-
‘የሚያሳድገው አምላክ’ ነው!መጠበቂያ ግንብ—2008 | ሐምሌ 15
-
-
የሚተኛው ዘሪ
13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ዘር ስለሚዘራው ሰው የተናገረውን ምሳሌ በአጭሩ ግለጽ። (ለ) በዘሪው የተመሰሉት እነማን ናቸው? ዘሩስ ምን ያመለክታል?
13 በማርቆስ 4:26-29 ላይ ደግሞ ስለ ሌላ ዘሪ የሚናገር ምሳሌ እናገኛለን። ምሳሌው እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ አጨዳ ይጀምራል።”
14 በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ዘሪ ማን ነው? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ይህ ዘሪ ኢየሱስን እንደሚያመለክት ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘እንደሚተኛና እሱ ሳያውቅ ዘሩ እንደሚበቅል’ መናገር ይቻላል? ኢየሱስ ዘሩ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም! በመጀመሪያው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ዘሪ ሁሉ ይሄኛውም ዘሪ፣ የመንግሥቱን ዘር በቅንዓት የሚሰብኩትን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ያመለክታል። መሬት ላይ የተዘራው ዘር ደግሞ የሚሰብኩትን ቃል የሚያመለክት ነው።b
15, 16. ኢየሱስ፣ አንድ ዘር ቃል በቃል ስለማደጉም ሆነ መንፈሳዊ እድገት ስለማድረግ የትኛውን እውነታ ጎላ አድርጎ ገልጿል?
15 ኢየሱስ፣ ዘሪው “ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል” ብሏል። ዘሪው እንዲህ ማድረጉ ግዴለሽ መሆኑን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአብዛኞቹን ሰዎች የተለመደ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳይ አገላለጽ ነው። ሐሳቡ የተገለጸበት መንገድ፣ ቀጣይነት ያለውን ሂደት ይኸውም ዘሪው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቀን እየሠራ ማታ ይተኛ እንደነበር የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወነውን ነገር ሲገልጽ “ያ ዘር በቅሎ ያድጋል” ብሏል። አክሎም ይህ ሁኔታ የተከናወነው ዘሪው “ሳያውቅ” መሆኑን ገልጿል። እዚህ ላይ ሊጎላ የተፈለገው ነገር እድገቱ የተካሄደው ‘በራሱ’ መሆኑ ነው።c
16 ኢየሱስ እዚህ ላይ ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? የተዘራው ዘሩ በማደጉና ሂደቱም የተከናወነው ቀስ በቀስ በመሆኑ ላይ ትኩረት እንዳደረገ ልብ በል። “ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች።” (ማር. 4:28) ይህ እድገት የሚከናወነው ቀስ በቀስ እንዲሁም ደረጃ በደረጃ ነው። እድገቱን ማፋጠን አይቻልም። መንፈሳዊ እድገትንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ባለው ግለሰብ ልብ ውስጥ እውነት የሚያድገው ይሖዋ በፈቀደው ጊዜ ደረጃ በደረጃ ነው።—ሥራ 13:48፤ ዕብ. 6:1
17. የእውነት ዘር ፍሬ ሲያፈራ የሚደሰቱት እነማን ናቸው?
17 ዘሪው “ፍሬው እንደ በሰለ” በአጨዳው የሚካፈለው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ የመንግሥቱ እውነት በአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ እንዲያድግ ሲያደርግ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ቀስ በቀስ እድገት በማድረግ ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ሕይወታቸውን ለእሱ ይወስናሉ። ከዚያም ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት በውኃ ይጠመቃሉ። ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ወንድሞች፣ ቀስ በቀስ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መቀበል ይችላሉ። አንድን ደቀ መዝሙር ያስገኘውን ዘር መጀመሪያ የዘራው ሰውም ሆነ በዚህ ሥራ በቀጥታ ያልተካፈሉት ሌሎች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የመንግሥቱን ዘር ያጭዳሉ። (ዮሐንስ 4:36-38ን አንብብ።) በእርግጥም ‘ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ ይላቸዋል።’
-
-
‘የሚያሳድገው አምላክ’ ነው!መጠበቂያ ግንብ—2008 | ሐምሌ 15
-
-
b ከዚህ ቀደም በወጣ መጠበቂያ ግንብ ላይ፣ ዘሩ ወደ ጉልምስና ማደግ የሚያስፈልጋቸውን የግለሰብ ክርስቲያኖች ባሕርያት እንደሚያመለክት እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉ የተለያዩ ነገሮች በክርስቲያኖች ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ዘሩ እንደተበላሸ ወይም ፍሬው እንደበሰበሰ አለመገለጹን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ዘሩ ምንም ሳይሆን ወደ ጉልምስና ያድጋል።—የሰኔ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-19 (እንግሊዝኛ) እንዲሁም “መንግሥትህ ትምጣ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 96-99 ተመልከት።
c ከማርቆስ ወንጌል ሌላ ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ 12:10 ላይ ብቻ ሲሆን ጥቅሱም የብረቱ መዝጊያ “ራሱ ዐውቆ” እንደተከፈተ ይገልጻል።
-