አምላክን እንድታገለግሉ የሚገፋፋችሁ ምንድን ነው?
“አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን ውደድ።”—ማርቆስ 12:30
1, 2. ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ መልኩ ምን አስደሳች ነገሮች እየተከናወኑ ናቸው?
የአንድ መኪና ትክክለኛ ዋጋ በውጫዊ መልኩ ብቻ አይወሰንም። የቀለም ቅቡ ውጪያዊ መልኩን ይበልጥ ማራኪ ሊያደርገውና ምርጥ ሞዴሉ ገዢን ሊስብ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት፣ ከውጭ በቀላሉ የማይታዩት ነገሮች ማለትም መኪናውን የሚያንቀሳቅሰው ሞተርና መኪናውን የሚቆጣጠሩት ሌሎች መሣሪያዎች ናቸው።
2 አንድ ክርስቲያን ለአምላክ የሚያቀርበው አገልግሎትም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። የይሖዋ ምሥክሮች አምላካዊ ሥራዎች የበዙላቸው ናቸው። በየዓመቱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበኩ ሥራ ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ ይውላል። ከዚህም በላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ፤ በተጨማሪም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጠመቁ ነው። አንተም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ከሆንክ አነስተኛ ቢመስልም እንኳ ለዚህ አስደሳች አሃዝ አንድ ዓይነት አስተዋጽኦ አበርክተሃል። በተጨማሪም ‘አምላክ ሥራህንና ለስሙ ያሳየኸውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳልሆነ’ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።—ዕብራውያን 6:10
3. ከሥራ በተጨማሪ ክርስቲያኖችን ሊያሳስባቸው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
3 ይሁን እንጂ በቡድንም ሆነ በግል የምናቀርበው አገልግሎት ትክክለኛ ዋጋ በአሃዝ ብዛት ብቻ አይለካም። ለሳሙኤል እንደተነገረው “ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) አዎን፣ በአምላክ ፊት ዋጋ ያለው ውስጣዊ ማንነታችን ነው። ሥራ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እሙን ነው። ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ሥራዎች የይሖዋን ትምህርት ከማስመስገናቸውም በላይ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ይስባሉ። (ማቴዎስ 5:14–16፤ ቲቶ 2:10፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) ሆኖም ሥራዎቻችን ጠቅላላውን ሁኔታ አይገልጹም። በኤፌሶን ይገኝ የነበረው ጉባኤ መልካም ሥራዎችን ያስመዘገበ ቢሆንም ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ያሳሰበው ጉዳይ ነበረ። ለጉባኤው “ሥራህን . . . አውቃለሁ። ዳሩ ግን የምነቅፍብህ አንድ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና” ሲል ተናገረ።—ራእይ 2:1–4
4. (ሀ) ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ማድረግ ስላለብን ብቻ በዘልማድ የምንፈጽመው ተግባር ሊሆንብን የሚችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ራስን መመርመር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 አንድ አደጋ አለ። ለረጅም ጊዜያት ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ማድረግ ስላለብን ብቻ እንዲሁ በዘልማድ የምናከናውነው ነገር ሊሆንብን ይችላል። አንዲት ክርስቲያን እህት የነበረችበትን ሁኔታ በሚከተለው መንገድ ገልጻለች፦ “ወደ አገልግሎት እወጣለሁ፣ ወደ ስብሰባዎች እሄዳለሁ፣ አጠናለሁ፣ እጸልያለሁ፤ ሁሉንም የማደርገው ግን ምንም ስሜት ሳይኖረኝ እንዲሁ በደመ ነፍስ ነበር።” እርግጥ፣ የአምላክ አገልጋዮች ‘እንደተጣሉ’ ወይም ‘ቅስማቸው እንደተሰበረ’ ቢሰማቸውም እንኳ የሚችሉትን ያህል ለማድረግ መጣራቸው ያስመሰግናቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:9፤ 7:6) ሆኖም ክርስቲያናዊ ልማዳችን አሰልቺ ከሆነብን ምሳሌያዊ ሞተሩን በጥንቃቄ መመርመር አለብን። በጣም ጥሩ ናቸው የሚባሉ መኪናዎች እንኳ በየጊዜው ጥገና ያስፈልጋቸዋል፤ በተመሳሳይም ሁሉም ክርስቲያኖች ዘወትር ራሳቸውን መመርመር ያስፈልጋቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ሌሎች ሥራችንን ሊመለከቱ ቢችሉም እንድንሠራ የሚገፋፋን ምን እንደሆነ ሊያውቁ አይችሉም። ስለዚህ እያንዳንዳችን ‘አምላክን እንዳገለግል የሚገፋፋኝ ምንድን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ በጥሞና ልናስብበት ይገባል።
ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት እንዳይኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶች
5. ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው ብሏል?
5 ኢየሱስ ለእስራኤላውያን ከተሰጧቸው ሕጎች ሁሉ የትኛው ሕግ እንደሚበልጥ ሲጠየቅ “አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” በማለት በውጫዊ መልክ ላይ ሳይሆን በውስጣዊ ግፊት ላይ የሚያተኩር አንድ ትእዛዝ ጠቀሰ። (ማርቆስ 12:28–30) ኢየሱስ በዚህ መንገድ አምላክን እንድናገለግል የሚገፋፋን ኃይል ፍቅር መሆን እንዳለበት ለይቶ አመልክቷል።
6, 7. (ሀ) ሰይጣን የቤተሰብ ክልልን በተንኮል የሚያጠቃው በምን መንገድ ነው? ለምንስ? (2 ቆሮንቶስ 2:11) (ለ) አስተዳደግ አንድ ሰው ለመለኮታዊ ሥልጣን የሚኖረውን አመለካከት ሊነካበት የሚችለው እንዴት ነው?
6 ሰይጣን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የፍቅርን ባሕርይ የመኮትኮት ችሎታችንን ለመግታት ይፈልጋል። ይህን ዓላማ ለማሳካት የሚጠቀምበት አንዱ ዘዴ በቤተሰብ ክልል ላይ ጥቃት ማድረስ ነው። ለምን? ምክንያቱም ፍቅር ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጣችን የሚቀረጸውና ዘላቂ መሠረቱ የሚጣለው በቤተሰብ ውስጥ ስለሆነ ነው። ሰይጣን በልጅነት የተማሩት ነገር በጉልምስና ወቅት ሊጠቅም እንደሚችል የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጠንቅቆ ያውቃል። (ምሳሌ 22:6) በልጅነታችን ስለ ፍቅር እንዳናውቅ ለማድረግ በተንኮል ይጥራል። ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ብዙዎች ፍቅር በሰፈነበት ሳይሆን የመረረ ጠብ፣ ንዴትና ስድብ በሞላባቸው ቤተሰቦች ውስጥ እንዲያድጉ በማድረግ ዓላማውን ያሳካል።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 4:31, 32፤ 6:4 የግርጌ ማስታወሻ፤ ቆላስይስ 3:21
7 የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የተባለው መጽሐፍ አንድ አባት የወላጅነት ኃላፊነቱን የሚያከናውንበት መንገድ “ልጆቹ ካደጉ በኋላ ለመለኮታዊም ሆነ ለሰብዓዊ ሥልጣን የሚኖራቸውን አመለካከት በጣም ይነካዋል” የሚል አስተያየት ይሰጣል።a አንድ ከመጠን በላይ ቁጥጥር የሚያበዛ ኃይለኛ አባት ያሳደገው ክርስቲያን “ይሖዋን መታዘዝ ለእኔ ቀላል ነው፤ እሱን መውደድ ግን በጣም ይከብደኛል” ብሏል። እርግጥ በአምላክ አመለካከት “መታዘዝ ከመሥዋዕት” የሚበልጥ ስለሆነ ታዛዥነት በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ሳሙኤል 15:22) ይሁን እንጂ እንዲያው ታዛዥ ከመሆን የበለጠ እንድናደርግና ይሖዋን እንድናመልክ የሚገፋፋንን ፍቅር ለመኮትኮት ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
“የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል”
8, 9. የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖረን ሊገፋፋን የሚገባው እንዴት ነው?
8 ይሖዋን በሙሉ ልባችን እንድንወደው የሚያስችለንን ፍቅር እንድንኮተኩት የሚያንቀሳቅሰን ከሁሉ የበለጠው ነገር ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለን አድናቆት ነው። “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።” (1 ዮሐንስ 4:9) አንዴ ይህን የፍቅር መግለጫ ከተገነዘብንና ካደነቅን ይህ ድርጊት እኛም በበኩላችን ፍቅር እንድናሳይ ይገፋፋናል። “[ይሖዋ] አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።”—1 ዮሐንስ 4:19
9 ኢየሱስ የሰውን ዘር እንዲያድን የተሰጠውን ሥራ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። “እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል።” (1 ዮሐንስ 3:16፤ ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዕዋት በማድረግ መንፈስ ያሳየው ፍቅር በአድናቆት አጸፋውን እንድንመልስ ሊገፋፋን ይገባል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በውኃ ከመስጠም ድነሃል እንበል። የተደረገልህን ሁሉ ረስተህ ዝም ብለህ ሰውነትህን አደራርቀህ ወደ ቤት ትሄዳለህን? በጭራሽ አታደርገውም! ላዳነህ ሰው ትልቅ ውለታ እንዳለብህ ይሰማሃል። እንዲያውም ያ ሕይወትህን ያዳነልህ ሰው ምን ጊዜም የማትረሳው ትልቅ ባለውለታህ ነው። ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ የዋሉልን ውለታ ከዚህ ያነሰ ነውን? ቤዛው ባይኖር ኖሮ ሁላቸንም በምሳሌያዊ አባባል በኃጢአትና በሞት ውስጥ እንሰጥም ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለእኛ ካሳየው ከዚህ ታላቅ ፍቅር የተነሣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን።—ሮሜ 5:12, 18፤ 1 ጴጥሮስ 2:24
10. (ሀ) ቤዛው የግል ሕይወታችንን እንዲነካ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የክርስቶስ ፍቅር ግድ የሚለን እንዴት ነው?
10 በቤዛው ላይ አሰላስል። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ያህል ቤዛው የአንተንም ሕይወት የሚነካ ይሁን፦ “አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” (ገላትያ 2:20) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ . . . በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ” በማለት ስለጻፈ እንደዚህ ያለው ማሰላስል በውስጣችን ልባዊ የሆነ ግፊት እንዲቀጣጠል ያደርጋል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ዘ ጀሩሳሌም ባይብል የክርስቶስ ፍቅር “በውስጣችን ኃይለኛ ግፊት ያሳድርብናል” ይላል። ስለ ክርስቶስ ፍቅር ስናስብ አንድ ነገር ለማድረግ እንገፋፋለን፣ በጥልቅ እንነካለን እንዲያውም በውስጣችን ኃይለኛ ግፊት ያሳድርብናል። ፍቅሩ ልባችንን ይነካውና ለተግባር ያንቀሳቅሰናል። የጄ ቢ ፊሊፕስ ትርጉም በቀላል አነጋገር እንዳቀረበው “ለተግባር የሚያነሳሳን የክርስቶስ ፍቅር ነው።” በፈሪሳውያን ላይ እንደታየው ሌላ ማንኛውም ዓይነት ግፊት ዘላቂ ውጤት አያስገኝም።
‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ’
11. ፈሪሳውያን ለሃይማኖታዊ ሥራዎች የነበራቸውን አመለካከት ግለጽ።
11 ፈሪሳውያን የአምላክን አምልኮ ትርጉም አሳጥተውት ነበር። ሰዎች ለአምላከ ፍቅር እንዲኖራቸው ከማበረታታት ይልቅ ሥራን የመንፈሳዊነት መለኪያ አድርገው ያጎሉ ነበር። ብዛት ባላቸው ዝርዝር ሕጎች መጠመዳቸው ከውጪ ጻድቅ እንዲመስሉ ቢያደርጋቸውም በውስጣቸው ግን “የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ” ነበሩ።—ማቴዎስ 23:27
12. ኢየሱስ አንድን ሰው ከፈወሰ በኋላ ፈሪሳውያን ልባቸው የደነዘዘ መሆኑን ያሳዩት እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ በአንድ ወቅት እጁ የሰለለበትን አንድ ሰው በርኅራኄ ፈውሶ ነበር። ይህ ሰው ያለ ጥርጥር አካላዊና ስሜታዊ ችግር ፈጥሮበት ከነበረው ሕመም ሲፈወስ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ሆኖም ፈሪሳውያን ከእሱ ጋር አልተደሰቱም። እንዲያውም ፈውሱ የተከናወነበትን ሁኔታ ማለትም ኢየሱስ በሰንበት እርዳታ ማበርከቱን ነቀፉ። ፈሪሳውያን የሕጉን ፊደል በመተርጎማቸው የሕጉን እውነተኛ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ሳይረዱ ቀሩ። ኢየሱስ ‘ስለ ልባቸው ድንዛዜ ማዘኑ’ አያስደንቅም! (ማርቆስ 3:1–5) ከዚህም በላይ ደቀ መዛሙርቱን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” ሲል መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 16:6) ፈሪሳውያን ያደረጓቸው ነገሮችና የነበሯቸው ዝንባሌዎች ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍረዋል።
13. የፈሪሳውያን ሁኔታ ለእኛ ምን ትምህርት ይሆነናል?
13 የፈሪሳውያን ሁኔታ ሥራን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ያስተምረናል። እርግጥ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ” ስለሆነ ሥራ አስፈላጊ ነው። (ያዕቆብ 2:26) ይሁን እንጂ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሌሎች ሰዎችን በማንነታቸው ሳይሆን በሚያደርጉት ነገር የመፍረድ ዝንባሌ አላቸው። አንዳንድ ጊዜ በራሳችን ላይም እንኳ በዚህ መንገድ ልንፈርድ እንችላለን። ሥራ የመንፈሳዊነት ብቸኛ መለኪያ የሆነ ይመስል በኃይል ያሳስበን ይሆናል። ዝንባሌያችንን የመመርመርን አስፈላጊነት ልንዘነጋ እንችላለን። (ከ2 ቆሮንቶስ 5:12 ጋር አወዳድር።) የሕጉን ፊደል በመታዘዝ ዋና ዓላማውን ግን ቸል ብለን ‘ትንኝን የምናጠራና ግመልን የምንውጥ’ መሆን የለብንም፤ እንዲህ ካደረግን ድርቅ ብለን ሕግ የምንከተል ሰዎች ልንሆን እንችላለን።—ማቴዎስ 23:24
14. ፈሪሳውያን እንደ ቆሻሻ ጽዋ ወይም ወጭት ሆነው የነበሩት እንዴት ነው?
14 ፈሪሳውያን ያላስተዋሉት ነገር አንድ ሰው ከልቡ ይሖዋን የሚወድ ከሆነ ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚገልጹ ሥራዎች የሚያደርግ መሆኑን ነው። መንፈሳዊነት ከውስጥ ወደ ውጪ ይፈሳል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተሳሳተ አስተሳሰብ የነበራቸውን ፈሪሳውያንን እንዲህ በማለት አውግዟቸው ነበር፦ “እናንት ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጪ ስለምታጠሩ፣ ወዮላቸሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ ውጪው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።”—ማቴዎስ 23:25, 26
15. ኢየሱስ ከውጪያዊ መልክ የበለጠ ነገርን እንደሚመለከት የሚጠቁሙ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
15 የአንድ ጽዋ ወይም ወጭት ሌላው ቀርቶ የአንድ ሕንፃ ውጫዊ መልክ እንኳ ሁሉንም ነገር አይገልጽም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በውስጡ ይደረግ በነበረው ነገር ምክንያት “የወንበዴዎች ዋሻ” ብሎ በጠራው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውበት ተደንቀው ነበር። (ማርቆስ 11:17፤ 13:1) በቤተ መቅደሱ ላይ የሆነው ነገር ክርስቲያን ነን በሚሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ መፈጸሙን የሕዝበ ክርስትና መዝገብ ያሳያል። ኢየሱስ በስሙ “ተአምራት” የሚያደርጉ ሰዎችን “ዓመፀኞች” እንደሚላቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:22, 23) ከዚህ ጋር ሙሉ በሙሉ በሚጻረር መንገድ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በጣም አነስተኛ የሆነ ገንዘብ ያኖረችን አንዲት መበለት “ይህች ደሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ . . . ከጉድለቷ የነበራትን ሁሉ ትዳሯን ሁሉ ጣለች” ብሏታል። (ማርቆስ 12:41–44) ይህ ፍርደ ገምድልነት ነውን? በጭራሽ አይደለም። ኢየሱስ በሁለቱም ሁኔታዎች የይሖዋን አመለካከት አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 8:16) ከሥራዎቹ በስተጀርባ ያሉትን ግፊቶች ተመለከተና በዚያው መሠረት ፈረደ።
“ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ”
16. እንቅስቃሴያችንን ሁልጊዜ ከሌላ ክርስቲያን የአገልግሎት እንቅስቃሴ ጋር ማወዳደር የሌለብን ለምንድን ነው?
16 ጤናማ ዝንባሌ ካለን ሁልጊዜ ራሳችንን ከሌሎች ጋር አናነጻጽርም። ለምሳሌ ያህል፣ ሌላ ክርስቲያን በአገልግሎት የሚያሳልፈውን ሰዓት ያህል ላሳልፍ ወይም ከእሱ እኩል ልሥራ በማለት መፎካከር ምንም አጠቅምም። ኢየሱስ ይሖዋን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹም ነፍስህና በፍጹም ኃይልህ ውደድ ያለው አንተን እንጂ ሌላን ሰው አይደለም። የእያንዳንዱ ሰው ችሎታ፣ ጥንካሬና ሁኔታ ይለያያል። ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ፍቅር በአገልግሎት ብዙ ጊዜ እንድታሳልፍ ምናልባትም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ማለትም አቅኚ እንድትሆን ይገፋፋሃል። ሆኖም ከበሽታ ጋር እየታገልክ ከሆነ በአገልግሎት የምታሳልፈው ሰዓት ከምትፈልገው ያነሰ ሊሆን ይችላል። ተስፋ አትቁረጥ። ለአምላክ ያለን ታማኝነት በአገልግሎት በምናሳልፈው ሰዓት አለካም። ትክክለኛ ዝንባሌ በመያዝ ልትደሰት ትችላለህ። ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል” ሲል ጻፈ።—ገላትያ 6:4
17. የመክሊቶቹን ምሳሌ በራስህ አባባል በአጭሩ ግለጽ።
17 በማቴዎስ 25:14–30 ላይ የተመዘገበውን ስለ መክሊቶቹ የሚናገረውን የኢየሱስ ምሳሌ ተመልከት። አንድ ወደ ሩቅ አገር የሚሄድ ሰው ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን አከፋፈላቸው። “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፣ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠ።” ጌታው ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ለመተሳሰብ ሲመጣ ምን አገኘ? አምስት መክሊቶች የተሰጠው ባሪያ ሌሎች አምስት መክሊቶችን አተረፈ። በተመሳሳይም ሁለት መክሊቶች የተሰጠው ባሪያ ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አተረፈ። አንድ መክሊት የተሰጠው ባሪያ መክሊቱን ቀበረው፤ የጌታውን ሀብት ከፍ ለማድረግ ምንም ያደረገው ነገር አልነበረም። ጌታው ሁኔታውን የተመለከተው እንዴት ነው?
18, 19. (ሀ) ጌታው ሁለት መክሊቶች የሰጠውን ባሪያ አምስት መክሊቶችን ከሰጠው ባሪያ ጋር ያላወዳደረው ለምንድን ነው? (ለ) የመክሊቶቹ ምሳሌ ስለ ማመስገንና ራሳችንን ከሌሎች ጋር ስለ ማወዳደር ምን ያስተምረናል? (ሐ) ሦስተኛው ባሪያ የተፈረደበት ለምንድን ነው?
18 በመጀመሪያ ደረጃ አምስት መክሊቶችና ሁለት መክሊቶች ተሰጥቷቸው የነበሩትን ባሪያዎች በየተራ እንመልከት። ሁለቱንም ባሪያዎች ጌታቸው “አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ!” ብሏቸዋል። አምስት መክሊቶች የተሰጠው ባሪያ ሁለት መክሊቶች ብቻ ቢያተርፍ ኖሮ ይህን ይለው ነበር? ሊለው አይችልም! በሌላ በኩል ደግሞ ሁለት መክሊቶችን ያተረፈውን ባሪያ ‘አምስት መክሊቶችን ለምን አላተረፍክም? ይህ ባሪያ ምን ያህል እንዳተረፈልኝ ትመለከታለህ!’ አላለውም። አዎን፣ በኢየሱስ የተመሰለው ርኁሩኁ ጌታ ሰዎችን ከሰዎች ጋር አያወዳድርም። መክሊቶች የሰጣቸው “እንደ ዓቅማቸው” ስለሆነ እያንዳንዳቸው ከሚችሉት በላይ እንዲመልሱ አልጠበቀባቸውም። ሁለቱም ለጌታቸው በሙሉ ነፍሳቸው ስለሠሩ እኩል ተመስግነዋል። ሁላችንም ከዚህ ትምህርት ማግኘት እንቸላለን።
19 እርግጥ፣ ሦስተኛው ባሪያ አልተመሰገነም። እንዲያውም በውጭ ወዳለው ጨለማ ተጥሏል። አንድ መክሊት ብቻ ስለተቀበለ አምስት መክሊቶችን የተቀበለውን ያህል እንዲያተርፍ አይጠበቅበትም ነበር። ሆኖም ሙከራ እንኳ አላደረገም ነበር! ‘ክፉና ሀኬተኛ ልቡ’ ለጌታው ፍቅር እንደሌለው ስለጠቆመ ይህ ባሪያ ሊፈረድበት ይገባ ነበር።
20. ይሖዋ አቅማችንን የሚመለከተው እንዴት ነው?
20 ይሖዋ ሁላችንም በፍጹም ኃይላችን እንድንወደው ቢጠብቅብንም ‘እርሱ ራሱ ፍጥረታችንን የሚያውቅና እኛ አፈር መሆናችንን የሚያስብ’ መሆኑን ማወቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው! (መዝሙር 103:14) ምሳሌ 21:2 ይሖዋ የአገልግሎት አሃዞችን ሳይሆን “ልብን ይመዝናል” ይላል። ከአቅማችን በላይ የሆኑ የገንዘብ፣ የአካል፣ የስሜት ወይም ሌሎች ችግሮቻችንን ይረዳልናል። (ኢሳይያስ 63:9) ሆኖም ያሉንን ጥሪቶች በሙሉ የምንችለውን ያህል እንድንጠቀምባቸው ይጠብቅብናል። ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም ፍጹማን ካልሆኑ አምላኪዎቹ ጋር ባለው ግንኙነት ከእነሱ ፍጽምናን አይጠብቅባቸውም። ይሖዋ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ሁሉ ምክንያታዊ ነው፤ ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን አይጠብቅም።
21. አምላክን የምናገለግለው በፍቅር ተገፋፍተን ከሆነ ምን መልካም ውጤቶች ይገኛሉ?
21 ይሖዋን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም አሳብና በፍጹም ኃይል መውደድ “ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው።” (ማርቆስ 12:33) በፍቅር ከተገፋፋን በአምላክ አገልግሎት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ጴጥሮስ ፍቅርና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያት “ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋል” በማለት ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 1:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
ለክለሳ ያህል
◻ አምላክን እንድናገለግል የሚገፋፋን ኃይል ምን መሆን አለበት?
◻ የክርስቶስ ፍቅር ይሖዋን እንድናገለግል የሚገፋፋን እንዴት ነው?
◻ ፈሪሳውያን ከተጠመዱበት ከየትኛው ወጥመድ መጠበቅ አለብን?
◻ አገልግሎታችንን ሁልጊዜ ከሌላ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር ማወዳደራችን ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የግለሰቦች ችሎታ፣ ጥንካሬና ሁኔታ ይለያያል