የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ግንቦት 2018
ከግንቦት 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 7-8
“የራሳችሁን የመከራ እንጨት ተሸክማችሁ ያለማቋረጥ ተከተሉኝ”
(ማርቆስ 8:34) ከዚህ በኋላ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 8:34
ራሱን ይካድ፦ ወይም “በራሱ ላይ ያለውን መብት ሁሉ አሳልፎ ይስጥ።” ይህም ግለሰቡ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለመካድ ወይም በራሱ ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት ለአምላክ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ይጠቁማል። የግሪክኛው አገላለጽ “ራሱን እምቢ ማለት አለበት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህ አገላለጽ እንዲህ ተብሎ መተርጎሙ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ‘ራስን መካድ’ የራስን ፍላጎት፣ ምኞት ወይም ምቾት እምቢ ማለትን ሊጨምር ይችላል። (2ቆሮ 5:14, 15) ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደካደው በሚገልጸው የማርቆስ ዘገባም ላይ ይኸው የግሪክኛ ግስ ተጠቅሶ ይገኛል።—ማር 14:30, 31, 72
የሕይወትን ሩጫ እንዴት እየሮጣችሁ ነው?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰብስበው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ሰዎች “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ [የመከራውን እንጨት አዓት] ይከተለኝ” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 12:40) ይህን ጥሪ ስንቀበል ባለማቋረጥ የመከራውን እንጨት ለመሸከም መዘጋጀት ያለብን ራስን መካድ ብቻ በራሱ ልዩ ሽልማት ስላለው ሳይሆን የአንዳፍታ ጥንቃቄ ጉድለት፣ የአንድ ጥሩ ማስተዋል መዛባት ቀደም ብሎ የተገነባውን ሁሉ ሊያበላሸው፣ አልፎ ተርፎም የዘላለም ደህንነታችንንም ሳይቀር አደጋ ላይ ሊጥለው ስለሚችል ነው። አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ ዕድገት የሚመጣው ቀስ በቀስ ሲሆን ዘወትር ካልተጠነቀቅን ግን በአንድ ጊዜ ባዶ ሊሆን ይችላል።
(ማርቆስ 8:35-37) ሕይወቱን ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔና ለምሥራቹ ሲል ሕይወቱን የሚያጣ ሁሉ ግን ያድናታል። 36 ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ሕይወቱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37 ሰው ለሕይወቱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?
የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ያህል መሥዋዕት ትከፍላለህ?
3 በዚያው ወቅት ኢየሱስ ትኩረት የሚስቡ ሁለት ጥያቄዎችን አንስቷል፤ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር። (ማቴ. 16:26) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ግልጽ ነው። አንድ ሰው፣ ዓለም ሁሉ የእሱ ቢሆንና ሕይወቱን ወይም ነፍሱን ቢያጣ ምንም አይጠቀምም። አንድ ሰው ባሉት ነገሮች ሊደሰት የሚችለው በሕይወት ሲኖር ብቻ ነው። ኢየሱስ “ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?” በማለት ያነሳው ሁለተኛ ጥያቄ አድማጮቹ፣ “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” በማለት ሰይጣን በኢዮብ ዘመን የሰነዘረውን ክስ እንዲያስታውሱ አድርጓቸው ይሆናል። (ኢዮብ 2:4) ሰይጣን የሰነዘረው ሐሳብ ይሖዋን ከማያመልኩ አንዳንድ ሰዎች ጋር በተያያዘ እውነት ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ሕይወታቸውን ላለማጣት ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወይም የትኛውንም የሥነ ምግባር ሕግ ከመጣስ ወደኋላ አይሉም። ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት አላቸው።
4 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በዚህ ዓለም ውስጥ ጥሩ ጤንነትና ሀብት ሊሰጠን እንዲሁም ረጅም ዕድሜ መኖር እንድንችል ሊረዳን እንዳልሆነ እናውቃለን። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር የምንችልበት አጋጣሚ ሊከፍትልን ሲሆን እኛም ይህን ተስፋ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (ዮሐ. 3:16) አንድ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ያነሳው የመጀመሪያ ጥያቄ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋውን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” ማለት እንደሆነ ይገነዘባል። የዚህ ጥያቄ መልስ ‘ምንም ጥቅም የለውም’ የሚል ነው። (1 ዮሐ. 2:15-17) ኢየሱስ ላነሳው ሁለተኛ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ‘በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት የማግኘት ተስፋዬ እውን እንዲሆን በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ በአኗኗራችን የሚታይ ሲሆን ይህም ተስፋችን ምን ያህል እውን ሆኖ እንደሚታየን የሚጠቁም ነው።—ከዮሐንስ 12:25 ጋር አወዳድር።
(ማርቆስ 8:38) በዚህ አመንዝራና ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።”
የሰው ልጅ ማን ነው?
በእርግጥም፣ የኢየሱስ ተከታዮች የእሱን ሞገስ ለማግኘት ከፈለጉ ደፋሮችና የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ መሆን አለባቸው። ኢየሱስ “በዚህ አመንዝራና ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ ያፍርበታል” ብሏል። (ማርቆስ 8:38) አዎን፣ ኢየሱስ በዚያ ጊዜ ሲመጣ “ለእያንዳንዱ እንደ ምግባሩ ይከፍለዋል።”—ማቴዎስ 16:27
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 7:5-8) በመሆኑም እነዚህ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። 7 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’ 8 የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”
የአንባቢያን ጥያቄዎች
የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ለእጅ መታጠብ ትልቅ ቦታ ይሰጡ የነበረው ለምንድን ነው?
▪ የኢየሱስ ጠላቶች በእሱና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ጥፋት ከሚፈላልጉባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህ ነበር። የሙሴ ሕግ አንድን ሰው የሚያረክሱት ነገሮች ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል፤ ከእነዚህ መካከል ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾች፣ የሥጋ ደዌ በሽታ እንዲሁም የሰዎችን ወይም የእንስሳት አስከሬኖችን መንካት ይገኙበታል። በተጨማሪም ሕጉ ከርኩሰት መንጻት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዟል። ይህ የመንጻት ሥርዓት መሥዋዕት በማቅረብ፣ በመታጠብ ወይም ውኃ በመርጨት ሊፈጸም ይችላል።—ዘሌ. ከምዕ. 11 እስከ 15፤ ዘኁ. ምዕ. 19
አይሁዳውያን ረቢዎች በእነዚህ ሕጎች ላይ ብዙ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጡ ነበር። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው፣ አንድን ሰው ሊያረክሰው የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ እንዲሁም ግለሰቡ ሌሎች ሰዎችን ሊያረክስ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ተጨማሪ ሕግ አውጥተው ነበር። ከዚህም ሌላ ሊረክሱ የሚችሉና የማይችሉ ዕቃዎች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም የመንጻት ሥርዓት የሚካሄድበት መንገድና ለመንጻት የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ የሚገልጹ ደንቦች ነበሯቸው።
የኢየሱስ ተቃዋሚዎች “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። (ማር. 7:5) እነዚህ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ያሳሰባቸው አንድ ሰው ንጽሕናውን ለመጠበቅ ሲል እጁን የመታጠቡ ጉዳይ አልነበረም። ረቢዎች ምግብ ከመብላታቸው በፊት ሌላ ሰው ውኃ እያፈሰሰላቸው እጃቸውን የመታጠብ ልማድ ነበራቸው። ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ውኃውን ለማፍሰስ ስለሚያገለግለው ዕቃ፣ ስለ ውኃው ዓይነት፣ ስለሚያስታጥባቸው ሰው እንዲሁም እጃቸውን እስከ የት ድረስ መታጠብ እንዳለባቸው የተለያየ አመለካከት አላቸው።”
ኢየሱስ ሰዎች ያወጧቸውን እንዲህ ያሉትን ሕጎች አስመልክቶ ያለው አቋም ግልጽ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ [ከይሖዋ] እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’ የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”—ማር. 7:6-8
(ማርቆስ 7:32-35) በዚያም ሰዎች መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት አንድ ሰው ወደ እሱ አምጥተው እጁን እንዲጭንበት ተማጸኑት። 33 እሱም ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደው። ከዚያም ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አስገባ፤ እንትፍ ካለ በኋላም የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። 34 ወደ ሰማይ እየተመለከተም በረጅሙ ተንፍሶ “ኤፈታ” አለው፤ ይህም “ተከፈት” ማለት ነው። 35 በዚህ ጊዜ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ።
‘ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ’ አላችሁን?
9 ሰውዬው መስማት የተሳነውና መናገር የሚቸግረው ሰው ነበር። ኢየሱስ ይህ ሰው የተሰማውን የመረበሽ ወይም የእፍረት ስሜት ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አንድ ያልተለመደ ነገር አደረገ። ሰውዬውን ከሕዝቡ ለይቶ ገለል ወዳለ ስፍራ ወሰደው። ከዚያም ኢየሱስ የሚያደርገውን ነገር ለማስረዳት ለሰውዬው ምልክት አሳየው። “ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ።” (ማርቆስ 7:33) ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለከተና ቃተተ። እነዚህ ድርጊቶች ለሰውዬው ‘አሁን ለአንተ የማደርግልህ ከአምላክ ባገኘሁት ኃይል ነው’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። በመጨረሻም ኢየሱስ “ተከፈት” አለ። (ማርቆስ 7:34) በዚያን ጊዜ ሰውዬው መሥማትና አጥርቶ መናገር ቻለ።
10 ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው እንዴት ያለ አሳቢነት ነው! ለስሜታቸው ይጠነቀቅ ነበር፤ እንዲህ ያለው የአዛኝነት ባሕርይ ደግሞ የሌሎችን ስሜት የሚጎዳ ነገር እንዳያደርግ ይገፋፋዋል። እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ረገድ የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበርና ማንጸባረቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) ይህም የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ እንዳስገባን በሚያሳይ መንገድ እንድንናገርና እንድናደርግ ይጠይቅብናል።
11 ለእኛ እንዲደረግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች በማድረግ ሰብአዊ ክብራቸውን ከጠበቅን ለሌሎች ስሜት አሳቢ መሆናችንን በጉባኤ ውስጥ ማሳየት እንችላለን። (ማቴዎስ 7:12) ይህም ስለምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን እንዴት ብለን እንደምንናገር ጠንቃቆች መሆንንም ይጨምራል። (ቆላስይስ 4:6) ‘ሳይታሰብ የሚሰነዘሩ ቃላት እንደ ሰይፍ ሊያቆስሉ እንደሚችሉ’ አስታውስ። (ምሳሌ 12:18) በቤተሰብ መካከልስ? እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች አንዱ ለሌላው ስሜት ያስባሉ። (ኤፌሶን 5:33) ሻካራ ቃላትን ከመናገር፣ የነቀፋ ውርጅብኝ ከማውረድና የሚከነክን የሽሙጥ ቃል ከመናገር ይቆጠባሉ። እነዚህ ሁሉ በቀላሉ የማይሽር የስሜት ቁስል ሊያስከትሉ ይችላሉ። ልጆችም ቢሆኑ ስሜት አላቸው፤ አፍቃሪ ወላጆች ይህን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። እርማት መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እንደነዚህ ያሉት ወላጆች የልጆቻቸውን ክብር በሚጠብቅ መንገድ እርማት በመስጠት ልጆቻቸውን ከማበሳጨት ይቆጠባሉ። (ቆላስይስ 3:21) በዚህ መንገድ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት ስናሳይ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለን እናንጸባርቃለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 7:1-15) ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና አንዳንድ ጸሐፍት ወደ እሱ ተሰበሰቡ። 2 ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ በረከሰ ማለትም ባልታጠበ እጅ ምግብ ሲበሉ አዩ። 3 (ፈሪሳውያንና አይሁዳውያን ሁሉ የአባቶችን ወግ አጥብቀው ስለሚከተሉ እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤ 4 ከገበያ ሲመለሱም ካልታጠቡ በስተቀር አይበሉም። ጽዋዎችን፣ ገንቦዎችንና የነሐስ ዕቃዎችን ውኃ ውስጥ እንደመንከር ያሉ ከአባቶቻቸው የወረሷቸውና አጥብቀው የሚከተሏቸው ሌሎች በርካታ ወጎችም አሉ።) 5 በመሆኑም እነዚህ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። 7 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’ 8 የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።” 9 ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ በዘዴ ገሸሽ ታደርጋላችሁ። 10 ለምሳሌ ሙሴ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይገደል’ ብሏል። 11 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ቁርባን (ማለትም ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ) ነው” ቢል’ 12 ከዚያ በኋላ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። 13 በመሆኑም ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የአምላክን ቃል ትሽራላችሁ። እንዲህ ያለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።” 14 ከዚያም ሕዝቡን እንደገና ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሁላችሁም ስሙኝ፤ የምናገረውንም አስተውሉ። 15 ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰውን የሚያረክሰው ከውስጡ የሚወጣው ነው።”
ከግንቦት 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 9-10
“እምነት የሚያጠናክር ራእይ”
(ማርቆስ 9:1) ቀጥሎም “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት በታላቅ ኃይል መምጣቱን እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም” አላቸው።
ትንቢት የሚያተኩረው በክርስቶስ ላይ ነው
9 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጠውን ከላይ የተጠቀሰውን ማስረጃ ካቀረበ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በ32 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተከበረውም የቂጣ በዓል አልፏል። በኢየሱስ አምነው የነበሩ ብዙ ሰዎች በስደት፣ በፍቅረ ነዋይ ወይም በኑሮ ጭንቀቶች የተነሳ ሳይሆን አይቀርም እርሱን መከተል አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ሰዎች ሊያነግሡት ሲሞክሩ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ግራ የተጋቡና ተስፋ የቆረጡ ይመስላል። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተአምር እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ ራሱን ለማስከበር ሲል ከሰማይ ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። (ማቴዎስ 12:38, 39) ይህን ጥያቄያቸውን አለማስተናገዱ አንዳንዶቹን ግራ ሳያጋባቸው አልቀረም። ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ” እንዳለው ሲነግራቸው ጉዳዩን መረዳት በጣም ከበዳቸው።—ማቴዎስ 16:21-23
10 ከዘጠኝ እስከ አሥር ወር በሚያህል ጊዜ ውስጥ ‘ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ’ ይደርሳል። (ዮሐንስ 13:1) የታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ በጣም ስላሳሰበው ለእምነት የለሾቹ አይሁዳውያን ነፍጓቸው የነበረውን ያንኑ ነገር ማለትም ከሰማይ የመጣ ምልክት ለአንዳንዶቹ ለማሳየት ተስፋ ሰጣቸው። ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት ሰዎች መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ” አላቸው። (ማቴዎስ 16:28) ኢየሱስ መሲሐዊው መንግሥት በ1914 እስከሚቋቋምበት ጊዜ ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ በሕይወት ይኖራሉ ማለቱ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ኢየሱስ በጣም ለሚቀርቡት ሦስት ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ ሲቀመጥ የሚኖረውን አስደናቂ ክብር በትንሹ ለማሳየት አስቧል። ክብሩን የገለጠበት ይህ ራእይ የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ይባላል።
(ማርቆስ 9:2-6) ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ 3 ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር። 4 ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር። 5 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው። 6 እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር።
ትንቢት የሚያተኩረው በክርስቶስ ላይ ነው
11 ይህ ከሆነ ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። ቦታው የአርሞንዔም ተራራ ሸንተረር ሳይሆን አይቀርም። በዚያም ኢየሱስ “በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።” እንዲሁም ነቢዩ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩዋቸው። ይህ አስደናቂ ክንውን የተፈጸመው በምሽት ሳይሆን ስለማይቀር ለራእዩ የበለጠ ድምቀት ሰጥቶታል። እንዲያውም ራእዩ በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ጴጥሮስ ለኢየሱስ፣ ለሙሴና ለኤልያስ ሦስት ድንኳን ለመትከል ሐሳብ አቀረበ። ጴጥሮስ ገና ተናግሮ ሳያበቃ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።—ማቴዎስ 17:1-6
(ማርቆስ 9:7) ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 9:7
ድምፅ፦ ይሖዋ ለሰው ልጆች በቀጥታ እንደተናገረ ከሚገልጹ በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙ ሦስት ዘገባዎች መካከል ይህ ሁለተኛው ነው።—ለማር 1:11 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፤ ዮሐ 12:28
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 10:6-9) ይሁን እንጂ በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 7 ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ 8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። 9 ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”
የማርቆስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
10:6-9፦ አምላክ የትዳር ጓደኛሞች ዕድሜ ልክ አብረው እንዲኖሩ ዓላማው ነበር። በመሆኑም ባልና ሚስቶች በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ለመፋታት ከመጣደፍ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።—ማቴ. 19:4-6
(ማርቆስ 10:17, 18) ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው። 18 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 10:17, 18
ጥሩ መምህር፦ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሰው “ጥሩ መምህር” የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመበት ኢየሱስን ለማወደስ እንደሚያስችል የማዕረግ ስም አድርጎ ነው፤ በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ክብር እንዲሰጣቸው ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ተገቢ በሆነ መንገድ “መምህር” እና “ጌታ” ተብሎ መጠራቱን ባይቃወምም (ዮሐ 13:13) ሰዎች ለአባቱ ክብር እንዲሰጡ ይፈልግ ነበር።
ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም፦ እዚህ ላይ ኢየሱስ መልካምና ክፉ የሆነውን የመወሰን ሉዓላዊ መብት ያለው ከሁሉ የላቀው የጥሩነት መሥፈርት ይሖዋ መሆኑን እየገለጸ ነበር። አዳምና ሔዋን ዓመፀኞች በመሆን ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ መብላታቸው ይህን መብት ለራሳቸው መውሰድ እንደፈለጉ የሚያሳይ ነበር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ መሥፈርቶችን የማውጣት መብት ያለው አባቱ ብቻ እንደሆነ በትሕትና ተቀብሏል። አምላክ በቃሉ ውስጥ በሰፈሩት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች አማካኝነት መልካም የሆነውን ነገር አብራርቶልናል እንዲሁም አስተምሮናል።—ማር 10:19
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 9:1-13) ቀጥሎም “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት በታላቅ ኃይል መምጣቱን እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም” አላቸው። 2 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ 3 ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር። 4 ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር። 5 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው። 6 እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር። 7 ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። 8 ከዚያም ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም። 9 ከተራራው እየወረዱ ሳሉ የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አዘዛቸው። 10 እነሱም ቃሉን በልባቸው አኖሩ፤ ነገር ግን ከሞት መነሳት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 11 ከዚያም “ጸሐፍት፣ ኤልያስ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 12 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጀመሪያ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል፤ ይሁንና የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? 13 ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት በእርግጥ መጥቷል፤ እነሱም የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።”
ክርስቲያናዊ ሕይወት
“አምላክ ያጣመረውን . . .”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 10:4
የፍቺ የምሥክር ወረቀት፦ ሕጉ ፍቺ ለመፈጸም የሚያስብ ሰው ሕጋዊ ሰነድ እንዲያዘጋጅ ምናልባትም ሽማግሌዎችን እንዲያማክር ያዝዝ ነበር፤ ይህ ሕግ ግለሰቡ እንዲህ ያለውን ከባድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጊዜ ይሰጠዋል። የዚህ ሕግ ዓላማ ሰዎች በችኮላ ፍቺ እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንዲሁም ሴቶች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ መርዳት ነው። (ዘዳ 24:1) ይሁንና በኢየሱስ ዘመን የሃይማኖት መሪዎች ፍቺ መፈጸም ቀላል ነገር እንዲሆን አድርገው ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የታሪክ ምሁር የነበረውና እሱ ራሱ ከሚስቱ የተፋታው ፈሪሳዊው ጆሴፈስ “በማንኛውም ምክንያት (ደግሞም ወንዶች ሚስቶቻቸውን ለመፍታት ብዙ ሰበቦችን ያቀርባሉ)” መፋታት እንደሚቻል ተናግሯል።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 10:11
ሚስቱን ፈቶ፦ ወይም “ሚስቱን አሰናብቶ።” ማርቆስ ያሰፈረውን ኢየሱስ የተናገረውን ይህን ሐሳብ ልንረዳው የሚገባው ይበልጥ የተሟላ ሐሳብ ከያዘው ከማቴ 19:9 አንጻር ነው፤ ማቴ 19:9 “በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር” የሚለውን ሐሳብ አካትቶ ይዟል። ኢየሱስ ፍቺን አስመልክቶ የተናገረው ማርቆስ የጻፈው ሐሳብ የሚሠራው “በፆታ ብልግና” (ግሪክኛው ፖርኒያ) ሳይሆን በሌላ ምክንያት ፍቺ ለፈጸመ ሰው ነው።
በማመንዘር ሚስቱን ይበድላል፦ እዚህ ላይ ኢየሱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን “በማንኛውም ምክንያት” እንዲፈቱ የሚፈቅደውን ሰፊ ተቀባይነት የነበረውን የረቢዎች ትምህርት እየተቃወመ ነበር። (ማቴ 19:3, 9) አንድ ባል በሚስቱ ላይ ምንዝር ይፈጽማል የሚለው ሐሳብ ለብዙ አይሁዳውያን እንግዳ ነገር ነበር። ረቢዎቻቸው ባል መቼም ቢሆን በሚስቱ ላይ ሊያመነዝር እንደማይችል ከዚህ ይልቅ ታማኝነቷን ልታጓድል የምትችለው ሚስትየዋ ብቻ እንደሆነች ያስተምሩ ነበር። ባልየውም ከሚስቱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሥነ ምግባር ግዴታ እንዳለበት የሚገልጸው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ኢየሱስ ሴቶችን እንደሚያከብር የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ሴቶች ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ያደርጋል።
ከግንቦት 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 11-12
“ከሁሉ የበለጠ የሰጠችው እሷ ናት”
(ማርቆስ 12:41, 42) ኢየሱስ በመዋጮ ሣጥኖቹ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ ይመለከት ጀመር፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር። 42 በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 12:41, 42
በመዋጮ ሣጥኖቹ፦ ጥንታዊ የአይሁድ ምንጮች እነዚህ የመዋጮ ሣጥኖች ወይም ዕቃዎች የመለከት ወይም የቀንድ ቅርጽ እንደነበራቸው ይገልጻሉ፤ እነዚህ የመዋጮ ዕቃዎች ከላይ በኩል ትንሽ ቀዳዳ እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል። ሰዎች በእነዚህ የመዋጮ ሣጥኖች ውስጥ ለተለያየ ዓላማ የሚውል ገንዘብ ይከቱ ነበር። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል በዮሐ 8:20 ላይም የሚገኝ ሲሆን ‘ግምጃ ቤት’ ተብሎ ተተርጉሟል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው “ግምጃ ቤቱ” በሴቶች ግቢ ውስጥ ያለን አካባቢ ያመለክታል። (ተጨማሪ መረጃ ለ11ን ተመልከት።) የረቢዎች ጽሑፍ እንደሚገልጸው በዚህ ግቢ ግድግዳዎች ዙሪያ 13 የመዋጮ ሣጥኖች ይገኙ ነበር። በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከመዋጮ ሣጥኖቹ የተሰበሰበው ገንዘብ አንድ ላይ የሚቀመጥበት ዋና ግምጃ ቤት እንደነበር ይታመናል።
በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው፦ ቃል በቃል “አንድ ኳድራንስ።” ኮድራንተስ (ኳድራንስ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ነው) የሚለው የግሪክኛ ቃል የሮማውያንን የመዳብ ወይም የነሐስ ሳንቲም ያመለክታል፤ 64 ኳድራንስ የአንድ ዲናር ዋጋ ነበረው። እዚህ ላይ ማርቆስ አይሁዳውያን በስፋት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ሳንቲሞች ዋጋ ለመግለጽ የሮማውያንን ገንዘብ ተጠቅሟል።—ተጨማሪ መረጃ ለ14ን ተመልከት።
ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች፦ ቃል በቃል “ሁለት ሌፕታ” ሲሆን ሌፕተን የሚለው የግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው፤ ‘ትንሽና ስስ የሆነ ነገር’ የሚል ትርጉም አለው። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሌፕተን በጥንቷ እስራኤል ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ትንሹ የመዳብ ወይም የነሐስ ሳንቲም ነው፤ 128 ሌፕታ የአንድ ዲናር ዋጋ ነበረው።—ከቃላት መፍቻው ላይ “ሌፕተን” የሚለውን ርዕስና ተጨማሪ መረጃ ለ14ን ተመልከት።
(ማርቆስ 12:43) ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።
ይሖዋ በሙሉ ነፍስ የምታቀርቡትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
16 ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም በኒሳን 11፣ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ብዙ ሰዓታት አሳለፈ፤ በዚሁ ጊዜም በምን ሥልጣን ነገሮችን እንደሚያደርግ እንዲሁም ቀረጥን፣ ትንሣኤንና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ለቀረቡለት አስቸጋሪና ድንገተኛ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ ቆየ። ጻፎችንና ፈሪሳውያንንም ከሚያደርጓቸው ሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ‘የመበለቶችን ቤት ስለሚበሉ’ አወገዛቸው። (ማርቆስ 12:40) ከዚያም ኢየሱስ ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ወደ ሴቶች ሸንጎ ገብቶ አረፍ አለ፤ በዚህ ቦታ በአይሁዳውያን ወግ መሠረት 13 የገንዘብ ማስቀመጫ ዕቃዎች ተቀምጠው ነበር። ኢየሱስ ለጥቂት ጊዜ ተቀምጦ ሰዎች መዋጮአቸውን ሲያኖሩ በጥንቃቄ ይመለከት ነበር። ብዙ ሃብታሞች መዋጮ ለማድረግ የመጡ ሲሆን ምናልባትም የአንዳንዶቹ ሁኔታ ራስን የማመጻደቅ አልፎ ተርፎም የይታይልኝ ዓይነት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ሳይሆን አይቀርም። (ከማቴዎስ 6:2 ጋር አወዳድር።) የኢየሱስ ትኩረት አንዲት ሴት ላይ አረፈ። ሌላ ሰው ቢሆን ስለ እርሷም ሆነ ስላኖረችው ስጦታ የተለየ ነገር ላያስተውል ይችላል። ይሁን እንጂ የሌሎችን ልብ የማወቅ ችሎታ የነበረው ኢየሱስ “ድሃ መበለት” መሆኗን አውቋል። ምን ያህል ስጦታ እንዳስቀመጠችም በትክክል ያውቅ ነበር፤ “እጅግ አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ነበሩ።—ማርቆስ 12:41, 42 NW
17 ኢየሱስ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ነገር በዓይናቸው እንዲያዩ ሲል ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራቸው። ኢየሱስ ይህች መበለት “በመዝገብ ውስጥ . . . ከሁሉ አብልጣ ጣለች” ሲል ተናገረ። በእርሱ አመለካከት ሌሎች የጣሉት በአንድ ላይ ቢደመር እንኳ ከእርሷ ጋር አይተካከልም። “የነበራትን ሁሉ” ማለትም እጅዋ ላይ የቀረቻትን ጥቂት ገንዘብ ሰጠች። ይህ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከባት ተማምና እንደነበር ያሳያል። በመሆኑም ለአምላክ በመስጠት እንደ ምሳሌ ተደርጋ የተጠቀሰችው ከቁሳዊ ጠቀሜታ አንጻር እምብዛም ዋጋ ያልነበረው ስጦታ ያመጣችው ሴት ናት። ይሁን እንጂ ስጦታዋ በአምላክ ፊት በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ነበረው!—ማርቆስ 12:43, 44፤ ያዕቆብ 1:27
(ማርቆስ 12:44) ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።”
ይሖዋ በሙሉ ነፍስ የምታቀርቡትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
17 ኢየሱስ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ነገር በዓይናቸው እንዲያዩ ሲል ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራቸው። ኢየሱስ ይህች መበለት “በመዝገብ ውስጥ . . . ከሁሉ አብልጣ ጣለች” ሲል ተናገረ። በእርሱ አመለካከት ሌሎች የጣሉት በአንድ ላይ ቢደመር እንኳ ከእርሷ ጋር አይተካከልም። “የነበራትን ሁሉ” ማለትም እጅዋ ላይ የቀረቻትን ጥቂት ገንዘብ ሰጠች። ይህ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከባት ተማምና እንደነበር ያሳያል። በመሆኑም ለአምላክ በመስጠት እንደ ምሳሌ ተደርጋ የተጠቀሰችው ከቁሳዊ ጠቀሜታ አንጻር እምብዛም ዋጋ ያልነበረው ስጦታ ያመጣችው ሴት ናት። ይሁን እንጂ ስጦታዋ በአምላክ ፊት በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ነበረው!—ማርቆስ 12:43, 44፤ ያዕቆብ 1:27
w87-E 12/1 30 አን. 1
መሥዋዕትነት የሚያስከፍልህን ነገር ለመስጠት ፈቃደኛ ነህ?
ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ብዙ ጠቃሚ ትምህርት አለ። ምናልባትም ከሁሉ የሚበልጠው ትምህርት ግን የሚከተለው ነው፦ ሁላችንም በቁሳዊ ሀብታችን እውነተኛውን አምልኮ የመደገፍ መብት ቢኖረንም በአምላክ ዓይን እጅግ ከፍ ተደርጎ የሚታየው፣ ያን ያህል የማያስፈልገንን ነገር መስጠታችን ሳይሆን ለእኛ በጣም ውድ ዋጋ ያለውን ነገር መስጠታችን ነው። በሌላ አባባል ለይሖዋ የምንሰጠው እምብዛም የማያጎድለንን ነገር ነው ወይስ እውነተኛ መሥዋዕትነት የሚያስከፍለንን ነገር?
‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ
15 በዚያን ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ከመጡት ሰዎች ሁሉ ይህች መበለት ተለይታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሷ የሚያስገርም አይደለም? ይህ ምሳሌ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር የሚያደንቅ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። የምናቀርበው ስጦታ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ሊሆን ቢችልም እንኳ በሙሉ ነፍሳችን እስካደረግነው ድረስ ይሖዋ በደስታ ይቀበለዋል። ይሖዋ ይህን አስደሳች ሐቅ ለማስገንዘብ ሊጠቀምበት የሚችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 11:17) ሰዎቹንም ያስተምር ነበር፤ ደግሞም “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም? እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 11:17
ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት፦ ኢሳ 56:7ን ጠቅሰው ከጻፉት የወንጌል ጸሐፊዎች መካከል “ለሕዝቦች [ለሰዎች] ሁሉ የጸሎት ቤት” የሚለውን አገላለጽ ያካተተው ማርቆስ ብቻ ነው። (ማቴ 21:13፤ ሉቃስ 19:46) በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ የተገነባው እስራኤላውያንም ሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የባዕድ አገር ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩበትና ወደ እሱ የሚጸልዩበት ቦታ እንዲሆን ታስቦ ነበር። (1ነገ 8:41-43) ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለንግድ በመጠቀም የዘራፊዎች ዋሻ እንዲሆን ያደረጉትን አይሁዳውያን ማውገዙ ትክክል ነበር። ምክንያቱም ይህ ድርጊታቸው ሕዝቦች ሁሉ ወደ ይሖዋ የጸሎት ቤት በመምጣት ወደ እሱ እንዳይቀርቡ እንዲሁም ስለ እሱ የማወቅ አጋጣሚ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነበር።
(ማርቆስ 11:27, 28) እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በቤተ መቅደሱም ሲዘዋወር የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች መጥተው 28 “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።
በበለስ ዛፍ ተጠቅሞ ስለ እምነት ማስተማር
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ። ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ማስተማር ጀመረ። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት። ይህን ያሉት ከአንድ ቀን በፊት ገንዘብ መንዛሪዎቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በአእምሯቸው ይዘው ሳይሆን አይቀርም።—ማርቆስ 11:28
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 12:13-27) ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንን እና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ። 14 እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? 15 እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡና አሳዩኝ” አላቸው። 16 እነሱም አመጡለት፤ እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት። 17 ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ። 18 በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን ደግሞ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ 19 “መምህር፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሚስትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር መተካት እንዳለበት ጽፎልናል። 20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አገባና ዘር ሳይተካ ሞተ። 21 ከዚያም ሁለተኛው አገባት፤ ሆኖም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22 ሰባቱም ዘር አልተኩም። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 23 እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” 24 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም? 25 ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ። 26 ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም? 27 እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።”
ከግንቦት 28–ሰኔ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 13–14
“ሰውን መፍራት ወጥመድ እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ”
(ማርቆስ 14:29) ይሁንና ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለው።
(ማርቆስ 14:31) እሱ ግን “አብሬህ መሞት ቢኖርብኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” በማለት አጥብቆ ይናገር ጀመር። የቀሩትም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።
(ማርቆስ 14:50) በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ።
(ማርቆስ 14:47) ይሁን እንጂ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።
(ማርቆስ 14:54) ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ተከተለው፤ ከዚያም ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ጀመር።
(ማርቆስ 14:66-72) ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በታች በኩል ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ሴት አገልጋዮች አንዷ መጣች። 67 እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከዚህ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። 68 እሱ ግን “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” ሲል ካደ፤ ከዚያም ወደ መግቢያው ሄደ። 69 አገልጋይዋም እዚያ አየችውና በአጠገቡ ለቆሙት “ይህ ከእነሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ትናገር ጀመር። 70 አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በዚያ ቆመው የነበሩት ጴጥሮስን እንደገና “የገሊላ ሰው ስለሆንክ፣ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” ይሉት ጀመር። 71 እሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” ሲል ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። 72 ወዲያውኑ ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ከዚያም እጅግ አዝኖ ያለቅስ ጀመር።
ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል
14 ጴጥሮስ ሰዎቹን በጥንቃቄ ሲከተል ከቆየ በኋላ በኢየሩሳሌም ከሚገኙት ትላልቅ ቤቶች ወደ አንዱ ደረሰ። ይህ ቤት ባለጸጋ የሆነውና ተደማጭነት ያለው የሊቀ ካህናቱ የቀያፋ ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ቤቶች ከፊት በኩል ትልቅ በር ያለው ግቢ ይኖራቸዋል። ጴጥሮስ የግቢው በር ላይ ሲደርስ እንዳይገባ ተከለከለ። ከሊቀ ካህናቱ ጋር የሚተዋወቀውና ግቢው ውስጥ ገብቶ የነበረው ዮሐንስ ወጥቶ በር ጠባቂዋን በማነጋገር ጴጥሮስን አስገባው። ከዚያ በኋላ ግን ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር አብሮ የቆየ አይመስልም፤ ወይም ደግሞ ከጌታው ጎን ለመቆም ሲል ወደ ቤት ውስጥ ለመግባት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ላይ የሚመሠክሩት ሐሰተኛ ምሥክሮች ችሎቱ ወደሚካሄድበት ቤት ሲገቡና ሲወጡ እየተመለከተ የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም እሳት ከሚሞቁት አንዳንድ ባሪያዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ጋር ግቢው ውስጥ ቆሞ ነበር።—ማርቆስ 14:54-57፤ ዮሐንስ 18:15, 16, 18
it-2-E 619 አን. 6
ጴጥሮስ
ጴጥሮስ በአንድ ሌላ ደቀ መዝሙር እርዳታ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ይህ ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ወደ ሊቀ ካህናቱ መኖሪያ ተከትሎት ወይም ይዞት ሳይሄድ አይቀርም። (ዮሐ 18:15, 16) ጴጥሮስ ጨለማ ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ተደብቆ ከመቆም ይልቅ ሄዶ እሳት ይሞቅ ጀመር። በእሳቱ ብርሃን የተነሳ ሰዎች ጴጥሮስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን መለየት ቻሉ፤ የገሊላ ሰው መሆኑን የሚያሳውቀው አነጋገሩ ደግሞ ጥርጣሬያቸውን ይበልጥ አጠናከረላቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከአንዴም ሦስት ጊዜ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው ተናገረ፤ እንዲያውም የተናገረው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ራሱን ይረግም ጀመር። ወዲያው ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሲጮኽ ተሰማ፤ ኢየሱስም “ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው።” በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። (ማቴ 26:69-75፤ ማር 14:66-72፤ ሉቃስ 22:54-62፤ ዮሐ 18:17, 18፤ “COCKCROWING” እና “OATH” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ሆኖም ኢየሱስ ቀደም ሲል ጴጥሮስን አስመልክቶ ያቀረበው ጸሎት ምላሽ ስላገኘ የጴጥሮስ እምነት ሙሉ በሙሉ አልጠፋም።—ሉቃስ 22:31, 32
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 14:51, 52) ሆኖም እርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት በቅርብ ርቀት ይከተለው ጀመር፤ ሊይዙትም ሞከሩ፤ እሱ ግን በፍታውን ትቶ ራቁቱን አመለጠ።
የማርቆስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
14:51, 52—‘ዕራቁቱን የሸሸው’ ወጣት ማን ነው? ይህን ሁኔታ የጠቀሰው ማርቆስ ብቻ ስለሆነ ዕራቁቱን የሸሸው እሱ ራሱ ነው ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው።
(ማርቆስ 14:60-62) ከዚያም ሊቀ ካህናቱ በመካከላቸው ቆሞ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው። 61 እሱ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና “አንተ ብሩክ የሆነው አምላክ ልጅ ክርስቶስ ነህ?” እያለ ይጠይቀው ጀመር። 62 ኢየሱስም “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለ።
ኢየሱስ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ
ቀያፋ፣ ማንኛውም ሰው የአምላክ ልጅ እንደሆነ ቢናገር አይሁዳውያን በጣም እንደሚቆጡ ያውቃል። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ አምላክ አባቱ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ አይሁዶች ‘ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል እንዳደረገ’ በመግለጽ ሊገድሉት ፈልገው ነበር። (ዮሐንስ 5:17, 18፤ 10:31-39) ቀያፋ ይህን ስሜታቸውን ስለሚያውቅ “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” በማለት ተንኮል ያዘለ ጥያቄ አቀረበለት። (ማቴዎስ 26:63) ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተናግሮ ያውቃል። (ዮሐንስ 3:18፤ 5:25፤ 11:4) አሁን ይህን ባይናገር የአምላክ ልጅ እንዲሁም ክርስቶስ መሆኑን እንደ መካድ ሊቆጠር ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለ።—ማርቆስ 14:62
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 14:43-59) ወዲያውም ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 45 ይሁዳም በቀጥታ መጥቶ ወደ እሱ በመቅረብ “ረቢ!” ብሎ ሳመው። 46 ሰዎቹም ያዙት፤ ደግሞም አሰሩት። 47 ይሁን እንጂ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። 48 ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? 49 በየዕለቱ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ነበርኩ፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይሁንና ይህ የሆነው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” 50 በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ። 51 ሆኖም እርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት በቅርብ ርቀት ይከተለው ጀመር፤ ሊይዙትም ሞከሩ፤ 52 እሱ ግን በፍታውን ትቶ ራቁቱን አመለጠ። 53 ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍትም በሙሉ ተሰበሰቡ። 54 ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ተከተለው፤ ከዚያም ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ጀመር። 55 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የምሥክሮች ቃል እየፈለጉ ነበር፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም። 56 እርግጥ ብዙዎች በእሱ ላይ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፤ ሆኖም ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም። 57 አንዳንዶችም ተነስተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት ይመሠክሩበት ነበር፦ 58 “‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” 59 በዚህ ጉዳይም ቢሆን የምሥክርነት ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም።