-
በእርግጥ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነውን?መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሚያዝያ 1
-
-
የኢየሱስ ተከታዮች ትርጉም ያለው ጥያቄ አነሡ
የኢየሱስ ተከታዮች ተገርመው መሆን አለበት። ኢየሱስ ውብ የሆነው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሕንጻ ሙሉ በሙሉ እንደሚወድም በእርግጥኝነት ተናግሮ ነበር! እንዲህ ያለው ትንበያ በጣም የሚያስደንቅ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሄደው አረፍ እንዳሉ አራቱ ደቀ መዛመርት “ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:3 NW፤ ማርቆስ 13:1-4) እነርሱ ቢገነዘቡትም ባይገነዘቡትም ኢየሱስ የሰጠው መልስ ድርብ ተፈጻሚነት ነበረው።
የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጥፋትና የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከክርስቶስ መገኘትና ከመላው ዓለም የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ የተለዩ ነገሮች ናቸው። የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በሰጠው ረዘም ያለ መልስ ውስጥ ጥያቄው የሚዳስሳቸውን እነዚህን ሁሉ ዘርፎች ጠቅሷል። የኢየሩሳሌም ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ ነግሯቸዋል፤ እንዲሁም በሚገኝበት ማለትም በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበትና ጠቅላላውን የዓለም የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት በሚዘጋጅበት ጊዜ ነገሮች ምን መልክ ይኖራቸዋል ብለው መጠበቅ እንደሚችሉ ነግሯቸዋል።
የኢየሩሳሌም ጥፋት
በመጀመሪያ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና በዚያ ስለሚገኘው ቤተ መቅደስ ምን እንደተናገረ ልብ በል። ከዓለም ታላላቅ ከተሞች አንዷ በነበረችው በኢየሩሳሌም ላይ አስከፊ መከራ ስለሚመጣበት ጊዜ ከሦስት አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ ትንቢት ተናግሯል። በተለይ በሉቃስ 21:20, 21 ላይ የሚገኙትን ቃላት ልብ በል:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” ኢየሩሳሌም በጭፍራ የምትከበብ ከሆነ ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት “በመካከልዋ ያሉ” በቀላሉ ‘ፈቀቅ ሊሉ’ የሚችሉት እንዴት ነበር? ኢየሱስ ማምለጫ መንገድ እንደሚከፈትላቸው መናገሩ እንደነበር ግልጽ ነው። ታዲያ ተከፍቶላቸው ነበርን?
በ66 እዘአ በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮማ ሠራዊት የአይሁዳውያንን ዓማፂ ኃይሎች መክቶ ወደ ኢየሩሳሌም እያሳደደ ካባረራቸው በኋላ መውጫ አሳጣቸው። ሮማውያን ከተማዋ ውስጥ ሳይቀር ገፍተው በመግባት እስከ ቤተ መቅደሱ ቅጥር ድረስ ገሰገሱ። ይሁን እንጂ ጋለስ ለሠራዊቱ በጣም ግራ የሚያጋባ ትእዛዝ አስተላለፈ። ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አዘዛቸው! ይህ ሁኔታ ያስፈነደቃቸው አይሁዳውያን ወታደሮች የሸሹትን ሮማውያን ጠላቶቻቸውን እያሳደዱ ወጓቸው። አዎን፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረለት ማምለጫ መንገድ ተከፈተ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የእርሱን ማስጠንቀቂያ በመስማት ከኢየሩሳሌም ወጡ። እንዲህ ማድረጋቸው ጥበብ ነበር፤ ምክንያቱም ልክ ከአራት ዓመታት በኋላ የሮማ ሠራዊት በጄነራል ቲቶ እየተመራ እንደገና መጣ። በዚህ ጊዜ ለማምለጥ መሞከር የማይታሰብ ነበር።
የሮማ ሠራዊት እንደገና ኢየሩሳሌምን ከበበ፤ በዙሪያዋም ቅጥር ቀጠረ። ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል” ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር።a (ሉቃስ 19:43) ወዲያው ኢየሩሳሌም ተያዘች፤ ክብራማው ቤተ መቅደስ የፍርስራሽ ክምር ሆነ። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት አንድ በአንድ ፍጻሜያቸውን አገኙ!
ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአእምሮው በኢየሩሳሌም ላይ ከሚመጣው ጥፋት የበለጠ ነገር ይዞ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ መገኘቱን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ጭምር እንዲሰጣቸው ጠይቀውት ነበር። በወቅቱ ባይገነዘቡትም ይህ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ የሚቀመጥበትን ጊዜ የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተንብዮአል?
-
-
በእርግጥ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነውን?መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሚያዝያ 1
-
-
a ቲቶ ድል እንደሚቀዳጅ ሳይታለም የተፈታ ነበር። የሆነ ሆኖ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ያሰበው ሳይሳካለት ቀርቷል። በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የከተማዋ መሪዎች ያላንዳች ግልጽ ምክንያት በግትርነት አሻፈረኝ ብለዋል። ከዚህም ሌላ መጨረሻ ላይ የከተማይቱን ቅጥር ደርምሰው ሲገቡ ቤተ መቅደሱ እንዳይፈርስ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋየ! ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስና ቤተ መቅደሷም ጨርሶ እንደሚወድም በግልጽ ተቀምጧል።— ማርቆስ 13:1, 2
-