ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
‘በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ጊዜ ይመጣል።’—ዮሐንስ 5:28, 29
1. ሙሴ እየነደደ ከነበረው ቁጥቋጦ ውስጥ ምን የሚያስደንቅ ነገር ሲነገር ሰማ? ከብዙ ጊዜ በኋላ እነዚህን ቃላት በድጋሚ የተናገረው ማን ነው?
ከዛሬ 3,500 ዓመታት በፊት እጅግ እንግዳ የሆነ አንድ ነገር ተከሰተ። ሙሴ በኮሬብ ተራራ አቅራቢያ የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ፣ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል ከተያያዘው ቁጥቋጦ መካከል የይሖዋ መልአክ ተገለጠለት። የዘፀአት መጽሐፍ “ሙሴም ቊጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ” በማለት ይዘግባል። ከዚያም ከቁጥቋጦው ውስጥ ስሙ ሲጠራና “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” ተብሎ ሲነገር ሰማ። (ዘፀአት 3:1-6) ይህ ከሆነ ከብዙ ጊዜ በኋላ ማለትም በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በድጋሚ ተናገረ።
2, 3. (ሀ) አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ምን ሽልማት ይጠብቃቸዋል? (ለ) የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
2 ኢየሱስ በትንሣኤ ከማያምኑ አንዳንድ ሰዱቃውያን ጋር እየተወያየ ሳለ እንዲህ አላቸው:- “ሙሴ ስለ ቊጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’ በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤ ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።” (ሉቃስ 20:27, 37, 38) ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ በፊት የሞቱት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከአምላክ አመለካከት አንጻር ሕያው መሆናቸውን በእነዚህ ቃላት አረጋግጧል። ልክ እንደ ኢዮብ እነርሱም ‘የግዳጃቸውን’ ማለትም በሞት አንቀላፍተው የሚቆዩበትን ዘመን ፍጻሜ ይጠብቃሉ። (ኢዮብ 14:14 NW) እነዚህ ሰዎች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ያገኛሉ።
3 በሰው ዘር ታሪክ በሙሉ ስለሞቱት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱም ትንሣኤ ያገኛሉ? የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ከማየታችን በፊት ሰዎች ሲሞቱ ወዴት እንደሚሄዱ የአምላክ ቃል የሚናገረውን እንመልከት።
ሙታን የት ናቸው?
4. (ሀ) ሰዎች ሲሞቱ ወዴት ይሄዳሉ? (ለ) ሲኦል ምንድን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል። የሞቱ ሰዎች በሲኦል እሳት አይቃጠሉም ወይም ደግሞ ያልተጠመቁ ሰዎች ነፍሳት ገነት ውስጥ እንዳይገቡ ታግደው አይሠቃዩም፤ በአጭር አነጋገር ሰዎች ሲሞቱ ወደ አፈር ይመለሳሉ። በመሆኑም የአምላክ ቃል በሕይወት ያሉትን ሰዎች “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና” በማለት ይመክራል። (መክብብ 9:5, 10፤ ዘፍጥረት 3:19) “ሲኦል” የሚለውን ቃል የማያውቁ በርካታ ሰዎች አሉ። ይህ ቃል ዕብራይስጥኛ ሲሆን የቃሉ መገኛ በትክክል አይታወቅም። በርካታ ሃይማኖቶች ሙታን በሕይወት እንዳሉ ያስተምራሉ፤ ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል በሲኦል ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሞቱና ምንም ነገር እንደማያውቁ ይናገራል። ሲኦል የሰው ልጆች መቃብር ነው።
5, 6. ያዕቆብ በሞተበት ጊዜ ወዴት ሄደ? በዚያስ እነማን ነበሩ?
5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሲኦል” የሚለው ቃል ተጠቅሶ የምናገኘው በዘፍጥረት 37:35 ላይ ነው። ያዕቆብ ጠፍቶ የነበረው የሚወደው ልጁ ዮሴፍ የሞተ ስለመሰለው ከሐዘኑ መጽናናት ባለመቻሉ እንዲህ አለ:- “በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] እወርዳለሁ።” ያዕቆብ መሞትና በሲኦል ውስጥ መግባት ተመኝቶ ነበር። ይህ ከሆነ ከብዙ ጊዜ በኋላ በአካባቢው ረሃብ በመከሰቱ ዘጠኙ የያዕቆብ ትልልቅ ልጆች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ መሄድ ነበረባቸው፤ በዚህ ጊዜ ታናሽ ወንድማቸውን ብንያምን ይዘውት ሊሄዱ ፈለጉ። ያዕቆብ ግን “ልጄ አብሮአችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቶአል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፣ ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] ታወርዱታላችሁ” በማለት ከለከላቸው። (ዘፍጥረት 42:36, 38) እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ሞትን ከሲኦል ጋር አያያዙት እንጂ ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት አልገለጹም።
6 ዮሴፍ ከጊዜ በኋላ በግብጽ ውስጥ የምግብ አስተዳዳሪ እንደሆነ የዘፍጥረት መጽሐፍ ይዘግባል። በመሆኑም ያዕቆብ ከዮሴፍ ጋር ለመገናኘት ወደ ግብጽ በማምራት 147 ዓመት ሆኖት እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በዚያው ምድር ተቀመጠ። መሞቻው ሲቃረብ ልጆቹ አስከሬኑን ከነዓን በሚገኘው ማክፌላ ዋሻ እንዲቀብሩ ጠየቃቸው። (ዘፍጥረት 47:28፤ 49:29-31፤ 50:12, 13) በዚህ መንገድ ያዕቆብ ከአባቱ ከይስሐቅና ከአያቱ ከአብርሃም ጋር አብሮ ተቀበረ።
‘ወደ ወገኖቻቸው ተሰበሰቡ’
7, 8. (ሀ) አብርሃም ሲሞት ወዴት ሄደ? አብራራ። (ለ) ሌሎች ሰዎችም ሲሞቱ ወደ ሲኦል እንደገቡ የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 ይሖዋ ለአብርሃም የገባለት ቃል እንደሚፈጸም ካረጋገጠለትና ዘሩ እንደሚበዛ ተስፋ ከሰጠው በኋላ እርሱ ምን እንደሚገጥመው እንዲህ በማለት ነገረው:- “አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ።” (ዘፍጥረት 15:15) ይህም በትክክል ተፈጽሟል። ዘፍጥረት 25:8 ስለ አብርሃም ሲናገር “ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ” ይላል። ወገኖቹ የተባሉት እነማን ናቸው? በዘፍጥረት 11:10-26 ላይ የአብርሃም ቅድመ አያቶች፣ ከኖህ ልጅ ከሴም ጀምሮ በቅደም ተከተል ተዘርዝረዋል። አብርሃም በሞተበት ጊዜ የተሰበሰበው በሞት አንቀላፍተው በሲኦል ውስጥ ከሚገኙት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ነው።
8 “ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ” የሚለው አነጋገር በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። የአብርሃም ልጅ እስማኤልና የሙሴ ወንድም አሮን ሲሞቱ ሲኦል ውስጥ ገብተው ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል። (ዘፍጥረት 25:17፤ ዘኍልቍ 20:23-29) ሙሴም እንዲሁ መቃብሩን ማንም አይወቀው እንጂ ሲኦል ውስጥ ገብቷል። (ዘኍልቍ 27:13፤ ዘዳግም 34:5, 6) በተጨማሪም እስራኤላውያንን ለመምራት በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱና በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድ በሙሉ ሞቶ ወደ ሲኦል ወርዷል።—መሳፍንት 2:8-10
9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “ሲኦል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና “ሔድስ” የሚለው ግሪክኛ ቃል ተመሳሳይ ቦታን እንደሚያመለክቱ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በሲኦል ወይም በሔድስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
9 ይህ ከሆነ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ዳዊት በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ነገሠ። እርሱም በሞተበት ጊዜ “ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ” ተብሎ ተገልጿል። (1 ነገሥት 2:10) ዳዊት ሲኦል ውስጥ ገብቷል? የሚገርመው ነገር በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ዳዊት ሞት አንስቶ በመዝሙር 16:10 ላይ የሚገኘውን “በሲኦል ውስጥ አትተወኝም” የሚለውን ጥቅስ ጠቀሰ። ጴጥሮስ በዚያን ጊዜም ቢሆን ዳዊት በመቃብሩ ውስጥ እንዳለ ከተናገረ በኋላ እነዚህ ቃላት በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ እንዲህ በማለት ገለጸ:- “ይህንን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም እንደማይበሰብስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ። ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን።” (የሐዋርያት ሥራ 2:29-32) በጥንቱ ቅጂ ላይ ብንመለከት፣ ጴጥሮስ እዚህ ላይ የተጠቀመው “ሲኦል” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር አቻ ትርጉም ያለውን “ሔድስ” የሚለውን ግሪክኛ ቃል ነው። በመሆኑም በሔድስ ውስጥ እንደሚገኙ የተነገረላቸው ሙታን በሲኦል ውስጥ ናቸው ከተባለላቸው ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ትንሣኤ እስከሚያገኙ ድረስ በሞት እንዳንቀላፉ ይቆያሉ።
በሲኦል ውስጥ ዓመጸኞች አሉ?
10, 11. አንዳንድ ዓመጸኞች በሞቱበት ጊዜ ወደ ሲኦል ወይም ወደ ሔድስ ሄደዋል የምንለው ለምንድን ነው?
10 እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብጽ ወጥተው በበረሃ በሰፈሩበት ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ዓመጽ ቀስቅሰው ነበር። ሙሴ ሕዝቡ የዓመጹ መሪ ከነበሩት ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን እንዲለይ አሳሰበ። እነዚህ ዓመጸኞች ሳያስቡት ሊሞቱ ነበር። ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ:- “እነዚህ ሰዎች እንደማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ቢሆኑና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ብቻ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ እኔን እግዚአብሔር አልላከኝም። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።” (ዘኍልቍ 16:29, 30) ስለዚህ ምድር አፏን ከፍታ የዋጠቻቸውም ሆኑ እሳት ከሰማይ ወርዳ የበላቻቸው ቆሬና ከእርሱ ጋር የተባበሩት 250 ሰዎች በሙሉ ሲኦል ወይም ሔድስ ውስጥ ገብተዋል።—ዘኍልቍ 26:10
11 ንጉሥ ዳዊትን የረገመው ሳሚ በተተኪው ንጉሥ ሰሎሞን ቅጣቱን ተቀብሏል። ዳዊት “በደል እንደሌለበት ሰው አትተወው፤ ጥበበኛ ነህና መደረግ ያለበትን ታውቃለህ፤ ሽበቱን በደም ወደ መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] አውርድ” በማለት ሰሎሞንን አዝዞት ነበር። ከዚያም ሰሎሞን ሳሚን እንዲገድል በናያስን አዘዘው። (1 ነገሥት 2:8, 9, 44-46) ሌላው የበናያስ ሰይፍ ሰለባ የሆነው ደግሞ የቀድሞው የእስራኤል ሠራዊት አለቃ የነበረው ኢዮአብ ነው። “ከነሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ]” አልወረደም። (1 ነገሥት 2:5, 6, 28-34) እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች “ክፉዎች ተመልሰው ወደ ሲኦል ይወርዳሉ፤ እግዚአብሔርን የሚዘነጉ ሕዝቦችም ሁሉ እንደዚሁ” የሚለውን ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን መዝሙር እውነተኝነት ያረጋግጣሉ።—መዝሙር 9:17
12. አኪጦፌል ማን ነበር? በሞተበትስ ጊዜ ወዴት ሄደ?
12 የዳዊት የግል አማካሪ የሆነ አኪጦፌል የሚባል ሰው ነበር። ይህ ሰው የሚሰጠው ምክር ልክ ከይሖዋ እንደመጣ ተደርጎ ይታይ ነበር። (2 ሳሙኤል 16:23) የሚያሳዝነው እምነት ይጣልበት የነበረው ይህ አገልጋይ ከሐዲ ሆነና በዳዊት ልጅ በአቤሴሎም የሚመራው የመንግሥት ግልበጣ እንቅስቃሴ ደጋፊ ሆነ። ዳዊት ይህንን ክህደት በተዘዋዋሪ መንገድ ለመጥቀስ ፈልጎ ይመስላል እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤ ቢሆንማ ኖሮ በታገሥሁት ነበር፤ የሚጠላኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤ ቢሆንማ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር። . . . ሞት ሳይታሰብ ድንገት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በመካከላቸው አድራለችና።” (መዝሙር 55:12-15) አኪጦፌልና ተባባሪዎቹ በሞቱበት ጊዜ ወደ ሲኦል ሄደዋል።
በገሃነም ውስጥ ያሉት እነማን ናቸው?
13. ይሁዳ ‘የጥፋት ልጅ’ የተባለው ለምንድን ነው?
13 እስቲ የዳዊትን ሁኔታ በታላቁ ዳዊት በኢየሱስ ላይ ከደረሰው ነገር ጋር እናወዳድር። ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ አኪጦፌል ከሐዲ ሆኗል። የይሁዳ የክህደት ተግባር ከአኪጦፌል ድርጊት እጅግ በጣም የከፋ ነበር። ምክንያቱም የካደው የአምላክን አንድያ ልጅ ነው። የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያጠናቅቅ ባቀረበው ጸሎት ላይ ስለ ተከታዮቹ እንዲህ በማለት ለይሖዋ ተናግሯል:- “እኔ ከእነርሱ ጋር ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።” (ዮሐንስ 17:12) እዚህ ላይ ኢየሱስ ይሁዳን ‘የጥፋት ልጅ’ ያለው፣ ይህ ሰው ሲሞት የትንሣኤ ተስፋ እንደሌለው ለማመልከት ነው። ይሁዳ፣ አምላክ ለትንሣኤ ከሚያስባቸው ሰዎች መካከል አይደለም። የሄደው ወደ ሲኦል ሳይሆን ወደ ገሃነም ነው። ገሃነም ምንድን ነው?
14. ገሃነም ምንን ያመለክታል?
14 ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ደቀ መዛሙርታቸውን ሁሉ ‘የገሃነም ልጆች’ ስለሚያደርጉ አውግዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:15) በዚያ ዘመን በሞት የሚቀጡ ወንጀለኞች ተገቢ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሊደረግላቸው እንደማይገባ ስለሚታመን አስከሬናቸው በሄኖም ሸለቆ በሚገኘው የቆሻሻ መጣያ ይጣል ነበር፤ ሕዝቡም ይህንን ቦታ በሚገባ ያውቀዋል። ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ብሎ በተራራው ስብከቱ ላይ ስለ ገሃነም ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 5:29, 30) ገሃነምን በመጥቀስ የሰጠው ትምህርት ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው ለአድማጮቹ ግልጽ ነበር። ገሃነም፣ የትንሣኤ ተስፋ የሌለው ጥፋትን ያመለክታል። በኢየሱስ ዘመን ከኖረው ከአስቆሮቱ ይሁዳ በተጨማሪ፣ ሲሞቱ ሲኦል ወይም ሔድስ ውስጥ ሳይሆን ገሃነም ውስጥ የገቡ ሌሎች ሰዎች አሉ?
15, 16. በሞቱበት ጊዜ ወደ ገሃነም የሄዱ ሰዎች እነማን ናቸው? ወደዚያስ የሄዱት ለምንድን ነው?
15 የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹም ነበሩ። ኃጢአት የሠሩት ሆን ብለው ነው። በፊታቸው የዘላለም ሕይወት ወይም የሞት ምርጫ ቀርቦላቸው ነበር። የሆነ ሆኖ አምላክን ባለመታዘዝ ከሰይጣን ጋር ወገኑ። በሞቱበት ጊዜ ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም የማግኘት ተስፋ አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደ ገሃነም ሄደዋል።
16 የአዳም የመጀመሪያ ልጅ ቃየን ወንድሙን አቤልን ገደለና ኮብላይ ሆነ። ሐዋርያው ዮሐንስ ቃየንን “የክፉው ወገን” በማለት ገልጾታል። (1 ዮሐንስ 3:12) ቃየን በሞተበት ጊዜ እንደ ወላጆቹ ገሃነም ገብቷል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። (ማቴዎስ 23:33, 35) የቃየን ሁኔታ ከጻድቁ ከአቤል ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው! “አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:4) አዎን፣ አቤል በአሁኑ ጊዜ በሲኦል ሆኖ ትንሣኤ የሚያገኝበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ነው።
‘የመጀመሪያው’ እና “የተሻለው” ትንሣኤ
17. (ሀ) በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” ወደ ሲኦል የሚሄዱት እነማን ናቸው? (ለ) በሲኦልና በገሃነም ውስጥ ያሉት ሙታን ምን ይጠብቃቸዋል?
17 ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ያነበቡ ሰዎች በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” የሚሞቱ ሰዎች ሁኔታ ምን ይሆን ብለው ይጠይቁ ይሆናል። (ዳንኤል 8:19) ራእይ ምዕራፍ 6 በመጨረሻው ዘመን ስለሚጋልቡ አራት ፈረሰኞች ይዘግባል። የሚገርመው ነገር ከእነዚህ ፈረሰኞች ውስጥ የመጨረሻው ጋላቢ ሞት ተብሏል፤ ከኋላውም ሲኦል ወይም ሔድስ ይከተለው ነበር። ስለዚህ ከሲኦል ፊት የሚጋልበው ፈረሰኛ በሚፈጽመው ድርጊት ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው በሞት የሚቀጩ በርካታ ሰዎች፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ በሲኦል ሆነው ይጠባበቃሉ። (ራእይ 6:8) በሲኦል (በሔድስ) እና በገሃነም ውስጥ ያሉት ሙታን ምን ይጠብቃቸዋል? በአጭር አነጋገር በሲኦል ውስጥ ያሉ ትንሣኤ ያገኛሉ፤ በገሃነም ውስጥ ያሉ ደግሞ ለዘላለም ይጠፋሉ ወይም ከህልውና ውጪ ይሆናሉ።
18. “በመጀመሪያው ትንሣኤ” ተካፋይ የሚሆኑት ተስፋቸው ምንድን ነው?
18 ሐዋርያው ዮሐንስ “በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ” በማለት ጽፏል። “በመጀመሪያው ትንሣኤ” ተካፋይ የሚሆኑት ከክርስቶስ ጋር የሚነግሡት ከሆኑ የቀረው የሰው ዘር ምን ተስፋ አለው?—ራእይ 20:6
19. አንዳንዶች ‘የተሻለው ትንሣኤ’ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
19 የአምላክ አገልጋዮች ከሆኑት ከኤልያስና ከኤልሳዕ ዘመን ጀምሮ፣ ተአምር በሆነው ትንሣኤ አማካኝነት ሰዎች እንደገና ሕይወት አግኝተዋል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተርኳል:- “ሴቶች ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም።” አቋማቸውን ጠብቀው የጸኑት እነዚህ ታማኝ ሰዎች፣ ለጥቂት ዓመታት ብቻ ኖረው የሚሞቱበትን ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ትንሣኤ በተስፋ ይጠባበቁ ነበር! እውነትም ‘የተሻለ ትንሣኤ’ ይከናወናል።—ዕብራውያን 11:35
20. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?
20 ይሖዋ ይህንን ክፉ ዓለም ከማጥፋቱ በፊት ለእርሱ ታማኝ እንደሆንን ብንሞት፣ “የተሻለውን ትንሣኤ” የማግኘት የተረጋገጠ ተስፋ ይኖረናል። ይህ ትንሣኤ የተሻለ የተባለው የዘላለም ሕይወት ተስፋንም ስለሚጨምር ነው። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ትንሣኤ የተዘጋጀበት ዓላማ በይበልጥ ይብራራል። በተጨማሪም የትንሣኤ ተስፋ አቋማችንን ጠብቀን እንድንጸና እንዲሁም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ይብራራል።
ታስታውሳለህ?
• ይሖዋ “የሕያዋን አምላክ” እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው?
• በሲኦል ውስጥ ያሉ ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
• በገሃነም ውስጥ ያሉ ሙታን መጨረሻቸው ምንድን ነው?
• አንዳንዶች ‘የተሻለው ትንሣኤ’ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ሲኦል የገቡ ሁሉ ልክ እንደ አብርሃም ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ ይጠብቃሉ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳም፣ ሔዋን፣ ቃየንና የአስቆሮቱ ይሁዳ ገሃነም የገቡት ለምንድን ነው?