የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 24—ኤርምያስ
ጸሐፊው:- ኤርምያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ እና ግብፅ
ተጽፎ ያለቀው:- በ580 ከክ. ል. በፊት
የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ647 እስከ 580 ከክ. ል. በፊት
ነቢዩ ኤርምያስ የኖረው አደገኛ በሆነና ሥርዓት አልበኝነት በነገሠበት ዘመን ነበር። ይሖዋ ኤርምያስን በነቢይነት የሾመው ፈሪሃ አምላክ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ13ኛው ዓመት ይኸውም በ647 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። የይሖዋ ቤት በጥገና ላይ እያለ የይሖዋ ሕግ መጽሐፍ ተገኘና ለንጉሡ ተነበበለት። ንጉሡ ይህ ሕግ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ለጊዜው ብቻ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ ከማድረግ ያለፈ ነገር ማድረግ አልቻለም። ለ55 ዓመታት የገዛው የኢዮስያስ አያት ምናሴም ሆነ ለ2 ዓመት ብቻ ከገዛ በኋላ የተገደለው አባቱ አሞጽ ክፉ ድርጊት ፈጽመዋል። እነዚህ ነገሥታት ርካሽ በሆኑና ልቅ የጾታ ብልግና በሚፈጸምባቸው ፈንጠዝያዎች እንዲሁም በሚሰቀጥጡ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲካፈል ሕዝቡን አደፋፍረውታል። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ “ለሰማይዋ ንግሥት” የማጠንና ለአጋንንት አማልክት የሰው መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ አዳበሩ። ምናሴ ኢየሩሳሌምን በንጹሐን ደም በክሏት ነበር።—ኤር. 1:2፤ 44:19፤ 2 ነገ. 21:6, 16, 19-23፤ 23:26, 27
2 ኤርምያስ የተሰጠው ሥራ ቀላል አልነበረም። ፈጽሞ ለማመን የሚያስቸግር እልቂት እንደሚደርስ ይኸውም ይሁዳና ኢየሩሳሌም ባድማ እንደሚሆኑ፣ ውብ የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በእሳት እንደሚጋይና ሕዝቡ በምርኮ እንደሚወሰዱ ትንቢት በመናገር የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ማገልገል ነበረበት! ኢዮአካዝን፣ ኢዮአቄምን፣ ዮአኪንንና (ኢኮንያንንና) ሴዴቅያስን በመሳሰሉ ክፉ ነገሥታት ግዛት ውስጥ ለ40 ዓመታት በኢየሩሳሌም ትንቢት መናገር ነበረበት። (ኤር. 1:2, 3) ቆየት ብሎም ወደ ግብፅ በሄደ ጊዜ በዚያ የነበሩ አይሁዳውያን ስደተኞች ይፈጽሙት የነበረውን ጣዖት አምልኮ በተመለከተ ትንቢት መናገር ነበረበት። መጽሐፉ ተጽፎ ያለቀው በ580 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። በመሆኑም የኤርምያስ መጽሐፍ ብዙ ዓበይት ክንውኖች የተፈጸሙባቸውን 67 ዓመታት የሚሸፍን ታሪክ ይዟል።—52:31
3 በዕብራይስጥ ቋንቋ የነቢዩና የመጽሐፉ ስም የሚጠራው ይርመያህ ወይም ይርመያሁ ተብሎ ሲሆን ትርጉሙም “ይሖዋ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ወይም ይሖዋ ይገላግላል [ከማኅፀን ለማለት ሳይሆን አይቀርም]” ማለት እንደሆነ ይገመታል። የኤርምያስ መጽሐፍ በሁሉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። በራሱ በኤርምያስ የሕይወት ዘመን በግልጽ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በርካታ ትንቢቶች የመጽሐፉን ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ። ከዚህ በላይ የኤርምያስ ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል። (ማቴ. 2:17, 18፤ 16:14፤ 27:9) ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ባጸዳበት ወቅት በኤርምያስ 7:11 ላይ ያሉትን ቃላት በኢሳይያስ 56:7 ላይ ከሚገኙት ቃላት ጋር አጣምሮ መናገሩ የኤርምያስን መጽሐፍ እንዳነበበው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ማር. 11:17፤ ሉቃስ 19:46) እንዲያውም ኢየሱስ በነበረው ልበ ሙሉነትና ድፍረት የተነሣ አንዳንዶች ኤርምያስ ነው ብለው አስበው ነበር። (ማቴ. 16:13, 14) ኤርምያስ ስለ አዲስ ቃል ኪዳን የተናገረውን ትንቢት (ኤር. 31:31-34) ጳውሎስ በዕብራውያን 8:8-12 እና 10:16, 17 ላይ ጠቅሶታል። ጳውሎስ ኤርምያስ 9:24ን ጠቅሶ “የሚመካ በጌታ ይመካ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 1:31) ኤርምያስ የባቢሎንን አወዳደቅ አስመልክቶ የተጠቀመበት ምሳሌ (ኤር. 51:63, 64) በራእይ 18:21 ላይ ይበልጥ ጠንከር ባለ ሁኔታ ተገልጿል።
4 የአርኪኦሎጂ ግኝቶችም በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ ይደግፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የባቢሎናውያን ዜና መዋዕል ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በ617 ከክርስቶስ ልደት በፊት በመያዝ ንጉሡን (ዮአኪንን) አውርዶ በቦታው እርሱ የመረጠውን (ሴዴቅያስን) እንደሾመ ይናገራል።—24:1፤ 29:1, 2፤ 37:1a
5 ከጥንቶቹ ነቢያት መካከል ከሙሴ ሌላ የኤርምያስን ያህል የሕይወት ታሪኩ ይበልጥ በተሟላ መልኩ የሠፈረ ነቢይ የለም። ኤርምያስ ምን ይሰማው እንደነበር በመግለጽ ስለ ራሱ ብዙ ነገሮችን ያሰፈረ ሲሆን ትሕትናውና ከልብ የመነጨ ርኅራኄው ከልበ ሙሉነቱና ከድፍረቱ ጋር አንድ ላይ ተጣምረው ተገልጸዋል። ኤርምያስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን ካህንና ትክክለኛ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤ እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፉን አጠናቅሯል። ኤርምያስ፣ “በብንያም አገር” ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በምትገኘው ዓናቶት የምትባል የካህናት ከተማ ውስጥ የሚኖረው የካህኑ ኬልቅያስ ልጅ ነበር። (1:1) የኤርምያስ የአጻጻፍ ስልት ግልጽ፣ የማያሻማና በቀላሉ የሚገባ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ምሳሌያዊ አገላለጾችና ምናባዊ ሥዕሎች በብዛት ይገኛሉ፤ ትንቢቱ በስድ ንባብና በግጥም መልክ የተጻፉ መልእክቶችን አጣምሮ የያዘ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
36 በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረው ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ገንቢና ጠቃሚ ነው። ይህ ነቢይ የተወውን የቆራጥነት ምሳሌ ተመልከት። ከአምላክ በራቀው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያልነበረውን መልእክት ሲያውጅ አልፈራም። ከክፉዎች ጋር ለመወዳጀት ፈቃደኛ አልነበረም። የይሖዋ መልእክት አጣዳፊ መሆኑን በመገንዘብ ራሱን ለይሖዋ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከማቅረቡም በላይ በዚህ ሥራ እስከ መጨረሻው ገፍቶበታል። የአምላክ ቃል በአጥንቱ ውስጥ እንደ ረመጥ እሳት እንደሆነበት እንዲሁም ሐሴትና የልብ ደስታ እንደሰጠው ገልጿል። (ኤር. 15:16-20፤ 20:8-13) እኛም ለይሖዋ ቃል እንደዚህ ዓይነት ቅንዓት እናሳይ! እንዲሁም ባሮክ ኤርምያስን እንደረዳው ሁሉ እኛም ከአምላክ አገልጋዮች ጎን በታማኝነት በመቆም እንደግፋቸው። የሬካባውያን ልባዊ ታዛዥነትና አቤሜሌክ ስደት ላይ ለነበረው ነቢይ ያሳየው ደግነት ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል።—36:8-19, 32፤ 35:1-19፤ 38:7-13፤ 39:15-18
37 ወደ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ቅንጣት ታህል ዝንፍ ሳይል ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ ደግሞ ይሖዋ ትንቢት ለመናገር ባለው ችሎታ ላይ ያለንን እምነት እንደሚያጠነክርልን ምንም ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ያህል ኤርምያስ ራሱ በሕይወት እያለ ፍጻሜያቸውን ያገኙትን ትንቢቶች ተመልከት:- የሴዴቅያስ መማረክና የኢየሩሳሌም መጥፋት (21:3-10፤ 39:6-9)፣ የንጉሥ ሰሎም (ኢዮአካዝ) ከሥልጣን መውረድና በምርኮ እያለ መሞት (ኤር. 22:11, 12፤ 2 ነገ. 23:30-34፤ 2 ዜና 36:1-4)፣ የንጉሥ ኢኮንያን (ዮአኪን) በምርኮ ወደ ባቢሎን መወሰድና (ኤር. 22:24-27፤ 2 ነገ. 24:15, 16) የሐሰተኛው ነቢይ የሐናንያ በአንድ ዓመት ውስጥ መሞት (ኤር. 28:16, 17)። እነዚህና ሌሎች ትንቢቶች በሙሉ ይሖዋ አስቀድሞ እንደተናገረው ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከጊዜ በኋላ የተነሡት ነቢያትና የአምላክ አገልጋዮችም የኤርምያስን ትንቢቶች እውነተኛና ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና የምትቆየው ለ70 ዓመታት እንደሆነ ከኤርምያስ ጽሑፍ ተገንዝቦ የነበረ ሲሆን ዕዝራም በ70ው ዓመት መጨረሻ ላይ የኤርምያስ ቃል ፍጻሜውን እንዳገኘ ጠቅሷል።—ዳን. 9:2፤ 2 ዜና 36:20, 21፤ ዕዝራ 1:1፤ ኤር. 25:11, 12፤ 29:10
38 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የጌታ እራት በዓልን ባቋቋመበት ወቅት፣ አዲሱን ቃል ኪዳን አስመልክቶ ኤርምያስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ጠቁሟል። የኃጢአት ይቅርታ ስለሚያገኙበትና የይሖዋ መንፈሳዊ ሕዝብ በመሆን ስለሚሰበሰቡበት ኪዳን ሲናገር “በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን” በማለት ጠርቶታል። (ሉቃስ 22:20፤ ኤር. 31:31-34) መንፈሳዊ ልጆች በመሆን በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉት ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በሰማይ እንዲገዙ የመንግሥት ቃል ኪዳን የገባላቸው ሰዎች ናቸው። (ሉቃስ 22:29፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) ይህ መንግሥት በኤርምያስ ትንቢት ውስጥ በርካታ ጊዜያት ተጠቅሷል። እምነት የለሿን ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ያ ሁሉ ፍርድ ቢነገርም ኤርምያስ የሚከተለውን የተስፋ ብልጭታ ፈንጥቆ ነበር:- “‘እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል’ ይላል እግዚአብሔር።” አዎን፣ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ጽድቃችን” የሚባል ንጉሥ ይነሳል።—ኤር. 23:5, 6
39 ኤርምያስ “ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር፣ ለማስነሣላቸውም ለንጉሣቸው፣ ለዳዊት ይገዛሉ” በማለት እንደገና ስለ መቋቋምም ተናግሯል። (30:9) በመጨረሻም፣ የዳዊትን ዘር ለማብዛትና “በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ዘር” እንዲኖር ለማድረግ “በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ” በማለት እስራኤልንና ይሁዳን በተመለከተ ይሖዋ የተናገራቸውን መልካም ቃላት ገልጿል። (33:15, 21) ቀሪዎቹ ከባቢሎን እንደተመለሱ ሁሉ የዚህ ጻድቅ “ቅርንጫፍ” መንግሥትም በምድር ሁሉ ላይ ፍትሕንና ጽድቅን ማስፈኑ ምንም አያጠራጥርም።—ሉቃስ 1:32
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 326, 480