የአንባብያን ጥያቄዎች
ቶቴ (በዚያን ጊዜ) የሚለው የግሪክኛ ቃል ቀጥሎ የሚፈጸምን ነገር ለማስታወቅ እንደሚሠራበት እረዳለሁ። ታዲያ ማቴዎስ 24:9 “በዚያን ጊዜ [ቶቴ] ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል” ሲል በሉቃስ 21:12 ላይ የሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ “ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል” የሚለው ለምንድን ነው?
ቶቴ የሚለው ቃል ቀጥሎ የሚፈጸምን ማለትም ተከታታይን ነገር ለማስታወቅ ሊሠራበት የሚችል መሆኑ እውነት ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን በዚህ መንገድ ብቻ ይጠቀምበታል ብለን ማሰብ የለብንም።
ባዎር አርንትና ግንግሪች የጻፉት ኤ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ኤንድ አዘር ኧርሊ ክርስቺያን ሊትሬቸር የተባለው መጽሐፍ ቶቴ የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሁለት መሠረታዊ መንገዶች እንደሚሠራበት ይጠቁማል።
አንዱ አጠቃቀም “በዚያን ጊዜ” ነው። ይህ “ቀደም ሲል የተፈጸመ ነገር” ሊሆን ይችላል። ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን የተሰጠው በማቴዎስ 2:17 ላይ “ያን ጊዜ . . . የተባለው ተፈጸመ” የሚለው ነው። ይህ ተከታታይ የሆነ ነገርን ሳይሆን ባለፈው ጊዜ በአንድ ወቅት የተፈጸመን ነገር ያመለክታል። በተመሳሳይም ቶቴ “ወደፊት የሚፈጸምን ነገር” ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በ1 ቆሮንቶስ 13:12 ላይ የሚገኘው “ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ” የሚለው ነው። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እዚህ ላይ ጳውሎስ ቶቴ የሚባለውን ቃል የተጠቀመበት ‘ወደፊት በአንድ በተወሰነ ነጥብ ላይ’ የሚል ትርጉም ለማስተላለፍ ነው።
በዚህ መዝገበ ቃላት መሠረት የቶቴ ሌላው አጠቃቀም “ቀጥሎ የሚሆነውን ነገር ማስታወቅ” ነው። ይህ መዝገበ ቃላት ሐዋርያት የመገኘቱን ምልክት አስመልክተው ለኢየሱስ ላቀረቡት ጥያቄ እርሱ የሰጣቸውን መልስ በያዙ ሦስት ዘገባዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጠናል።a መዝገበ ቃላቱ “ቀጥሎ የሚሆነውን ነገር በማስታወቅ” ረገድ ቶቴ ለሚለው ቃል አጠቃቀም ምሳሌዎች እንዲሆኑ ማቴዎስ 24:10, 14, 16, 30፤ ማርቆስ 13:14, 21ንና ሉቃስ 21:20, 27ን ጠቅሷል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመርመር በጊዜ ረገድ ተከታታይ የሆነውን ነገር ለመረዳት ያስችላል። በተጨማሪም ይህ ስለ ወደፊቱ ሁኔታዎች አፈጻጸም የሚገልጸውን የኢየሱስን ትንቢት ለመረዳት ይጠቅማል።
ሆኖም በእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ ቶቴ የተባለው ቃል በሚገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ ቀጥሎ የሚፈጸመውን ነገር ያስታውቃል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ የለብንም። ለምሳሌ ያህል በማቴዎስ 24:7, 8 ላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንደሚነሣና የምግብ እጥረቶችና የመሬት መንቀጥቀጦች እንደሚከሰቱ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረ እናነባለን። ቁጥር 9 “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ይቀጥላል። ስደት ከመጀመሩ በፊት አስቀድመው የተነገሩት ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረቶችና የመሬት መንቀጥቀጦች በሙሉ መከሰት አለባቸው ምናልባትም ከተፈጸሙ በኋላ ይቆማሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናልን?
ይህ ምክንያታዊ ካለመሆኑም በላይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በዚህ መንገድ እንደተፈጸመ የሚያረጋግጥ ነገር የለም። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ የአዲሱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት መስበክ ከጀመሩ በኋላ ከባድ ተቃውሞ እንዳጋጠማቸው የተናገረው ወዲያውኑ ነው ማለት ይቻላል። (ሥራ 4:5-21፤ 5:17-40) ኢየሱስ የተናገራቸው ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረቶችና የመሬት መንቀጥቀጦች በሙሉ ከመጀመሪያው ስደት በፊት ተፈጽመው ነበር ለማለት በፍጹም አንችልም። ከዚህ በተቃራኒ ስደቱ የመጣው አስቀድመው ከተነገሩት ብዙ ነገሮች “በፊት” ነው፤ ይህም “ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል” በማለት ሉቃስ ከገለጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ሉቃስ 21:12) ይህም በማቴዎስ 24:9 ላይ የገባው ቶቴ የሚለው ቃል “በዚያን ጊዜ” የሚል ትርጉም እንዳለው ያመለክታል። ጦርነት፣ የምግብ እጥረቶችና የመሬት መንቀጥቀጦች ባሉበት ወቅት ወይም በዚያን ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች ይሰደዳሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እነዚህ በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ ዘገባዎች በየካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14 እና 15 ላይ ባሉት አምዶች ላይ ቀርበዋል። “በዚያን ጊዜ” ተብሎ የተተረጎመው ቶቴ የተባለው ቃል በደማቅ ፊደል ተጽፏል።