ምዕራፍ 131
ምንም ጥፋት የሌለበት ንጉሥ በእንጨት ላይ ተሰቀለ
ማቴዎስ 27:33-44 ማርቆስ 15:22-32 ሉቃስ 23:32-43 ዮሐንስ 19:17-24
ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተቸነከረ
ከራሱ በላይ በተሰቀለው ምልክት የተነሳ አፌዙበት
ኢየሱስ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ሰጠ
ኢየሱስ ከከተማዋ ብዙም ወደማይርቅ ቦታ ተወሰደ፤ በዚያም እሱና ሁለት ዘራፊዎች ይሰቀላሉ። ጎልጎታ የሚባለው ይህ ስፍራ የራስ ቅል ቦታ የሚል ትርጉም አለው፤ ቦታው ‘ከሩቅ ይታያል።’—ማርቆስ 15:40
ሞት የተፈረደባቸው ሦስቱ ሰዎች ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ተደረገ። ከዚያም ከርቤና ሐሞት የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ ሰጧቸው። መጠጡን ያዘጋጁት የኢየሩሳሌም ሴቶች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ሮማውያንም ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ሥቃዩ እንዳይሰማቸው የሚያደርገው ይህ መጠጥ እንዳይሰጣቸው አይከለክሉም። ኢየሱስ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው ፈቃደኛ አልሆነም። ለምን? በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት አእምሮው እንዲደነዝዝ አልፈለገም፤ ንቁ ሆኖ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን ለመጠበቅ ቆርጧል።
ኢየሱስ እጆቹን ዘርግቶ በእንጨቱ ላይ ተጋደመ። (ማርቆስ 15:25) ከዚያም ወታደሮቹ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ምስማር ቸነከሩ፤ ምስማሮቹ ሥጋውንና ጅማቶቹን በስተው ሲገቡ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትላሉ። እንጨቱ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ሲደረግ ደግሞ የሰውነቱ ክብደት ምስማሮቹ በገቡባቸው ቦታዎች ላይ ስለሚያርፍ ሥቃዩ በጣም ይበረታል። ያም ቢሆን ኢየሱስ ወታደሮቹን አልተቆጣቸውም። ከዚህ ይልቅ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ሲል ጸለየ።—ሉቃስ 23:34
ሮማውያን ሞት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሠራውን ጥፋት የሚገልጽ ምልክት የማንጠልጠል ልማድ አላቸው። ጲላጦስ “የአይሁዳውያን ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሑፍ በመከራው እንጨት ላይ አንጠለጠለ። ምልክቱ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክኛ በመሆኑ አብዛኛው ሰው ሊያነበው ይችላል። ጲላጦስ ይህን ማድረጉ ኢየሱስን ላስገደሉት አይሁዳውያን ያለውን ንቀት ያሳያል። በዚህ የተበሳጩት የካህናት አለቆች ጲላጦስን “እሱ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” በማለት ተቃውሟቸውን ገለጹ። ጲላጦስ ግን በድጋሚ የእነሱ መሣሪያ መሆን ስላልፈለገ “እንግዲህ የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ።—ዮሐንስ 19:19-22
በንዴት የበገኑት ካህናት፣ ቀደም ሲል በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረቡትን የሐሰት ክስ እንደገና አነሱ። በመሆኑም በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ራሳቸውን እየነቀነቁ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ! እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ወርደህ ራስህን አድን” እያሉ ማፌዛቸውና መሳደባቸው የሚያስገርም አይደለም። በተመሳሳይም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት እርስ በርሳቸው “አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት ይውረድ” ተባባሉ። (ማርቆስ 15:29-32) ከተሰቀሉት መካከል ምንም ጥፋት የሌለበት ኢየሱስ ብቻ ቢሆንም በቀኙና በግራው የተሰቀሉት ዘራፊዎች እንኳ ሳይቀር ነቀፉት።
አራቱ ሮማውያን ወታደሮችም በኢየሱስ ላይ መቀለድ ጀመሩ። ወታደሮቹ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ሲጠጡ ቆይተው ሊሆን ይችላል፤ አሁን በኢየሱስ ላይ ለማፌዝ የወይን ጠጁን ወደ እሱ አቀረቡት፤ ኢየሱስ ወይኑን ተቀብሏቸው ሊጠጣ እንደማይችል ግልጽ ነው። ሮማውያኑ በኢየሱስ አናት ላይ የተንጠለጠለውን ምልክት እየጠቆሙ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ከሆንክ ራስህን አድን” በማለት ዘበቱበት። (ሉቃስ 23:36, 37) እስቲ አስበው! መንገድ፣ እውነትና ሕይወት መሆኑን ያስመሠከረው ሰው ግፍ እየተፈጸመበትና እየተፌዘበት ነው። ያም ቢሆን እያዩት ያሉትን አይሁዳውያን፣ የሚያፌዙበትን ሮማውያን ወታደሮች እንዲሁም እንጨት ላይ ከጎኑ የተሰቀሉትን ሁለት ወንጀለኞች ሳይነቅፍ የደረሰበትን መከራ በጽናት ተቋቋመ!
አራቱ ወታደሮች መደረቢያዎቹን ወስደው አራት ቦታ ቆራረጧቸው። ከዚያም የትኛውን እንደሚወስዱ ለመወሰን ዕጣ ተጣጣሉ። ኢየሱስ ከውስጥ የለበሰው ግን “ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ” ከፍተኛ ጥራት ያለው ልብስ ነው። ወታደሮቹ “ከምንቀደው ዕጣ ተጣጥለን ለማን እንደሚደርስ እንወስን” ተባባሉ። ይህን ሲያደርጉ “መደረቢያዎቼን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፉን ቃል ፈጽመዋል።—ዮሐንስ 19:23, 24፤ መዝሙር 22:18
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዘራፊዎቹ አንዱ ኢየሱስ በእርግጥም ንጉሥ መሆን እንዳለበት አስተዋለ። በመሆኑም ጓደኛውን እንዲህ ሲል ገሠጸው፦ “አንተ ራስህ ተመሳሳይ ፍርድ ተቀብለህ እያለ ትንሽ እንኳ አምላክን አትፈራም? እኛስ ላደረግነው ነገር የሚገባንን ቅጣት በሙሉ እየተቀበልን ስለሆነ በእኛ ላይ የተፈጸመው ፍርድ ተገቢ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም የሠራው ጥፋት የለም።” ቀጥሎም ኢየሱስን “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ተማጸነው።—ሉቃስ 23:40-42
ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መለሰለት፤ ኢየሱስ ‘ከእኔ ጋር በመንግሥቴ ትሆናለህ’ አላለውም። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ ለወንጀለኛው የሰጠው ተስፋ ለሐዋርያቱ ከገባው ቃል ይኸውም በመንግሥቱ ከእሱ ጋር በዙፋን እንደሚቀመጡ ከሰጣቸው ተስፋ የተለየ ነው። (ማቴዎስ 19:28፤ ሉቃስ 22:29, 30) ይሁንና ይህ አይሁዳዊ ወንጀለኛ፣ ይሖዋ መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ዘሮቻቸው እንዲኖሩበት በምድር ላይ ስላዘጋጀው ገነት ሰምቶ ሊሆን ይችላል። ዘራፊው የሞተው እንዲህ ያለ ተስፋ እንደተዘጋጀለት አውቆ ነው።