በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ እምነት ማሳደር ሕይወትን ያድናል
ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ለመጨረሻ ጊዜ በሄደበት ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ” በማለት በመገረም ተናገረ። ይህ ቤተ መቅደስ የአይሁድ ሕዝብ የሚኮሩበትና ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ቦታ ነው። ሆኖም ኢየሱስ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” በማለት መለሰለት።—ማርቆስ 13:1, 2
ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው! ቤተ መቅደሱ ከተገነባባቸው ድንጋዮች አንዳንዶቹ በጣም ግዙፍ ናቸው። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ የተናገረው ነገር ኢየሩሳሌም እንደምትደመሰስና ምናልባትም ቤተ መቅደሱ የአምልኮ ማዕከል የሆነለት የአይሁድ ብሔር ጭምር እንደሚጠፋ የሚያመለክት ነው። በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” በማለት ተጨማሪ ጥያቄዎች አቀረቡለት።—ማርቆስ 13:3, 4
ኢየሱስ “ፍጻሜው ግን ገና ነው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ መጀመሪያ ጦርነት፣ የመሬት መናወጥ፣ ረሃብና ቸነፈር በተለያዩ ቦታዎች እንደተከሰቱ ወሬ ይሰማሉ። ከዚያም የአይሁድ ብሔር አስፈሪ የሆኑ በርካታ መቅሠፍቶች ይገጥሙታል፤ አዎን “ታላቅ መከራ ይሆናል።” ሆኖም አምላክ ‘የተመረጡትን’ ማለትም ታማኝ ክርስቲያኖችን ለማዳን ሲል ጣልቃ ይገባል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?—ማርቆስ 13:7፤ ማቴዎስ 24:7, 21, 22፤ ሉቃስ 21:10, 11
በሮም ላይ ማመጽ
ከላይ ያለው ትንቢት ከተነገረ 28 ዓመታት ያለፉ ሲሆን በኢየሩሳሌም የሚገኙት ክርስቲያኖች አሁንም መጨረሻውን እየተጠባበቁ ነው። የሮም ግዛት በጦርነት እየታመሰ ከመሆኑም በላይ የምድር መናወጥ፣ ረሃብና ቸነፈር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው። (በገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁዳ የእርስ በርስ ውጊያና የጎሳ ግጭት ምንጭ ሆናለች። ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም ግንብ ተከልሎ የሚኖረው ሕዝብ በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም አለው። ሕዝቡ እንደ መብላት፣ መሥራት፣ ማግባትና ልጅ መውለድ ያሉትን ዕለታዊ እንቅስቃሴዎች እንደ ወትሮው ያከናውናል። ግዙፍ የሆነው ቤተ መቅደስ በከተማዋ ውስጥ መኖሩ ሰዎች ከተማዋ እንደተረጋጋችና ምንም እንደማይደርስባት እንዲሰማቸው አድርጓል።
በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከሐዋርያው ጳውሎስ የተላከ ደብዳቤ ደረሳቸው። ሐዋርያው እነዚህን ክርስቲያኖች ላሳዩት ጽናት ያመሰገናቸው ቢሆንም አንዳንድ የጉባኤው አባላት የጥድፊያ ስሜት የሌላቸው መሆኑ አሳስቦታል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ስተው እንደወደቁ ወይም ክርስቲያናዊ ጉልምስና እንደጎደላቸው ገለጸ። (ዕብራውያን 2:1፤ 5:11, 12) ጳውሎስ እንዲህ በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው:- “መታመናችሁን [“ድፍረታችሁን፣” የ1954 ትርጉም] አትጣሉ። . . . ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ‘የሚመጣው እርሱ ይመጣል፤ አይዘገይም። ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አትሰኝም።’” (ዕብራውያን 10:35-38) በእርግጥም ይህ ወቅታዊ ምክር ነው! ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች እምነት በማሳደር ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ፍጻሜ በንቃት ይከታተሉ ይሆን? እውነት ኢየሩሳሌም በቅርቡ ትጠፋለች?
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በኢየሩሳሌም ውስጥ ሁኔታው ከቀን ወደ ቀን እየከፋ ሄደ። በመጨረሻም በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፍሎረስ የተባለው ምግባረ ብልሹ የሆነ የሮም ገዥ፣ ለሮም መንግሥት መከፈል የነበረበትን “የተጠራቀመ የቀረጥ ዕዳ” ለማስገበር ቅዱስ ከሆነው የቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት 17 ታላንት ወሰደ። በዚህ በጣም የተቆጡት አይሁዶች በሮም መንግሥት ላይ ዓመጹ። የአይሁድ ዓማጺያን ወደ ኢየሩሳሌም በመጉረፍ በዚያ ያሉትን የሮም ወታደሮች ፈጇቸው። ከዚያም ይሁዳ ከሮም አገዛዝ ነፃ እንደወጣች በድፍረት አወጁ። በዚህም የተነሳ በይሁዳና በሮም መካከል ጦርነት ተነሳ!
በሶርያ የነበረው ሮማዊ አገረ ገዢ ሴስቲየስ ጋለስ፣ በሦስት ወራት ውስጥ 30,000 ወታደሮችን አስከትሎ የአይሁዳውያንን ዓመጽ ለመግታት ወደ ደቡብ ዘመተ። ሠራዊቱ ኢየሩሳሌም የደረሰው በዳስ በዓል ወቅት ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ወታደሮቹ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ዘልቀው ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ። በቁጥር ጥቂት የሆኑት ዓማጺያን ሸሽተው በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ ተሸሸጉ። የሮም ወታደሮች በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚገኘውን ግንብ ማፍረስ ጀመሩ። አረማዊ ወታደሮች የይሁዳን ቅዱስ ቦታ ማርከሳቸው ለአይሁዳውያኑ በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው! በከተማዋ ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ግን ኢየሱስ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አስታወሱ። ‘የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ በዚያን ጊዜ በይሁዳ የምትገኙ ወደ ተራራዎች ሽሹ’ ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:15, 16) ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት አምነው እርምጃ ይወስዱ ይሆን? ከዚያ በኋላ ከተከናወኑት ሁኔታዎች መመልከት እንደሚቻለው በሕይወት መትረፋቸው የተመካው የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመስማታቸው ላይ ነው። ይሁን እንጂ እንዴት መሸሽ ይችላሉ?
ሴስትየስ ጋለስ በድንገትና ባልታወቀ ምክንያት ሠራዊቱን ይዞ ወደ ባሕሩ ዳርቻ አፈገፈገ፤ ዓማጺያኑም ሮማውያኑን እየተከታተሉ አሳደዷቸው። በዚህ መንገድ በከተማዋ ላይ አንዣብቦ የነበረው መከራ በአስገራሚ ሁኔታ በአጭሩ ተገታ! ክርስቲያኖችም ኢየሱስ በተናገረው ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ላይ እምነት በማሳደር ከኢየሩሳሌም ወጥተው ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በተራራው ላይ ወደምትገኝ ፔላ የተባለች ገለልተኛ ከተማ ሸሹ። እነዚህ ክርስቲያኖች በጥሩ ጊዜ አምልጠዋል። ብዙም ሳይቆይ ዓማጺያኑ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱ ሲሆን የቀሩትን የከተማዋ ነዋሪዎች በዓመጹ እንዲተባበሯቸው ማስገደድ ጀመሩ።a አስተማማኝ መሸሸጊያ ያገኙት በፔላ ያሉት ክርስቲያኖች ግን እዚያው ሆነው ሁኔታውን እየተከታተሉ ነው።
ብጥብጥ ተነሳ
በጥቂት ወራት ውስጥ ሌላ የሮም ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም መገስገስ ጀመረ። በ67 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጄኔራል ቨስፔዢያን ከልጁ ከቲቶ ጋር 60,000 ወታደሮችን ያቀፈ ታላቅ ሠራዊት ይዞ ተንቀሳቀሰ። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ይህ ኃያል ሠራዊት በመንገዱ ላይ የሚያጋጥሙትን ተቃዋሚዎች ሁሉ እየደመሰሰ ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰ። በዚህ መሃል በኢየሩሳሌም ያሉት ተቀናቃኝ የአይሁድ አንጃዎች ጭካኔ የተሞላበት ፍልሚያ እያካሄዱ ነው። የከተማዋ የእህል ጎተራዎች የፈረሱ ሲሆን በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያሉት ቤቶች ወደሙ፤ ከ20,000 በላይ የሚሆኑ አይሁዳውያንም ተገደሉ። ቨስፔዢያን ‘አምላክ ከእኔ ይበልጥ የሮም ጄኔራል ሆኖ ይዋጋል፤ ጠላቶቻችን እርስ በርስ እየተፋጁ ነው’ በማለት ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገውን ጉዞ አዘገየው።
የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው ኔሮ ሲሞት ቨስፔዢያን የይሁዳን ዘመቻ ለልጁ ለቲቶ በመተው ዙፋኑን ለመረከብ ወደ ሮም ሄደ። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የማለፍ በዓል ሲቃረብ ኢየሩሳሌም በነዋሪዎቿና በዓሉን ለማክበር በመጡ ሰዎች ተጨናንቃ እያለች ቲቶ ከተማዋን ከበባት። የቲቶ ወታደሮች የይሁዳን ገጠራማ አካባቢዎች ደን መንጥረው ባዘጋጇቸው የሾሉ እንጨቶች ተጠቅመው በከተማዋ ግንብ ዙሪያ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቅጥር ሠሩ። ይህም ኢየሱስ “ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከበው አንቺን [ያስጨንቁሻል]” በማለት የተናገረው ትንቢት በትክክል እንዲፈጸም አድርጓል።—ሉቃስ 19:43
ብዙም ሳይቆይ ከተማዋ በድርቅ ተመታች። መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች የሞቱና በጣም የደከሙ ሰዎችን ቤቶች መዝረፍ ጀመሩ። ቢያንስ አንዲት የተጨነቀች ሴት ሕፃን ልጇን ገድላ በመብላቷ “ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ . . . የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ” የሚለው ትንቢት ተፈጽሟል።—ዘዳግም 28:53-57
በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ከአምስት ወራት ከበባ በኋላ ወደቀች። ከተማዋም ሆነ ታላቁ ቤተ መቅደሷ የዘራፊዎች ሲሳይ ከመሆናቸውም በላይ በእሳት ጋዩ፤ ሕንፃዎቹም ፈራረሱ። (ዳንኤል 9:26) በአጠቃላይ 1,100,000 ያህል ሰዎች ሲሞቱ 97,000 የሚሆኑ ደግሞ ለባርነት ተሸጡ።b (ዘዳግም 28:68) ይሁዳ ባድማ ሆነች። በእርግጥም በአይሁዶች ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ባሕል ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ተወዳዳሪ የሌለው ብሔራዊ እልቂት ነው።c
በፔላ ያሉት ክርስቲያኖች ሕይወታቸው በመትረፉ ለአምላክ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቀረቡ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሠፈሩ ትንቢቶች ላይ እምነት በማሳደራቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል!
በዛሬው ጊዜም እያንዳንዳችን እነዚህን ክስተቶች መለስ ብለን ስንመለከት ‘እየቀረበ ባለው በታላቁ መከራ ወቅት ሕይወቴን ሊያተርፍልኝ የሚችል እምነት አለኝ? “አምነው ከሚድኑት ወገን” ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።—ዕብራውያን 10:39፤ ራእይ 7:14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ጆሴፈስ እንደዘገበው ዓማጺያኑ ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለሳቸው በፊት ሮማውያንን ለሰባት ቀናት አሳድደዋቸዋል።
b በሁሉም የሮም ግዛቶች ውስጥ ከነበሩት አይሁዳውያን መካከል ከአንድ ሰባተኛ በላይ የሚሆኑት እንደተገደሉ ይገመታል።
c የአይሁድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልፍሬድ ኢደርሻይም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በእስራኤል ላይ የመጣው [ይህ] መከራ አስከፊ ከሆነው የቀድሞው ታሪኳም ሆነ ከዚያ በኋላ ከሚያጋጥሟት አሳዛኝ ሁኔታዎች ሁሉ የማይወዳደር [ነበር]።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙት ምልክቶች
ጦርነቶች:-
ጎውል (39-40 ከክ.ል.በኋላ)
ሰሜን አፍሪካ (41 ከክ.ል.በኋላ)
ብሪታንያ (43, 60 ከክ.ል.በኋላ)
አርሜንያ (58-62 ከክ.ል.በኋላ)
በይሁዳ የተካሄዱ የእርስ በርስ ጦርነቶችና የጎሳ ግጭቶች (50-66 ከክ.ል.በኋላ)
የመሬት መናወጦች:-
ሮም (54 ከክ.ል.በኋላ)
ፖምፔ (62 ከክ.ል.በኋላ)
በትንሹ እስያ (53, 62 ከክ.ል.በኋላ)
ቀርጤስ (62 ከክ.ል.በኋላ)
ረሃብ:-
ሮም፣ ግሪክ፣ ግብጽ (42 ከክ.ል.በኋላ ገደማ)
ይሁዳ (46 ከክ.ል.በኋላ ገደማ)
ቸነፈር:-
ባቢሎን (40 ከክ.ል.በኋላ)
ሮም (60, 65 ከክ.ል.በኋላ)
ሐሰተኛ ነቢያት:-
ይሁዳ (56 ከክ.ል.በኋላ ገደማ)
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሮማውያን ከ67-70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጳለስጢና ያደረጉት ዘመቻ
ጴጤሌማይስ
የገሊላ ባሕር
ፔላ
ፔሪያ
ሰማርያ
ኢየሩሳሌም
የጨው ባሕር
ይሁዳ
ቂሳሪያ
[ምንጭ]
ካርታው ብቻ:- Based on maps copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ጠላቶቻችን እርስ በርስ እየተፋጁ ነው።’—ቨስፔዢያን
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሮማውያን ሠራዊት በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን አጠፋት
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ቅርጹ:- Soprintendenza Archeologica di Roma; ቨስፔዢያን:- Bildarchiv Preussischer Kulturbesitz/Art Resource, NY