የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 38—ዘካርያስ
ጸሐፊው:- ዘካርያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት በ518
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከክ. ል. በፊት ከ520-518
ዘካርያስ ትንቢት መናገር በጀመረበት ወቅት በኢየሩሳሌም የሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ ተቋርጦ ነበር። ሰሎሞን የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ ለመገንባት 7 ዓመት ተኩል የወሰደበት ሲሆን (1 ነገ. 6:37, 38) ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ግን ኢየሩሳሌም ከደረሱ 17 ዓመታት ቢያልፉም ግንባታው ለመጠናቀቅ ገና ብዙ ይቀረው ነበር። በመጨረሻም አርጤክስስ (ባርድያ ወይም ጋውማታ) ግንባታው እንዳይከናወን ሲያዝዝ ሥራው ከነጭራሹ ቆመ። አሁን ግን ንጉሡ የጣለው ዕገዳ ቢኖርም ሥራው እንደገና መካሄድ ጀምሯል። ይሖዋ፣ ሐጌና ዘካርያስን በመላክ ሕዝቡ ግንባታውን እንደገና እንዲጀምሩና እስከ ፍጻሜው ድረስ እንዲገፉበት እያበረታታቸው ነበር።—ዕዝራ 4:23, 24፤ 5:1, 2
2 ሥራው እንደ ታላቅ ተራራ የማይገፋ ይመስል ነበር። (ዘካ. 4:6, 7) አይሁዳውያኑ ጥቂት ሲሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው ግን በጣም ብዙ ናቸው፤ ከዚህም በላይ ከዳዊት መስመር የሆነ ዘሩባቤል የተባለ ገዢ ቢኖራቸውም ንጉሥ አልነበራቸውም፤ እንዲሁም በሌላ መንግሥት አገዛዝ ሥር ነበሩ። ጠንካራ እምነት መያዝና ወገብን ጠበቅ ማድረግ በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት መዳከምና የራስን ጥቅም ወደ ማሳደድ ማዘንበል እንዴት ቀላል ነበር! ሕዝቡ፣ አምላክ በወቅቱ በነበረው ዓላማና ወደፊት በሚፈጽመው ታላቅ ዓላማ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ዘካርያስ ለሥራው አበርትቷቸዋል። (8:9, 13) በዚህ ወቅት፣ አድናቆት እንዳልነበራቸው አባቶቻቸው ዓይነት አካሄድ መከተል ተገቢ አልነበረም።—1:5, 6
3 ዘካርያስ ማን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘካርያስ በሚለው ስም የተጠሩ ወደ 30 ያህል ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ የጻፈው ግለሰብ ‘የአዶ ልጅ፣ የበራክዩ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ’ እንደሆነ ተገልጿል። (ዘካ. 1:1፤ ዕዝራ 5:1፤ ነህ. 12:12, 16) ስሙ (በዕብራይስጥ ዘክሃርያህ) “ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም አለው። የዘካርያስ መጽሐፍ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” ለስሙ ሲል ሕዝቡን በማስታወስ እንደሚንከባከባቸው ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። (ዘካ. 1:3 NW) በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ታሪኩ ቢያንስ የሁለት ዓመት ጊዜ እንደሚሸፍን ይጠቁማሉ። የቤተ መቅደሱ ግንባታ የቀጠለውና ዘካርያስ ትንቢት መናገር የጀመረው “ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር” (ጥቅምት/ኅዳር 520 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ነው። (1:1) በተጨማሪም መጽሐፉ “ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ካሴሉ በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ በአራተኛው ቀን” (ታኅሣሥ 1, 518 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ) ስለተከናወነው ነገር ይጠቅሳል። (7:1) በመሆኑም የዘካርያስ ትንቢት የተነገረውና በጽሑፍ የሠፈረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ520-518 ባሉት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።—ዕዝራ 4:24
4 የዘካርያስን መጽሐፍ የሚያጠኑ ሰዎች ስለ መጽሐፉ ትክክለኛነት በቂ ማረጋገጫዎች ያገኛሉ። የጢሮስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ጢሮስን ያጠፋት ለ13 ዓመታት ከበባ ካደረገ በኋላ ነበር። ይሁንና ጢሮስ በዚህ ወቅት ሙሉ በሙሉ አልተደመሰሰችም። ዘካርያስ፣ ጢሮስ ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ተንብዮ ነበር። ታላቁ እስክንድር የደሴት ከተማ የሆነችውን ጢሮስን ያጠፋት በባሕር ላይ ያስገነባው ዝነኛ መተላለፊያ በተሠራበት ወቅት ነው፤ እስክንድር ከተማይቱን ያላንዳች ምሕረት በእሳት ያጋያት ሲሆን ይህም ዘካርያስ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።a—ዘካ. 9:2-4
5 መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚያሳየው ከሁሉ የበለጠው አሳማኝ ማስረጃ ግን መሲሑን፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በሚመለከት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ሲሆን የሚከተሉትን ጥቅሶች በማወዳደር ይህን ማየት ይቻላል:- ዘካርያስ 9:9ን ከማቴዎስ 21:4, 5 እና ከዮሐንስ 12:14-16፤ ዘካርያስ 12:10ን ከዮሐንስ 19:34-37፤ እንዲሁም ዘካርያስ 13:7ን ከማቴዎስ 26:31 እና ከማርቆስ 14:27 ጋር አወዳድር። በተጨማሪም በዘካርያስ 8:16 እና ኤፌሶን 4:25፤ በዘካርያስ 3:2 እና ይሁዳ 9 እንዲሁም በዘካርያስ 14:5 እና ይሁዳ 14 መካከል ያሉትን ተመሳሳይነቶች ልብ ማለት ይገባል። በእርግጥም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚታየው ስምምነት በጣም የሚያስደንቅ ነው!
6 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ከምዕራፍ 9 በኋላ የመጽሐፉ አጻጻፍ ስልት መቀየሩ ይኸኛውን ክፍል የጻፈው ዘካርያስ አለመሆኑን እንደሚጠቁም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የአጻጻፉ ስልት የተለወጠው መልእክቱም በመለወጡ ነው። የመጀመሪያዎቹ ስምንት ምዕራፎች ያተኮሩት በዘካርያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች በወቅቱ በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ላይ ሲሆን ከ9 እስከ 14 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ደግሞ ነቢዩ ወደፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች ጽፏል። ማቴዎስ፣ ዘካርያስ የጻፋቸውን ቃላት ጠቅሶ ኤርምያስ እንደተናገራቸው አድርጎ የጻፈበትን ምክንያት በተመለከተ አንዳንዶች ጥያቄ አንስተዋል። (ማቴ. 27:9፤ ዘካ. 11:12) የኋለኞቹ ነቢያት የሚባሉት መጻሕፍት አሁን ባለን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሚገኘው በኢሳይያስ ሳይሆን በኤርምያስ የሚጀምሩበት ወቅት የነበረ ይመስላል፤ በመሆኑም ማቴዎስ ዘካርያስን ሲጠቅስ “ኤርምያስ” ብሎ የተናገረው፣ በአይሁዳውያን ዘንድ የሚሠራበትን በአንድ ክፍል ውስጥ ያሉትን ቅዱሳን ጽሑፎች በአጠቃላይ በመጀመሪያው መጽሐፍ ስም የመጥራት ልማድ ተከትሎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ራሱ መጻሕፍት በመባል የሚታወቁትን ክፍሎች ሁሉ አጠቃልሎ ሲናገር “በመዝሙር መጻሕፍት” ብሏል።—ሉቃስ 24:44b
7 የዘካርያስ መጽሐፍ፣ እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ድረስ ባለው ክፍል ውስጥ ዳንኤል እና ሕዝቅኤል ካዩአቸው ጋር የሚመሳሰሉና በጥቅሉ ሲታይ ከቤተ መቅደሱ ዳግመኛ መገንባት ጋር የተያያዙ ስምንት ተከታታይ ራእይዎች ይዟል። ከእነዚህ ራእይዎች ቀጥሎ ከልብ የመነጨ አምልኮን፣ ተመልሶ መቋቋምንና የይሖዋን የጦርነት ቀን የሚመለከቱ አዋጆችና ትንቢቶች ይገኛሉ።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
23 የዘካርያስን ትንቢት የሚያጠኑና የሚያሰላስሉበት ሁሉ እምነት የሚያጠነክር እውቀት ያገኙበታል። ዘካርያስ፣ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” [NW] በሚለው መጠሪያ ከ50 ጊዜ በላይ የተጠቀመ ሲሆን ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደሚዋጋላቸውና እንደሚጠብቃቸው እንዲሁም በሚያስፈልጋቸው መጠን መንፈሱን እንደሚሰጣቸው ገልጿል። የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት የሚሆን እንደ ተራራ የማይገፋ የሚመስል ተቃውሞ ባጋጠማቸው ጊዜ ዘካርያስ እንዲህ ብሏል:- “ለዘሩባቤል የተላከው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ‘በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። ‘ታላቅ ተራራ ሆይ፤ አንተ ምንድን ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ።’” ቤተ መቅደሱ በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ተጠናቀቀ። በተመሳሳይም ዛሬ በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ማስወገድ እንችላለን። ሁኔታው ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደተናገረው ነው:- “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህንን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም።”—ዘካ. 4:6, 7፤ ማቴ. 17:20
24 የዘካርያስ መጽሐፍ በምዕራፍ 13 ከቁጥር 2 እስከ 6 ላይ እስከ ዛሬም ድረስ የይሖዋ ድርጅት አንዱ መለያ ስለሆነው የታማኝነት ባሕርይ የሚገልጽ ምሳሌ ይዟል። እንዲህ ያለው ታማኝነት ከየትኛውም ሰብዓዊ ዝምድና ሌላው ቀርቶ ከቅርብ የሥጋ ዝምድና እንኳ የበለጠ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። አንድ ሰው በይሖዋ ስም በሐሰት ትንቢት ቢናገር ማለትም ከመንግሥቱ መልእክት ጋር የሚቃረን ነገር ቢናገርና በአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሰዎችን ለማሳሳት ቢሞክር የዚህ ሰው ቤተሰቦች ጉባኤው ያሳለፈውን ማንኛውንም የፍርድ ውሳኔ በታማኝነት መደገፍ ይገባቸዋል። በሐሰት ትንቢት የተናገረው የቅርብ ወዳጃችን ቢሆንም በኃጢአቱ እንዲያፍርና ልቡ እንዲቆስል ተመሳሳይ አቋም መውሰድ ይኖርብናል።
25 ቀደም ባሉት አንቀጾች ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ “ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ” ንጉሥ በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚገባ፣ ‘በሠላሳ ብር’ አልፎ እንደሚሰጥ፣ በሚያዝበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚበተኑና ተሰቅሎ እያለ ወታደሮቹ በጦር እንደሚወጉት በዘካርያስ መጽሐፍ ውስጥ በትክክል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ዘካ. 9:9፤ 11:12፤ 13:7፤ 12:10) በተጨማሪም ትንቢቱ የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚሠራውን ግለሰብ “ቅርንጫፍ” ብሎ ይጠራዋል። ኢሳይያስ 11:1-10ን፣ ኤርምያስ 23:5ን እና ሉቃስ 1:32, 33ን ስናወዳድር ይህ ቅርንጫፍ “በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል” የተባለለት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እንረዳለን። ዘካርያስ ይህን “ቅርንጫፍ” በተመለከተ “በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል” በማለት የተናገረ ሲሆን ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “ኢየሱስ . . . እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል” እንዲሁም ‘በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል’ በማለት ከጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ዘካ. 6:12, 13፤ ዕብ. 6:20፤ 8:1) በመሆኑም ትንቢቱ “ቅርንጫፍ” የተባለው በሰማያት በአምላክ ቀኝ ሊቀ ካህናትና ንጉሥ መሆኑን እንዲሁም ይሖዋ ከሁሉ በላይ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።”—ዘካ. 14:9
26 ነቢዩ ስለዚያ ጊዜ ሲናገር “በዚያን ቀን” እና “በዚያ ቀን” የሚሉትን ሐረጎች በአጠቃላይ ወደ 20 ጊዜ ገደማ ደጋግሞ የተጠቀመባቸው ሲሆን ትንቢቱን ሲደመድምም በእነዚህ አገላለጾች ተጠቅሟል። እነዚህ አገላለጾች ብዙ ጊዜ የተጠቀሱባቸውን ቦታዎች ስንመረምር፣ ይህ ቀን ይሖዋ የጣዖታትን ስም ከምድር የሚያጠፋበትና ሐሰተኛ ነቢያትን የሚያስወግድበት ጊዜ መሆኑን እንገነዘባለን። (13:2, 4) ይህ ቀን ይሖዋ ከጠበኞቹ ብሔራት ጋር የሚዋጋበትና በመካከላቸው ሽብር እንዲኖር በማድረግ እነርሱን ጠራርጎ የሚያጠፋበት እንዲሁም “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ተራራ ሸለቆ” በኩል ለሕዝቦቹ መጠጊያ የሚያዘጋጅበት ቀን ነው። (14:1-5, 13፤ 12:8, 9) አዎን፣ “ሕዝቡን የራሱ መንጋ አድርጎ በዚያ ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣ NW] ያድናቸዋል።” እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለሱ በታች ሆኖ ባልንጀራውን ይጋብዛል። (ዘካ. 9:16፤ 3:10፤ ሚክ. 4:4) ይህ ቀን የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በሕዝቦቹ ‘መካከል የሚኖርበት’ እንዲሁም ‘የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም የሚፈልቅበት’ ክብራማ ቀን ነው። ዘካርያስ “በዚያ ቀን” ስለሚሆኑት ነገሮች የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በሚመጣው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” በአምላክ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩትን ሁኔታዎች የሚጠቁሙ ናቸው።—ዘካ. 2:11፤ 14:8፤ ራእይ 21:1-3፤ 22:1
27 ይሖዋ “የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። እነሆ፣ መላዋ ምድር በዚህ መንገድ ትበለጽጋለች:- ‘ብዙ ሕዝብና ኃያላን መንግሥታት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ፤ ከየወገኑና ከየቋንቋው የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ ይዘው:- “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” ይሉታል።’ “በዚያ ቀን” በፈረሶች ሻኲራ ላይ እንኳ ሳይቀር “ቅድስና ለይሖዋ!” ተብሎ ይጻፋል። እነዚህ በጣም አስደሳች የሆኑ ትንቢቶች የይሖዋ ስም በመንግሥቱ ዘር አማካኝነት እንደሚቀደስ የሚገልጹ በመሆናቸው ብንመረምራቸው ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን!—ዘካ. 4:10፤ 8:22, 23፤ 14:20 NW
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 531 እና 1136
b ኢንሳይክሎፒድያ ጁዳይካ 1973፣ ጥራዝ 4 አምድ 828፤ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 1080-1081