ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
በመከራ እንጨት ላይ የደረሰበት ሥቃይ
ከኢየሱስ ጋር ሁለት ዘራፊዎች ሊገደሉ እየተወሰዱ ነው። የሰዎቹ አጀብ ከከተማው እምብዛም ሳይርቅ ጎልጎታ ወይም የራስ ቅል የሚባል ሥፍራ ቆመ።
የእሥረኞቹ ልብስ ወለቀ። ከዚያም ከርቤ የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ ተሰጣቸው። የኢየሩሳሌም ሴቶች ያዘጋጁት መጠጥ ሳይሆን አይቀርም። ሮማውያኑም ቢሆኑ ይህን ሰውነት የሚያደነዝዘውን መጠጥ ለእሥረኞቹ አልከለከሉም። ኢየሱስ ግን ቀመሰውና ሊጠጣው አልወደደም። ለምን ቢባል እምነቱ በከፍተኛ ደረጃ በሚፈተንበት በዚህ ጊዜ ስሜቱን በሙሉ ለመቆጣጠር ስለፈለገ ነው።
አሁን ኢየሱስ እጆቹ ከአናቱ በላይ ተወጠሩና በእንጨቱ ላይ ተዘረጋ። ከዚያም ወታደሮቹ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ትላልቅ ሚስማሮች ቸነከሩበት። ሚስማሮቹ ጅማቱንና ሥጋውን እየበሱ ሲገቡ ኢየሱስ በሥቃይ ይቃትት ነበር። እንጨቱ ቀጥ ብሎ ሲቆም የሰውነቱ ክብደት ሚስማሩ የገባበትን ሥጋ ይበልጥ ስለሚያቆስለው የተሰማው ሥቃይ በጣም ከባድ ነበር። ቢሆንም ኢየሱስ ከመዛት ይልቅ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ለሮማውያኑ ወታደሮች ጸለየላቸው።
ጲላጦስ በምሰሶው ላይ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሕፈት ለጥፎ ነበር። ይህን የጻፈው ኢየሱስን ስለሚያከብረው ብቻ ሳይሆን የአይሁድ ካህናት ሳይወድ በግድ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ እንዲወሰንበት በማድረጋቸው ምክንያት በጣም ስለጠላቸው ጭምር ነበር። ስለዚህም ጲላጦስ ሰው ሁሉ እንዲያነበው ሲል በሶስት ቋንቋዎች፣ ማለትም በዕብራይስጥ፣ የመንግሥት ቋንቋ በሆነው በላቲንና በዘመኑ በብዛት ይሠራበት በነበረው በግሪክኛ ቋንቋ አስጻፈው።
ሊቃነ ካህናቱ፣ ቀያፋና ሐና ጭምር በነገሩ ተቆጡ። ይህ ስለ ኢየሱስ ጥሩነት የሚናገረው መግለጫ ሊቃነ ካህናቱ በዕለቱ ያገኙትን ድል የሚያበላሽባቸው ሆነ፣ በዚህም ምክንያት “እርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ” አሉት። ጲላጦስ ግን የካህናት መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ስለታከተው በቁርጠኝነትና በጥላቻ “የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” አላቸው።
አሁን ካህናቱ ከብዙ ሰዎች ጋር ሆነው በመስቀያው ቦታ ተሰበሰቡ። ካህናቱም የጽሕፈቱን ምሥክርነት ለማስተባበል ሞከሩ። ቀደም ሲል በአይሁድ ሸንጎ ተሰጥቶ የነበረውን የሐሰት ምሥክሮች ቃል ማስተጋባት ጀመሩ። መንገደኞች ራሳቸውን እየነቀነቁ በሟሽሟጠጥ “ቤተመቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው ራስህን አድን። የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ [ከመከራ እንጨት (አ.ዓ.ት)] ውረድ” ማለታቸው አያስደንቅም።
ካህናቱና ሃይማኖታዊ አጫፋሪዎቻቸው “ሌሎችን አዳነ፣ ራሱን ሊያድን አይችልም” እያሉ ተሳለቁበት። “የእሥራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን [ከመከራው እንጨት (አ.ዓ.ት)] ይውረድ፣ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኗል፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው” አሉ።
ወታደሮቹም በዚህ የመሳለቅ መንፈስ ተወሰዱና በኢየሱስ ላይ መቀለድ ጀመሩ። ኮምጣጣ ወይን ጠጅ በውሃ ጥም ወደተሰነጠቀው ከንፈሩ ሳያደርሱ ጠጋ አደረጉና እንዲጠጣ ሰጡት። “የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ ራስህን አድን” እያሉ ተገዳደሩት። በቀኝና በግራው የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንኳን ተዘባበቱበት። እስቲ ቆም ብለህ አስብ። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች በሙሉ የበለጠው፣ ፍጥረትን በሙሉ በመፍጠር ሥራ ከይሖዋ አምላክ ጋር የተካፈለው ኢየሱስ ይህን ሁሉ ውርደት በቆራጥነት ተሸከመ።
ወታደሮቹ የኢየሱስን መጎናጸፊያ ወሰዱና ለአራት ከፈሉት። ለማን እንደሚደርስ ለማወቅ እጣ ተጣጣሉ። እጀ ጠባቡ ግን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስለነበር አንድ ወጥ ነበር እንጂ የተሰፋ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ወታደሮቹ እርስ በርሳቸው “ለማን እንዲሆን በእርሱ እጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ስለዚህም ሳያውቁት “ልብሴን እርስ በእርስ ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም አደረጉ።
ከጊዜ በኋላ ከወንበዴዎቹ አንዱ ኢየሱስ በእውነት ንጉስ መሆን እንደሚኖርበት ተገነዘበ። ስለዚህም ጓደኛውን በመገሰጽ እንዲህ አለው፦ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው። ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም።” ከዚያም ወደ ኢየሱስ ዘወር ብሎ “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው።
ኢየሱስም መልሶ “ዛሬ እውነት እልሃለሁ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው። ይህም ቃሉ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛና ይህን ንሥሐ የገባ ክፉ አድራጊ ከሙታን አስነስቶ የአርማጌዶን ተራፊዎችና ጓደኞቻቸው በሚያዘጋጁአት ምድራዊ ገነት ውስጥ ሲያኖረው ይፈጸማል። ማቴዎስ 27:33-44፤ ማርቆስ 15:22-32፤ ሉቃስ 23:27, 32-43፤ ዮሐንስ 19:17-24
◆ ኢየሱስ ከርቤ የተቀላቀለበትን ወይን ጠጅ አልጠጣም ያለው ለምን ነበር?
◆ ኢየሱስ በተሰቀለበት እንጨት ላይ ጽሕፈት የተለጠፈው ለምን ነበር? በዚህስ ምክንያት በጲላጦስና በሊቃነ ካህናቱ መካከል ምን ውዝግብ ተነሳ?
◆ ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ እያለ ምን ተጨማሪ ስድብ ደረሰበት? ለዚህስ ምክንያት የሆነው ምን ሊሆን ይችላል?
◆ በኢየሱስ ልብስ ላይ በተፈጸመው ነገር ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው?
◆ ከወንበዴዎቹ አንዱ ምን የአቋም ለውጥ አደረገ? ኢየሱስ ጥያቄውን የሚፈጽምለት እንዴት ነው?