እርግጥ ነው አንድ ሰው ከሀዲ ቢሆን መንፈሳዊ እረኞች ወዲያውኑ መንጋውን ለመከላከል እርምጃ ይወስዳሉ። — 2 ጢሞቴዎስ 2:16–18፤ ቲቶ 3:10, 11
8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማማ ሰው ስናገኝ በአስተዋይነት ምን ልናደርግ እንችላለን?
8 ከጉባኤው ውጪ የሐሰት ትምህርት የሚያራምዱትንም በተመለከተ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስን አባታዊ ምክር በሥራ ላይ ልናውለው እንችላለን። ከእነሱ ጋር እንዴት ቅርርብ ልንፈጥር እንችላለን? ይህ ሊደርስ የሚችለው እውነትን እንዲያውቁ ልንረዳቸው በምንችልና እንዲሁ የሐሰት ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ሲሉ የክርክር ጥያቄዎችን የሚያስነሡትን ሰዎች ለይተን ለማወቅ ካልቻልን ነው። ለምሳሌ ያህል በምስክርነቱ ሥራችን ላይ ሳለን በአንዳንድ ነጥቦች ላይ የማይስማማ ነገር ግን በውይይቱ መቀጠል የሚፈልግ ሰው ያጋጥመን ይሆናል። (ሥራ 17:32–34) ይህ በራሱ ምንም ችግር አይፈጥርም ምክንያቱም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማወቅ ፍላጎት ላለው ለማንኛውም ሰው የሚያሳምኑ ማስረጃዎችን ይዘን ለማብራራት ተመልሰን ብንሄድም ደስ ይለናል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ሆኖም አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማወቅ ምንም ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል።
9. እምነታችንን የሚመለከት ግድድር ሲያጋጥመን እንዴት ዓይነት ምላሽ ልንሰጥ ይገባል?
9 ብዙ ሰዎች እውነት ፈላጊዎች ሳይሆኑ ለረጅም ሰዓት በየሳምንቱ ይከራከራሉ። የሌላውን እምነት በማንቋሸሽ የራሳቸውን የዕብራይስጥ፣ የግሪክኛ ቋንቋ ወይም የዝግመተ ለውጥ ሳይንስ እውቀታቸውን እየካቡ ማንነታቸውን ለማሳወቅ ይፈልጋሉ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ሲያጋጥሟቸው አንዳንድ ምስክሮች እውነትን እንደያዙ ማስመስከር እንዳለባቸው ተሰምቷቸው በሐሰት ኃይማኖት እምነቶች፣ በፍልስፍና ወይም በሳይንሳዊ ስሕተት ላይ ካተኮሩ ሰዎች ጋር ለረጅም ጊዜ ተቀራርበው ቀጥለዋል። ኢየሱስ በዕብራይስጥ ወይም በግሪክኛ ቋንቋ ተምረናል ከሚሉት የሃይማኖት መሪዎች ጋር ተከራክሮ ማሸነፍ ይችል የነበረ ቢሆንም እንደዚህ ያለ ነገር ለማድረግ አለመፈለጉን ማስታወሱ መልካም ነው። ሲከራከሩት አጭር መልስ ይሰጣቸውና እውነተኛ በጎች ወደሆኑት ወደ ትሑታኑ ሰዎች ፊቱን መለስ ያደርግ ነበር። — ማቴዎስ 22:41–46፤ 1 ቆሮንቶስ 1:23 እስከ 2:2
10. ኮምፒውተር ያላቸውና ከኤሌክትሮኒክ የመጽሔት ዓምዶች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችሉ ክርስቲያኖች ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው ለምንድን ነው?
10 ዘመናዊ ኮምፒውተሮች ለክፉ ባልንጀርነት ሌላ ዓይነት መንገድ ከፍተዋል። አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ደንበኞቻቸውን በኮምፒውተርና በስልክ ተጠቅመው ላዘጋጁት የኤሌክትሮኒክ የመጽሔት ዐምድ እንዲልኩ አስችለዋቸዋል። ስለዚህም አንድ ሰው ሁሉም ደንበኞች ማንበብ የሚችሉትን አንድ ዓይነት መልእክት በዚያ መጽሔት ዐምድ ላይ ሊያወጣ ይችላል ማለት ነው። ይህ ዝግጅት ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚመለከት የኤሌክትሮኒክ ክርክር እየተባለ ወደሚጠራ ሁኔታ አምርቷል። አንድ ክርስቲያን እንደዚህ ባለው ክርክር ውስጥ ይገባና ከጉባኤ ከተወገደ የክህደት አስተሳሰብ ካለው ግለሰብ ጋር ረጅም ሰዓት ያሳልፍ ይሆናል። በ2 ዮሐንስ 9–11 ላይ ያለው መመሪያ ጳውሎስ ከክፉ ባልንጀራ ስለመሸሽ የሰጠውን አባታዊ ምክር ደመቅ ያደርገዋል።a
ከመታለል ሽሽ
11. በቆሮንቶስ ከተማ የነበረው የንግድ ሁኔታ ለየትኛው ነገር አጋጣሚ ከፍቶ ነበር?
11 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የቆሮንቶስ ከተማ ብዙ ሱቆች ያሏትና የንግድ ሥራ የበዛባት ማዕከል ነበረች። (1 ቆሮንቶስ 10:25) ለኢዝሚያን የስፖርት ጨዋታ የመጡት ብዙ ሰዎች በድንኳን ይቀመጡ ስለነበር ነጋዴዎች በተንቀሳቃሽ ሱቆችና መደብሮች አማካኝነት ይሸጡ ነበር። (ከሥራ 18:1–3 ጋር አወዳድር።) ይህ ሁኔታ ለጳውሎስ ድንኳን እየሰፋ ለመሸጥ የሚያስችል ሥራ አስገኝቶለታል። በተጨማሪም የሥራ ቦታውን የምሥራቹን በማስፋፋት ሊጠቀምበት ችሏል። ፕሮፌሰር ጄ መርፊ ኦኮኖር “ግርግር በበዛበት ገበያ ውስጥ ከሚገኝ ሱቅ . . . ሰው የበዛበትን መንገድ ጨምሮ አብረውት ከሚሠሩትና ከደንበኞቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ጳውሎስ በውጭ ካሉትም ጋር ለመገናኘት ይችል ነበር። ገበያ ቀዝቀዝ ሲል በራፉ ላይ ይቆምና ሊሰሙ ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች ማነጋገር ይችል ነበር። . . . የነበረው ግሩም ጠባይና እምነት በቶሎ ከአካባቢው ሰዎች ጎልቶ እንዲታይ አድርጎት መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት እውቀት ለማግኘት የሚፈልጉት ብቻ ሳይሆኑ እንዲሁ ከጉጉት የተነሣ የሚመጡትና ሥራ ፈቶችም ጭምር ወደ እርሱ ተስበው ነበር። . . . ስለ እርሱ የሰሙ የቤት እመቤቶች ዕቃ እንገዛለን በሚል ሽፋን ከባለሟሎቻቸው ጋር መጥተው ሊያዳምጡት ይችሉ ነበር። አስጨናቂ ጊዜ ሲያጋጥማቸው ማለትም ስደት ወይም ሌላ ተመሳሳይ ችግር ሲደርስባቸው አማኞች ደንበኞች ነን በማለት ወደ እሱ ጠጋ በማለት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ይችሉ ነበር። የሥራ ቦታው ከከተማው የማዘጋጃ ቤት ሹሞች ጋርም ያገናኘው ነበር።”
12, 13. 1 ቆሮንቶስ 15:33 በሥራ ቦታ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ የሥራ ቦታው ‘ለመጥፎ ቅርርብ’ ሊያጋልጠው ይችል እንደነበረ ተገንዝቧል። እኛም እንዲሁ ሊሰማን ይገባናል። ጳውሎስ “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚለውን በብዙዎች ላይ ይታይ የነበረውን ዝንባሌ መጥቀሱ አስፈላጊ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:32) ከዚያ ቀጥሎ ወዲያውኑ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል” የሚለውን አባታዊ ምክሩን አስከተለ። የሥራ ቦታና ደስታ ለማግኘት መፈለግ የተደበቀ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉት እንዴት ይሆን?
13 ክርስቲያኖች አብረዋቸው ከሚሠሩት ጋር ለመግባባት ይፈልጋሉ። በዚህም ምስክርነቱን ለመስጠት የሚያስችል ጥሩ መንገድ እንደተከፈተላቸው ብዙ ተሞክሮዎች ያሳያሉ። አንድ የመሥሪያ ቤት ጓደኛ ግን የተደረገለትን የወዳጅነት አቀራረብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት አብረን ጥሩ ጊዜ እናሳልፍ የሚል ግብዣ ሊያቀርብ ይፈልግ ይሆናል። እሱ ወይም እሷ በድንገት ምሳ ሊጋብዙን ወይም ከሥራ በኋላ ትንሽ ጎራ ብለን እንጠጣ ሊሉ ወይም ቅዳሜና እሁድ በአንድ ዓይነት መዝናኛ አብረን እናሳልፍ የሚል ግብዣ ሊያቀርቡ ይችላሉ። እንዲህ ያለው ሰው ደግና ንጹሕ መስሎ ሊታይ ግብዣውም ክፋት የሌለበት ሊመስል ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ ሲመክረን “አትሳቱ” ብሎናል።
14. በጓደኝነት የተነሣ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተታለሉት እንዴት ነው?
14 ጥቂት ክርስቲያኖች ስተዋል። ቀስ በቀስ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መቀራረቡን ላላ ባለ አቋም ማየት ጀመሩ። ምናልባት በአንድ ዓይነት ስፖርት ወይም የጊዜ ማሳለፊያ ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎት ስላላቸው በዚያ ተቀራርበው ሊሆን ይችላል። ወይም በሥራ ገበታ ላይ የሚገኝ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው በደግነቱና በአሳቢነቱ ለየት ያለ ሆኖ ከእርሱ ጋር ረዘም ያለ ሰዓት በማሳለፍ እንዲያውም በጉባኤ ውስጥ ካለ ሰው ይልቅ የእሱ ባልንጀርነት ይሻላል ከሚለውም ሐሳብ በመነሣት የጀመረ ቅርርብ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ቅርርቡ ከአንድ የጉባኤ ስብሰባ ብቻ ወደ መቅረት ሊያመራ ይችላል። ይህም አንድ ማታ ላይ በጣም ከማምሸት የተነሣ የተለመደውን የጥዋት የመስክ አገልግሎት ማቋረጥ ማለት ሊሆን ይችላል። ክርስቲያኑ በመሠረቱ የማይቀበለውን ዓይነት ፊልም ወይም ቪዲዮ መመልከትን ያስከትል ይሆናል። ‘አይ፣ በእኔ ላይ እንደዚህ ያለ ነገር አይደርስብኝም’ ብለን እናስብ ይሆናል። የተታለሉ ብዙዎች ይህ ጥያቄ ቢቀርብላቸው ኖሮ መጀመሪያ ላይ እንደዚሁ ብለው መልሰው ሊሆን ይችል ነበር። ራሳችንን ‘የጳውሎስን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ምን ያህል ቆራጥ ነኝ?’ ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል።
15. ጎረቤቶቻችንን በተመለከተ ምን ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት ልንይዝ ይገባናል?
15 ስለ ሥራ ቦታ ጠቅሰን የተመለከትነው ቁምነገር ከጎረቤቶቻችን ጋር በምናደርገው ቅርርብም ላይ ይሠራል። በጥንቷ የቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ የነበሩት ክርስቲያኖች ጎረቤቶች እንደነበሩአቸው ጥርጥር የለውም። በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጎረቤቶች ጋር በደንብ መግባባትና መረዳዳት የተለመደ ነገር ነው። በገለልተኛ ስፍራ በመኖራቸው ምክንያት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሲኖሩ ይደጋገፉ ይሆናል። በአንዳንድ ባሕሎች የቤተሰብ ትስስሩ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ በየጊዜው ብዙ ጊዜ ምግብ ይገባበዙ ይሆናል። ኢየሱስ እንዳደረገው ሚዛናዊ አመለካከት መያዙ በጣም አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 8:20, 21፤ ዮሐንስ 2:12) ከጎረቤቶቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ክርስቲያኖች ከመሆናችን በፊት እናደርግ እንደነበረው የማድረግ ዝንባሌ አሁንም እናሳያለንን? ከዚህ ይልቅ እንደዚህ ያሉትን ግንኙነቶች አስበንባቸው ምን ዓይነት ገደቦችን ማበጀት እንደሚቻል በሕሊናችን ተጠቅመን ልንወስን አይገባንምን?
16. በማቴዎስ 13:3, 4 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ልንረዳቸው የሚገባን እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት “አንዳንዱም በመንገድ ላይ ወደቀ፣ ወፎችም መጥተው በሉት” በማለት ከዘር ጋር አመሳስሎ የተናገረበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 13:3, 4, 19) በዚያን ዘመን በመንገድ ዳር የነበረ አፈር ብዙ እግሮች ስለሚመላለሱበት ከመረገጥ ብዛት ይጠነክር ነበር። በብዙ ሰዎች ላይ የሚታየው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ሕይወታቸው በሙሉ በጎረቤቶች፣ በዘመዶች፣ በሚመጡና በሚሄዱ ሌሎች ሰዎች ጭምር ጊዜ እስኪያጡ ድረስ የተጣበበ ነው። ይህም በበኩሉ የልባቸው አፈር እንዲረጋገጥና የእውነት ቃል ሥር እንዳይሰድ እንቅፋት ይሆናል። ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰውም ተመሳሳይ የሆነ የልብ ጥንካሬ ሊያድርበት ይችላል።
17. ከጎረቤቶቻችንና ከሌሎች ጋር የምናደርገው መቀራረብ እንዴት ሊነካን ይችላል?
17 አንዳንድ ዓለማዊ ጎረቤቶችና ዘመዶች የወዳጅነት መንፈስ ያላቸውና ሰው የሚረዱ ሊሆኑ ቢችሉም ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት የማያሳዩና ለጽድቅም ምንም ፍቅር የሌላቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ ያሳዩ ይሆናል። (ማርቆስ 10:21, 22፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ክርስቲያን መሆናችን ሰው እንድንጠላና የጎረቤት ፍቅር የሌለን ሰዎች እንድንሆን አያደርገንም። ኢየሱስ ለሌሎች እውነተኛ ፍቅር እንድናሳይ መክሮናል። (ሉቃስ 10:29–37) ስለ ባልንጀራ ምርጫችን እንድንጠነቀቅ ጳውሎስ የሰጠንንም ምክር እኩል ኃይል ያለው በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ መሆኑንም እናስታውስ። የመጀመሪያውን ምክር እንደምንሠራበት ሁሉ የኋለኛውንም በሥራ ላይ ማዋል እንዳለብን መርሳት የለብንም። ሁለቱንም መሠረታዊ ሥርዓቶች ዘወትር ካላስታወስን ልማዳችን ሊለወጥ ይችላል። ሐቀኝነትን በተመለከተ ወይም የቄሳርን ሕግ በመታዘዝ ረገድ የአንተ ልማድ ከጎረቤቶችህ ወይም ከዘመዶችህ ልማድ ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? ለምሳሌ ያህል ግብር በሚከፈልበት ጊዜ ገቢን አሳንሶ ማስመዝገብ ወይም የንግድን ትርፍ አሳንሶ መናገር አስፈላጊና ለመኖር ሲባል መደረግ ያለበት ትክክለኛ ነገር ነው የሚል ስሜት ሊኖራቸው ይችላል። ስላላቸው አመለካከት ሌላውን ሰው ለማሳመን ድንገት ቡና ለመጠጣት በሚገናኙበት ወይም አጭር ጉብኝት ለማድረግ ብቅ ሲሉ አንዳንድ ሐሳቦችን ጣል ያደርጉ ይሆናል። ይህ ሁኔታ አስተሳሰብህን ወይም የሐቀኛነት ልማድህን እንዴት ሊነካው ይችላል? (ማርቆስ 12:17፤ ሮሜ 12:2) “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል።”
የወጣትነት ልማዶችም ጭምር
18. 1 ቆሮንቶስ 15:33 ለወጣቶችም ጭምር የሚሠራው እንዴት ነው?
18 ወጣቶች በተለይ በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ይነካሉ። አንዳንድ ልጆች ያላቸው አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም አካኋናቸው የወላጆቻቸውን ወይም የወንድሞቻቸውንና የእኅቶቻቸውን እንደሚመስል ተመልክተህ አታውቅምን? ስለዚህ ልጆች አብረዋቸው የሚጫወቱትን ወይም በትምህርት ቤት ያሉ ጓደኞቻቸውን ቢመስሉ ልንደነቅ አይገባም። (ከማቴዎስ 11:16, 17 ጋር አወዳድር።) ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ ወላጆቻቸውን በሚያቃልል መንገድ ከሚናገሩ ልጆች ጋር ቢውሉ እንዲህ ያለው ነገር ልጆቼን አይነካም ብለህ ልታስብ ትችላለህን? ሌሎች ወጣቶች የብልግና ንግግር ሲናገሩ ደጋግመው ቢሰሙስ ምን ይሆናሉ? በትምህርት ቤት ያሉ ወይም ጎረቤቶቻቸው የሆኑ እኩዮቻቸው ስለ አዲስ የጫማ ስታይል ወይም ስለ አንድ ዓይነት የጌጥ ፋሽን በጣም ሲያደንቁ ቢሰሙ ምን ይሆናሉ? ወጣት ክርስቲያኖች እንደነዚህ ዓይነት ተጽእኖዎች ምንም የማይጎዷቸው ጠንካራ ሰዎች ናቸው ብለን ልናስብ ይገባናልን? ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ ለተናገረው ነገር የዕድሜ ገደብ አለው ብሏልን?
19. ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ ምን ዓይነት አመለካከት ለመቅረጽ መጣር ይገባቸዋል?
19 ወላጅ ከሆንክ ልጆችህን የሚመለከት ውሳኔ ስታደርግና ከልጆችህ ጋር ስለ ጉዳዩ ስትወያይ ይህንን ምክር በአእምሮህ ትይዛለህን? ምክሩ ልጆችህ በጉርብትናም ሆነ በትምህርት ቤት የሚያገኙአቸው ሌሎች ልጆች ሁሉ ጥሩ አይደሉም ማለቱ እንዳልሆነ ከተስማማህ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ሊረዳህ ይችል ይሆናል። እንደ አንዳንዶቹ ጎረቤቶችህ፣ ዘመዶችህና የሥራ ጓደኞችህ ከእነዚህም ልጆች ውስጥ አንዳንዶቹ ደስ የሚሉና ጨዋ ሊሆኑ ይችላሉ። ልጆችህ ይህንኑ እንዲገነዘቡና ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን አባታዊ ምክር በሥራ ላይ ስታውል ሚዛናዊ መሆንህ እንዲገባቸው ለመርዳት ሞክር። ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መያዝህን ሲያስተውሉ ይህ ሁኔታ አንተን እንዲመስሉ ሊረዳቸው ይችላል። — ሉቃስ 6:40፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22
20. ወጣቶች ሆይ፣ ልትወጡት የሚገባ ምን ፈተና ያጋጥማችኋል?
20 እናንተም ገና ወጣቶች የሆናችሁ ለወጣትም ሆነ ለሽማግሌ ማለትም ለማንኛውም ክርስቲያን የሚጠቅም መሆኑን አውቃችሁ የጳውሎስን ምክር በሥራ ላይ እንዴት ልታውሉ እንደምትችሉ በጥሞና ልታስቡበት ሞክሩ። ይህ ፈታኝ ቢሆንም፣ ፈተናውን ታግለህ ለመወጣት ለምን ፈቃደኛ አትሆንም? ሌሎቹን ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምረህ የምታውቃቸው መሆኑ እንደ አንድ ክርስቲያን ወጣት በመሆን ያዳበርካቸውን ልማዶች አያበላሹብህም ማለት አይደለም። — ምሳሌ 2:1, 10–15
ልማዶቻችንን ከብልሽት ለመከላከል ቁርጥ ያለ እርምጃ እንውሰድ
21. (ሀ) ከሰዎች ጋር መቀራረብን በተመለከተ ምን ነገር ያስፈልገናል? (ለ) አንዳንድ የጓደኝነት ዓይነቶች አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
21 ሁላችንም ባልንጀራ ያስፈልገናል። ቢሆንም ባልንጀሮቻችን በጥሩ ወይም በመጥፎ እኛን መንካታቸው እንደማይቀር በማስታወስ ንቁ ሆነን መጠበቅ አለብን። ይህ ነገር እውነት መሆኑ በአዳምና ከዚያ በኋላ በነበሩት ብዙ መቶ ዘመናት በኖሩት ሰዎች ሁሉ ላይ የታየ ነገር ነው። ለምሳሌ በይሁዳ ግዛት ላይ ነግሦ የነበረው ጥሩው ንጉሥ ኢዮሳፍጥ የይሖዋን ሞገስና በረከት አግኝቶ ነበር። ነገር ግን ልጁ የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን የንጉሥ አክአብን ሴት ልጅ እንዲያገባ ከፈቀደ በኋላ ኢዮሳፍጥ ከአክአብ ጋር መቀራረብ ጀመረ። ይህ መጥፎ ቅርርብ ኢዮሳፍጥን ሊያስገድለው ነበር። (2 ነገሥት 8:16–18፤ 2 ዜና መዋዕል 18:1–3, 29–31) ጓደኞቻችንን በሚመለከት ጥበብ የጎደለው ምርጫ ብናደርግ ለእኛም በጣም አደገኛ ሊሆንብን ይችላል።
22. ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
22 እንግዲያው በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ የሰጠንን ፍቅራዊ ምክር ልብ እንበለው። እነዚህ ቃላት በተደጋጋሚ የሰማናቸውና በቃላችን ልንደጋግማቸው የምንችል ተራ ቃላት ብቻ አይደሉም። በቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት ወንድሞቹና እኅቶቹ እንዲሁም ለእኛም ጭምር የነበረውን አባታዊ ፍቅር ያንጸባርቃል። እነዚህ ቃሎች ጥረታችን ሁሉ እንዲሳካ የሚፈልገው የሰማዩ አባታችን ያዘጋጀልንን ምክር ለመያዛቸው ምንም አያጠራጥርም። — 1 ቆሮንቶስ 15:58
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በእንደነዚህ ዓይነቶቹ የመጽሔት ዐምዶች መጠቀም የባለቤቱ መብት በሕግ የተጠበቀባቸውን ፕሮግራሞች ወይም ጽሑፎች ያለባለቤቱ ወይም ያለደራሲው ፈቃድ ኮምፒውተራቸው ውስጥ እንዲገለብጡ ይፈትናቸዋል። ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ የባለቤትነት መብት ሕግ ጋር የሚጋጭ ይሆናል። — ሮሜ 13:1
ታስታውሳለህን?
◻ ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስ 15:33ን የጻፈው ከየትኛው ልዩ ምክንያት የተነሣ ነው?
◻ የጳውሎስን ምክር በምንሠራበት ቦታ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ስለ ጎረቤቶቻችን ምን ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት ልንይዝ ይገባናል?
◻ 1 ቆሮንቶስ 15:33 በተለይ ለወጣቶች የሚስማማ ምክር የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ የሚሠራበትን ቦታ ምሥራቹን ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌሎች ወጣቶች ክርስቲያናዊ ልማዶችህን ሊያበላሹብህ ይችላሉ