የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 62—1 ዮሐንስ
ጸሐፊው:- ሐዋርያው ዮሐንስ
የተጻፈበት ቦታ:- በኤፌሶን ወይም በአቅራቢያው
ተጽፎ ያለቀው:- በ98 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ለጽድቅ ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ይህም የኢየሱስን አስተሳሰብ በጥልቅ ማስተዋል እንዲችል ረድቶታል። በመሆኑም ስለ ፍቅር አበክሮ መግለጹ ምንም አያስገርመንም። ይህ ሲባል ግን ዮሐንስ ስሜታዊ ነበር ማለት አይደለም። ይልቁንም ኢየሱስ ‘የነጐድጓድ ልጅ [ቦአኔርጌስ]’ ሲል ጠርቶታል። (ማር. 3:17) ከዚህም ሌላ፣ ዮሐንስ ሦስቱን ደብዳቤዎቹን የጻፈው ስለ እውነትና ስለ ጽድቅ ጠበቃ በመሆን ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ሐዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ የተናገረለት ክህደት ብቅ ብሎ ነበር። ሦስቱ የዮሐንስ መልእክቶች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ‘የክፉውን’ ደባ ለመመከት በሚያደርጉት ውጊያ ጥንካሬ እንዲያገኙ አግዘዋቸው ስለነበር በእርግጥ ወቅታዊ ነበሩ ለማለት ይቻላል።—2 ተሰ. 2:3, 4፤ 1 ዮሐ. 2:13, 14፤ 5:18, 19
2 ከመልእክቶቹ ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው ደብዳቤዎቹ የተጻፉት ከማቴዎስና ከማርቆስ ወንጌሎች ብዙ ቆይተው እንዲሁም ጴጥሮስና ጳውሎስ በሚስዮናዊነት ሲያገለግሉ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች በኋላ ነው። በመሆኑም መልእክቶቹ በተጻፉበት ወቅት ከዚያ በፊት የነበሩት ሁኔታዎች እጅግ ተለውጠው ነበር። በደብዳቤዎቹ ውስጥ፣ የክርስቲያን ጉባኤ ገና ጨቅላ በነበረበት ወቅት ትልቅ ስጋት ፈጥሮ ስለነበረው ስለ አይሁድ እምነት የተጠቀሰ ነገር ካለመኖሩም ሌላ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ የተጠቀሰ አንድም ጥቅስ አናገኝም። በሌላ በኩል ግን ዮሐንስ ስለ “መጨረሻው ሰዓት” እንዲሁም “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” ስለ መኖራቸው ተናግሯል። (1 ዮሐ. 2:18) ዮሐንስ አንባቢዎቹን “ልጆቼ” እንደሚለው በመሰሉ አባባሎች የጠራቸው ሲሆን ራሱን ደግሞ “ሽማግሌው” ሲል ጠርቷል። (1 ዮሐ. 2:1, 12, 13, 18, 28፤ 3:7, 18፤ 4:4፤ 5:21፤ 2 ዮሐ. 1፤ 3 ዮሐ. 1) ይህ ሁሉ ሦስቱ ደብዳቤዎች የተጻፉት ከጊዜ በኋላ መሆኑን ያሳያል። አንደኛ ዮሐንስ 1:3, 4 የዮሐንስ ወንጌልም በተመሳሳይ ጊዜ መጻፉን የሚጠቁም ይመስላል። ሦስቱ የዮሐንስ መልእክቶች ሐዋርያው ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ማለትም በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በኤፌሶን አቅራቢያ እንደተጻፉ ይታመናል።
3 አራተኛውን ወንጌል የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። አንደኛ ዮሐንስ ከዚህ ወንጌል ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ መልእክቱን የጻፈው በእርግጥ ዮሐንስ መሆኑን ያረጋግጣል። ለምሳሌ ያህል፣ መልእክቱን የከፈተው ‘በአብ ዘንድ ለነበረውና ለእኛም ለተገለጠው ለዘላለም ሕይወት ቃል’ የዓይን ምሥክር እንደሆነ በመግለጽ ነው። እነዚህ ቃላት ከዮሐንስ ወንጌል መግቢያ ጋር አስገራሚ ተመሳሳይነት አላቸው። ሙራቶሪያን ፍራግመንት በመባል የሚታወቀው ሰነድም ይሁን እንደ ኢራኒየስ፣ ፖሊካርፕ እና ፓፒየስ ያሉት በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበሩ ጸሐፊዎች የመልእክቱን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።a ዩሲቢየስ (ከ260–342 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) እንደገለጸው ከሆነ የአንደኛ ዮሐንስ መልእክት ትክክለኛነት ፈጽሞ ጥያቄ ተነስቶበት አያውቅም።b ይሁንና አንዳንድ የጥንት ትርጉሞች በምዕራፍ 5 ቁጥር 7 መጨረሻና ቁጥር 8 መጀመሪያ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ መጨመራቸውን ልብ ልንለው ይገባል:- “በሰማይ የሚመሠክሩ ሶስት ናቸው እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። እሌህ ሶስትም አንድ ናቸው።” (የ1879 ትርጉም) ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ በማናቸውም በግሪክኛ በተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ የማይገኝ ሲሆን የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ ተብሎ የገባ መሆኑ ግልጽ ነው። ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ያዘጋጇቸውን ትርጉሞች ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ባሉት በብዙዎቹ ትርጉሞች ውስጥ ይህ ሐሳብ አይገኝም።—1 ዮሐ. 1:1, 2c
4 ዮሐንስ መልእክቱን የጻፈበት ምክንያት ‘ወዳጆቼ’ በማለት የጠራቸውን ‘ልጆቹን፣’ ከመካከላቸው ከወጡትና ከእውነት መንገድ ሊያስቷቸው ከሚሞክሩት “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” የሐሰት ትምህርት ለመታደግ ነበር። (2:7, 18) አምላክ ሚስጥራዊ የሆነ ልዩ እውቀት ሰጥቶናል የሚሉት የኖስቲሲዝም ትምህርት ተከታዮችን ጨምሮ የግሪካውያን ፍልስፍና ክርስቶስን በሚቃወሙት በእነዚህ ከሃዲዎች ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው አልቀረም።d ዮሐንስ፣ ስለ ሦስት ነገሮች ይኸውም ስለ ኃጢአት፣ ስለ ፍቅርና ስለ ክርስቶስ ተቃዋሚዎች በሰፊው በመጻፍ ክህደትን በጽኑ ተቃውሟል። ኃጢአትን አስመልክቶ ያሰፈረው ሐሳብም ሆነ ስለ ኃጢአት የቀረበውን የኢየሱስን መሥዋዕት በመደገፍ የተናገረው ነገር፣ እነዚህ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ኃጢአት እንደሌለባቸውና የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደማያስፈልጋቸው በመናገር ራሳቸውን ያመጻድቁ እንደነበር ይጠቁማል። በራሳቸው ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮረው ‘እውቀታቸው’ ራስ ወዳዶች እንዲሆኑና ለሌሎች ፍቅር እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። ዮሐንስም በተደጋጋሚ ጊዜ ስለ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር አበክሮ በመግለጽ ይህንን ሁኔታ አጋልጧል። ከዚህም በላይ ዮሐንስ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ መሆኑንና ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ሕልውና እንደነበረው እንዲሁም በአምላክ ለሚያምኑ የሰው ልጆች መዳን ለማስገኘት ሲል ሥጋ በመልበስ ወደ ምድር የመጣ የአምላክ ልጅ መሆኑን በመግለጽ የሐሰት ትምህርታቸውን ተቃውሟል። (1:7-10፤ 2:1, 2፤ 4:16-21፤ 2:22፤ 1:1, 2፤ 4:2, 3, 14, 15) ዮሐንስ እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎች “የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” በማለት በድፍረት የጠራቸው ሲሆን የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁባቸውን በርካታ መንገዶችም ዘርዝሯል።—2:18, 22፤ 4:3
5 በመልእክቱ ላይ የየትኛውም ጉባኤ ስም አለመጠቀሱ ደብዳቤው ለመላው የክርስቲያን ማኅበር የተጻፈ መሆኑን ያሳያል። በደብዳቤው መክፈቻም ሆነ መደምደሚያ ላይ የሰላምታና የመሰነባበቻ ቃላት አለመኖራቸው ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። እንዲያውም አንዳንዶች ይህ መልእክት፣ ደብዳቤ ሳይሆን አንድን ርዕሰ ጉዳይ በሚመለከት የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ እንደሆነ ይገልጻሉ። በመልእክቱ ውስጥ በብዛት የሚገኘው “እናንተ” የሚለው የብዙ ቁጥር አመልካች ተውላጠ ስም፣ ጸሐፊው መልእክቱን የጻፈው ለግለሰብ ሳይሆን ለአንድ ቡድን መሆኑን ያሳያል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊርቋቸው የሚገቡ “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” ይገኛሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በመጀመሪያ የሰሙትን እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የሚለውን መልእክት’ አጥብቀው መከተል የሚገባቸው ሲሆን የአምላክን ቃል በድፍረት በመናገርና ጽድቅን በማድረግ ከእሱ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር እንዲሁም በእውነተኛው ትምህርት መመላለሳቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። (2:18፤ 3:11፤ 2:27-29) ከዚህም በተጨማሪ ‘ከሥጋ ምኞት፣ ከዐይን አምሮትና ከኑሮ ትምክሕት’ ራቁ የሚለው ማስጠንቀቂያም እጅግ ጠቃሚ ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ፍቅረ ንዋይንና የዓለምን ክፉ ምኞት በሚያበረታቱት በእነዚህ ነገሮች ተጠምደዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘላለም እንደሚኖር’ ስለሚያውቁ ከዓለምና ከምኞቱ ይርቃሉ። ዓለማዊ ምኞቶች፣ አክራሪነትና ጥላቻ በበዛበት በዚህ ዘመን ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅና ፈቃዱን መፈጸም እጅግ ጠቃሚ ነው!—2:15-17
12 የአንደኛ ዮሐንስ መልእክት፣ ከአብ በሚመነጨው ብርሃንና ከክፉው በሚወጣው እውነትን በሚያዳፍን ጨለማ መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ መግለጹ እጅግ ይጠቅመናል። ከዚህም በተጨማሪ ሕይወት ሰጪ በሆነው የአምላክ ትምህርትና የክርስቶስ ተቃዋሚዎች በሚያስፋፉት የሚያባብል ውሸት እንዲሁም ከአብና ከልጁ ጋር አንድነት ያላቸው ሰዎች የሞሉበት ጉባኤ ባለው ፍቅርና ‘ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ መካከል ወጡ’ የተባለላቸው ሰዎች በሚያንጸባርቁት እንደ ቃየን ያለ የጥላቻ መንፈስ መካከል ያለውን ልዩነት ዘርዝሯል። (2:19፤ 1:5-7፤ 2:8-11, 22-25፤ 3:23, 24, 11, 12) ለእነዚህ ነገሮች ያለን አድናቆት ‘ዓለምን የማሸነፍ’ ልባዊ ምኞት ሊያሳድርብን ይገባል። ይሁንና ዓለምን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ጠንካራ እምነት በማዳበርና ‘አምላክን በመውደድ’ ነው። አምላክን መውደድ ሲባል ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።—5:3, 4
13 ‘አምላክን መውደድ’—ይህ ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ብርቱ ኃይል በመልእክቱ ውስጥ በግሩም ሁኔታ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል! በምዕራፍ 2 ላይ ዓለምን በመውደድና አብን በመውደድ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት በጉልህ ተቀምጧል። ትንሽ አለፍ ብሎም ‘አምላክ ፍቅር መሆኑ’ ተገልጾልናል። (4:8, 16) ይህ ፍቅር በተግባር የሚገለጽ ነው! አብ ‘ልጁን የዓለም አዳኝ’ አድርጎ መላኩ የዚህ ፍቅር የላቀ መግለጫ ነው። (4:14) ይህን ማወቃችን “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” ከሚሉት የሐዋርያው ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ልባዊ የአድናቆት ስሜትና ከፍርሃት ነፃ የሆነ ፍቅር ሊያሳድርብን ይገባል። (4:19) እኛም እንዲሁ አብና ልጁ ያላቸው ዓይነት ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ማለትም ፍቅራችን በተግባር የሚገለጽና የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እንድናደርግ የሚገፋፋን መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ ነፍሱን ለእኛ ሲል አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ “እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።” አዎን፣ ወንድሞቻችንን በቃል ብቻ ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” ለመውደድ ከአንጀት የመነጨ የርኅራኄ ስሜት ሊኖረን ይገባል። (3:16-18) የዮሐንስ መልእክት በግልጽ እንደሚያሳየው፣ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ያደረጉ ሰዎችን ከአብና ከልጁ ጋር ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው በትክክለኛ እውነት ላይ የተመሠረተው ይህ ዓይነቱ ፍቅር ነው። (2:5, 6) ዮሐንስ “እኛም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከእውነተኛው አምላክ ጋር አንድነት አለን” ሲል የተናገረው በዚህ ግሩም የፍቅር ማሰሪያ ውስጥ ላሉት የመንግሥቱ ወራሾች ነው።—5:20 NW
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጂ. ደብልዩ. ብሩምሌይ የተዘጋጀው ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ጥራዝ 2, 1982 ገጽ 1095–1096
b ዚ ኢክሊዚያስቲከል ሂስትሪ፣ III, XXIV, 17
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 1019
d በጄ. ዲ. ዳግላስ የተዘጋጀው ኒው ባይብል ዲክሽነሪ ሁለተኛ እትም፣ 1986 ገጽ 426, 604