‘ምንጊዜም በጉን ይከተሉታል’
“ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ የሚከተሉት እነዚህ ናቸው።”—ራእይ 14:4
1. የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እሱን ስለመከተል ምን አመለካከት ነበራቸው?
ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ከሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ “በቅፍርናሆም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት እያስተማረ” ነበር። በዚህ ወቅት “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ” የተናገረው ነገር ስለዘገነናቸው “ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።” ከዚያም ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት እነሱም መሄድ ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቃቸው፤ ስምዖን ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ እንደሆንክ አምነናል፣ እንዲሁም አውቀናል” በማለት መለሰለት። (ዮሐ. 6:48, 59, 60, 66-69) የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እሱን መከተላቸውን አላቆሙም። በመንፈስ ቅዱስ ከተቀቡ በኋላም የኢየሱስን መመሪያ መከተላቸውን ቀጥለዋል።—ሥራ 16:7-10
2. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወይም “ታማኝና ልባም መጋቢ” የተባለው ማን ነው? (ለ) ባሪያው ‘በጉን በሄደበት ሁሉ በመከተል’ ረገድ መልካም ስም ያተረፈው እንዴት ነው?
2 በዘመናችን ስላሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ ‘ከመገኘቱና ከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት’ ጋር በተያያዘ በተናገረው ትንቢት ላይ በምድር ላይ ያሉ በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹን በቡድን ደረጃ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወይም “ታማኝና ልባም መጋቢ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ማቴ. 24:3, 45፤ ሉቃስ 12:42) በቡድን ደረጃ ሲታይ ይህ ባሪያ ‘በጉን በሄደበት ሁሉ በመከተል’ ረገድ መልካም ስም አትርፏል። (ራእይ 14:4, 5ን አንብብ።) የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት፣ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” በምታምንባቸው ነገሮችና በምትፈጽማቸው ድርጊቶች ራሳቸውን ባለማርከስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ድንግልናቸውን ጠብቀዋል። (ራእይ 17:5) አንድም የሐሰት መሠረተ ትምህርት “በአፋቸው” አልተገኘም፤ እንዲሁም ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ ቢኖሩም “ምንም ዓይነት እንከን” የለባቸውም። (ዮሐ. 15:19) ወደፊት ደግሞ በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ በመሄድ በጉን ‘ይከተሉታል።’—ዮሐ. 13:36
3. በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ መተማመናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ፣ ‘ለአገልጋዮቹ’ ማለትም ለባሪያው ክፍል አባላት “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው” ታማኝና ልባም ባሪያን ሾሞታል። ከዚህም በተጨማሪ ባሪያውን “በንብረቱ ሁሉ ላይ” ሾሞታል። (ማቴ. 24:45-47) “ንብረቱ” ከተባሉት መካከል ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ይገኙበታል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 10:16) ታዲያ በመንፈስ የተቀቡ ግለሰቦችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” በላያቸው በተሾመው ባሪያ ላይ ሊተማመኑ አይገባም? በታማኝና ልባም ባሪያ እንድንተማመን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። በዋነኝነት ከሚጠቀሱት መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ይሖዋ በታማኝና ልባም ባሪያ ይተማመናል። (2) ኢየሱስ በባሪያው ይተማመናል። ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ በታማኝና ልባም ባሪያ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመልከት።
ይሖዋ በባሪያው ይተማመናል
4. ታማኝና ልባም ባሪያ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
4 ታማኝና ልባም ባሪያ ወቅታዊና ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ሊያቀርብልን የቻለው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ይሖዋ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” ብሏል። (መዝ. 32:8) አዎን፣ ይሖዋ ለታማኙ ባሪያ መመሪያ ይሰጠዋል። በመሆኑም ከታማኝና ልባም ባሪያ ባገኘነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት፣ ጥልቅ የሆነ እውቀትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።
5. የአምላክ መንፈስ ባሪያውን እየረዳው እንዳለ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠትም ባሪያውን ባርኮታል። የይሖዋ መንፈስ በዓይን የማይታይ ቢሆንም መንፈሱን የተቀበሉት ሰዎች የሚያፈሩት ፍሬ ግን ይታያል። ታማኝና ልባም ባሪያ፣ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ እንዲሁም ስለ መንግሥቱ በዓለም ዙሪያ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ አስብ። የይሖዋ አምላኪዎች ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት እያወጁ ነው። ይህ ሁኔታ የአምላክ መንፈስ ባሪያውን እየረዳው እንዳለ የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ አይደለም? (የሐዋርያት ሥራ 1:8ን አንብብ።) ታማኝና ልባም ባሪያ በምድር ዙሪያ ለሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው ለማቅረብ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ማድረግ ይኖርበታል። ባሪያው እንደነዚህ ያሉ ውሳኔዎችን በሚያደርግበትና ያስተላለፈውን ውሳኔ በተግባር ላይ በሚያውልበት ጊዜ ፍቅርንና ገርነትን ጨምሮ ሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ያንጸባርቃል።—ገላ. 5:22, 23
6, 7. ይሖዋ በታማኙ ባሪያ ምን ያህል ይተማመንበታል?
6 ይሖዋ ለታማኙ ባሪያ አባላት የገባውን ቃል ማጤናችን በዚህ ባሪያ ላይ ምን ያህል እንደሚተማመንበት ለመገንዘብ ያስችለናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።” (1 ቆሮ. 15:52, 53) አምላክን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ አካልና የዘላለም ሕይወት ብቻ አይደለም። የሚበሰብስ አካል የነበራቸው እነዚህ ሰዎች፣ ከሞት ሲነሱ ያለመሞት ባሕርይ ማለትም ዘላለማዊ ሕይወትና ሊጠፋ የማይችል አካል ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ የማይበሰብስ በሌላ አባባል የማይፈርስ አካል ይኖራቸዋል። ምናልባትም ራሱን ችሎ መኖር የሚችል አካል ይኖራቸዋል፤ በሌላ አባባል ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ አካል ካላቸው ሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ 144, 000ዎቹ ሕልውናቸው የተመካው ከሌላ ምንጭ በሚገኝ ኃይል ላይ አይደለም። ከሞት የተነሱት እነዚህ ቅቡዓን በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል ደፍተው በዙፋን ላይ እንደተቀመጡ በራእይ 4:4 ላይ ተገልጿል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ንጉሥ የመሆን ክብር ያገኛሉ። ይሁንና አምላክ በእነሱ እንደሚተማመን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ።
7 ራእይ 19:7, 8 እንዲህ ይላል፦ “የበጉ ሠርግ [ደርሷል]፤ ሙሽራዋ ራሷን [አዘጋጅታለች]። . . . አዎ፣ የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቷታል፤ ምክንያቱም ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታል።” ይሖዋ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የልጁ ሙሽራ እንዲሆኑ አጭቷቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች የማይበሰብስ አካልና ያለመሞት ባሕርይ የማግኘት እንዲሁም ንጉሥና ‘የበጉ ሙሽራ’ የመሆን አስደናቂ ሽልማት ይሰጣቸዋል! እነዚህ ሽልማቶች፣ ይሖዋ ‘ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ የሚከተሉትን’ ቅቡዓን እንደሚተማመንባቸው የሚያሳዩ ግሩም ማስረጃዎች ናቸው።
ኢየሱስ በባሪያው ይተማመንበታል
8. ኢየሱስ በመንፈስ በተቀቡት ተከታዮቹ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹን ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመንባቸው የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያቱ የሚከተለውን ቃል ገብቶላቸው ነበር፦ “እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል፤ አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማዕዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ እንዲሁም በዙፋን ተቀምጣችሁ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እንድትፈርዱ ነው።” (ሉቃስ 22:28-30) ኢየሱስ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር የገባው ቃል ኪዳን 144,000ዎቹን ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ይጨምራል። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1) ኢየሱስ በእነዚህ ክርስቲያኖች ባይተማመንባቸው ኖሮ አብረውት እንዲገዙ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ይገባ ነበር?
9. ከክርስቶስ ‘ንብረቶች’ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
9 በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝና ልባም ባሪያን “በንብረቱ ሁሉ ላይ” ይኸውም ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በሙሉ ሾሞታል። (ማቴ. 24:47) እነዚህ ንብረቶች የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤትን፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ትልልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾችንና የመንግሥት አዳራሾችን ያካትታሉ፤ እንዲሁም የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ይጨምራሉ። አንድ ግለሰብ በጣም ውድ የሆነ ንብረቱን እንዲያስቀምጥለትና እንዲጠቀምበት የሚሰጠው ለሚተማመንበት ሰው አይደለም?
10. ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅቡዓን ተከታዮቹ ጋር እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
10 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ትንሽ ቀደም ብሎ ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ በመገለጥ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸዋል፦ “እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:20) ታዲያ ኢየሱስ የገባውን ቃል ጠብቋል? በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ቁጥር፣ ባለፉት 15 ዓመታት ከ40 በመቶ የሚበልጥ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን 70,000 ገደማ የነበሩት ጉባኤዎች በአሁኑ ጊዜ ከ100,000 በላይ ሆነዋል። ምን ያህል አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተገኝተዋል? ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ 4.5 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት ሆነዋል፤ ይህም በአማካይ በየቀኑ 800 ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው። እነዚህ አስደናቂ ጭማሪዎች ክርስቶስ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹ የጉባኤ ስብሰባዎች በሚያደርጉበት ጊዜ እንደሚመራቸውና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራቸው እንደሚደግፋቸው ያሳያሉ።
ባሪያው ታማኝና ልባም ነው
11, 12. ባሪያው ታማኝና ልባም መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በታማኝና ልባም ባሪያ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበት ከሆነ እኛስ እንዲህ ማድረግ አይገባንም? ደግሞም ባሪያው የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ታማኝ መሆኑን አስመሥክሯል። ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላለፉት 130 ዓመታት ሲታተም ቆይቷል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው የጉባኤ፣ የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎች ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ያጠናክሩናል።
12 ታማኙ ባሪያ፣ የይሖዋ መመሪያ ግልጽ ከመሆኑ በፊት እርምጃ ባለመውሰድ እንዲሁም መመሪያው ግልጽ በሚሆንበት ወቅት ወደኋላ ባለመቅረት ልባም መሆኑንም አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች የሚያሳድዱትን ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበትና ከአምላክ የራቀ አኗኗር በቸልታ ሲያልፉ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ሲደግፉ ታማኝና ልባም ባሪያ ግን የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት መከተል አደጋ እንደሚያስከትል ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። ታማኙ ባሪያ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውና ወቅታዊ የሆኑ ማሳሰቢያዎችን ማቅረብ የቻለው የይሖዋ አምላክና የኢየሱስ ክርስቶስ በረከት ስላልተለየው ነው። በመሆኑም በባሪያው ላይ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን ይገባል። ታዲያ በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
በጉን ከሚከተሉት ቅቡዓን ጋር ‘አብሮ መሄድ’
13. በዘካርያስ ትንቢት መሠረት በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘካርያስ መጽሐፍ ‘ዐሥር ሰዎች አንድን አይሁዳዊ አብረን እንሂድ’ እንደሚሉት ይገልጻል። (ዘካርያስ 8:23ን አንብብ።) አሥሩ ሰዎች ‘አይሁዳዊውን’ ሲያናግሩት “ከእናንተ” በማለት በብዙ ቁጥር መጠቀማቸው ይህ ሰው አንድን ቡድን እንደሚያመለክት ይጠቁማል። በዘመናችን ይህ አይሁዳዊ ‘የአምላክ እስራኤል’ ክፍል የሆኑትን ቅቡዓን ቀሪዎች ያመለክታል። (ገላ. 6:16) “ከየወገኑና ከየቋንቋው [የተውጣጡት] ዐሥር ሰዎች” ደግሞ የሌሎች በጎች ክፍል የሆነውን እጅግ ብዙ ሕዝብ ያመለክታሉ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢየሱስን በሄደበት እንደሚከተሉት ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝቦችም ከታማኝና ልባም ባሪያ ጋር ‘አብረው ይሄዳሉ።’ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር አብረው መሥራታቸው ፈጽሞ ሊያሳፍራቸው አይገባም። (ዕብ. 3:1) ኢየሱስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “ወንድሞች” ብሎ ለመጥራት አላፈረም።—ዕብ. 2:11
14. የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወንድሞቹን በታማኝነት ስንደግፍ እሱን እንደደገፍነው አድርጎ ይቆጥረዋል። (ማቴዎስ 25:40ን አንብብ።) ታዲያ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች በመንፈስ ለተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች ድጋፍ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የሚችሉበት ዋነኛው መንገድ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ እነሱን በማገዝ ነው። (ማቴ. 24:14፤ ዮሐ. 14:12) ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በምድር ላይ ያሉት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የሌሎች በጎች ቁጥር ጨምሯል። ምድርን የመውረስ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ ሲሳተፉ፣ አቅማቸው ከፈቀደ ደግሞ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ሲሰማሩ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመንፈስ የተቀቡትን ክርስቲያኖች ያግዟቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) በተለያዩ መንገዶች የገንዘብ መዋጮ በማድረግ የስብከቱን ሥራ መደገፍም ይቻላል።
15. ታማኙ ባሪያ ለሚያቀርብልን ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እንዲሁም ድርጅታዊ አሠራርን በተመለከተ ለሚያስተላልፈው ውሳኔ በግለሰብ ደረጃ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
15 ታማኝና ልባም ባሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎችና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት የሚያቀርብልንን ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንመለከተዋለን? ይህን ምግብ በአድናቆት በመመገብ የተማርነውን ነገር በተግባር እናውላለን? ባሪያው ድርጅታዊ አሠራርን በተመለከተ ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ምን ምላሽ እንሰጣለን? የተሰጠንን መመሪያ በፈቃደኝነት ስንታዘዝ በይሖዋ ዝግጅት ላይ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ያዕ. 3:17
16. ሁሉም ክርስቲያኖች የኢየሱስን ወንድሞች መስማት ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 ኢየሱስ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል” ብሏል። (ዮሐ. 10:27) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ያደርጋሉ። ‘አብረዋቸው ስለሚሄዱት’ ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም ኢየሱስን ሊሰሙት ይገባል። የእሱን ወንድሞችም መስማት ይገባቸዋል። ደግሞም የአምላክን ሕዝቦች በመንፈሳዊ የመንከባከቡ ኃላፊነት በዋነኝነት በአደራ የተሰጠው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። ይሁንና የክርስቶስን ወንድሞች ድምፅ መስማት ምን ማድረግን ይጨምራል?
17. ታማኙን ባሪያ መስማት ሲባል ምን ማለት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ የሚገኘውን ታማኝና ልባም ባሪያ የሚወክለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ነው፤ የበላይ አካሉ በምድር ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት ያደራጃል። የበላይ አካሉ አባላት ተሞክሮ ያካበቱ በመንፈስ የተቀቡ ሽማግሌዎች ናቸው። “በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡ” የሚለው አገላለጽ በተለይ በእነሱ ላይ ይሠራል። (ዕብ. 13:7) በመንፈስ የተቀቡት እነዚህ የበላይ ተመልካቾች፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ከ100,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን ወደ 7,000,000 የሚጠጉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በመንፈሳዊ ስለሚንከባከቡ “የጌታ ሥራ [የበዛላቸው]” ናቸው። (1 ቆሮ. 15:58) ታማኙን ባሪያ መስማት ሲባል ከበላይ አካሉ ጋር ሙሉ በሙሉ መተባበር ማለት ነው።
ባሪያውን የሚሰሙ ይባረካሉ
18, 19. (ሀ) ታማኝና ልባም ባሪያን የሚሰሙት ሁሉ የሚባረኩት እንዴት ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
18 ታማኝና ልባም ባሪያ ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ ‘ብዙዎችን ወደ ጽድቅ ሲመልስ’ ቆይቷል። (ዳን. 12:3) “ብዙዎች” ከተባሉት መካከል በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት የመትረፍ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ይገኙበታል። በአምላክ ፊት እንዲህ ዓይነት የጽድቅ አቋም ማግኘት እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው!
19 ወደፊት ‘ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም [144,000ቹ ማለት ነው] ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ’ የታማኙን ባሪያ ድምፅ ሲሰሙ የነበሩ ሰዎች ምን ያገኛሉ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:2-4) እንግዲያው የክርስቶስንና እምነት የሚጣልባቸውን በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞቹን ድምፅ እንስማ።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ይሖዋ፣ በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ እንደሚተማመን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
• ኢየሱስ ክርስቶስ በታማኝና ልባም ባሪያ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን የሚያሳየው ምንድን ነው?
• በታማኙ መጋቢ ልንተማመን የሚገባው ለምንድን ነው?
• በታማኙ ባሪያ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለልጁ ሙሽራ እንዲሆኑ ያጨው እነማንን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ‘ንብረቱን’ ለታማኝና ልባም ባሪያ በአደራ ሰጥቶታል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብከቱ ሥራ ስንካፈል በመንፈስ የተቀቡትን ክርስቲያኖች እንደግፋቸዋለን