በእርግጥ ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው እነማን ናቸው?
ይሖዋ ሰብአዊውን ዘር ይወዳል። ይህ ፍቅሩ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ አባታችን አዳም ያጠፋብንን ለማስመለስ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ ሰጠን። አዳም ያጠፋብን ነገር ምን ነበር? ፍጹም ሰብአዊ ሕይወት እና ይህ የያዛቸውን መብቶችና ተስፋዎችን ሁሉ ነበር። (ዮሐንስ 3:16) ቤዛው ኢየሱስ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር መግለጫም ነው።—ማቴዎስ 20:28
መለኮታዊው ፍቅር በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ ላይ የተመሠረቱ የአምላክ ስጦታ የሆኑ ሁለት ተስፋዎችን በመክፈቱ ታይቷል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመሞቱ በፊት መለኮታዊ ድጋፍ ላገኙ ሰዎች ክፍት የነበረው ብቸኛ ተስፋ የምድራዊ ገነት ሕይወት ነበር። (ሉቃስ 23:43) ከጴንጠቆስጤ 33 እዘአ በኋላ ግን ይሖዋ “ለታናሽ” መንጋ ሰማያዊ ተስፋ ሰጠ። (ሉቃስ 12:32) በቅርብ ጊዜ ግን ምን ሆነ? ከ1931 ጀምሮ የመንግሥቱ መልእክት ይበልጥ ያተኮረው በ“ሌሎች በጎች” ላይ ነው። ከ1935 ወዲህ እነዚህን በግ መሰል ሰዎች በክርስቶስ አማካኝነት ወደ ራሱ እየሰበሰበ ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) አምላክ በልባቸው ውስጥ በምድራዊ ገነት የዘላለም ሕይወት ተስፋን አሳድሯል። የሚመኙትም ፍጹም ምግብ ለመመገብ፣ በእንስሳት ላይ ፍቅራዊ የበላይነትን መቀዳጀትና ለዘላለምም ከጻድቃን ሰዎች ጋር አብሮ መሆን ነው።
ርኅሩኅ ካህናትና ነገሥታት
ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ኢየሱስን ያነሣሣው ፍቅር ስለሆነ ርኅሩኅ ሰማያዊ ንጉሥ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ሆኖም በሺህ ዓመት ግዛቱ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ ለማንሣት ብቻውን ሆኖ አይሠራም። ይሖዋ በሰማይ ሌሎች ርኅሩኅ ነገሥታት እንዲኖሩ ዝግጅት አድርጓል። አዎን፣ “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ለሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”—ራእይ 20:1-6
ክርስቶስ አብረውት የሚገዙ ምን ያህል ሰዎች ይኖሩታል? ለዚህ ታላቅ መብትስ የሚመረጡት እንዴት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጽዮን ተራራ 144,000 ተመልክቷል። “ከሰዎች የተዋጁ” በመሆናቸው ፈተና ማሳለፍ፣ የአለፍጽምናን ሸክሞች መቻል፣ መሠቃየትና መሞት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ። (ራእይ 14:1-5፤ ኢዮብ 14:1) ስለዚህ እንዴት ዓይነት ርኅሩኅ ነገሥታት ይሆናሉ!
የመንፈስ ምስክርነት
144,000ዎቹ ከቅዱሱ ከይሖዋ “ቅባት” ተቀብለዋል። (1 ዮሐንስ 2:20) የተቀቡትም ለሰማያዊ ተስፋ ነው። “ያተማቸውና የመንፈሱንም መያዣ በልባቸው የሰጠ” አምላክ ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:21, 22
አዎን፣ ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ሰዎች እንደዚያ ለመሆናቸው የአምላክ መንፈስ ምስክርነት አላቸው። ይህን በሚመለከት ጳውሎስ በሮሜ 8:15-17 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን። አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” ቅቡዓኑ “አባ አባት” ብለው የሚጮኹት በአምላክ መንፈስ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት ነው።
አንድ ሰው ለሰማያዊው ጥሪ እንደ ተቀባ ዋና ማስረጃ የሚሆነው መንፈሱ ወይም የላቀ የልጅነት ስሜት ነው። (ገላትያ 4:6, 7) እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ከ144,000 የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች አንዱ በመሆን የአምላክን መንፈሳዊ ልጅነት እንዳገኘ ፍጹም እርግጠኛ ነው። ሰማያዊው ተስፋው ራሱ የኮተኮተው ምኞት ወይም ስሜት እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ የአምላክ መንፈስ በሱ ላይ በመሥራቱ ከይሖዋ የመጣ መሆኑን ሊመሰክር ይችላል።—1 ጴጥሮስ 1:3, 4
በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ገፋፊነት የቅቡዓኑ መንፈስ ወይም የሚያይለው ስሜታቸው አስገዳጅ ኃይል ሆኖ ይገፋፋቸዋል። የአምላክ ቃል ስለ ሰማያዊው ተስፋ ለሚናገረው ነገር አዎንታዊ ምላሽ እንዲኖራቸው ይገፋፋቸዋል። እንደዚሁም ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ከነሱ ጋር ላለው ግንኙነት በአዎንታዊ መንገድ ምላሽ ይሰጣሉ። በመሆኑም የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችና ወራሾች ለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው።
ቅቡዓኑ የአምላክ ቃል ስለ መንፈሳዊ ልጆቹና ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚናገረውን ሲያነቡ ወዲያውኑ በልባቸው “ይህ የሚናገረው ለእኔ ወይም ስለ እኔ ነው!” ወይም “ይህ ማለት እኔ ነኝ!” የሚል ስሜት ይሰማቸዋል። አዎን፣ የአባታቸው ቃል ስለ ሰማያዊ ሽልማት ተስፋዎች ሲናገር ስሜታቸው በደስታ ይቀሰቀሳል። “ተወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን” የሚለውን ሲያነቡ “ያ ማለት እኔ ነኝ!” ይላሉ። (1 ዮሐንስ 3:2) ቅቡዓኑ አምላክ ሕዝቦችን “ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት” እንዲሆኑ እንዳደረገ በሚያነቡበት ጊዜም የአእምሮ ዝንባሌያቸው “አዎን እኔንም ለዚያ ዓላማ ነው ያመጣኝ” ብሎ መመለስ ነው። (ያዕቆብ 1:18) ወደ “ኢየሱስ ክርስቶስ” እና ወደ ሞቱ ‘እንደተጠመቁ’ ያውቃሉ። (ሮሜ 6:3) ስለዚህ የክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ክፍል ለመሆናቸው ጽኑ እምነት አላቸው፤ የሱንም ሞት የሚመስል ሞት ስለ መሞትና ለሰማያዊ ሕይወት ስለ መነሣት ተስፋቸው ያሰላስላሉ።
ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ ቅቡዓኑ “መጠራታቸውንና መመረጣቸውን ያጸኑ ዘንድ” የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:5-11) በእምነት ይመላለሳሉ፤ ምድራዊ ተስፋ እንዳላቸው ሰዎች ሁሉ እነሱም በመንፈሳዊ ማደጋቸውን ይቀጥላሉ። ታዲያ ስለ መንፈስ ምስክርነት ምን ሌላ ነገር መናገር ይቻላል?
ለምን እንደሚካፈሉ
ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ለመሄድ የሚፈልጉት ባሁኑ ምድራዊ ሕይወት ስላልረኩ አይደለም። (ከይሁዳ 3, 4, 16 ጋር አወዳድር) ከዚህ ይልቅ የአምላክ ልጆች ለመሆናቸው መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳቸው ጋር ይመሰክራል። ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን እንደገቡም እርግጠኞች ናቸው። የዚህ ቃል ኪዳን ተዋዋይ ወገኖችም ይሖዋ አምላክና መንፈሳዊ እስራኤላውያን ናቸው። (ኤርምያስ 31:31-34፤ ገላትያ 6:15, 16፤ ዕብራውያን 12:22-24) ይህ ቃል ኪዳን በሥራ የዋለው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው፤ ደሙ ለይሖዋ ስም የሚሆኑ ሕዝቦችን ይዋጃል፤ እነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖችም የአብርሃም “ዘር” ክፍል ያደርጋቸዋል። (ገላትያ 3:26-29፤ ሥራ 15:14) አዲሱ ቃል ኪዳን ሁሉም መንፈሳውያን እስራኤላውያን ከሞት የማይጠፋ ሕይወት አግኝተው ወደ ሰማይ እስኪነሡ ድረስ ይሠራል።
ከዚህም በላይ እነዚያ እውነተኛ ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ክርስቲያኖች ለሰማያዊ መንግሥት በተገባው ቃል ኪዳን ውስጥም እንዳሉበት አይጠራጠሩም። ኢየሱስ “እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ። አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ በአስራ ሁለቱም በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን በሱና በተከታዮቹ መካከል የተደረገውን ቃል ኪዳን መጥቀሱ ነበር። (ሉቃስ 22:28-30) ይህ ቃል ኪዳን ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተመረቀላቸው በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ በተቀቡ ጊዜ ነበር። በክርስቶስና በተባባሪ ነገሥታቱ መካከል ይህ ቃል ኪዳን ለዘላለም የሚሠራ ይሆናል።—ራእይ 22:5
ሰማያዊው ጥሪ ያላቸው ክርስቲያኖች በአዲሱ ቃል ኪዳንና ለመንግሥት በተገባው ቃል ኪዳን ውስጥ ስለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው። ስለዚህ በዓመታዊው የጌታ እራት ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ጠጅ መካፈላቸው ተገቢ ነው። ያልቦካው ቂጣ የኢየሱስን ኃጢአት የለሽ ሰብአዊ አካል ያመለክታል፤ ወይኑም በሞት የፈሰሰውንና አዲሱን ቃል ኪዳን ያጸደቀውን ፍጹም ደሙን ያመለክታል።—1 ቆሮንቶስ 11:23-26
ይሖዋ ይህን እርግጠኛ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ በልብህ አሳድሮልህ ከሆነ እምነትህን በዚያ ላይ ጥለሃል። ያንን ተስፋ በመጥቀስ ጸሎት ታቀርባለህ። ተስፋው ሁለንተናህን ስለሚውጠው ከሰውነትህ ውስጥ ልታወጣው አትችልም። የሚቃጠል መንፈሳዊ ምኞት አለህ። ሁለት ልብ ከሆንክና ከተጠራጠርክ ግን ያለጥርጥር ከጌታ እራት ምሳሌዎች መካፈል የለብህም።
የተሳሳተ ግምት የሚኖረው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች መቀባቱ “ለወደደ ወይም ለሮጠ ሳይሆን ከአምላክ” መሆኑን ባለማወቅ ወይም ባለመቀበል ከመታሰቢያው ምሳሌዎች በስሕተት ይካፈላሉ። (ሮሜ 9:16) ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን መግባትና ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ተባባሪ ወራሽ ለመሆን መወሰንና መፈለግ የግለሰቡ ወይም የግለሰቧ ጉዳይ አይደለም። ዋጋ ያለው የይሖዋ ምርጫ ነው። በጥንቷ እስራኤል ካህናት በመሆን የሚያገለግሉትን አምላክ ራሱ መርጦ ነበር። ስለዚህም ለአሮን ቤተሰብ የመደበውን ክህነት በትዕቢት ተወጥሮ ለራሱ የፈለገውን ቆሬን በሞት ቀጥቷል። (ዘፀዓት 28:1፤ ዘኁልቁ 16:4-11, 31-35፤ 2 ዜና 26:18፤ ዕብራውያን 5:4, 5) በተመሳሳይም አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ጥሪ አምላክ ሳይሰጠው ከሰማያዊ ነገሥታትና ካህናት መሃል ሊሆን እንደ ተጠራ አድርጎ ራሱን ቢያቀርብ ይሖዋን ያስከፋል።—ከ1 ጢሞቴዎስ 5:24, 25 ጋር አወዳድር።
አንድ ሰው ከከባድ ችግሮች በሚነሣ ኃይለኛ ስሜት የተነሣ በስሕተት ሰማያዊ ጥሪ እንዳለው ሊገምት ይችላል። የትዳር ጓደኛ መሞት ወይም ሌላ አሳዛኝ መከራ አንድን ሰው በምድር ላይ የመኖር ፍላጎቱን ሊያጠፋበት ይችላል። ወይም ደግሞ የቅርብ ጓደኛው የቅቡዓን ክፍል ነኝ ባይ ይሆንና እሱም ተመሳሳይ ዕድል ሊመኝ ይችላል። ይህን መሳይ ምክንያቶች የሰማይ ሕይወት ለሱም እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አምላክ ለአንድ ሰው የልጅነትን መንፈስ የሚሰጥበት መንገድ ይህ አይደለም። አንድ ሰው ከምድራዊ ሕይወት ጋር በተያያዙ ደስ የማይሉ ሁኔታዎች ወይም ስሜታዊ ሥቃይ የተነሣ ወደ ሰማይ ለመሄድ ተመኝቶ ከሆነ አምላክ ምድርን በሚመለከት ላለው ዓላማ ምስጋና እንዳጣ ያሳያል።
የቀድሞ ሃይማኖታዊ አመለካከቶቹም አንድን ሰው በስሕተት ሰማያዊ ጥሪ አለኝ እንዲል ሊያነሣሱት ይችላሉ። ምናልባት በአንድ ወቅት ሰማያዊ ሕይወትን ለታማኝ ሰዎች እንደ ብቸኛ ተስፋ አድርጎ የሚያስተምር የሐሰት ሃይማኖት አባል የነበረ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን በተሳሳቱ የቀድሞ ስሜቶችና አመለካከቶች ከመነዳት መጠንቀቅ ያስፈልገዋል።
ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል
ሐዋርያው ጳውሎስ “ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፤ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ፤ ከጽዋውም ይጠጣ። ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና ይጠጣልምና” ብሎ ሲጽፍ አንድ በጣም ትልቅ ቁም ነገር አመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 11:27-29) ስለዚህ አንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰማያዊ ጥሪ እንዳገኘ ማሰብ የጀመረ የተጠመቀ ክርስቲያን ጉዳዩን በጥሞናና በጸሎት ሊያስብበት ይገባል።
እንዲህ ዓይነቱ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፦ “የሰማያዊ ሕይወትን ሐሳብ ሌሎች ሰዎች አጋብተውብኛልን?” አምላክ ሰዎችን ለእንዲህ ዓይነቱ መብት እንዲመለመሉ ስላልመደበ ይህ አድራጎት ተገቢ አይደለም። አንድ ሰው በውስጡ በጣም ደስ የሚሉ ስሜቶችና ሐሳቦች የሚመጡበት መሆኑም በአምላክ የተቀባ መሆኑን አያመለክትም። እንደዚሁም ያን ዓይነት ስሜት የሚያሳድር መልእክት ያላቸው ድምፆች እንዲሰሙ በማድረግ አይደለም አምላክ የመንግሥቱን ወራሾች የሚቀባው።
አንዳንዶች ራሳቸውን እንዲህ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፦ “ክርስቲያን ከመሆኔ በፊት በአደንዛዥ መድኃኒቶች ያላግባብ እጠቀም ነበርን? ስሜትን የሚነኩ መድኃኒቶች እየወሰድኩ ነውን? ለአእምሮ ወይም ለመንፈስ ጭንቀት ችግሮች ሕክምና አድርጌያለሁን?” አንዳንዶች ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ሲመስላቸው መጀመሪያ ይህን ሐሳብ ለማስወገድ እንደታገሉ ተናግረዋል። ሌሎችም አምላክ ለጊዜው ምድራዊ ተስፋቸውን እንደ ወሰደባቸውና ከዚያ በኋላ ግን ሰማያዊ ተስፋ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት አሠራር ከመለኮታዊ አሠራር ጋር ይቃረናል። ከዚህም በላይ እምነት ተጠራጣሪ አይደለም፤ እርግጠኛ ነው እንጂ።—ዕብራውያን 11:6
እንደዚሁም አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፦ “ክብር ወይም ታዋቂነትን እመኛለሁን? በአሁኑ ጊዜ የሥልጣን ምኞት የሚያጠቃኝ ነኝን? ወደፊትስ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ንጉሥና ካህን ከሚሆኑት አንዱ በመሆን የሥልጣን ቦታ ለማግኘት እጓጓለሁን?” በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ጥሪው ባጠቃላይ ወደ ሰማያዊው መንግሥት ለመግባት በተዘረጋበት ጊዜ የአስተዳደር አካሉ አባል በመሆን ወይም ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በመሆን የኃላፊነት ቦታን የያዙት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች አልነበሩም። ብዙዎቹ ሴቶች ስለነበሩ ምንም ዓይነት ልዩ ሥልጣን አልነበራቸውም። ወይም ደግሞ በመንፈስ መቀባት የላቀ የአምላክ ቃል መረዳትን አያመጣም ምክንያቱም ጳውሎስ አንዳንድ ቅቡዓንን ማስተማርና መምከር አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚናገር ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:1-3፤ ዕብራውያን 5:11-14) ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን እንደ ተከበሩ ሰዎች አድርገው አይመለከቱም፤ የተቀቡ መሆናቸውን ለማሳየትም የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳቸው አይስቡም። ከዚህ ይልቅ “የክርስቶስ ልብ” ካላቸው ሰዎች ሊጠበቅ የሚገባውን ትሕትና ያሳያሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:16) ከዚህ በተጨማሪ ተስፋቸው ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ የአምላክን የጽድቅ ብቃቶች ሁሉም ክርስቲያኖች ማሟላት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።
አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ አለኝ ስላለ ልዩ ዕውቀት አይገልጥለትም። አምላክ ለምድራዊ ድርጅቱ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብበት የመገናኛ ቦይ አለው። (ማቴዎስ 24:45-47) ስለዚህ ማንም ሰው የተቀባ ክርስቲያን መሆኑ ምድራዊ ተስፋ ካላቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” የበለጠ ጥበብ እንደሚያስገኝለት ማሰብ የለበትም። (ራእይ 7:9) መንፈሳዊ መቀባት በመመስከር ችሎታ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችን በሚገባ በመመለስ፣ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በመስጠት አይለካም ምክንያቱም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም በነዚህ ጉዳዮች ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። እንደ ቅቡዓኑ ሁሉ እነሱም (ምድራዊ ተስፋ ያላቸው) ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያናዊ ኑሮ ይኖራሉ። እንዲያውም ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት ሳምሶንና ሌሎችም የአምላክ መንፈስ አድሮባቸዋል፣ በቅንዓትና በማስተዋል ተሞልተው ነበር። ሆኖም ‘እንደ ታላቅ ዳመና ከሆኑት’ ከእነዚያ መካከል ማንም ሰማያዊ ተስፋ አልነበረውም።—ዕብራውያን 11:32-38፤ 12:1፤ ዘፀአት 35:30, 31፤ መሳፍንት 14:6, 19፤ 15:14፤ 1 ሳሙኤል 16:13፤ ሕዝቅኤል 2:2
መራጩ ማን መሆኑን አስታውሱ
አንድ የእምነት ባልደረባ ስለ ሰማያዊ ጥሪ ጥያቄ ቢኖረው አንድ የተሾመ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ከሱ ጋር ሊወያይ ይችላል። ይሁን እንጂ ማንም ሰው ለሌላው ይህን ውሳኔ ሊያደርግለት አይችልም። ሰማያዊውን ተስፋ የሚሰጠውም ይሖዋ ነው። እውነተኛ ሰማያዊው ጥሪ ያለው ግለሰብ ይህ ተስፋ ካለው መሰል ክርስቲያኖችን ይህ ተስፋ ያለው ስለመሆኑ መጠየቅ አያስፈልገውም። ቅቡዓን “ዳግመኛ የተወለዱት ከሚጠፋ ዘር አይደለም። በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።” (1 ጴጥሮስ 1:23) በመንፈሱና በቃሉ አማካኝነት አምላክ ግለሰቡን ሰማያዊ ተስፋ ያለው “አዲስ ፍጥረት” የሚያደርግ “ዘር” ይተክልበታል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) አዎን፣ ምርጫውን የሚያደርገው ይሖዋ ነው።
ስለዚህ ከአዲሶች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ስናጠና ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን እንዲሞክሩ ሐሳብ ማቅረብ ጥሩ አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ የተቀባ ክርስቲያን ታማኝነቱን ቢተውና ተተኪ ቢያስፈልግስ? በዚህ ጊዜ አምላክ ሰማያዊውን ጥሪ ለሰማያዊው አባታችን የታማኝነት አገልግሎት በማቅረብ ብዙ ዓመታት ላሳለፈ ሰው ይሰጣል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።
በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መልእክት በአብዛኛው የሚያተኩረው ሰዎች የክርስቶስ ሰማያዊ ሙሽራ አባሎች በመሆናቸው ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “መንፈሱና ሙሽራይቱ ‘ና!’ ይላሉ።” ይህ በምድራዊ ገነት ሕይወት ለሚያገኙት የተዘረጋ ጥሪ ነው። (ራእይ 22:1, 2, 17) ቅቡዓኑ በዚህ ሥራ ግምባር ቀደም ሆነው ሲሰለፉ “ትሕትናን” ሁሉ እያሳዩ ‘መመረጣቸውንና መጠራታቸውን እርግጠኛ ለማድረግ’ ይተጋሉ።—ኤፌሶን 4:1-3፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-11