ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ራስን መከላከያ ስልቶችን ባጠና ይሻል ይሆን?
“በትምህርት ቤት ውስጥ በጣም መጥፎ ልጆች አሉ” አለ ጄሲ። “በኮሪደሩ በኩል ስታልፍ እስኒከር ጫማህን፣ ጃኬትህን ወይም ሱሪህን ከፈለጉ ይወስዱብሃል። እንዳታመለክት ሌላ ጊዜ አይለቁህም።”
ብዙ ወጣቶች በየቀኑ የሚያጋጥማቸውን ጥቃት እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ማሰብ አስፈልጓቸዋል። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚማሩ አምስት ተማሪዎች አንዱ ሽጉጥ፣ ጩቤ፣ ሰንጢ፣ ዱላ ወይም ሌላ መሣሪያ ይይዛል። ብዙ ተማሪዎች እነዚህን ነገሮች ይዘው ትምህርት ቤት ይሄዳሉ።” ጃይሮ የሚባል በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወጣት ይህን በዓይኑ አይቷል። ጃይሮ እንዲህ ይላል:- “ትምህርት ቤታችን በመሣሪያ መመርመሪያ አማካኝነት ተማሪዎችን በመፈተሽ ረገድ [በኒው ዮርክ ከተማ] የመጀመሪያው ቢሆንም ልጆቹ ሰንጢዎችና ሽጉጦች እንዳይዙ አላገዳቸውም። ልጆቹ መሣሪያዎቹን እንዴት ወደ ትምህርት ቤቱ እንደሚያስገቧቸው ባላውቅም የጦር መሣሪያዎች ይይዛሉ።”
ብዙ ወጣቶች ጥቃት እንዳይሰነዘርባቸው በመስጋት ራሳቸውን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ የሚያሳስባቸው ለምን እንደሆነ ሊገባን ይችላል። ወጣቷ ሎላ እንዲህ ብላለች:- “የጆሮ ጌጦቿን ለመውሰድ ሲሉ አንዲት ወጣትን ከገደሏት በኋላ በእኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ራስን የመከላከያ ትምህርቶች መሰጠት ጀመሩ። አብዛኞቹ ተማሪዎች ተመዘገቡ።” ሌሎች ወጣቶች የሚረጩ ኬሚካሎችና ሌሎች መሣሪዎችን ለመያዝ ወስነዋል። ጥያቄው ራስን መከላከያ ስልቶች በእርግጥ ከአደጋ ሊጠብቁህ ይችላሉን? የሚል ነው።
ራስን መከላከያ ስልቶች
ራስን መከላከያ ስልቶችን የተካኑ ሰዎች በአየር ላይ ሲገለባበጡ እንዲሁም ለእይታ በሚማርክ አኳኋን በቡጢና በእርግጫ ሲማቱ ዘወትር በቴሌቪዥን ይታያሉ። በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ ወረበሎች ሲዘረሩ ይታያል። በጣም የሚገርም ነው! ራስን መከላከያ ስልቶች የመጨረሻ መፍትሔ መስለው ይቀርባሉ። ሆኖም እውነታው ሕይወት በፊልም ላይ እንደሚታየው ዓይነት አለመሆኗ ነው። አንድ የረጅም ዓመታት የካራቴ ልምድ ያለው ሰው እንዲህ ብሏል:- “አንዲት ጥይት ትበቃሃለች። መሣሪያ የያዘው ሰው ራቅ ያለ ከሆነ ምንም ልታደርግ አትችልም። እንደልብ መንቀሳቀስ በማያመች ቦታ ከሆንክም ይህን ያህል ለውጥ የለውም።”
በተጨማሪም አንድ ሰው ራስን መከላከያ ስልቶችን ለመማር ብዙ ገንዘብ ማጥፋትና ለበርካታ ዓመታት ከባድ ሥልጠና መውሰድ እንደሚያስፈልገው አስታውስ። ደግሞም ሥልጠናውን ካልቀጠልክበት እነዚህን ማራኪ እንቅስቃሴዎች የማድረግ ችሎታህን ፈጽሞ ልትረሳ ትችላለህ። እንደ ቦክስ ስለ መሳሳሉት ሌሎች ራስን መከላከያ ስልቶችም እንደዚሁ ሊባል ይችላል። ከዚህም በላይ ራስን መከላከያ ስልቶች እንደምትችል ከታወቀ አላስፈላጊ ትኩረት ልትስብ ትችላለህ። ጠብ ጫሪዎች ከአንተ ጋር መጋጠም ይፈልጉ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ራስን መከላከያ ስልቶችን መማር ከዚህ የበለጠ አደጋ አለው። በቅርቡ ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቦ ነበር:- “ሁሉም አሊያም አብዛኞቹ ራስን መከላከያ ስልቶች ከሦስቱ ዋና ዋና የምሥራቅ እስያ ሃይማኖቶች ማለትም ከቡድሂዝም፣ ከታኦይዝምና ከኮንፈሺያኒዝም ጋር ጥብቅ ትስስር ያላቸው ናቸው።” ሌላ ጽሑፍ ደግሞ እንዲህ ሲል አክሏል:- “በካራቴ የሚደረገው እያንዳንዱ ነገር ማለትም እያንዳንዱ እንቅስቃሴና ስሜት ከዜን መሠረታዊ ሥርዓቶች የመጣ ስለ መሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።” ዜን ለሃይማኖታዊ ማሰላሰል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ የቡድሂዝም እምነት ቅርንጫፍ ነው። “ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው [ከሐሰት ሃይማኖት] ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል” ከሚሉት በ2 ቆሮንቶስ 6:17 ላይ ከሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አንፃር ሲታይ ይህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥረ መሠረት ያላቸው ተግባሮች ለክርስቲያኖች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥሩባቸዋል።
የማጥቂያ መሣሪያዎችን መጠቀም
ታዲያ በኪሳችን ወይም በቦርሳችን ሽጉጥ ወይም ሰንጢ ብንይዝስ? እንደዚያ ማድረግህ ልበ ሙሉነት እንዲሰማህ ሊያደርግ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም አላስፈላጊ በሆነ መንገድ ራስህን አደጋ ላይ ከጣልክ ወይም በራስህ ላይ ችግር የምትጋብዝ ከሆነ ይህ ልበ ሙሉነት ሕይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል” ሲል ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 11:27) በተጨማሪም ራስህ ያልጋበዝከው ችግር ቢመጣብህ መሣሪያ መምዘዝህ ግጭቱን ይበልጥ እንደሚያባብሰው የተረጋገጠ ነው። ልትገደል ወይም ሌላ ሰው ልትገድል ትችላለህ። የኃይል ድርጊት ከመጠቀም መቆጠብ ስትችል እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ብትወስድ የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላክ ጉዳዩን እንዴት ይመለከተዋል?— መዝሙር 11:5፤ 36:9
አንዳንዶች የግድያ መሣሪያውን እጠቀምበታለሁ ብለው እንደማያስቡ የተረጋገጠ ነው። መሣሪያውን ሌሎችን ለማስፈራራት ሲሉ ብቻ እንደሚይዙት ይናገሩ ይሆናል። ሆኖም ሄልዝ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “የጦር መሣሪያ አሠልጣኞች በሚከተለው ሐሳብ ይስማማሉ:- ልትጠቀምበት ዓላማ ከሌለህ ሽጉጥ አትያዝ። ሽጉጥ መያዛችንን ለማሳየት ብንሞክር አንዳንድ አጥቂዎችን ሊያስፈራራቸው ቢችልም ሌሎችን ያናድዳቸዋል።”
“የማይጎዱ” የሚባሉትን የሚረጩ ኬሚካሎች የመሳሰሉትን መሣሪያዎች ስለ መጠቀም ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ መሣሪያዎች በአንዳንድ ቦታዎች ሕጋዊ ካለመሆናቸውም በላይ ከባድ ጉዳቶች ያስከትላሉ። በዕፅ አእምሮው የዞረ አጥቂን ከማሽመድመድ ይልቅ የበለጠ ሊያናድዱት ይችላሉ። ነፋስ ኬሚካሎቹን ከአጥቂዎችህ ይልቅ አንተ ፊት ላይ ሊበትናቸው ይችላል። ለዚያውም የሚረጨውን ኬሚካል ቀድመህ ካወጣህ ነው። ጥቃት ሰንዛሪው እጅህን ወደ ኪስህ ወይም ወደ ቦርሳህ ስታደርግ ሲመለከት ሽጉጥ ለማውጣት ያሰብክ መስሎት የራሱን ከባድ እርምጃ ለመውሰድ ሊወስን ይችላል። ስለዚህ አንድ መርማሪ ፖሊስ የሚከተለውን ሐሳብ ሰንዝሯል:- “ለጊዜው የሚያሽመደምድ ፈሳሽ [የሚረጭ ኬሚካል] ወይም ሌላ መሣሪያ መጠቀም ዋስትና ሊሆን አይችልም። ወይም ደግሞ መሣሪያውን ቀድመህ ልትጠቀምበት እንደምትችል እርግጠኛ መሆን አትችልም። ጊዜ የማይሰጥ ችግር ከመጣ መሣሪያዎች ፈጽሞ አይረዱም። ሰዎች ግን ከመጠን በላይ ይተማመኑባቸዋል።”
ለመሣሪያዎች ሊኖረን የሚገባ አምላካዊ አመለካከት
የኃይል ድርጊት ይፈጸምብኛል የሚል ስጋት በኢየሱስ ዘመንም ነበር። ብዙውን ጊዜ የደጉ ሳምራዊው ምሳሌ ተብሎ የሚጠራው በስፋት የሚታወቀው ምሳሌው ወንበዴዎች ስለ ደበደቡት ሰው የሚገልጽ ነው። (ሉቃስ 10:30-35) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሰይፍ እንዲይዙ የጠየቃቸው ራሳቸውን ለመከላከል እንዲችሉ አልነበረም። እንዲያውም ከዚያ በኋላ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ተናግሯል።— ማቴዎስ 26:51, 52፤ ሉቃስ 22:36-38
ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን ለመጉዳት አስበው መሣሪያ አይታጠቁም። (ከኢሳይያስ 2:4 ጋር አወዳድር።) በሮሜ 12:18 ላይ የሚገኘውን “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። ታዲያ ይህ ማለት ፈጽሞ መከላከያ የላቸውም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም።
ጥበብ ከጦር መሣሪያዎች የተሻለ ነው
ለማንኛውም ነገር አዲስ መሣሪያ በሚፈለሰፍበት ዘመን ከማናቸውም ሰው ሠራሽ መሣሪያ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ራስህን የምትጠብቅበትን ዘዴ በእጅህ ልታደርግ እንደምትችል ብታውቅ ትገረም ይሆናል። መክብብ 9:18 ላይ “ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች” የሚል እናነባለን። ይህ አንዳንዶች “ብልጣ ብልጥነት” ከሚሉት ዓይነት ጥበብ የበለጠ ነው። ይህ ጥበብ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ከማዋል የሚገኝና ብዙውን ጊዜ የኃይል ድርጊት ከሚፈጸሙባቸው ሁኔታዎች ከመጀመሪያው ለመራቅ የሚረዳ ነው።
ለምሳሌ ያህል የኃይል ድርጊት ስለሚፈጸምበት ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል የገለጸው ጃይሮ “በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፣ የራሳችሁን ጉዳይ ልትጠነቀቁ” የሚሉትን በ1 ተሰሎንቄ 4:11 ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በሥራ ላይ በማዋል ከችግር ይርቃል። ጃይሮ እንዲህ ይላል:- “ጠብ እንደሚፈጠር ካወቅህ ጉዳይህ እንዳልሆነ በማወቅ ወደ ቤትህ መሄድ አለብህ። አንዳንዶች ከዚያ አካባቢ ባለመጥፋት ችግር ውስጥ ይወድቃሉ።”
ወጣቷ ሎላ “ከሁሉ የበለጠ ጥበቃ የሆነልኝ ሁሉም ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኔን እንዲያውቅ ማድረጌ ነው” ብላለች። “እኔ በእነሱ ላይ ጉዳት እንደማላደርስ ስለሚያውቁ ሰዎች ምንም አያደርጉኝም።” ኤሊዩ እንዲህ ሲል አክሏል:- “የይሖዋ ምሥክር ነኝ ማለት ብቻ በቂ አይደለም። አንተ ከሌሎች የተለየህ መሆንህን ማየት መቻል አለባቸው።” ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል’ መሆን የለባቸውም። (ዮሐንስ 15:19) ሆኖም የበላይነት መንፈስ እንዳታሳይ ተጠንቀቅ። (ምሳሌ 11:2) አንድ ወጣት “በኮሪደሩ ውስጥ በማን አለብኝነት ደረትህን ነፍተህ አትሂድ” ሲል ጉዳዩን ገልጾታል። ይህ ሊያበሽቃቸው ይችላል። ሉቺ የተባለ አንድ ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ይላል:- “ተግባቢ ነኝ፤ በክፍሌ ውስጥ ካሉት ተማሪዎች ጋር እጫወታለሁ፤ ሆኖም እነሱ የሚያደርጉትን ለማድረግ አልሞክርም።”
አለባበስህም በጣም አስፈላጊ ነው። “የሌሎችን ትኩረት የሚስቡ ልብሶችን ላለመልበስ እጠነቀቃለሁ” ስትል አንዲት ወጣት ተናግራለች። “ቆንጆ ሆኜ ለመታየት በጣም ውድ የሆኑ ልብሶችን የግድ መልበስ እንዳለብኝ አድርጌ አላስብም።” መጽሐፍ ቅዱስ ልከኛ አለባበስ እንዲኖረን የሚሰጠንን ምክር መከተላችን ጎልተን እንዳንታይና ችግር ውስጥ እንዳንገባ ይጠብቀናል።— 1 ጢሞቴዎስ 2:9
የኃይል ድርጊት ከተቃጣብህ
ሆኖም ጉዳት ከሚያስከትሉ ነገሮች ለመራቅ ጥረት ብታደርግም እንኳ የኃይል ድርጊት ቢቃጣብህስ? በመጀመሪያ “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች። ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” የሚለውን በምሳሌ 15:1 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ለመተግበር ሞክር። ወጣቱ ኤሊዩ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ይህን ምክር ሠርቶበታል። እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ጠብ ለመጫር ተብለው የሚሰነዘሩ ቃላትን ያን ያህል አክብዶ ማየት አያስፈልግም። አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚያስከትለው ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ነው።” ‘ክፉውን በክፉ ከመመለስ’ በመቆጠብ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ልታደርግ ትችል ይሆናል።— ሮሜ 12:17
ሆኖም ሁኔታውን በለሰለሰ አንደበት ለማብረድ ያደረግኸው ጥረት ካልተሳካ ራስህን ለመከላከል አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ አለበህ። በቡድን ሆነው የመጡ ወጣቶች እስኒከር ጫማህን ወይም ውድ የሆኑ ሌሎች ንብረቶችን እንድትሰጣቸው ከጠየቁህ ስጣቸው። ሕይወትህ ከንብረቶችህ የበለጠ ውድ ነው። (ሉቃስ 12:15) ለመደባደብ ካሰቡ ቀስ ብለህ ከእነሱ ተለይ። እንዲያውም ብትሮጥ ይሻላል! ምሳሌ 17:14 [አዓት] “ጥል ከመነሣቱ በፊት ትተህ ሂድ” ይላል። (ከሉቃስ 4:29, 30 እና ዮሐንስ 8:59 ጋር አወዳድር።) ማምለጥ የማይቻል ከሆነ የኃይል ድርጊቱን የምትችለውን ያህል ከመከላከል በቀር ምንም ምርጫ ላይኖርህ ይችላል። ከዚያ በኋላ የደረሰብህን ነገር ለወላጆችህ ተናገር። ምናልባት በሆነ መንገድ ሊረዱህ ይችሉ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው አሁን የምንኖረው ዓመፅ በሞላበት ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ይሁን እንጂ ሽጉጥ መያዝ ወይም የካራቴ አመታት መማር ከአደጋ ሊጠብቅህ አይችልም። ጠንቃቃ ሁን። ችግር ሲያጋጥምህ አምላካዊ ጥበብ ተጠቀም። ከሁሉም በላይ በይሖዋ ላይ እምነትና ትምክህት ይኑርህ። እንደ መዝሙራዊው “የኃይል ድርጊት ከሚፈጽም ሰው ታድነኛለህ” ብለህ በልበ ሙሉነት ልትጸልይ ትችላለህ።— መዝሙር 18:48 አዓት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራስን መከላከያ ስልቶች ለክርስቲያኖች መፍትሔ አይሆኑም