ምዕራፍ 55
ለጉባኤህ ድጋፍ ማድረግ የምትችልባቸው መንገዶች
በዓለም ዙሪያ በሺዎች በሚቆጠሩ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን በደስታ እያገለገሉ ይገኛሉ። የሚሰጣቸውን ትምህርትና መመሪያ በአድናቆት የሚቀበሉ ከመሆኑም ሌላ ጉባኤውን መደገፍ ያስደስታቸዋል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል?
1. ጊዜህንና ጉልበትህን ተጠቅመህ ጉባኤውን መደገፍ የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ሁላችንም ጉባኤውን በተለያዩ መንገዶች መርዳት እንችላለን። ለምሳሌ በጉባኤህ ውስጥ በዕድሜ የገፉ ወይም የታመሙ አሉ? ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ልትረዳቸው ትችላለህ? አሊያም የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎች ገዝቶ እንደማምጣት ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንደማገዝ ባሉ ሌሎች መንገዶች ድጋፍ ልታደርግላቸው ትችል ይሆን? (ያዕቆብ 1:27ን አንብብ።) የስብሰባ አዳራሻችንን በማጽዳቱ ወይም በመጠገኑ ሥራም እርዳታ ልናበረክት እንችላለን። እነዚህን ነገሮች እንድናደርግ ማንም አያስገድደንም። ለአምላክና ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ‘በገዛ ፈቃዳችን ራሳችንን እንድናቀርብ’ ያነሳሳናል።—መዝሙር 110:3
የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤውን መርዳት የሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ብቃቱን ያሟሉ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ፣ በኋላም ሽማግሌ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። ወንድሞችም ሆኑ እህቶች አቅኚ በመሆን የስብከቱን ሥራ በትጋት መደገፍ የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ቦታዎችን በመገንባቱ ሥራ ሊያግዙ ወይም እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው ጉባኤዎች ተዛውረው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
2. ገንዘባችንን እና ንብረታችንን ተጠቅመን ጉባኤውን መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው?
‘ባሉን ውድ ነገሮች ይሖዋን ማክበር’ እንችላለን። (ምሳሌ 3:9) ገንዘባችንን እና ንብረታችንን ተጠቅመን ጉባኤውንም ሆነ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ መደገፍ መቻላችን ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማናል። (2 ቆሮንቶስ 9:7ን አንብብ።) የምናደርገው መዋጮ አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳትም ይውላል። ብዙ ወንድሞችና እህቶች በቋሚነት ‘የተወሰነ ገንዘብ በማስቀመጥ’ መዋጮ ያደርጋሉ። (1 ቆሮንቶስ 16:2ን አንብብ።) መዋጮ ለማድረግ በአምልኮ ቦታዎቻችን የሚገኙ የመዋጮ ሣጥኖችን ወይም donate.jw.orgን መጠቀም እንችላለን። ይሖዋ ገንዘባችንን እና ንብረታችንን ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ለእሱ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት አጋጣሚ ሰጥቶናል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ለጉባኤው ድጋፍ ማድረግ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።
3. ገንዘባችንን እና ንብረታችንን ተጠቅመን ጉባኤውን መደገፍ እንችላለን
ይሖዋና ኢየሱስ በደስታ የሚሰጡ ሰዎችን ይወዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አቅሟ የፈቀደውን ያህል መዋጮ ላደረገች አንዲት ድሃ መበለት ያለውን አድናቆት ገልጿል። ሉቃስ 21:1-4ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋን ለማስደሰት ብዙ ገንዘብ መዋጮ ማድረግ አለብን?
ይሖዋና ኢየሱስ በራሳችን ተነሳስተን መዋጮ ስናደርግ ምን ይሰማቸዋል?
መዋጯችን ጥቅም ላይ የሚውለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የምናደርገው መዋጮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎችን ለመደገፍ የሚውለው እንዴት ነው?
4. በፈቃደኝነት መርዳት እንችላለን
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች የአምልኮ ቦታቸውን ጥሩ አድርገው ለመያዝ የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ገንዘብ በማዋጣት ብቻ አልነበረም። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 34:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
እያንዳንዱ እስራኤላዊ የአምልኮ ቦታውን ወይም የይሖዋን ቤት ጥሩ አድርጎ በመያዝ ረገድ ምን እርዳታ ያበረክት ነበር?
የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹን እስራኤላውያን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት እንደሆነ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የስብሰባ አዳራሻችንን በንጽሕና መያዛችንና መጠገናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አንተ መርዳት የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
5. ወንድሞች በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለማገልገል ጥረት ማድረግ ይችላሉ
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ወንዶች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ጉባኤውን ለመርዳት ጥረት እንዲያደርጉ ያበረታታል። እንዲህ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ ራያን ጉባኤውን ይበልጥ ለመርዳት ምን አድርጓል?
መጽሐፍ ቅዱስ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል የትኞቹን ብቃቶች ማሟላት እንዳለባቸው ይናገራል። አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:1-13ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የይሖዋ ምሥክሮች ለሥራቸው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
ይሖዋ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን ተጠቅመን ጉባኤውን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።
ክለሳ
ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን ተጠቅመን ጉባኤውን መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው?
ገንዘባችንን ጉባኤውን ለመደገፍ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
ጉባኤውን በየትኞቹ መንገዶች መደገፍ ትፈልጋለህ?
ምርምር አድርግ
አምላክ በአሁኑ ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹ አሥራት እንዲያቀርቡ የማይጠብቅባቸው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ኃላፊነቶችን የሚሰጠው ለተጠመቁ ወንዶች ነው። ሆኖም አንዲት የተጠመቀች እህት እነዚህን ኃላፊነቶች መወጣት ቢኖርባትስ?
“በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት” (መጠበቂያ ግንብ የካቲት 2021)
ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች ለወንድሞቻቸው ጽሑፎች ለማድረስ ሲሉ ምን መሥዋዕትነት ይከፍላሉ?
ለሥራችን የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኝበት መንገድ ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው እንዴት ነው?
“የይሖዋ ምሥክሮች ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)