ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ናችሁ?
1. በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች የሚለዋወጡ መሆናቸው በምን ረገዶች ማስተካከያ ማድረግ ይጠይቅብናል?
1 መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 7:31 ላይ ይህን ዓለም፣ ሁልጊዜ የሚለዋወጡ ትእይንቶችና ተዋናዮች እንደሚቀርቡበት መድረክ አድርጎ ገልጾታል። በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች የሚለዋወጡ መሆናቸው እኛም በስብከት ዘዴያችን፣ በፕሮግራማችንና በአቀራረባችን ላይ አልፎ አልፎ ማስተካከያ እንድናደርግ ይጠይቅብናል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ናችሁ?
2. ድርጅቱ ከሚያደርገው ማስተካከያ ጋር እኩል መሄድ ያለብን ለምንድን ነው?
2 የስብከት ዘዴያችን፦ የክርስቲያን ጉባኤ በየጊዜው ማስተካከያዎችን በማድረግ ይታወቃል። ኢየሱስ መጀመሪያ ላይ ደቀ መዛሙርቱን በላካቸው ጊዜ የምግብ ከረጢት ወይም በቦርሳቸው ገንዘብ እንዳይዙ አሳስቧቸው ነበር። (ማቴ. 10:9, 10) ይሁንና ኢየሱስ፣ ወደፊት ደቀ መዛሙርቱን የሚጠሏቸው ሰዎች እንደሚኖሩና የስብከቱ ሥራ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚስፋፋ ስለተገነዘበ ከጊዜ በኋላ በዚህ መመሪያ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። (ሉቃስ 22:36) ባለፈው መቶ ዓመት የይሖዋ ድርጅት የተለያዩ የስብከት ዘዴዎችን ሲጠቀም ቆይቷል፤ ለምሳሌ ወንድሞች በወቅቱ የሚያስፈልገውን ነገር ከግምት በማስገባት ምሥክርነት መስጫ ካርዶችን፣ የሬዲዮ ፕሮግራሞችንና የድምፅ ማጉያ መሣሪያ የተገጠመላቸው መኪኖችን ይጠቀሙ ነበር። በዛሬው ጊዜ በበርካታ አካባቢዎች ሰዎች ቤታቸው ስለማይገኙ ከቤት ወደ ቤት ከሚደረገው አገልግሎት በተጨማሪ ለአደባባይና መደበኛ ላልሆነ ምሥክርነት ትኩረት ተሰጥቷል። እንዲሁም ሰዎች ቀን ላይ ሥራ የሚውሉ ከሆነ አመሻሹ ላይ ከቤት ወደ ቤት እንድንሄድ ተበረታተናል። የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ አቅጣጫውን ሲቀይር እናንተስ ከድርጅቱ ጋር እኩል ለመሄድ ጥረት እያደረጋችሁ ነው?—ሕዝ. 1:20, 21
3. ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችን በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
3 መግቢያችን፦ በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት የሚያሳስባቸው ነገር ምንድን ነው? የኢኮኖሚው ሁኔታ? የቤተሰብ ጉዳይ? ወይስ ጦርነት? በክልላችን ያሉ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችና ያሉበትን ሁኔታ መረዳታችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ተስማሚ የሆነ መግቢያ ለመዘጋጀት ያስችለናል። (1 ቆሮ. 9:20-23) የምናነጋግራቸው ሰዎች የሚያሳስባቸውን ነገር ሲገልጹልን የተለመደ መልስ ሰጥተን የተዘጋጀነውን ሐሳብ መናገራችንን ከመቀጠል ይልቅ አቀራረባችንን አስተካክለን እነሱን በሚያሳስባቸው ነገር ላይ መወያየታችን በጣም የተሻለ ነው።
4. ማስተካከያ ለማድረግ ፈጣኖች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
4 በቅርቡ የዚህ ዓለም የመጨረሻ “ትእይንት” ተደምድሞ ታላቁ መከራ ይጀምራል። “የቀረው ጊዜ አጭር” ነው። (1 ቆሮ. 7:29) ታዲያ በቀረን አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሥራ ለማከናወን እንድንችል ነገ ዛሬ ሳንል ማስተካከያ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!