‘ሰዓቱ ስንት ነበር?’
“ስንት ሰዓት ነው?” ይህን ጥያቄ ምን ያህል አዘውትረህ ጠይቀሃል? በዚህ በጥድፊያ የተሞላ ዘመን የጊዜ ጉዳይ ሁልጊዜ ያሳስበናል። አብዛኞቹ የዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን ማለትም ማለዳ ከእንቅልፍ መነሳት፣ ወደ ሥራ መሄድ፣ ምግባችንን መብላት፣ ከጓደኞቻችን ጋር መገናኘትና የመሳሰሉት ሁሉ በጊዜ ገደብ የሚገዙ ናቸው። ሰዓት ስንት መሆኑን የሚነግሩን በርካታ መሣሪያዎች አሉን። ከእነዚህም መካከል የግድግዳ ሰዓቶች፣ የእጅ ሰዓቶች ደውሎችና ሬድዮኖች ይገኙበታል።
እንደኛ ዘመን የጊዜ መለኪያ መሣሪያዎች ያልነበሩአቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ሰዎችስ? ጊዜን የሚቆጥሩት በምን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ መዝግብ ስለዚህ አንዳች የሚነግረን ነገር አለን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመበትን ጊዜ ማወቅህ በአምላክ ቃል ላይ ያለህን ማስተዋል በመጨመር የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን አስደሳች ያደርግልሃል።
ከአምላክ የተሰጡ የጊዜ አመልካቾች
በቀድሞ ዘመን አንድ ድርጊት የተፈጸመበት ጊዜ ተለይቶ የሚታወቀው “ቀንና ሌሊቱን እንዲለዩ” ፈጣሪ በሰማይ ያደረጋቸውን “ሁለት ታላላቅ ብርሃናት” ፀሐይንና ጨረቃን በመመልከት ነበር። (ዘፍጥረት 1:14-16) ለምሳሌ ሁለቱ መላእክት ሎጥንና ቤተሰቡን ለጥፋት ከተመደበችው ከሰዶም ከተማ እንዲሸሹ ያስቸኰሏቸው “ጐህ በቀደደ ጊዜ” ነበር። (ዘፍጥረት 19:15, 16) እንደዚሁም የአብርሃም ታማኝ ሎሌ ርብቃን ወዳገኘበት ምንጭ ሲደርስ “ምሽት” ወቅት ነበር።—ዘፍጥረት 24:11, 15
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ትክክለኛና አንድን ወቅት ለይተው የሚያመለክቱ የጊዜ ስያሜዎችም ተሰጥተዋል። ለምሳሌ የመስፍኑ የጌዲዮን አመጸኛ ልጅ የነበረው አቢሜሌክ በሴኬም ከተማ ላይ “ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልዶ” እንዲወድቅበት ተመክሯል። (መሳፍንት 9:33) እንዲህ ያለ ምክር የተሰጠው ለጦር ስልት አመቺ እንዲሆን ታስቦ ነበር። ከአቤሜሌክ ሠራዊት ጀርባ ሆና ጮራዋን የፈነጠቀችው የማለዳ ፀሐይ የሴኬም ተከላካዮች “በተራሮች” ተጠልለው የሚመጡትን አጥቂ ጭፍሮች እንዳይመለከቱ አግዶአቸዋል።—መሳፍንት 9:36-41
ጊዜን የሚያመለክቱ ፈሊጣዊ አነጋገሮች
ዕብራውያን ጊዜን ለማመልከት ውብና አስደሳች አገላለጾችን ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ አገላለጾች የአካባቢውን ሁኔታና ባሕል እንድንረዳ ከማስቻላቸውም በላይ ስለአንዳንድ ድርጊቶች አፈጻጸም እንድናስተውል ይረዱናል።
ለምሳሌ ዘፍጥረት 3:8 አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ ያነጋገራቸው “ቀኑ በመሸ ጊዜ” እንደነበር ይነግረናል። ይህም የቀኑ ትኩሳት አልፎ ጸሐይ ልትገባ ስትቀርብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ የምሽት ጊዜ የመዝናናትና የዕረፍት ሰዓት ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያለው ከፍተኛ የፍርድ ጉዳይ ውሎ እንዲያድር ስላልፈለገ በዚያው በነበረው ጊዜ ተጠቅሞ ጉዳዩን ዘግቶታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ዘፍጥረት 18:1, 2 የይሖዋ ሁለት መላእክት በመምሬ አጠገብ ወደነበረው የአብርሃም ድንኳን የመጡት “በቀትር ጊዜ” እንደነበር ይገልጻል። በይሁዳ ኰረብታዎች ላይ ፀሐይ ከአናት በላይ ስትሆን ምን ያህል ትኩሳት እንደሚኖራት መገመት ትችላለህ። ሙቀቱ በጣም ኃይለኛ የነበረ ሊሆን ይችላል። ምሳ የሚበላበትና የሚታረፍበት ሰዓት ነበር። (ዘፍጥረት 43:16, 25፤ 2 ሳሙኤል 4:5ን ተመልከቱ) በመሆኑም አብርሃም ምናልባትም ምሳ ከበላ በኋላ ሳይሆን አይቀርም ንፋስ ለማግኘት በሚችልበት “በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ” ነበር። እንግዶቹን ሲያይ “ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፣” ከዚያም እንጐቻ እንድታዘጋጅ ለሣራ ለመንገር “ወደ ድንኳኑ ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባ” እና “ወደላሞቹ ሮጠ፤ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ” የሚሉትን ጥቅሶች ስናነብ በዕድሜ ገፍቶ የነበረውን የአብርሃምን እንግዳ ተቀባይነት ይበልጥ እናደንቃለን። ይህ ሁሉ የፀሐይ ትኩሳት በሚያይልበት በቀትር ጊዜ ነበር!—ዘፍጥረት 18:2-8
የዕብራውያን የሌሊት ሰዓቶች
ዕብራውያን ሌሊቱን “ትጋቶች” በሚባሉ ሦስት ወቅቶች ይከፍሉ ነበር። እያንዳንዱ ትጋት ጸሐይ ከጠለቀችበት ጀምሮ እስክትወጣ ያለውን ጊዜ አንድ ሶስተኛ ወይም በወቅቶች መፈራረቅ ምክንያት እንደጨለማው ጊዜ ማጠርና መርዘም ወደ አራት ሰዓት የሚሆነውን ጊዜ ይሸፍን ነበር። (መዝሙር 63:6) ጌዴዎን የሜዶናውያንን ሠፈር ያጠቃው ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በሚደርሰው “በመካከለኛው ትጋት ትጋቱም በተጀመረ ጊዜ” ነበር። በዚህ ሰዓት የተደረገ ጥቃት ያለአንዳች ጥርጥር ዘቦቹ እንቅልፍ ከብዷቸው ሳይጠነቀቁ የነበሩበት ሰዓት ነበር። በእርግጥም ጠንቃቃው ጌዴዎን ለጥቃቱ ከዚህ ይበልጥ የተመቸ ጊዜ ሊመርጥ አይችልም ነበር!—መሳፍንት 7:19
እሥራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ በነበሩበት ጊዜ በደረቁ ምድር ላይ እንዲሻገሩ ይሖዋ “ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው።” ግብጻውያኑ በደረሱባቸው ሰዓት “ንጋት” ላይ ነበርና ይሖዋ የግብጻውያንን ሠፈር ማወቅ ጀመረና በመጨረሻም “ባሕሩ ማለዳ ወደ መፍሰስ እንዲመለስ” በማድረግ አጠፋቸው። (ዘፀአት 14:21-27) ስለዚህ ባሕሩ እስኪከፈልና እሥራኤላውያንም በመካከሉ እስኪሻገሩ አንድ ሌሊት ያህል ጊዜ ወስዷል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ቀኑን በ12 ሰዓቶች ከፋፍለው መቁጠር ጀምረው ነበር። ኢየሱስ ከምሳሌዎቹ በአንዱ ላይ “ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን?” በማለት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነበር። (ዮሐንስ 11:9) እነዚህ ሰዓቶች የሚቆጠሩት ከፀሐይ መውጣት እስከ መግባት ወይም ደግሞ በግምት ከጧቱ አሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ነበር። ስለዚህ “ሦስተኛ ሰዓት” ማለት ከጧቱ ሦስት መሆኑ ነው። በጴንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የፈሰሰው በዚህ ሰዓት ነበር። ሕዝቡ ደቀመዛሙርትን “ጉሽ የወይን ጠጅ እንደጠገቡ” አድርገው ሲወነጅሏቸው ጴጥሮስ ያንን ክስ ውድቅ አድርጎታል። ምክንያቱም በዚያ የጧት ሰዓት ማንም ሊሰክር አይችልም!—ሥራ 2:13, 15
በተመሳሳይም ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ያለው በየትኛው ሰዓት እንደነበረ መገንዘባችን ለቃሉ ተጨማሪ ትርጉም ይሰጠናል። በዮሐንስ 4:6 መሠረት “ስድስት ሰዓት ያህል” ወይም ቀትር ነበር። በሰማሪያ ኮረብታ ገጠር ረፋዱን ሁሉ በእግራቸው ሲኳትኑ ከቆዩ በኋላ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ሊራቡና ሊጠሙ ይችሉ ነበር። ለዚህ ነበር ደቀመዛሙርቱ ምግብ ይዘው በተመለሱ ጊዜ ኢየሱስን ብላ ብለው የለመኑት ኢየሱስ የይሖዋን ሥራ በመሥራቱ ምግብ የመብላትን ያህል ብርታትና እርካታ አግኝቶ እንደነበረ ብዙም ያወቁት ነገር አልነበረም። የኢየሱስ አባባል ከምሳሌያዊ አነጋገር የበለጠ ትርጉም የነበረው መሆኑ አያጠራጥርም። ምንም እንኳን ምግብ ከበላ ብዙ ሰዓቶች አልፈው የነበረ ሊሆን ቢችልም የአምላክን ሥራ በመሥራቱ ቃል በቃል ኃይልና ብርታት አግኝቶ ነበር።—ዮሐንስ 4:31-34
እንደ ዓመቱ ወቅቶች ሁኔታ የጸሐይ መውጫና መግቢያ ሰዓቶች ስለሚለዋወጡ ድርጊቶች ስለተፈጸሙበት ጊዜ የሚገለጸው የሰዓት መጠን ብዙውን ጊዜ ግምታዊ ነበር። በመሆኑም ብዙውን ጊዜ ድርጊቶቹ ስለተፈጸሙበት ሰዓት ሦስተኛ ሰዓት፣ ስድስተኛ ሰዓት፣ ወይም ዘጠነኛ ሰዓት (በተለይ እንደ እንግሊዝኛ ትርጉሞች) የሚል ቃል እናነባለን። ይህም በግምት በእነዚያ በተጠቀሱት ሰዓቶች ገደማ ማለት ነው። (ማቴዎስ 20:3, 5፤ 27:45, 46፤ ማርቆስ 15:25, 33, 34፤ ሉቃስ 23:44፤ ዮሐንስ 19:14፤ ሥራ 10:3, 9, 30) ይሁን እንጂ ለተራኪው ሰዓቱን መጥቀስ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የማያሻሙ የተወሰኑ ሰዓቶች ተሰጥተዋል። ለምሳሌ ልጁ በጐ የሆነው በኢየሱስ ኃይል መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ለፈለገው ሰውዬ ባሮቹ “ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው” አሉት።—ዮሐንስ 4:49-54
የሌሊት ሰዓት ክፍልፍሎች
በሮማ ግዛት ዘመን አይሁዳውያን ሌሊቱን በሦስት ትጋት ከፋፍለው ይቆጥሩ የነበሩበትን ልማድ ትተው ሌሊቱን በአራት ትጋቶች ከፋፍለው ይቆጥሩ የነበሩትን የግሪካውያንና የሮማውያንን አቆጣጠር መጠቀም የጀመሩ ይመስላል። በማርቆስ 13:35 ላይ ኢየሱስ አራቱን ትጋቶች እንደጠቀሰ ግልጽ ነው። “በማታ” የተባለው ትጋት ከጸሐይ መግባት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ያለውን ጊዜ ይይዛል። ሁለተኛው ትጋት የሆነው “እኩለ ሌሊት” ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በእኩለ ሌሊት ያበቃል። “የዶሮ ጩኸት” ከእኩለ ሌሊት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። የመጨረሻው ትጋት የሆነው “ማለዳ” ደግሞ ጐህ ሲቀድ ወይም በ12 ሰዓት አካባቢ ያበቃል።
በተለይ “ዶሮ ጩኸት” የተባለው ትጋት ትኩረታችንን የሚስብ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ በማርቆስ 14:30 ላይ ለጴጥሮስ “ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎታል። አንዳንድ ተቺዎች “ሁለት ጊዜ” የሚለው ቃል ሁለት የተወሰነ የጊዜ ነጥቦችን ማለት እኩለ ሌሊትንና ንጋትን (ጐሕን) ያመለክታል ሲሉ በጀምስ ሃስቲንግ የታተመው የክርስትና የወንጌሎች መዝገበ ቃላት የተሰኘው መጽሐፍ ግን “ግልጽ የሆነው ሐቅ ማታ በምሥራቁ ዓለምም ሆነ በሌላ ሥፍራ ዶሮች ሌሊት የሚጮኹት ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ባሉት የተለያዩና እኩል ያልሆኑ ሰዓቶች” መሆኑን ያመለክታል። በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስ ጴጥሮስ እሱን የሚክድበትን የተወሰነ ሰዓት መጥቀሱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቃሉ በትክክል እንደሚፈጸም ለጴጥሮስ ምልክት መስጠቱ ነበር። በእርግጥም በዚያ ሌሊት ኢየሱስ እንደተናገረው በትክክል ተፈጽሞአል።—ማርቆስ 14:72
ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ “ከመሬት በመቶ የሚቆጠሩ ሜትሮች” ርቀው “በባሕር መካከል” ሳሉ በውሃ ላይ እየሄደ ወደእነሱ የመጣው “በአራተኛው ክፍል” ማለት ከሌሊቱ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ነበር። ደቀመዛሙርቱ “ምትሐት ነው” ብለው መታወካቸውና በፍርሐት መጮኻቸው” አሁን ግልጽ ሆኖ ሊገባን ይችላል። (ማቴዎስ 14:23-26) በሌላ በኩል ኢየሱስ በተራራው ላይ ብቻውን ሆኖ በመጸለይ ብዙ ሰዓት እንዳሳለፈም ያሳያል። ጊዜው የዮሐንስ መጥምቁ ራስ በሔሮድስ አንጢጳስ የተቆረጠበት ሰሞንና የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት የመጨረሻው ዓመት መጀመሪያ ላይ ስለነበረ ኢየሱስ በዚህ የግል ጸሎቱ ለአባቱ የሚያሳስበው ብዙ ነገር እንደነበረው አያጠራጥርም።
ከአራቱ ትጋት በተጨማሪ ሌሊቱ በ12 ሰዓቶች ተከፋፍሎ ይቆጠር ነበር። ጳውሎስን ወደ ቂሣርያ በደህና ለመሸኘት ሻለቃው ቀላውዲዎስ ሉስዩስ የመቶ አለቆቹን “ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት” አራት መቶ ሰባ ወታደሮችን እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው። (ሥራ 23:23, 24) ስለዚህ ጳውሎስ በጨለማ ሽፋን ከኢየሩሳሌም በደህና ተወሰደ።
የቀኑን ሰዓት እወቁ
በጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች መካከል ምን እንደደረሰ ማንበብና ማሰላሰል የደስታና የመንፈሳዊ ብርታት ምንጭ ነው። በምታነቡበት ጊዜ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሰዓት ከግምት ካስገባችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ የምታገኙትን ደስታ ይጨምርላችኋል። ለምን? ምክንያቱም በዚህ አይነት ስታጠኑ የአምላክን ቃል በሚገባ ለመረዳት ትችላላችሁ። በዚህ ረገድ በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማሕበር የታተሙት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል እና ባለ ማመሣከሪያው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከፍ ያለ እርዳታ ይሰጧችኋል። ‘ሰዓቱ ስንት ነው?’ ለሚለው ጥያቄአችሁ መልስ እንድታገኙ ይረዱአችኋል።