ምዕራፍ 58
ዳቦውን አበዛ፤ ስለ እርሾ አስጠነቀቀ
ኢየሱስ 4,000 ወንዶችን መገበ
ስለ ፈሪሳውያን እርሾ አስጠነቀቀ
በገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በዲካፖሊስ ክልል ብዙ ሕዝብ ወደ ኢየሱስ ጎረፈ። ሕዝቡ ወደ እሱ የመጡት ሲያስተምር ለማዳመጥና ከበሽታዎቻቸው ለመፈወስ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ስንቃቸውን የሚያስቀምጡባቸው ትላልቅ ቅርጫቶች ይዘዋል።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ። እንዲሁ ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው መንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ፤ ደግሞም አንዳንዶቹ የመጡት ከሩቅ ነው።” ደቀ መዛሙርቱ ግን “በዚህ ገለልተኛ ስፍራ እነዚህን ሰዎች የሚያጠግብ በቂ ዳቦ ከየት ማግኘት ይቻላል?” ብለው ጠየቁት።—ማርቆስ 8:2-4
ኢየሱስም “ስንት ዳቦ አላችሁ?” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ “ሰባት ዳቦና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት። (ማቴዎስ 15:34) ኢየሱስ ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጥ አደረገ። ከዚያም ዳቦውንና ዓሣዎቹን ወስዶ ወደ አምላክ ጸለየ፤ ለደቀ መዛሙርቱም እንዲያከፋፍሉ ሰጣቸው። የሚገርመው ሁሉም በልተው ጠገቡ። ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 4,000 ወንዶች የተመገቡ ቢሆንም የተረፈው ምግብ ሰባት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ሆነ!
ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እሱና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ወደ መጌዶን በጀልባ ተሻገሩ። እዚያም ሲደርስ ፈሪሳውያንና አንዳንድ የሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ኢየሱስ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቅ ሊፈትኑት ሞከሩ።
ኢየሱስ ዓላማቸው ስለገባው እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሲመሽ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ ጠዋት ላይ ደግሞ ‘ሰማዩ ቢቀላም ደመና ስለሆነ ዛሬ ብርድ ይሆናል፣ ዝናብም ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን መልክ በማየት መተርጎም ትችላላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መተርጎም አትችሉም።” (ማቴዎስ 16:2, 3) ከዚያም ኢየሱስ ለፈሪሳውያንና ለሰዱቃውያን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት እንደማይሰጣቸው ነገራቸው።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፈሩና በባሕሩ ሰሜን ምሥራቅ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤተሳይዳ አቀኑ። መንገድ ላይ እያሉ ደቀ መዛሙርቱ በቂ ዳቦ እንዳልያዙ አስተዋሉ። የያዙት አንድ ዳቦ ብቻ ነው። በሌላ በኩል ኢየሱስ ከፈሪሳውያንና የሄሮድስ ደጋፊዎች ከሆኑ ሰዱቃውያን ጋር በቅርቡ ያደረገውን ውይይት በአእምሮው ይዞ “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጣቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ስለ እርሾ የተናገረው ዳቦ ስለረሱ መሰላቸው። ኢየሱስ እንደተሳሳቱ ስለገባው “ዳቦ ባለመያዛችሁ ለምን ትከራከራላችሁ?” አላቸው።—ማርቆስ 8:15-17
ኢየሱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ ብዙም አልቆየም። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ፣ ዳቦ አለመያዛቸው እንደማያሳስበው ማስተዋል ነበረባቸው። “አታስታውሱም? አምስቱን ዳቦ ለ5,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ ጊዜ ስንት ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ ሰበሰባችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። እነሱም “አሥራ ሁለት” አሉት። ኢየሱስ ቀጥሎም “ሰባቱን ዳቦ ለ4,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ ጊዜ ስንት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ አነሳችሁ?” አላቸው። እነሱም “ሰባት” አሉት።—ማርቆስ 8:18-20
ከዚያም ኢየሱስ “ታዲያ የነገርኳችሁ ስለ ዳቦ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም?” ብሎ ጠየቃቸው። አክሎም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አለ።—ማቴዎስ 16:11
በመጨረሻ ደቀ መዛሙርቱ ነጥቡን አስተዋሉ። እርሾ ሊጥ እንዲቦካና ዳቦ እንዲነፋ ለማድረግ ያገለግላል። ኢየሱስ እዚህ ላይ እርሾን የጠቀሰው ብክለትን ለማመልከት ነው። ደቀ መዛሙርቱ፣ በካይ ከሆነው ‘የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ትምህርት’ እንዲጠነቀቁ ማሳሰቡ ነው።—ማቴዎስ 16:12