ምዕራፍ 23
ጥምቀት—ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብ!
ኢየሱስ ክርስቲያኖች መጠመቅ እንዳለባቸው አስተምሯል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) ይሁንና ጥምቀት ምንድን ነው? በተጨማሪም አንድ ሰው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
1. ጥምቀት ምንድን ነው?
“መጠመቅ” የሚለው ቃል ውኃ ውስጥ “መጥለቅ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው። ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ከጠለቀ በኋላ “ከውኃው እንደወጣ” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማርቆስ 1:9, 10) በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠመቁት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመግባት ወይም በመጥለቅ ነው።
2. አንድ ሰው መጠመቁ ምን ያሳያል?
አንድ ሰው መጠመቁ ሕይወቱን ለይሖዋ አምላክ ለመስጠት እንደወሰነ ያሳያል። ግለሰቡ ይህን ውሳኔ የሚያደርገው እንዴት ነው? ከመጠመቁ በፊት በግሉ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እሱን ለዘላለም ማገልገል እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ይሖዋን ብቻ ለማምለክና በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ ለመስጠት ቃል ይገባል። ‘ራሱን ለመካድ’ እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርትና ምሳሌ ‘ያለማቋረጥ ለመከተል’ ይወስናል። (ማቴዎስ 16:24) ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠት መወሰኑና መጠመቁ ከይሖዋና ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለዋል።
3. አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ከመጠመቅህ በፊት ስለ ይሖዋ መማርና በእሱ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባት ይኖርብሃል። (ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።) እውቀትህና እምነትህ እያደገ ሲሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ስለ እሱ ለመስበክና እሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች ለመመራት እንድትነሳሳ ያደርግሃል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ 1 ዮሐንስ 5:3) አንድ ሰው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ መመላለስና እሱን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ሲችል ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠትና ለመጠመቅ መወሰኑ አይቀርም።—ቆላስይስ 1:9, 10a
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከኢየሱስ ጥምቀት ምን ትምህርት እንደምናገኝና አንድ ሰው ለዚህ ወሳኝ እርምጃ መዘጋጀት የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
4. ከኢየሱስ ጥምቀት ትምህርት ማግኘት እንችላለን
ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ይበልጥ ለማወቅ ማቴዎስ 3:13-17ን አንብቡ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ የተጠመቀው በሕፃንነቱ ነው?
የተጠመቀው እንዴት ነው? እንዲሁ ውኃ በመረጨት ነው?
ኢየሱስ በምድር ላይ አምላክ የሰጠውን ልዩ ተልእኮ ማከናወን የጀመረው ከተጠመቀ በኋላ ነው። ሉቃስ 3:21-23ን እና ዮሐንስ 6:38ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ለየትኛው ሥራ ነው?
5. ጥምቀት ሊደረስበት የሚችል ግብ ነው
ሕይወትህን ለአምላክ ስለ መወሰንና ስለ መጠመቅ ስታስብ መጀመሪያ ላይ ፍርሃት ሊያድርብህ ይችላል። ሆኖም ይሖዋን ይበልጥ እያወቅከው ስትሄድ ይህን ትልቅ ውሳኔ ለማድረግ ብቁ እንደሆንክ ይሰማሃል። ይህን ውሳኔ ያደረጉ ሰዎችን ተሞክሮ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ዮሐንስ 17:3ን እና ያዕቆብ 1:5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
አንድ ሰው ለመጠመቅ ብቁ እንዲሆን ምን ሊረዳው ይችላል?
ሀ. ለዘላለም ልናገለግለው እንደምንፈልግ ለይሖዋ በጸሎት በመንገር ሕይወታችንን ለእሱ ለመስጠት እንወስናለን
ለ. ስንጠመቅ ሕይወታችንን ለአምላክ ለመስጠት እንደወሰንን ለሌሎች እናሳያለን
6. ስንጠመቅ የይሖዋ ቤተሰብ አባል እንሆናለን
ስንጠመቅ አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አባል እንሆናለን። ያደግንበት ቦታ ወይም የኋላ ታሪካችን የተለያየ ቢሆንም የምናምንባቸው ነገሮችም ሆኑ የምንመራባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተመሳሳይ ናቸው። መዝሙር 25:14ን እና 1 ጴጥሮስ 2:17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ጥምቀት አንድ ሰው ከይሖዋ ጋርም ሆነ ከሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ለመጠመቅ ዝግጁ አይደለሁም።”
አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ያም ሆኖ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣርህ አስፈላጊ እንደሆነ ታምናለህ?
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ክርስቲያኖች መጠመቅ እንዳለባቸው አስተምሯል። አንድ ሰው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባት፣ በእሱ መሥፈርቶች መመራትና ሕይወቱን ለእሱ ለመስጠት መወሰን አለበት።
ክለሳ
ጥምቀት ምንድን ነው? መጠመቅ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
አንድ ሰው መጠመቁ ምን ያሳያል?
አንድ ሰው ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠት ከመወሰኑና ከመጠመቁ በፊት የትኞቹን ነገሮች ማድረግ አለበት?
ምርምር አድርግ
ጥምቀት ምንድን ነው? ብዙዎች ስለ ጥምቀት ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?
ለመጠመቅ የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው ለመጠመቅ የተነሳሳበትን ምክንያት አስመልክቶ ምን እንዳለ አንብብ።
“እውነቱ ምን እንደሆነ ራሴ እንዳረጋግጥ ፈልገው ነበር” (መጠበቂያ ግንብ የካቲት 1, 2013)
ጥምቀት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብ የሆነው ለምንድን ነው? እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ መዘጋጀት የምትችለውስ እንዴት ነው?
“መጠመቅ ይኖርብኝ ይሆን?” (ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 37)
a አንድ ሰው ከዚህ በፊት በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ተጠምቆ የነበረ ቢሆንም እንኳ እንደገና መጠመቅ ያስፈልገዋል። ለምን? ምክንያቱም ቀደም ሲል የተጠመቀበት ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አያስተምርም።—የሐዋርያት ሥራ 19:1-5ን እና ምዕራፍ 13ን ተመልከት።