“ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል?”
“እነሆ፣ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፣ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።”—ኢሳይያስ 42:9
1, 2. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ጠየቁ? (ለ) ኢየሱስ ስለ ጥምሩ ምልክት የሰጣቸው መልስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?
መለኮታዊ ትምህርት የሚመነጨው “በመጀመሪያ መጨረሻውን” ከሚናገረው ከይሖዋ አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 46:10) ቀደም ሲል የነበረው ርዕስ ሐዋርያት እንዲህ ያለውን ትምህርት ከኢየሱስ ለማግኘት ፈልገው “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው እንደጠየቁት ገልጿል።—ማርቆስ 13:4
2 ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መልስ ሲሰጥ የአይሁድ ሥርዓት ሊጠፋ መቃረቡን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎችን የሚያጠቃልል ጥምር ምልክት ሰጣቸው። ይህም ምልክት በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ በደረሰው ጥፋት ተፈጽሟል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ትንቢት ለብዙ ዘመናት የሚዘልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍጻሜ ነበረው። የተጠቀሱት ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ በ1914 ሲያበቁ የአሁኑ ክፉ ሥርዓት ‘በታላቁ መከራ’ ሊጠፋ መቃረቡን የሚያመለክቱ ከፍተኛ ስፋት ያላቸው ምልክቶች ይፈጸማሉ።a (ሉቃስ 21:24) እነዚህ ምልክቶች በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት የዓለም ጦርነቶችና ሌሎች ከፍተኛ እልቂት ያስከተሉ ነገሮች መፈጸማቸውን ሊመሰክሩ የሚችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በተጨማሪም እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች ከ33 እስከ 70 እዘአ የተፈጸመው ሁኔታ ትንቢታዊ ጥላ የሆነለት የኢየሱስ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜ መቅረቡን የሚያመለክቱ ናቸው።
3. ኢየሱስ ስለ ሌላ ምልክት ሲናገር ምን ተጨማሪ ክስተቶች እንደሚኖሩ ተነበየ?
3 የሉቃስ ወንጌል የተወሰኑትን የአሕዛብ ዘመናት ከጠቀሰ በኋላ በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ የተገለጹት ተመሳሳይ ዘገባዎች ጥምር ከሆነው ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት’ በተጨማሪ ተከታታይ ስለሆኑ ሌሎች ክስተቶች ይናገራሉ። (ማቴዎስ 24:3) (በገጽ 15 ላይ በጥቅሱ ውስጥ ይህ ነጥብ የተገለጸበት ቦታ በሁለት መስመሮች ተለይቷል።) ማቴዎስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፣ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።”—ማቴዎስ 24:29–31
መከራና በሰማይ አካላት ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች
4. ኢየሱስ በሰማይ አካላት ላይ ስለሚፈጸሙት ሁኔታዎች ስለተናገራቸው ነገሮች ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
4 ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው? ሦስቱም ወንጌሎች የተናገሩት በሰማይ ላይ ስለሚፈጸሙ ነገሮች ነው፦ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፣ ከዋክብትም ይወድቃሉ። እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት “ከመከራው” በኋላ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። ይህ ደግሞ ኢየሱስ የተናገረው በ70 እዘአ ስለተፈጸመው መከራ ነው ወይስ ገና ወደፊት በዚህ በኛ ዘመን ስለሚፈጸመው ታላቅ መከራ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።—ማቴዎስ 24:29፤ ማርቆስ 13:24
5. በዘመናችን ስለሚፈጸመው መከራ በፊት ምን ተብሎ ይታመን ነበር?
5 የአምላክ ሕዝቦች የአሕዛብ ዘመን ከተፈጸመበት ከ1914 ጀምሮ ስለ “ታላቁ መከራ” ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። (ራእይ 7:14) ለብዙ ዓመታት በዘመናችን የሚፈጸመው ታላቅ መከራ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ይጀምርና በመሀል ትንሽ ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን በሚሆነው ጦርነት’ እንደሚደመደም ያስቡ ነበር። ነገሩ እንዲህ ቢሆን ‘በሥርዓቱ መደምደሚያ’ በሚኖሩት የመሸጋገሪያ አሥርተ ዓመታት ምን ይፈጸማል?—ራእይ 16:14 የ1980 ትርጉም ፤ ማቴዎስ 13:39፤ 24:3፤ 28:20
6. ኢየሱስ የተነበያቸው በሰማይ አካላት ላይ የሚፈጸሙት ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር?
6 በመሀሉ ባለው የመሸጋገሪያ ጊዜ በተሰበሰቡት የአምላክ ሕዝቦች አማካኝነት የሚደረገውን የስብከት ሥራ የሚጨምረው ጥምሩ ምልክት ይታያል ተብሎ ይታሰብ ነበር። እንዲሁም በሰማይ አካላት ላይ እንደሚፈጸም የተተነበየው ነገር ከ1914– 1918 ካለው የመክፈቻ ጊዜ በኋላ በሚኖረው የመሸጋገሪያ ጊዜ ይፈጸማል ተብሎ ይታሰብ ነበር። (ማቴዎስ 24:29፤ ማርቆስ 13:24, 25፤ ሉቃስ 21:25) በሰማይ ላይ ቃል በቃል የሚፈጸሙ ነገሮች ማለትም በሕዋ ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ሮኬቶች፣ ኮስሚክ ወይም ጋማ ጨረሮች መሥራት እንዲሁም በጨረቃ ላይ ማረፍ መቻሉ ወይም የጦር ሰፈሮችን ለመመሥረት መታሰቡ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
7. ታላቁን መከራ በሚመለከት ምን የተስተካከለ ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር?
7 ይሁን እንጂ በጥር 15, 1970 መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ ኢየሱስ ትንቢት በተለይም ስለመጪው ታላቅ መከራ ስለሚናገረው ክፍል አዲስ ማብራሪያ ተሰጠ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸመውን ነገር ስንመለከት በዘመናችን የሚፈጸመው መከራ ከ1914–1918 ባለው ጊዜ ጀምሮ በመሀሉ በአሥር የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንደገና ሊጀምር እንደማይችል ተገለጸ። መጽሔቱ ሲደመድም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይህ ከእንግዲህ የማይሆነው ‘ታላቅ መከራ’ የዓለም ሐሰት ሃይማኖት ግዛት (ሕዝበ ክርስትና ጭምር) የምትጠፋበትና ወዲያው በመቀጠል ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ ጦርነት ’ በአርማጌዶን የሚደረግበት ስለሆነ ገና ወደፊት የሚፈጸም መከራ ነው።”
8. በዘመናችን ስለሚፈጸመው መከራ በተሰጠው የተስተካከለ ማብራሪያ መሠረት ማቴዎስ 24:29 የተብራራው እንዴት ነበር?
8 ይሁን እንጂ ማቴዎስ 24:29 ላይ የተገለጹት በሰማይ ላይ የሚታዩ ክስተቶች የሚፈጸሙት “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው” ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የግንቦት 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ እዚህ ላይ የተጠቀሰው መከራ በጥንት በ70 እዘአ የተደመደመው መከራ ነው የሚል ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ሆኖም በዘመናችን በሰማይ አካላት ላይ የሚፈጸመው ክስተት በ70 እዘአ ከተፈጸመ ነገር በኋላ “ወዲያው” ተፈጸመ ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? በአምላክ ዓይን በነዚህ ጊዜያት መካከል ያለፉት መቶ ዘመናት አጭር ናቸው የሚል ምክንያት ቀርቦ ነበር። (ሮሜ 16:20፤ 2 ጴጥሮስ 3:8) ይሁን እንጂ ይህንን ትንቢት፣ በተለይም የማቴዎስ 24:29–31ን ትንቢት ጠለቅ ብለን ከመረመርነው ከዚህ የተለየ ማብራሪያ ይጠቁመናል። ይህም መንገዳችን ‘ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ እንዴት እየበራ እንደመጣ’ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው። (ምሳሌ 4:18)b ለየት ያለ ማብራሪያ መስጠት ተገቢ የሆነበትን ምክንያት እስቲ እንመርመር።
9. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ በሰማይ አካላት ላይ ይፈጸማሉ ብሎ ለተናገራቸው ነገሮች ድጋፍ የሚሰጡት እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ፀሐይ እንደምትጨልም፣ ጨረቃም ብርሃንዋን እንደምትነሳና ከዋክብትም እንደሚወድቁ የሚገልጸውን ትንቢት የተናገረው ለአራት ሐዋርያቱ ነበር። እነዚህ ሐዋርያት አይሁዳውያን እንደመሆናቸው መጠን እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ ያስታውሱ ነበር። ለምሳሌ ያህል በሶፎንያስ 1:15 ላይ የአምላክ የፍርድ ቀን “የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን” ተብሎ ተጠርቷል። ብዙ ዕብራውያን ነቢያትም ፀሐይ እንደምትጨልም፣ ጨረቃ እንደማታበራና ከዋክብትም ብርሃናቸውን እንደማይሰጡ ተናግረዋል። እንዲህ ያለውን አነጋገር በባቢሎን፣ በኤዶም በግብጽና በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ላይ በተነገሩት መለኮታዊ መልእክቶች ውስጥ ማግኘት ይቻላል።—ኢሳይያስ 13:9, 10፤ 34:4, 5፤ ኤርምያስ 4:28፤ ሕዝቅኤል 32:2, 6–8፤ አሞጽ 5:20፤ 8:2, 9
10, 11. (ሀ) ኢዩኤል የሰማይ አካላትን አስመልክቶ ምን ተንብዮ ነበር? (ለ) በ33 እዘአ የተፈጸሙት የትኞቹ የኢዩኤል ትንቢት ክፍሎች ነበሩ? ያልተፈጸሙትስ?
10 ጴጥሮስና ሦስቱ ሐዋርያት ኢየሱስ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ በኢዩኤል ትንቢት ውስጥ ምዕራፍ 2:28–31 እና 3:15 ላይ የሚገኘውን ትንቢት አስታውሰው ይሆናል። እንዲህ ይላል፦ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ . . . በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፣ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።” “ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፣ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል።”
11 በሥራ 2:1–4 እና 14–21 ላይ እንደተገለጸው አምላክ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 120 በሚያክሉ ወንዶችና ሴቶች ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈሱን አፍስሶ ነበር። በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ ኢዩኤል አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ አሳውቋል። ይሁን እንጂ ‘ፀሐይ እንደምትጨልም፣ ጨረቃ ወደ ደም እንደምትለወጥና ከዋክብት ብርሃናቸውን እንደሚነሱ’ የሚናገሩት የኢዩኤል ቃላትስ? በ33 እዘአም ሆነ የአይሁድ ሥርዓት ከዚያ በኋላ በቆየባቸው የ30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይኼኛው የትንቢቱ ክፍል እንደተፈጸመ የሚያመለክት ምንም ማስረጃ አናገኝም።
12, 13. ኢዩኤል በሰማይ አካላት ላይ ይፈጸማሉ ሲል አስቀድሞ የተናገራቸው ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነበር?
12 ይህ የኋለኛው የኢዩኤል ትንቢት ክፍል ‘ከታላቁና ከሚያስፈራው የይሖዋ ቀን መምጣት’ ማለትም ከኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር የተዛመደ እንደሆነ ግልጽ ነው። የኅዳር 15, 1966 መጠበቂያ ግንብ በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ስለደረሰው መከራ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ያ ጊዜ በእርግጥም ለኢየሩሳሌምና ለልጆችዋ ‘የይሖዋ ቀን’ ነበር። በዚያ ቀን ብዙ ‘ደም፣ እሳትና የጭስ ጭጋግ’ ነበር። በቀን በከተማይቱ ላይ የወደቀውን ጭጋግ የሚያስወግድ ፀሐይ አልነበረም። የሌሊቱም ጨረቃ ሰላማዊና ብርማ ቀለም ያለው ብርሃን የሚሰጥ ሳይሆን የፈሰሰውን ደም የሚያስታውስ ነበር።”c
13 አዎን፣ እነዚህ ኢዩኤል የተነበያቸው በሰማይ አካላት ላይ የሚፈጸሙ ክስተቶች እስካሁን እንደተመለከትናቸው እንደ ሌሎቹ ትንቢቶች ሁሉ አምላክ ፍርዱን ባወረደበት በዚህ ጊዜም ተፈጽመዋል። የፀሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት መጨለም የአይሁድ ሥርዓት የመደምደሚያ ዘመን በቆየበት ወቅት በሙሉ የቆየ ነገር ሳይሆን ቅጣት አስፈጻሚው ኃይል በኢየሩሳሌም ላይ በዘመተ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ ክስተት ነበር። ይሖዋ አምላክ በአሁኑ ሥርዓት ላይ የሚፈጽመው ቅጣት በሚጀምርበት ጊዜም ይህ የኢዩኤል ትንቢት በታላቅ ሁኔታ ይፈጸማል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው።
በሰማይ አካላት ላይ ከሚፈጸመው ነገር በፊት የሚመጣው መከራ የትኛው ነው?
14, 15. የኢዩኤል ትንቢት ማቴዎስ 24:29ን እንድንረዳ ምን አስተዋፅዖ ያደርጋል?
14 የኢዩኤል ትንቢት (ተመሳሳይ አነጋገር ከተጠቀሙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር በሚስማማ መንገድ) ያገኘው የመጀመሪያ መቶ ዘመን ፍጻሜ በማቴዎስ 24:29 ላይ ያለው አነጋገር እንዲገባን ይረዳናል። ኢየሱስ ፀሐይ እንደሚጨልም፣ ጨረቃ ብርሃንዋን እንደምትነሳና ከዋክብት እንደሚረግፉ የተናገረው ትንቢት የሮኬቶችን መፈልሰፍ፣ ጨረቃ ላይ የማረፍንና የመሳሰሉትን የሥርዓቱ ፍጻሜ ዘመን በቆየባቸው በነዚህ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች እንደማያመለክት ግልጽ ነው። እርሱ የተናገረው ገና ወደፊት ከሚመጣው ጥፋት ማለትም ‘ታላቅና አስፈሪ በሆነው በይሖዋ ቀን’ ከሚፈጸሙ ነገሮች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሁኔታዎች ነበር።
15 ይህም በሰማይ አካላት ላይ የሚደርሰው ነገር “ከዚያች . . . መከራ በኋላ ወዲያው” እንዴት እንደሚፈጸም የተሻለ ግንዛቤ እንድናገኝ ይረዳናል። ኢየሱስ በ70 እዘአ ስለተፈጸመው መከራ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከረዥም ጊዜ በኋላ በመላው ዓለም ሥርዓት ላይ የሚመጣውና ‘የመገኘቱ’ ዘመን መደምደሚያ የሆነው ታላቅ መከራ የሚጀምርበትን ጊዜ ማመልከቱ ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ይህ መከራ ገና ወደፊት የሚፈጸም ነው።
16. ማርቆስ 13:24 የሚያመለክተው የትኛውን መከራ ነው? ለምን እንዲህ እንላለን?
16 በማርቆስ 13:24 ላይ ያለው “በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ” የሚለው ቃልስ? “በዚያን” እና “ከዚያ” የሚሉት ቃላት ኤኬይኖስ የተባለው የግሪክኛ ቃል እርባታዎች ሲሆኑ ይህ ቃል ወደፊት ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚፈጸምን ነገር የሚያመለክት አመልካች ተውላጠ ስም ነው። ኤኬይኖስ ከረዥም ጊዜ በፊት የተነገረን ወይም ቀደም ብሎ የተጠቀሰን ነገር ወይም ገና ወደፊት ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ የሚፈጸምን ነገር ለማመልከት ሊያገለግል ይችላል። (ማቴዎስ 3:1፤ 7:22፤ 10:19፤ 24:38፤ ማርቆስ 13:11, 17, 32፤ 14:25፤ ሉቃስ 10:12፤ 2 ተሰሎንቄ 1:10) ስለዚህ ማርቆስ 13:24 “ከዚያ መከራ” ሲል ሮማውያን ያስነሱትን መከራ ሳይሆን ይሖዋ በአሁኑ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ የሚፈጽመውን ኃያል ድርጊት ማመልከቱ ነበር።
17, 18. ታላቁ መከራ እንዴት እንደሚካሄድ የራእይ መጽሐፍ ምን ፍንጭ ይሰጣል?
17 በራእይ ምዕራፍ 17 እስከ 19 የሚገኘው ትንቢትም ስለ ማቴዎስ 24:29–31፣ ማርቆስ 13:24–27 እና ሉቃስ 21:25–28 ካገኘነው አዲስ ግንዛቤ ጋር የሚስማማና ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በምን መንገድ? ታላቁ መከራ በአንድ ጊዜ ምት ጀምሮ እንደማያበቃ ወንጌሎች ያመለክታሉ። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ በሕይወት ቆይተው ‘የሰውን ልጅ ምልክት’ በማየት አንድ እርምጃ የሚወስዱ ይኸውም የሚያለቅሱና በሉቃስ 21:26 ላይ እንደተገለጸው “በፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ” የሚደክሙ ሰዎች ይኖራሉ። ይህ ታላቅ ፍርሃት የሚይዛቸው ጥፋታቸው በጣም እንደቀረበ የሚያመለክተውን “ምልክት” በማየታቸው ምክንያት ነው።
18 የራእይ መግለጫ ወደፊት የሚመጣው ታላቅ መከራ የሚጀምረው የዓለም አቀፋዊው “አውሬ” ወታደራዊ “ቀንዶች” “በታላቂቱ ጋለሞታ” ማለትም በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ተነስተው ሲያወድሟት መሆኑን ያመለክታል።d (ራእይ 17:1, 10–16) ይሁን እንጂ ነገሥታት፣ ነጋዴዎች፣ መርከበኞችና ሌሎችም በሐሰት ሃይማኖት መጥፋት ምክንያት እንደሚያለቅሱ ስለሚገልጽ በሕይወት የሚቆዩ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ። ብዙዎችም የሚቀጥለው ጥፋት የነሱ መሆኑን ማወቃቸው እንደማይቀር አያጠራጥርም።—ራእይ 18:9–19
ከዚያ በኋላ ምን ይመጣ ይሆን?
19. ታላቁ መከራ ሲጀምር ምን እንደሚሆን ልንጠብቅ እንችላለን?
19 የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌል ምንባቦች እንዲሁም ራእይ ምዕራፍ 17–19 በቅርቡ ስለሚፈጸሙ ሁኔታዎች እንድናውቅ ያስችሉናል። ታላቁ መከራ አምላክ በወሰነው ጊዜ በሐሰት ሃይማኖት ግዛት ማለትም በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ይጀምራል። ይህ ጥቃት በተለይ የከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም አምሳያ በሆነችው በሕዝበ ክርስትና ላይ የከፋ ይሆናል። ከዚህ የመከራው ክፍል ‘በኋላ ወዲያውኑ’ ‘በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ይጨነቃሉ።’—ማቴዎስ 24:29፤ ሉቃስ 21:25
20. በሰማይ አካላት ላይ የሚፈጸሙ ምን ነገሮች አሉ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
20 ‘ፀሐይ የምትጨልመው ጨረቃም ብርሃንዋን የምትነሳው፣ ከዋክብትም ከሰማይ የሚወድቁትና የሰማይ ኃይላት የሚናወጡት’ በምን መንገድ ነው? በታላቁ መከራ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የሃይማኖታዊው ዓለም ብርሃን ሆነው የቆዩት ስመ ጥር ቀሳውስት መጥፎነታቸው ተጋልጦ ራእይ 17:16 ላይ በተጠቀሱት “አሥር ቀንዶች” እንደሚጠፉ አያጠራጥርም። የፖለቲካ ኃይላትም እንደሚናወጡ ጥርጥር የለውም። በግዑዙ ሰማይ ላይስ አስደንጋጭ ሁኔታዎች ይፈጸሙ ይሆን? ጆሴፈስ የአይሁድ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበበት ጊዜ ተፈጸሙ ብሎ ከገለጻቸው ሁኔታዎች ይበልጥ እጅግ አስደንጋጭ የሆኑ ሁኔታዎች የሚፈጸሙ ይመስላል። አምላክ በጥንት ዘመናት በነዚህ የሰማይ አካላት አማካኝነት የማጥፋት ኃይል እንዳለው አሳይቷል።—ዘጸአት 10:21–23፤ ኢያሱ 10:12–14፤ መሳፍንት 5:20፤ ሉቃስ 23:44, 45
21. ወደፊት የሚመጣው “ምልክት” የሚታየው እንዴት ነው?
21 ሦስቱም የወንጌል ጸሐፊዎች እዚህ ነጥብ ላይ ሲደርሱ ቀጥሎ የሚፈጸመውን ሁኔታ ለማስተዋወቅ ቶት በተባለው የግሪክኛ ቃል (ከዚያም ማለት ነው) ተጠቅመዋል። “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል።” (ማቴዎስ 24:30፤ ማርቆስ 13:26፤ ሉቃስ 21:27) አብዛኞቹ የሰው ልጆች ባይገነዘቧቸውም የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የተፈጸመውንና የሰው ልጅ የማይታይ መገኘት ምልክት የሆነውን ጥምር ምልክት አስተውለዋል። ማቴዎስ 24:30 ግን ወደፊት ሌላ “ምልክት” ይኸውም “የሰው ልጅ ምልክት” እንደሚታይና የሰው ልጆች በሙሉ ይህን ለማየትና ለመገንዘብ እንደሚገደዱ ያመለክታል። ኢየሱስ ‘ከደመና ጋር በሚመጣበት ጊዜ’ ንጉሣዊ ሥልጣኑ በታላቅ ኃይል ስለሚገለጥ በመላው ዓለም የሚኖሩ ተቃዋሚ የሰው ልጆች በሙሉ የእርሱን ‘መምጣት’ (በግሪክኛ ኤርኮሜነን) ለማየትና ለመቀበል ይገደዳሉ።—ራእይ 1:7
22. በማቴዎስ 24:30 ላይ የተጠቀሰውን “ምልክት” ማየት ምን ውጤት ይኖረዋል?
22 ማቴዎስ 24:30 ቀጥሎ የሚሆነውን ሲያስተዋውቅ ቶት በተባለው ቃል በድጋሚ ይጠቀማል። ብሔራት የወሰዱት አቋም ያስከተለባቸው ውጤት ተሰምቷቸው ደረታቸውን እየደቁ ዋይ፣ ዋይ ይላሉ። ምናልባትም የሚያለቅሱት ጥፋታቸው በጣም እንደቀረበ በመገንዘባቸውም ሊሆን ይችላል። የአምላክ አገልጋዮች የሆንን ግን መዳናችን እንደቀረበ አውቀን ራሳችንን ቀና ስለምናደርግ ሁኔታችን ከዓለም ሕዝቦች እንዴት የተለየ ይሆናል! (ሉቃስ 21:28) በተጨማሪም ራእይ 19:1–6 በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኙ እውነተኛ አምላኪዎች በታላቂቱ ጋለሞታ መጥፋት ምክንያት እንደሚደሰቱ ይገልጻል።
23. (ሀ) ኢየሱስ የተመረጡትን የሚመለከት ምን ነገር ያደርጋል? (ለ) ስለ ቀሪዎቹ ወደ ሰማይ መወሰድስ ምን ሊባል ይቻላል?
23 የኢየሱስ ትንቢት በማርቆስ 13:27 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “በዚያን ጊዜም [ቶት] መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።” እዚህ ላይ ኢየሱስ ያተኮረው እስካሁን በምድር ላይ በሚገኙት የ144,000 “የተመረጡ ቀሪዎች” ላይ ነው። እነዚህ ቅቡዓን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሥርዓቱ መደምደሚያ መባቻ ላይ ቲኦክራሲያዊ አንድነት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይሁን እንጂ በሁኔታዎቹ የአፈጻጸም ቅደም ተከተል መሠረት ማርቆስ 13:27 እና ማቴዎስ 24:31 ከዚህ ስለሚበልጥ ሁኔታ ይገልጻሉ። “የተመረጡት” ቀሪዎች ‘በታላቅ የመለከት ድምፅ’ ከምድር ማዕዘናት ይሰበሰባሉ። የሚሰበሰቡት እንዴት ነው? የመጨረሻው ‘ማኅተም’ ይደረግባቸውና ‘የተጠሩት የተመረጡትና የታመኑት’ ክፍል መሆናቸውን ይሖዋ በግልጽ እንሚያረጋግጥላቸው አያጠያይቅም። አምላክ በወሰነው ጊዜም ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ።e ይህ ለነሱም ሆነ ታማኝ ባልንጀሮቻቸው ለሆኑት በገነቲቱ ምድር ላይ ዘላለማዊ የሆነ በረከት አግኝተው ለመኖር ‘ከታላቁ መከራ ለሚመጡት’ ምልክት የሚደረግባቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል።—ማቴዎስ 24:22፤ ራእይ 7:3, 4, 9–17፤ 17:14፤ 20:6፤ ሕዝቅኤል 9:4, 6
24. ማቴዎስ 24:29–31 ወደፊት ስለሚፈጸሙት ነገሮች ቅደም ተከተል ምን ይገልጻል?
24 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ንገረን . . .” ሲሉ ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጣቸው መልስ ሊረዱ ከሚችሉት የበለጡ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነበር። ቢሆንም የዚህ ትንቢት ጥላ በራሳቸው የሕይወት ዘመን ሲፈጸም ለመመልከት በመቻላቸው ተደስተዋል። ኢየሱስ በሰጠው መልስ ላይ ያደረግነው ጥናት ያተኮረው በቅርቡ በሚፈጸመው የትንቢቱ ክፍል ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:29–31፤ ማርቆስ 13:24–27፤ ሉቃስ 21:25–28) አሁንም እንኳ ቢሆን መዳናችን እንደቀረበ ለመመልከት እንችላለን። ታላቁ መከራ የሚጀምርበትን፣ ከዚያ በኋላ የሰው ልጅ ምልክት የሚታይበትን፣ ከዚያም አምላክ የተመረጡትን የሚሰበስብበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። በመጨረሻም ዘውድ የጫነውና ተዋጊው ንጉሣችን ኢየሱስ የይሖዋ ቅጣት አስፈጻሚ በመሆን በአርማጌዶን “ድል ለመንሣት” ይወጣል። (ራእይ 6:2) ይሖዋ ጠላቶቹን የሚበቀልበት ያ ታላቅ ቀን ከ1914 ጀምሮ የጌታ ኢየሱስ ቀን ሆኖ ለቆየው ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ዘመን ታላቅ ፍጻሜ ይሆናል።
25. ወደፊት በሚፈጸመው የሉቃስ 21:28 ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ልንካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
25 ሁላችሁም “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ለሚለው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እንድትችሉ ከመለኮታዊው ትምህርት መጠቀማችሁን ቀጥሉ። (ሉቃስ 21:28) ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለመቀደስ ወደፊት እየገሰገሰ በሄደ መጠን የተመረጡትና እጅግ ብዙ ሰዎች ምንኛ ታላቅ የሆነ የወደፊት ጊዜ ይጠብቃቸዋል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የይሖዋ ምስክሮችን ብትጠይቃቸው በዘመናችን የሚፈጸሙት ሁኔታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሆናቸውን በመግለጽ የዚህን ማስረጃ በደስታ ያቀረቡልሃል።
b በ1973 በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው የአምላክ የሺህ ዓመት መንግሥት ቀርቧል በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 296–323 ላይ እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ 9–103 ገጽ 11–14 ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ቀርቧል።
c ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ የሮማ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ስለፈጸመው የመጀመሪያ ጥቃት (በ66 እዘአ) እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሌሊት አውዳሚ የሆነ አውሎ ነፋስ ተነሣ። ማዕበልና ከባድ ዝናብ ወረደ፤ የማያቋርጥ መብረቅና የሚያስፈራ ነጎድጓድ ነበር። ምድሪቱ ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ባለበት ነውጥ ተመታች። ይህ አጠቃላይ የሆነ የነገሮች መዋቅር መፈራረስ የሰው ዘር እልቂት መድረሱን የሚያመለክት ጥላ እንደነበረ ግልጽ ነው። እነዚህ ምልክቶች አቻ የሌለው መዓት መምጣቱን እንደሚያመለክቱ ሊጠራጠር የሚችል ሰው አልነበረም።”
d ኢየሱስ “ታላቅ መከራ” (ግሬት ትሪቢዩሌሽን) እና “መከራ” (ኤ ትሪቢዩሌሽን) ብሎ የተናገረው በመጀመሪያ አፈጻጸሙ የአይሁዳውያንን ሥርዓት ጥፋት ያመለክታል። በዘመናችን ብቻ በሚፈጸሙት ቁጥሮች ላይ ግን “ከዚያ መከራ” (“ዘ ትሪቢዩሌሽን”) በማለት “ዘ” የሚለውን አመልካች ቃል ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 24:21, 29፤ ማርቆስ 13:19, 24) ራእይ 7:14 ይህንን ወደፊት የሚፈጸም ሁኔታ “ታላቁ መከራ” ወይም ቃል በቃል “ታላቅ የሆነው መከራ” (“ዘ ትሪቢዩሌሽን ዘ ግሬት”) ብሎ ጠርቶታል።
e በመጠበቂያ ግንብ 16–111 ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ የኢዩኤል 2:28–31 እና 3:15 ክፍሎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙት እንዴት ነበር?
◻ ማቴዎስ 24:29 የሚጠቅሰው መከራ የትኛው ነው? እንዲህ ብለን የምንደመድመውስ ለምንድን ነው?
◻ ማቴዎስ 24:29 በሰማይ አካላት ላይ ስለሚፈጸሙ ምን ነገሮች ያመለክታል? ይህስ ከመከራው በኋላ ወዲያው ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ሉቃስ 21:26, 28 ወደፊት የሚፈጸመው እንዴት ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተ መቅደሱ አካባቢ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.