በእርግጥ በምሥራቹ ታምናለህ?
“የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ።”—ማርቆስ 1:14, 15
1, 2. ማርቆስ 1:14, 15 የሚናገረው ስለምንድን ነው?
በ30 እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ከፍተኛ የስብከት ሥራ ጀመረ። “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል” እየሰበከ “ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” እያለ ያቀረበውን ጥሪ በርካታ የገሊላ ሰዎች በከፍተኛ ደስታ ተቀብለውታል።—ማርቆስ 1:14, 15
2 ኢየሱስ አገልግሎቱን የሚጀምርበትና ሰዎች መለኮታዊ ተቀባይነት የሚያስገኝላቸውን ምርጫ የሚያደርጉበት “ዘመን” ጀምሮ ነበር። (ሉቃስ 12:54-56) ንጉሥ እንዲሆን የተመረጠው ኢየሱስ በመምጣቱ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦ’ ነበር። የስብከት ሥራው ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ አነሳስቷቸዋል። ይሁን እንጂ ‘በወንጌል እንደሚያምኑ’ ያሳዩት እንዴት ነበር? እኛስ እንዴት ማሳየት እንችላለን?
3. ሰዎች በምሥራቹ እንደሚያምኑ ያሳዩት እንዴት ነው?
3 ሐዋርያው ጴጥሮስም ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ አሳስቧል። ጴጥሮስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ለነበሩት አይሁዳውያን “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” ብሏቸዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ንስሐ ገብተው በመጠመቅ የኢየሱስ ተከታዮች ሆነዋል። (ሥራ 2:38, 41፤ 4:4) በ36 እዘአ ንስሐ የገቡ አሕዛብ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። (ሥራ 10:1-48) በዘመናችንም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በምሥራቹ ላይ ያሳደሩት እምነት ኃጢአታቸውን ተናዝዘው ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ እያነሳሳቸው ነው። በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር ለመዳን የሚያበቃውን ምሥራች ተቀብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጽድቅን ይከተላሉ፤ እንዲሁም ከአምላክ መንግሥት ጎን ቆመዋል።
4. እምነት ምንድን ነው?
4 ይሁንና እምነት ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነትም ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 11:1) እምነት አምላክ በቃሉ አማካኝነት የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ የተፈጸሙ ያህል እርግጠኛ እንድንሆን ያስችለናል። የአንድ ንብረት ሕጋዊ ባለቤት መሆናችንን የሚያረጋግጥ ሠነድ የያዝን ያህል ነው። በተጨማሪም እምነት የማናያቸውን ነገሮች “የሚያስረዳ” ወይም በጥብቅ እንድናምን የሚያስችለን ማስረጃ ነው። ያገኘነው እውቀትና ልባችንን የሞላው የአድናቆት ስሜት በተስፋ የምንጠብቃቸውን ነገሮች ባናያቸውም እንኳ እውን እንደሆኑ አድርገን እንድናምንባቸው ያስችለናል።—2 ቆሮንቶስ 5:7፤ ኤፌሶን 1:18
እምነት ሊኖረን ይገባል!
5. እምነት ማዳበር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 መንፈሳዊ ፍላጎት ይዘን የምንወለድ ብንሆንም እንኳ እምነት ግን አብሮን የሚወለድ ባሕርይ አይደለም። እንዲያውም ‘እምነት ለሁሉ ሰው አይሆንም።’ (2 ተሰሎንቄ 3:1, 2) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች መውረስ እንዲችሉ እምነት ማሳየት አለባቸው። (ዕብራውያን 6:11, 12) ጳውሎስ በርካታ የእምነት ሰዎችን ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።” (ዕብራውያን 12:1, 2) ‘ቶሎ የሚከበን ኃጢአት’ የተባለው ምንድን ነው? እምነት የለሽ መሆን ብሎም ከዚህ በፊት የነበረንን እምነት ማጣት ነው። ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ‘ኢየሱስን በትኩረት መመልከት’ እና ምሳሌውን መከተል አለብን። በተጨማሪም የሥነ ምግባር ብልግናን መጥላት፣ የሥጋ ሥራዎችን መዋጋት እንዲሁም ከፍቅረ ነዋይ፣ ከዓለማዊ ፍልስፍናዎችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ ልማዶች መራቅ ይኖርብናል። (ገላትያ 5:19-21፤ ቆላስይስ 2:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10፤ ይሁዳ 3, 4) ከዚህም በላይ አምላክ ከእኛ ጋር እንደሆነና በቃሉ ውስጥ የሠፈረው ምክር በእርግጥ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ማመን ይኖርብናል።
6, 7. እምነታችን እንዲያድግ መጸለያችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
6 እምነት በራሳችን ጥረት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። እምነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም ኃይል ከሚያፈራቸው ፍሬዎች አንዱ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ታዲያ እምነታችን መጠናከር ቢያስፈልገው ምን ማድረግ አለብን? ኢየሱስ “እናንተ . . . ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” ብሏል። (ሉቃስ 11:13) አዎን፣ መንፈስ ቅዱስ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ሳይቀር የአምላክን ፈቃድ እንድናደርግ የሚያስችለንን እምነት ስለሚያፈራልን መንፈሱን ለማግኘት እንጸልይ።—ኤፌሶን 3:20
7 እምነታችን እንዲያድግ መጸለያችን ተገቢ ነው። ኢየሱስ በአንድ ልጅ ውስጥ ያደረውን ጋኔን ሊያስወጣ ሲል አባትየው “አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው” ሲል ተማጽኗል። (ማርቆስ 9:24) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “እምነት ጨምርልን” ብለዋል። (ሉቃስ 17:5) በመሆኑም ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን በመተማመን እምነት እንዲጨምርልን አምላክን እንጠይቅ።—1 ዮሐንስ 5:14
በአምላክ ቃል ማመን የግድ አስፈላጊ ነው
8. በአምላክ ቃል ማመናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተከታዮቹን “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:1) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአምላክና በልጁ እናምናለን። ይሁንና በአምላክ ቃልስ? መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለ ምክርና መመሪያ እንደያዘ ሙሉ በሙሉ አምነን ካጠናነውና በተግባር ካዋልነው በሕይወታችን ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል።—ዕብራውያን 4:12
9, 10. በያዕቆብ 1:5-8 ላይ የሚገኘውን ስለ እምነት የሚናገረውን ሐሳብ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
9 ከፍጽምና የራቅን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችን በመከራ የተሞላ ነው። ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ላይ እምነት ማሳደራችን በእርግጥ ጥቅም ያስገኝልናል። (ኢዮብ 14:1) ለምሳሌ ያህል የደረሰብንን ፈተና እንዴት መወጣት እንደምንችል አናውቅም እንበል። በዚህ ረገድ የአምላክ ቃል የሚከተለውን ምክር ይሰጠናል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።”—ያዕቆብ 1:5-8
10 ይሖዋ አምላክ ጥበብ እንደሚጎድለን አውቀን ብንለምነው አይነቅፈንም። ከዚህ ይልቅ ለፈተናው ተገቢ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። በእምነት ጓደኞቻችን አማካኝነት ወይም መጽሐፍ ቅዱስ በምናጠናበት ወቅት ሊጠቅሙን የሚችሉ ጥቅሶች እናገኝ ይሆናል። ወይም ደግሞ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በሌላ መንገድ አመራር ሊሰጠን ይችላል። ‘በምንም ሳንጠራጠር በእምነት ከለመንን’ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ፈተናዎችን መወጣት የምንችልበት ጥበብ ይሰጠናል። በነፋስ የተገፋ የባሕር ማዕበል ከመሰልን ከአምላክ አንዳች አገኛለሁ ብለን መጠበቅ አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም በጸሎትም ሆነ በሌሎች መንገዶች አልፎ ተርፎም በአምላክ ላይ ባለን እምነት ሁለት አሳብ እንዳለንና እንደምንወላውል ስለሚያሳይ ነው። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ቃልና ቃሉ በያዘው መመሪያ ላይ ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታና መመሪያ ልናገኝ የምንችልባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።
እምነትና ዕለታዊ ፍላጎቶች
11. በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነት የዕለት ፍላጎታችንን በተመለከተ ምን ዋስትና ይሰጠናል?
11 በአሁኑ ጊዜ ምግብና መጠለያ አጥተን በድህነት የምንኖር ብንሆንስ? በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነት ይሖዋ የዕለት ፍላጎቶቻችንን እንደሚያሟላልንና በአዲሱ ሥርዓት ለሚወድዱት ሰዎች ሁሉ የተትረፈረፈ ሥጋዊ ዝግጅት እንደሚያደርግላቸው በእርግጠኝነት እንድንጠባበቅ ያደርገናል። (መዝሙር 72:16፤ ሉቃስ 11:2, 3) ረሃብ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ነቢዩ ኤልያስ ምግብ እንዲያገኝ ባደረገው ዝግጅት ላይ ማሰላሰላችን ብርታት ሊሰጠን ይችላል። ከጊዜ በኋላ አምላክ አንዲት ሴት የነበራትን ዱቄትና ዘይት በተአምር እንዲበረክት በማድረግ እርሷ፣ ልጅዋና ኤልያስ በረሃብ እንዳይሞቱ ጠብቋቸዋል። (1 ነገሥት 17:2-16) በተመሳሳይም ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ተከብባ በነበረችበት ወቅት ይሖዋ ለነቢዩ ኤርምያስ የሚያስፈልገውን አሟልቶለታል። (ኤርምያስ 37:21) ኤርምያስም ሆነ ኤልያስ ያገኙት ምግብ ጥቂት ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ተንከባክቧቸዋል። በዛሬው ጊዜም በእሱ ለሚታመኑ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ያሟላላቸዋል።—ማቴዎስ 6:11, 25-34
12. እምነት መሠረታዊ ፍላጎታችን እንዲሟላልን የሚረዳን እንዴት ነው?
12 እምነት ማሳደራችንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋላችን ቁሳዊ ብልጽግና ባያስገኝልንም እንኳ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ሊያሟላልን ይችላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኞች፣ ትጉዎችና ታታሪዎች እንድንሆን ይመክረናል። (ምሳሌ 22:29፤ መክብብ 5:18, 19፤ 2 ቆሮንቶስ 8:21) ትጉ ሠራተኛ የሚል መልካም ስም ማትረፍ ያለውን ዋጋ አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። ጥሩ ሥራ በቀላሉ በማይገኝባቸው ቦታዎች እንኳ ጥሩ ችሎታ ያላቸው፣ ሐቀኛና ትጉ ሠራተኞች ከሌሎች የተሻለ ሥራ የማግኘት ዕድል አላቸው። እነዚህ ሰዎች ብዙ ቁሳዊ ሃብት ባይኖራቸውም አብዛኛውን ጊዜ መሠረታዊ ነገሮች የሚሟሉላቸው ከመሆኑም በላይ ጥረው ግረው ያገኙትን በመመገብ ይረካሉ።—2 ተሰሎንቄ 3:11, 12
እምነት የደረሰብንን ሐዘን ተቋቁመን እንድንኖር ይረዳናል
13, 14. የደረሰብንን ሐዘን ተቋቁመን እንድንኖር እምነት የሚረዳን እንዴት ነው?
13 የአምላክ ቃል የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ሐዘን ማስከተሉ እንደማይቀር ይገልጻል። ታማኙ የእምነት አባት አብርሃም ተወዳጅ ሚስቱ ሣራ በሞት ስትለየው አልቅሷል። (ዘፍጥረት 23:2) ዳዊት ልጁ አቤሴሎም መሞቱን ሲሰማ በሐዘን ምርር ብሎ አልቅሷል። (2 ሳሙኤል 18:33) ሌላው ቀርቶ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በወዳጁ በአልዓዛር ሞት አልቅሷል። (ዮሐንስ 11:35, 36) የምናፈቅረው ሰው በሞት ሲለየን በከፍተኛ ሐዘን ልንዋጥ እንችላለን። ሆኖም የአምላክ ቃል በያዛቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ሐዘኑን እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል።
14 ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሏል። (ሥራ 24:15) አምላክ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎችን በትንሣኤ ለማስነሳት ባደረገው ዝግጅት ማመን ይገባናል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አሁን በሞት አንቀላፍተው ያሉ ወደፊት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ እንዲሁም ያዕቆብና ልያ ይገኙበታል። (ዘፍጥረት 49:29-32) የምናፈቅራቸው ሰዎች ከሞት ተነስተው በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ራእይ 20:11-15) እስከዚያ ድረስ ግን እምነት የሚደርስብንን ሐዘን በሙሉ ባያስወግድልንም ሐዘናችንን መቋቋም እንድንችል ወደሚረዳን አምላክ እንድንቀርብ ያስችለናል።—መዝሙር 121:1-3፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3
እምነት የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸውን ያበረታል
15, 16. (ሀ) በእምነት የሚመላለሱ ክርስቲያኖች የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥማቸው መረበሽ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ያደረብንን የመንፈስ ጭንቀት ለመቋቋም ምን ማድረግ እንችላለን?
15 መጽሐፍ ቅዱስ በእምነት የሚመላለሱ ክርስቲያኖች በመንፈስ ጭንቀት ሊጠቁ እንደሚችሉም ያሳያል። ኢዮብ ከባድ ፈተና በደረሰበት ወቅት አምላክ እንደተወው ሆኖ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 29:2-5) ኢየሩሳሌምና ግንቦቿ መፈራረሳቸው ነህምያ በሐዘን እንዲዋጥ አድርጎት ነበር። (ነህምያ 2:1-3) ጴጥሮስ ኢየሱስን ከካደ በኋላ በተሰማው ከባድ ጸጸት ‘ምርር ብሎ አልቅሷል።’ (ሉቃስ 22:62) ጳውሎስ በተሰሎንቄ ጉባኤ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹን “የተጨነቁ ነፍሳትን አጽናኗቸው” ሲል አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW ) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ በእምነት የሚመላለሱ ክርስቲያኖች የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥማቸው መረበሽ አይኖርባቸውም። ታዲያ የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን?
16 የተለያዩ ከባድ ችግሮች ሊያጋጥሙንና በዚህም የተነሳ የመንፈስ ጭንቀት ሊያድርብን ይችላል። ሁኔታውን ልንወጣ እንደማንችለው እንደ አንድ ከባድ ችግር አድርገን ከማየት ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋል አንድ በአንድ መፍታት እንችል ይሆናል። ይህም ያደረብን የመንፈስ ጭንቀት ቀለል እንዲልልን ሊረዳን ይችላል። የምናከናውናቸውን ሥራዎች ሚዛናዊ ማድረግና በቂ እረፍት መውሰድም ሊረዳን ይችላል። በአምላክና በቃሉ ማመን እርሱ ለእኛ እንደሚያስብልን ያለንን ትምክህት ስለሚያጠናክርልን መንፈሳዊ ደኅንነት እንደሚያስገኝልን የተረጋገጠ ነው።
17. ይሖዋ እንደሚያስብልን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
17 ጴጥሮስ “በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት የሚያጽናና ዋስትና ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፣ የወደቁትንም ያነሣቸዋል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 145:14) እነዚህ የተስፋ ቃሎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው በእምነት ልንቀበላቸው ይገባል። አልፎ አልፎ የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥመን ቢችልም ጭንቀታችንን በሙሉ በሰማይ በሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ላይ መጣል እንደምንችል ማወቃችን ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነው!
እምነትና ሌሎች ፈተናዎች
18, 19. እምነት በሽታን ተቋቁመን እንድናሳልፍና የታመሙ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንድናጽናና የሚረዳን እንዴት ነው?
18 የምናፈቅራቸው ሰዎች ወይም እኛ ራሳችን ከባድ ሕመም ሲያጋጥመን እምነታችን ሊፈተን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አፍሮዲጡ፣ ጢሞቴዎስና ጥሮፊሞስ የመሳሰሉ ክርስቲያኖች በተአምራዊ መንገድ እንደተፈወሱ ባይናገርም ይሖዋ ሕመማቸውን መቋቋም የሚያስችላቸውን ኃይል እንደሰጣቸው አያጠራጥርም። (ፊልጵስዩስ 2:25-30፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:20) በተጨማሪም መዝሙራዊው “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ” ሰውን በተመለከተ “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 41:1-3) መዝሙራዊው በተናገራቸው ቃላት መሠረት የታመሙ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
19 መንፈሳዊ እርዳታ መስጠት የምንችልበት አንደኛው መንገድ የታመሙ ወንድሞቻችንን በጸሎታችን በማሰብና ከእነርሱ ጋር አብረናቸው በመጸለይ ነው። ተአምራዊ ፈውስ እንዲያገኙ ባንጸልይም የሚደርስባቸውን ሥቃይ መቋቋም የሚችሉበትን አቅምና መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲሰጣቸው መጠየቅ እንችላለን። ይሖዋ ብርታት የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ‘በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ የማይልበትን’ ጊዜ በተስፋ በመጠባበቅ እምነታቸው ሊጠናከር ይችላል። (ኢሳይያስ 33:24) ትንሣኤ ባገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነትና በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ታዛዥ የሰው ልጆች ከኃጢአት፣ ከበሽታና ከሞት ለዘለቄታው እንደሚገላገሉ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ‘ደዌያችንን ሁሉ የሚፈውሰው’ ይሖዋ ይህን የመሰለ ታላቅ ተስፋ ስለሰጠን እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 103:1-3፤ ራእይ 21:1-5
20. እምነት ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣውን “የጭንቀት ቀን” በጽናት እንድንወጣ ይረዳናል ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
20 እምነት ጤንነታችንና ጉልበታችን እያሽቆለቆለ የሚሄድበትን ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣውን “የጭንቀት ቀን” በጽናት ማሳለፍ እንድንችልም ይረዳናል። (መክብብ 12:1-7) በመሆኑም በመካከላችን የሚገኙ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች “አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ . . . በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፣ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ” ብሎ በእርጅና ዘመኑ እንደዘመረው መዝሙራዊ መጸለይ ይችላሉ። (መዝሙር 71:5, 9) አምላክን በማገልገል በርካታ ዓመታት አሳልፈው በእርጅና ዕድሜያቸው ላይ እንደሚገኙ ብዙ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ሁሉ መዝሙራዊውም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተሰምቶት ነበር። በይሖዋ ላይ ካላቸው እምነት የተነሳ ዘላለማዊ ክንዶቹ ምንጊዜም ድጋፍ እንደሚሆኗቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።—ዘዳግም 33:27
በአምላክ ቃል ላይ ያላችሁን እምነት አጥብቃችሁ ያዙ
21, 22. በአምላክ ላይ ያለን እምነት ወደ እርሱ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?
21 በምሥራቹና በጠቅላላው የአምላክ ቃል ላይ እምነት ማሳደራችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። (ያዕቆብ 4:8) ሉዓላዊ ገዣችን መሆኑ የሚያጠያይቅ ባይሆንም ፈጣሪያችንና አባታችንም ነው። (ኢሳይያስ 64:8፤ ማቴዎስ 6:9፤ ሥራ 4:24) መዝሙራዊው “አባቴ አንተ ነህ፣ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 89:26) እኛም በይሖዋና በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ላይ እምነት ካሳደርን እርሱን ‘የመድኃኒታችን መጠጊያ’ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። እንዴት ያለ አስደሳች መብት ነው!
22 ይሖዋ በመንፈስ ለተወለዱትና የእነርሱ ተባባሪ ለሆኑት ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች አባት ነው። (ሮሜ 8:15) ደግሞም በሰማይ በሚኖረው አባታችን ላይ ያለን እምነት አያሳፍረንም። ዳዊት “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ብሏል። (መዝሙር 27:10) ከዚህ በተጨማሪ “እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም” የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል።—1 ሳሙኤል 12:22
23. ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ ዝምድና እንዲኖረን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
23 እርግጥ ነው፣ ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ የሆነ ዝምድና እንዲኖረን ከፈለግን በምሥራቹ ላይ እምነት ማሳደርና ቅዱሳን ጽሑፎች በትክክል የአምላክ ቃል እንደሆኑ አድርገን መቀበል ይኖርብናል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) በይሖዋ ላይ ፍጹም እምነት ሊኖረንና ቃሉ መንገዳችንን እንዲያበራልን መፍቀድ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:105፤ ምሳሌ 3:5, 6) በርኅራኄው፣ በምሕረቱና በሚሰጠን ድጋፍ ላይ ተመክተን ወደ እርሱ በጸሎት ስንቀርብ እምነታችን ያድጋል።
24. ሮሜ 14:8 ምን የሚያጽናና ተስፋ ይዞልናል?
24 እምነት ራሳችንን ለአምላክ ለዘላለም እንድንወስን አነሳስቶናል። ብንሞትም እንኳ ራሳችንን የወሰንን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት አለን። አዎን፣ “በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።” (ሮሜ 14:8) ትምክህታችንን በአምላክ ቃል ላይ በመጣልና በምሥራቹ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር ይህን የሚያጽናና ተስፋ በልባችን ጠብቀን እንኑር።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• እምነት ምንድን ነው? ይህ ባሕርይ ሊኖረን የሚገባውስ ለምንድን ነው?
• በምሥራቹና በጠቅላላው የአምላክ ቃል ላይ እምነት ማሳደራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• እምነት ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?
• እምነታችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርምያስና ኤልያስ እምነት ስለነበራቸው ይሖዋ ደግፏቸዋል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ፣ ጴጥሮስና ነህምያ ጠንካራ እምነት ነበራቸው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ ዝምድና እንዲኖረን በምሥራቹ ማመን ይኖርብናል