ከሁሉ በሚሻለው የሕይወት መንገድ ላይ መጓዛችሁን ቀጥሉ!
“ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ ነን።”—ሮም 14:8
1. ኢየሱስ ከሁሉ ስለሚሻለው የሕይወት መንገድ ምን አስተምሯል?
ይሖዋ ከሁሉ በሚሻለው የሕይወት መንገድ ላይ እንድንጓዝ ይፈልጋል። ሰዎች የሚመርጧቸው የሕይወት ጎዳናዎች የተለያዩ ቢሆኑም ከሁሉ የተሻለው መንገድ አንድ ብቻ ነው። ከአምላክ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ከመኖርና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከመማር የተሻለ በሕይወታችን ውስጥ ልናደርገው የምንችለው አንዳች ነገር የለም። ኢየሱስ፣ አምላክን በመንፈስና በእውነት እንዲያመልኩት ተከታዮቹን ያስተማራቸው ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዮሐ. 4:24) ኢየሱስ ከሰጠው መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን መምራታችን ይሖዋን የሚያስደስተው ከመሆኑም ሌላ በረከቱን ያስገኝልናል።
2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሲሰሙ ምን እርምጃ ወሰዱ? “የጌታን መንገድ” መከተል ሲባል ምን ማለት ነው?
2 “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች አማኞች በመሆን ሲጠመቁ “ከሁሉ በሚሻለው የሕይወት መንገድ ላይ ለመጓዝ መምረጣችሁ በጣም አስደስቶናል!” እንድንላቸው የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። (ሥራ 13:48) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተለያዩ ብሔራት የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እውነትን የተቀበሉ ሲሆን ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በሕዝብ ፊት ለማሳየት ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:41) እነዚህ የጥንት ደቀ መዛሙርት “የጌታን መንገድ” የሚከተሉ ነበሩ። (ሥራ 9:2፤ 19:23) የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑት እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና ምሳሌውን በመከተል ላይ ያተኮረ አኗኗር ስለሚመሩ “የጌታን መንገድ” እንደሚከተሉ መገለጹ ተገቢ ነበር።—1 ጴጥ. 2:21
3. የይሖዋ ሕዝቦች የሚጠመቁት ለምንድን ነው? ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ሰዎች ተጠምቀዋል?
3 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ምሥራቹ እየተሰበከ ነው። ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከ2,700,000 የሚበልጡ ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ አቋም የወሰዱ ሲሆን ራሳቸውን ለእሱ መወሰናቸውን ለማሳየትም ተጠምቀዋል። ይህም ሲባል በየሳምንቱ በአማካይ ከ5,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው! እነዚህ ሰዎች ለመጠመቅ እንዲወስኑ መሠረት የሆናቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅር፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት ያገኙት እውቀትና በተማሩት ነገር ላይ ያዳበሩት እምነት ነው። ጥምቀት ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና የምንመሠርትበት ጊዜ በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት ወቅት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የጥንት አገልጋዮቹን በመንገዱ እንዲሄዱ እንደረዳቸው ሁሉ እኛም በታማኝነት እንድናገለግለው እንደሚረዳን ያለንን እምነት የሚያሳይ እርምጃ ነው።—ኢሳ. 30:21
መጠመቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
4, 5. መጠመቅ የሚያስገኛቸውን አንዳንድ በረከቶችና ጥቅሞች ጥቀስ።
4 ስለ አምላክ ከተማርክ በኋላ በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች አድርገህ በአሁኑ ጊዜ ያልተጠመቅህ አስፋፊ መሆን ችለህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት እድገት ማሳየትህ የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ ራስህን ለአምላክ መወሰንህን በጸሎት ነግረኸዋል? ለመጠመቅስ እያሰብክ ነው? ሕይወትህ ራስህን በማስደሰት ወይም ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ ሳይሆን ይሖዋን በማወደስ ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ሳትገነዘብ አልቀረህም። (መዝሙር 148:11-13ን አንብብ፤ ሉቃስ 12:15) ታዲያ መጠመቅ የሚያስገኛቸው አንዳንድ በረከቶችና ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
5 የተጠመቅህ ክርስቲያን ስትሆን ሕይወትህ የላቀ ዓላማ ይኖረዋል። የአምላክን ፈቃድ ስለምታደርግ ደስተኛ ትሆናለህ። (ሮም 12:1, 2) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደ ሰላምና እምነት ያሉ አምላካዊ ባሕርያትን እንድታፈራ ያስችልሃል። (ገላ. 5:22, 23) አምላክ ጸሎትህን የሚሰማልህ ከመሆኑም ሌላ ሕይወትህን ከእሱ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመምራት የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል። አገልግሎትህ አስደሳች ይሆንልሃል፤ እንዲሁም አምላክ በሚፈልገው መንገድ መመላለስህ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋህን ያጠናክርልሃል። ከዚህም ሌላ ራስህን ለአምላክ መወሰንህና መጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ከልብህ እንደምትፈልግ ያሳያል።—ኢሳ. 43:10-12
6. መጠመቃችን ምን ያሳያል?
6 ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ስንጠመቅ የይሖዋ መሆናችንን በሕዝብ ፊት እናሳያለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንዲያውም ከመካከላችን ለራሱ ብቻ ብሎ የሚኖር የለም፤ ለራሱ ብቻ ብሎም የሚሞት የለም” ሲል ጽፏል። “ምክንያቱም ብንኖር የምንኖረው ለይሖዋ ነው፤ ብንሞትም የምንሞተው ለይሖዋ ነው። ስለዚህ ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ ነን።” (ሮም 14:7, 8) አምላክ ነፃ ምርጫ በመስጠት አክብሮናል። ለአምላክ ካለን ፍቅር የተነሳ እንዲህ ያለውን የሕይወት መንገድ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ስናደርግ ልቡን ደስ እናሰኛለን። (ምሳሌ 27:11) ጥምቀት ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን የሚያሳይ ምልክት ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ገዥያችን እንዲሆን መምረጣችንን ለሕዝብ ይፋ የምናደርግበት እርምጃ ነው። መጠመቃችን በይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ላይ ከተነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከእሱ ጎን ለመቆም አቋም እንደወሰድን የሚያሳይ ነው። (ሥራ 5:29, 32) እኛ እንዲህ ስናደርግ ይሖዋም ከእኛ ጋር ይሆናል። (መዝሙር 118:6ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ጥምቀት አሁንም ሆነ ወደፊት በርካታ መንፈሳዊ በረከቶችን እንድናጭድ መንገድ ይከፍታል።
አፍቃሪ በሆነ የወንድማማች ማኅበር መታቀፍ
7-9. (ሀ) ኢየሱስ ሁሉን ትተው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል? (ለ) በማርቆስ 10:29, 30 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የገባው ቃል እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
7 ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” ብሎት ነበር። (ማቴ. 19:27) ጴጥሮስ እሱም ሆነ ሌሎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደፊት ምን እንደሚያገኙ ለማወቅ ፈልጎ ነበር። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለመስጠት ሲሉ ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። (ማቴ. 4:18-22) ታዲያ ኢየሱስ ምን ማረጋገጫ ሰጣቸው?
8 ማርቆስ በጻፈው ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ የሆነ የወንድማማች ማኅበር አባል እንደሚሆኑ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን ትቶ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን መቶ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት የማያገኝ ማንም የለም።” (ማር. 10:29, 30) ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ለእምነት ባልንጀሮቻቸው “ቤቶችን” ከሰጡ እንዲሁም ‘ወንድም፣ እህትና እናት’ ከሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች መካከል ሊዲያ፣ አቂላ፣ ጵርስቅላ እና ጋይዮስ ይገኙበታል።—ሥራ 16:14, 15፤ 18:2-4፤ 3 ዮሐ. 1, 5-8
9 ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ተከታዮቹ የሚተዉት “እርሻ” ሚስዮናውያንን፣ የቤቴል ቤተሰብ አባላትንና ዓለም አቀፍ አገልጋዮችን ጨምሮ ሌሎች ብዙዎች በተለያዩ አገሮች የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስፋፋት ሲሉ በፈቃዳቸው የሚተዉትን መተዳደሪያ ያመለክታል። በርካታ ወንድሞችና እህቶች ቀላል ሕይወት ለመምራት ሲሉ ‘ቤታቸውን’ ትተዋል፤ ይሖዋ እነዚህን ወንድሞችና እህቶች እንዴት እንደተንከባከባቸውና እሱን ማገልገላቸው ምን ያህል ደስታ እንዳስገኘላቸው ስንሰማ እንደሰታለን። (ሥራ 20:35) ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር አባል እንደመሆናቸው መጠን ‘አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋቸው’ ከሚያስገኘው በረከት ይቋደሳሉ።—ማቴ. 6:33
“በልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ” ተጠብቆ መኖር
10, 11. ‘የልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ’ ምንድን ነው? በዚህ ቦታ የመኖር መብት ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?
10 ራስን መወሰንና ጥምቀት ሌላም ታላቅ በረከት ይኸውም “በልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ” የመኖር መብት ያስገኛል። (መዝሙር 91:1ን በNW አንብብ።a) ጥበቃና ደኅንነት የሚገኝበት ይህ ምሳሌያዊ ቦታ ከመንፈሳዊ ጉዳት ከለላ የምናገኝበትን ሁኔታ ያመለክታል። ቦታው “ሚስጥራዊ” የተባለው መንፈሳዊ እይታ የሌላቸውና በአምላክ የማይተማመኑ ሰዎች የማያውቁት በመሆኑ ነው። ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን የምንኖርና በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት የምናሳድር ከሆነ ይሖዋን “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” የምንለው ያህል ነው። (መዝ. 91:2) ይሖዋ አምላክ አስተማማኝ መጠጊያ ይሆንልናል። (መዝ. 91:9) ታዲያ ከዚህ የበለጠ ምን ያስፈልገናል?
11 በይሖዋ “ሚስጥራዊ ቦታ” መኖር መቻላችን ከእሱ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረት መብት በማግኘት መባረካችንንም ያመለክታል። አንድ ሰው በይሖዋ ሚስጥራዊ ቦታ መኖር የሚጀምረው ራሱን ወስኖ ሲጠመቅ ነው። ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብና ለእሱ ሙሉ በሙሉ ታዛዥ በመሆን ወደ እሱ ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን፤ በዚህ መንገድ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና እናጠናክረዋለን። (ያዕ. 4:8) ከኢየሱስ ይበልጥ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ያለው ማንም የለም፤ ኢየሱስ በፈጣሪ ላይ ያለው እምነት ፈጽሞ ተናውጦ አያውቅም። (ዮሐ. 8:29) እኛም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ልንታመን ይገባል፤ እንዲሁም ራሳችንን ለእሱ ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችለንን እርዳታ ለመስጠት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም። (መክ. 5:4) አምላክ ለሕዝቦቹ ያቀረበው መንፈሳዊ ዝግጅት ከልብ እንደሚወደንና እሱን በማገልገል ረገድ ስኬታማ እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነው።
መንፈሳዊ ገነታችንን እንደ ውድ አድርጎ መመልከት
12, 13. (ሀ) መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው? (ለ) አዳዲሶችን እንዴት መርዳት እንችላለን?
12 ራስን መወሰንና ጥምቀት በረከት በሞላበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የመኖር መብት እንድናገኝም መንገድ ይከፍትልናል። ይህ መንፈሳዊ ገነት ከይሖዋ አምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ሰላማዊ ግንኙነት ካላቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን የምንኖርበት ልዩ መንፈሳዊ ሁኔታ ነው። (መዝ. 29:11፤ ኢሳ. 54:13) ዓለም እኛ ካለንበት መንፈሳዊ ገነት ጋር በትንሹ እንኳ ሊቀራረብ የሚችል ምንም ነገር የለውም። ይህ በተለይ በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በግልጽ ይታያል፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከብዙ አገሮች የመጡ እንዲሁም የተለያየ ቋንቋና ዘር ያላቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሰላም፣ አንድነትና የወንድማማች ፍቅር በሰፈነበት ሁኔታ አብረው ሲሆኑ ይታያሉ።
13 እኛ ያለንበት መንፈሳዊ ገነት በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ከሚታየው አስከፊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ይበልጥ ፍንትው ብሎ ይታያል። (ኢሳይያስ 65:13, 14ን አንብብ።) የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ ሌሎችም ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት እንዲገቡ የመጋበዝ መብት አለን። በቅርቡ የጉባኤው አባል የሆኑትንና በአገልግሎት ላይ ሥልጠና የሚያስፈልጋቸውን አስፋፊዎች መርዳት መቻልም ሌላ በረከት ነው። አቂላና ጵርስቅላ ለአጵሎስ “የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል [እንዳብራሩለት]” ሁሉ እኛም ከሽማግሌዎች በምናገኘው መመሪያ መሠረት አዳዲስ የሆኑ አንዳንዶችን የምንረዳ ከሆነ ልንባረክ እንችላለን።—ሥራ 18:24-26
ከኢየሱስ መማራችሁን ቀጥሉ
14, 15. ከኢየሱስ መማራችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሱን ምን ግሩም ምክንያቶች አሉን?
14 ከኢየሱስ መማራችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሱን ግሩም ምክንያቶች አሉን። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር ሠርቷል። (ምሳሌ 8:22, 30) ኢየሱስ ከሁሉ የሚሻለው የሕይወት መንገድ ይሖዋን በማገልገልና ለእውነት በመመሥከር ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 18:37) የአምላክ ልጅ ሌላ ዓይነት የሕይወት መንገድ መከተል ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበትና አርቆ ማስተዋል የጎደለው አካሄድ እንደሆነ አሳምሮ ያውቅ ነበር። ከባድ ፈተና እንደሚደርስበትና እንደሚሞት ተረድቶ ነበር። (ማቴ. 20:18, 19፤ ዕብ. 4:15) ኢየሱስ አርዓያችን እንደመሆኑ መጠን ታማኝነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮናል።
15 ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ፣ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ እንዲተው ከሰይጣን ፈተና ቀርቦለት ነበር፤ ሆኖም ሰይጣን አልተሳካለትም። (ማቴ. 4:1-11) ሰይጣን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያመጣብን ታማኝነታችንን መጠበቅ እንደምንችል ከዚህ ሁኔታ መማር እንችላለን። ሰይጣን ይበልጥ ትኩረት የሚያደርገው ሊጠመቁ ባሰቡ ወይም በቅርቡ በተጠመቁ ክርስቲያኖች ላይ ነው። (1 ጴጥ. 5:8) ከልብ የሚያስቡልን ሆኖም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ መረጃ ያላቸው የቤተሰባችን አባላት ተቃውሞ ያደርሱብን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያሉት ፈተናዎች፣ ጥያቄዎችን ስንመልስና ምሥክርነት ስንሰጥ እንደ አክብሮትና ዘዴኛነት ያሉ ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናሳይ አጋጣሚ ይፈጥሩልናል። (1 ጴጥ. 3:15) በመሆኑም እነዚህ አጋጣሚዎች በሚሰሙን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።—1 ጢሞ. 4:16
ከሁሉ ከተሻለው የሕይወት መንገድ ዝንፍ አትበሉ!
16, 17. (ሀ) በዘዳግም 30:19, 20 ላይ የተጠቀሱት ሕይወት ለማግኘት የሚያስችሉ ሦስት መሠረታዊ ብቃቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ሙሴ የጻፈውን ሐሳብ ኢየሱስ፣ ዮሐንስና ጳውሎስ የደገፉት እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ1,500 ዓመታት በፊት ሙሴ እስራኤላውያንን ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ እንዲመርጡ አሳስቧቸው ነበር። እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው።” (ዘዳ. 30:19, 20) እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ ይሁን እንጂ ሙሴ የጠቀሳቸው ሕይወት ለማግኘት የሚያስፈልጉት ሦስት መሠረታዊ ብቃቶች አልተለወጡም። ኢየሱስና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም እነዚህን ብቃቶች ጠቅሰዋቸዋል።
17 አንደኛ፣ ‘አምላካችን ይሖዋን መውደድ ይኖርብናል።’ ከጽድቅ መንገዶቹ ጋር ተስማምተን በመኖር አምላክን እንደምንወድ እናሳያለን። (ማቴ. 22:37) ሁለተኛ፣ የአምላክን ቃል በማጥናትና ትእዛዛቱን በማክበር ‘የይሖዋን ቃል ማድመጥ ይኖርብናል።’ (1 ዮሐ. 5:3) ይህንንም ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በሚደረግባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘት ያስፈልገናል። (ዕብ. 10:23-25) ሦስተኛ፣ ‘ከይሖዋ ጋር መጣበቅ ይገባናል።’ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ምንጊዜም በአምላክ ላይ እምነት እናሳድር፤ እንዲሁም ልጁን እንከተል።—2 ቆሮ. 4:16-18
18. (ሀ) መጠበቂያ ግንብ በ1914 ስለነበረው እውነት ምን ብሎ ነበር? (ለ) አሁን ስላገኘነው የእውነት ብርሃን ምን ሊሰማን ይገባል?
18 ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምቶ መኖር ምንኛ ታላቅ በረከት ነው! በ1914 የሚከተለው ጠቃሚ ሐሳብ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሰፍሮ ነበር፦ “በእርግጥም የተባረከና ደስተኛ የሆነ ሕዝብ አይደለንም? አምላካችን ይሖዋ ታማኝ አምላክ አይደለም? ከዚህ የተሻለ ነገር ያገኘ ሰው ካለ ያገኘውን ይከተል። ማናችሁም የተሻለ ነገር ካገኛችሁ ያገኛችሁትን እንደምትነግሩን ተስፋ እናደርጋለን። እኛ ግን ከአምላክ ቃል ካገኘነው እውቀት የተሻለም ሆነ ከዚህ ጋር በትንሹ እንኳ ሊወዳደር የሚችል ነገር ጨርሶ አላገኘንም። . . . እውነተኛውን አምላክ በትክክል ማወቃችን በሕይወታችን ውስጥ ያስገኘልንን ደስታ፣ ሰላምና በረከት ሙሉ በሙሉ ሊገልጽ የሚችል ብዕር ወይም አንደበት የለንም። ስለ አምላክ ጥበብ፣ ፍትሕ፣ ኃይልና ፍቅር ያገኘነው እውቀት የአእምሯችንንም ሆነ የልባችንን ጥማት ያረካልናል። ከዚህ የበለጠ ነገር አንፈልግም። ስለ አምላክ ያገኘነውን ይህን አስደናቂ እውቀት እያሳደግን ከመሄድ የበለጠ የምንፈልገው ነገር የለም።” (መጠበቂያ ግንብ ታኅሣሥ 15, 1914 ከገጽ 377-378) ላገኘነው መንፈሳዊ ብርሃንና እውነት ያለን አድናቆት አሁንም አልተለወጠም። በእርግጥም ‘በይሖዋ ብርሃን እየተመላለስን’ በመሆኑ ደስተኞች እንድንሆን የሚያነሳሳን የላቀ ምክንያት አለን።—ኢሳ. 2:5፤ መዝ. 43:3፤ ምሳሌ 4:18
19. ለመጠመቅ ብቁ የሆኑ ሁሉ ይህንን እርምጃ ለመውሰድ መዘግየት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
19 ‘በይሖዋ ብርሃን መመላለስ’ የምትፈልግ ቢሆንም ራስህን ወስነህ የተጠመቅክ ክርስቲያን ካልሆንክ እርምጃ ከመውሰድ አትዘግይ። ለመጠመቅ የሚያስችሉህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ለማሟላት የሚያስፈልጉህን ነገሮች በሙሉ አድርግ፤ ጥምቀት አምላክና ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር አድናቆታችንን የምናሳይበት ልዩ መንገድ ነው። ከሁሉ የላቀውን ንብረትህን ይኸውም ሕይወትህን ለይሖዋ ስጠው። ልጁን በመከተል የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደምትፈልግ አሳይ። (2 ቆሮ. 5:14, 15) ይህ ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም!
[የግርጌ ማስታወሻ]
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መጠመቃችን ምን ያሳያል?
• ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ምን በረከት ያስገኛል?
• ከኢየሱስ መማራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ከሁሉ ከተሻለው የሕይወት መንገድ ዝንፍ ሳንል ለመቀጠል ምን ይረዳናል?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጠመቅህ ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ እንደመረጥህ ያሳያል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ” ተጠብቀህ እየኖርክ ነው?