በእርግጥ አሳቢ የሆነ አካል አለ
ለሌሎች በእርግጥ አሳቢ የሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። የሌሎች ችግር እነርሱን ፈጽሞ እንደማይመለከት አድርገው እንደሚያስቡት የደነደነና የራስ ወዳድነት ስሜት የተጠናወታቸው ሰዎች ዓይነት አመለካከት የላቸውም። አንዳንድ ጊዜ ሕይወታቸውን እንኳ ሳይቀር አደጋ ላይ በመጣል በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ለማስታገሥ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ ከእነርሱ አቅም በላይ የሆኑ ኃይሎች ያወሳሰቡት ከባድ ሥራ ነው።
አንድ የእርዳታ ሠራተኛ እንደ ስግብግብነት፣ ፖለቲካዊ ሴራ፣ ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉት ነገሮች “ረሃብን ለማጥፋት በከፍተኛ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚደረገውን እንቅስቃሴ” ሊያመክኑት ይችላሉ በማለት ተናግሯል። ረሃብን ማጥፋት አሳቢ የሆኑ ሰዎች ከሚጋፈጧቸው በርካታ ችግሮች መካከል አንዱ ብቻ ነው። እንደ በሽታ፣ ድህነት፣ ግፍና አስከፊ ጦርነቶች ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር ጭምር ይፋለማሉ። ይሁን እንጂ ትግሉን በአሸናፊነት እየተወጡ ነውን?
ረሃብንና ሕመምን ለማስታገሥ “በከፍተኛ ብቃትና ቁርጠኝነት” የተሰለፉ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተገለጸውን ርኅሩኅ ሳምራዊ ይመስላሉ በማለት የአንድ የእርዳታ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል። (ሉቃስ 10:29-37) ሰዎቹ ምንም ያድርጉ ምን የችግሩ ሰለባዎች ቁጥር እየተበራከተ መሄዱን ይቀጥላል። በዚህም የተነሳ አስተዳዳሪው “ያ ደግ ሳምራዊ ለብዙ ዓመታት በየቀኑ በዚያው መንገድ የሚያልፍ ቢሆንና በየሳምንቱ በወንበዴዎች ተደብድቦ መንገድ ዳር የወደቀ ሰው ቢያገኝ ምን ያደርግ ነበር?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ውሎ አድሮ በጎ አድራጊዎቹ ትክት ብሏቸው ሊያቆሙ ይችላሉ። ሆኖም በእርግጥ አሳቢ የሆኑ ሰዎች ተሰላችተው አያቆሙም። (ገላትያ 6:9, 10) ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ለብሪታንያው ጁዊሽ ቴሌግራፍ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በናዚ ጀርመን አገዛዝ ወቅት “በኦውሽዊትዝ ይደርስ ከነበረው ሥቃይ በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያንን ሕይወት ለማትረፍ የእርዳታ እጃቸውን” በመዘርጋታቸው የይሖዋ ምሥክሮችን አወድሶ ጽፏል። ጸሐፊው ሲቀጥል “የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት ወቅት የነበረቻቸውን ዳቦ [ለአይሁድ] ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አካፍለዋቸዋል!” ምሥክሮቹ ያላቸውን በማካፈል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል።
ሆኖም የቱንም ያህል ዳቦ ብናካፍል የሰው ልጆችን ለዘለቄታው ከችግር ማላቀቅ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ይህ ማለት ግን ሩኅሩኅ ሰዎች የሚያከናውኑትን የደግነት ተግባር ማጣጣላችን አይደለም። ሥቃይን ጋብ ለማድረግ የሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚያ ምሥክሮች አብረዋቸው የታሰሩትን ሰዎች ሥቃይ በመጠኑም ቢሆን ጋብ አድርገውላቸዋል። ውሎ አድሮም የናዚ አገዛዝ ጠፍቷል። ሆኖም ለእንዲህ ዓይነቱ ጭቆና መንስኤ የሆነው የዓለም ሥርዓት እስካሁን ድረስ እንዳለ ነው። ስለ ሌላው ሰው ግድ የለሽ የሆኑ ሰዎች አሁንም ሞልተዋል። በእርግጥም “ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ።” (ምሳሌ 30:14) ለምን እንዲህ ይሆናል ብለህ ራስህን ሳትጠይቅ አትቀርም።
ድህነትና ጭቆና የኖረው ለምንድን ነው?
በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ “ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማርቆስ 14:7) ኢየሱስ ይህን ሲል ድህነትና ጭቆና ማብቂያ የላቸውም ማለቱ ነበርን? ሩኅሩኅ የሆኑ ሰዎች አሳቢነታቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኙ ዘንድ አምላክ ራሱ እንዲህ ዓይነት መከራ እንዲኖር አድርጓል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ያላቸው ዓይነት እምነት ነበረው ማለት ነውን? በፍጹም! ኢየሱስ እንዲህ ያለ እምነት አልነበረውም። ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ ድህነት የሰዎች የኑሮ ክፍል ሆኖ እንደሚቀጥል መጥቀሱ ብቻ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ እነዚህ ሁኔታዎች በምድር ላይ እንዲኖሩ የሰማይ አባቱ የመጀመሪያ ዓላማ እንዳልነበረ ያውቅ ነበር።
ይሖዋ አምላክ ምድርን የፈጠራት በድህነት፣ በግፍና በጭቆና የተሞላች እንድትሆን ሳይሆን ገነት እንድትሆን አድርጎ ነበር። ሕይወትን አስደሳች የሚያደርጉ ግሩም ስጦታዎችን በመለገስ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ያለውን ከፍተኛ አሳቢነት አሳይቷል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ይኖሩበት የነበረው የአትክልት ሥፍራ መጠሪያ ምን እንደነበር አስታውስ! ኤደን ማለትም “ደስታ” የሚል ስም ነበረው። (ዘፍጥረት 2:8, 9) ይሖዋ የሰው ልጆች ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ እያገኙ በጣም አሰልቺ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ አላደረገም። ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ሲያጠናቅቅ የሠራቸውን ነገሮች ተመለከተና “እጅግ መልካም ነበረ” በማለት ተናገረ።—ዘፍጥረት 1:31
ታዲያ በዛሬው ጊዜ ድህነት፣ ጭቆናና ሌሎች ሥቃይ የሚያስከትሉ ነገሮች በምድር ላይ የበዙት ለምንድን ነው? አሁን ያለው ክፉ የነገሮች ሥርዓት ሊኖር የቻለው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ ላይ ለማመፅ በመምረጣቸው ነው። (ዘፍጥረት 3:1-5) አምላክ ከፍጥረታቱ ታዛዥነትን መጠበቁ ትክክል መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ጥያቄ እንዲነሳ አድርገዋል። በዚህ ምክንያት ይሖዋ የአዳም ዝርያዎች ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። በዚህ ወቅትም ቢሆን አምላክ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ የሚደርሰው ነገር ያሳስበዋል። በእርሱ ላይ ማመፅ ያስከተለውን ጉዳት ሁሉ መልሶ ለማስተካከል ዝግጅት አድርጓል። ስለሆነም ይሖዋ በቅርቡ ድህነትንና ጭቆናን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት መከራ ያጠፋል።—ኤፌሶን 1:8-11
ከሰው አቅም በላይ የሆነ ችግር
ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በነበሩት በርካታ መቶ ዘመናት የሰው ልጅ ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ይበልጥ እየራቀ ሄዷል። (ዘዳግም 32:4, 5) የሰው ልጅ የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች አልቀበልም ብሎ በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ እርስ በርሱ ሲዋጋና ‘አንዱ ሌላውን እየጎዳ ሲገዛ’ ኖሯል። (መክብብ 8:9) በሥቃይ ላይ የሚገኘውን ብዙሀኑን በመከራ አለንጋ እየገረፈ ያለውን ሥርዓት አጥፍቶ እንከን የለሽ ኅብረተሰብ ለመመሥረት የተደረገው ጥረት ሁሉ ራሳቸውን ለአምላክ ሉዓላዊነት ከማስገዛት ይልቅ በራሳቸው መንገድ ለመሄድ በመረጡ ራስ ወዳድ ሰዎች ሲጨናገፍ ኖሯል።
ብዙዎች ምናልባትም እንደ አጉል እምነት አድርገው በመቁጠር ችላ የሚሉት ሌላ ችግር አለ። በመጀመሪያ በአምላክ ላይ ዓመፅ ያነሳሳው ፍጡር አሁንም ሰዎች ክፉዎችና ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ በማነሳሳት ላይ ነው። ይህ ፍጡር ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ሐዋርያው ዮሐንስ በተቀበለው ራእይ ላይ ዋነኛው የዋይታ ምንጭ ሰይጣን መሆኑንና ‘መላውን ዓለም በማሳት’ ረገድ ቀንደኛው ተጠያቂ እርሱ እንደሆነ ተገልጿል።—ራእይ 12:9-12
አንዳንድ ሰዎች እንደ እነርሱ ፍጡር ለሆኑት ሰዎች በማሰብ ምንም ያክል ቢደክሙ ሰይጣን ዲያብሎስን ማጥፋትም ሆነ በመከራ የሚማቅቁ ሰዎች እያደር እየተበራከቱ ያሉበትን ይህን ሥርዓት ፈጽሞ መለወጥ አይችሉም። ታዲያ ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው እንዴት ነው? መፍትሔው ለሌሎች ከልባቸው በሚጨነቁ ሰዎች ላይ የወደቀ አይደለም። ሰይጣንንና በእርሱ ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን በግፍ የተሞላ ሥርዓት ለማስወገድ ፈቃድም ሆነ ኃይል ያለው የአንድ አካል ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል።
“ፈቃድህ . . . በምድር ትሁን”
አምላክ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት ቃል ገብቷል። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ፈቃድም ሆነ ኃይል አለው። (መዝሙር 147:5, 6፤ ኢሳይያስ 40:25-31) የትንቢት መጽሐፍ በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች” የሚል ትንቢት ሰፍሮ ይገኛል። (ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው አምላክን በጸሎት እንዲለምኑ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው ይህን ለዘላለም የሚኖርና መልካም ነገሮችን የሚያመጣ ሰማያዊ መስተዳድር በአእምሮው ይዞ ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10
ይሖዋ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ከልቡ ስለሚያስብ ለእነዚህ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል። በመዝሙር 72 ላይ በሰፈሩት ትንቢታዊ ቃላት መሠረት የኢየሱስን አገዛዝ ለሚደግፉ ለድሆች፣ ለተጠቁና ለተጨቆኑ ዘላቂ እፎይታ እንዲያመጣላቸው አምላክ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ይሰጠዋል። በዚህም የተነሳ በመንፈስ የተገፋፋው መዝሙራዊ እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ትፈርዳለህ፣ የድሆችንም ልጆች ታድናለህ፤ ክፉውንም ታዋርደዋለህ። ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [“ደማቸው፣” NW] በፊቱ ክቡር ነው።”—መዝሙር 72:4, 12-14
ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ጊዜያችን ባየው ራእይ ውስጥ በአምላክ የተቋቋመ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ተመልክቷል። በመከራ ሥር ለሚገኙ የሰው ዘሮች እንዴት ያለ ግልግል ይሆንላቸዋል! ይሖዋ ስለሚያደርገው ነገር ሲተነብይ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”—ራእይ 21:1-5
አዎን፣ እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኛዎች በመሆናቸው ልናምንባቸው እንችላለን። ይሖዋ በቅርቡ እርምጃ በመውሰድ ድህነትን፣ ረሃብን፣ ጭቆናን፣ በሽታንና ማንኛውንም ዓይነት ግፍ ከምድር ገጽ ያጠፋል። ይህ መጽሔት ከቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ በመጥቀስ እንዳመለከተው እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት ደፍ ላይ እንዳለን በርካታ ማስረጃዎች ያሳያሉ። አምላክ አዲስ ዓለም አመጣለሁ ብሎ የገባው ቃል በቅርቡ ፍጻሜውን ያገኛል! (2 ጴጥሮስ 3:13) በቅርቡ ይሖዋ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል” እንዲሁም “ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8
እስከዚያው ድረስ በአሁኑ ጊዜ እንኳ ሳይቀር ለሌሎች ከልባቸው የሚያስቡ ሰዎች በመኖራቸው ልንደሰት እንችላለን። ከሁሉም ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ ይሖዋ አምላክ ራሱ የሚያስብልን መሆኑ ነው። በቅርቡ ማንኛውንም ዓይነት ጭቆናና ሥቃይ ሙሉ በሙሉ ያጠፋል።
ይሖዋ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ ትምክህት ልትጥል ትችላለህ። የእርሱ አገልጋይ የነበረው ኢያሱ ተመሳሳይ ትምክህት ነበረው። ያለምንም ማወላወል ለጥንቱ የአምላክ ሕዝብ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።” (ኢያሱ 23:14) ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ ሊገጥሙህ በሚችሉ ችግሮች ተውጠህ አትሸነፍ። የሚያስጨንቁህን ነገሮች ሁሉ በእርግጥ በሚያስብልህ በይሖዋ ላይ ጣል።—1 ጴጥሮስ 5:7
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ምድር ከድህነት፣ ከጭቆና፣ ከበሽታና ከግፍ የጸዳች ትሆናለች