ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
ኢየሱስ አምላክ የጠየቀውን ሁሉ ጨረሰ
ጦረኛው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንንና የእርሱን አመጸኛ ዓለም ሲያስወግድ ይህ ለመደሰት እንዴት ዓይነት ምክንያት ይሆናል! ሰላም የሰፈነበት የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት በመጨረሻው ይጀምራል!
በኢየሱስና በተባባሪ ነገሥታቱ አመራር ሥር የአርማጌዶን ተራፊዎች ያ የጽድቅ ጦርነት ያስከተለውን ፍርስራሽ ያጸዳሉ። ምድራዊ ተራፊዎችም ለጊዜው ልጆች ሳይወልዱ ስለማይቀሩ ምድርን ወደ ዕፁብ ድንቅ የመናፈሻ ዓይነት የአትክልት ሥፍራ በማልማቱ አስደሳች ሥራ እነርሱም ይካፈላሉ።
ውሎ አድሮም በዚህች ውብ ገነት እንዲደሰቱ ኢየሱስ ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን ሙታን ከመቃብራቸው ያወጣቸዋል። ይህንንም የሚያደርገው ራሱ “[በመታሰቢያ (አዓት)] መቃብር ያሉት ሁሉ . . . ይወጣሉ” ብሎ የሰጠውን ማረጋገጫ ለመፈጸም ነው።
ኢየሱስ ከሚያስነሣቸው መካከል በጎኑ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሞተው ክፉ አድራጊም ይገኝበታል። “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሲል ኢየሱስ ቃል እንደገባለት አስታውሱ። ያ ሰው ከኢየሱስ ጋር ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ወደ ሰማይ አይወሰድም። ወይም ደግሞ ኢየሱስ እንደገና ሰው ሆኖ ከእርሱ ጋር በምድራዊ ገነት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ከዚያ ከቀድሞው ክፉ አድራጊ ጋር ይሆናል ሲባል በገነት እንዲኖር ያስነሣውና በዚህ ገጽ ላይ በስዕል እንደተገለጸው አካላዊም ሆኑ መንፈሳዊ ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ያደርጋል ማለት ነው።
እስቲ አስበው! ኢየሱስ በሚሰጠው ፍቅራዊ ትኩረት ጠቅላላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ማለትም የአርማጌዶን ተራፊዎችና ልጆቻቸው እንዲሁም ለእርሱ ታዛዥ የሚሆኑት በሺህ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ትንሣኤ ያገኙ ሙታን ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ። ይሖዋ በንጉሣዊ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በመንፈስ ከሰዎች ጋር ይሆናል። ዮሐንስ ከሰማይ የሰማው ድምጽ እንደተናገረው “እንባዎችንም ከዓይኖቻቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ኀዘንም ቢሆን ወይም ሥቃይ ወይም ጩኸት ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” በምድር ላይ የሚሰቃይ ወይም የሚታመም ማንም ሰው አይገኝም።
በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ ሁኔታው አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት አዳምንና ሔዋንን እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሉአት በተናገራቸው ጊዜ እንደነበረው የመጀመሪያው ዓላማው ይሆናል። አዎ፤ ምድር ፍጹም በሆኑ ጻድቅ የሰው ዘሮች ትሞላለች። ይህም የሚሆነው የኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ጥቅሞች በሁሉም ሰው ላይ ስለሚሠሩ ነው። በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሞት አይኖርም።
ስለዚህ ኢየሱስ ይሖዋ እርሱ እንዲሠራው ጠይቆት የነበረውን ነገር ሁሉ ሠርቶ ይጨርሳል። በመሆኑም በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ መንግሥቱንና ፍጹም የተደረገውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለአባቱ ያስረክባል። ከዚያም አምላክ ሰይጣንንና አጋንንቱን እንደ በድን ሆነው ከማይንቀሳቀሱበት ሁኔታ ይለቃቸዋል። ለምን ዓላማ?
በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ በገነት ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እምነታቸው ተፈትኖ የማያውቅ ከሞት የተነሡ ይሆናሉ። ከመሞታቸው በፊት የአምላክን ዓላማዎች የማያውቁ ስለነበሩ በተስፋዎቹ ላይ እምነታቸውን ሊገልጹ አልቻሉም። ያኔ ከሞት ተነሥተው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማሩ በኋላ በገነት ውስጥ ምንም ተቃውሞ ሳያጋጥማቸው አምላክን ማገልገል ቀላል ነው። ግን ሰይጣን አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቋርጡ ለማድረግ እንዲሞክር ዕድል ቢሰጠው በፈተና ታማኝ ይሆናሉን? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት ሰይጣን ይፈታል።
ለዮሐንስ የተሰጠው ራእይ ከኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት በኋላ ሰይጣን ቁጥራቸው ያልተወሰነ ሕዝቦችን አምላክን ከማገልገል ዘወር ለማድረግ እንደሚሳካለት ያሳያል። ይሁን እንጂ የመጨረሻው ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ ሰይጣን፣ አጋንንቱና እርሱ ሊያሳስታቸው የቻለው በሙሉ ለዘላለም ይጠፋሉ። በሌላ በኩል ግን ተፈትነው የወጣላቸው ታማኞች የሰማዩ አባታቸውን በረከቶች በማግኘት ለዘላለም ዓለም በመኖር ይቀጥላሉ።
በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስ የአምላክን ታላላቅ ዓላማዎች ለማከናወን እጅግ አስፈላጊ ሥራ ሠርቷል፤ ገናም ይሠራል። በአምላክ የተሾመ ታላቅ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን በሚያከናውነው ነገር ሁሉ የተነሳ እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ይኖረናል! ሆኖም ሰው በነበረበት ጊዜ ያደረገውን ሁሉ ልንረሳው አንችልም።
ኢየሱስ በፈቃደኝነት ወደ ምድር መጥቶ ስለ አባቱ አስተምሮናል። ከዚህም በላይ የአምላክን ውድ ባሕርያት በአርዓያነቱ አንፀባርቋል። ልብን የሚማርክ ድፍረቱንና ጉብዝናውን፣ ተወዳዳሪ የሌለውን ጥበቡን፣ ግሩም የማስተማር ችሎታውን፣ ፍርሃት የለሽ አመራሩንና ከፍ ያለ የርኅራሄውንና ራሱን በተጨነቁ ሰዎች ቦታ በማስቀመጥ የሰው ችግር የሚሰማው መሆኑን ሁሉ በምናስብበት ጊዜ ልባችን ይነካል። ሕይወት ልናገኝ የምንችልበትን ብቸኛውን መንገድ ማለትም ቤዛውን ሲያቀርብ የደረሰበትን በቃል ሊገለጽ የማይችል ሥቃይ ስናስታውስ ልባችን ለእርሱ ባለን ጥልቅ አድናቆት ይነካል!
እውነትም በዚህ የኢየሱስ ሕይወት ጥናታችን ያየነው ምን ዓይነት ወንድ ነበር! ታላቅነቱ ግልጽ የሆነና አሌ የማይባል ነው። “እነሆ ሰውየው” ሲል ሮማዊው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የተናገራቸውን ቃላት እንድናስተጋባ እንገፋፋለን።
የቤዛዊ መስዋዕትነቱን ዝግጅቶች በመቀበል ከአዳም የተወረሰው የኃጢአትና የሞት ሸክም ሊወገድልን ይችላል። ኢየሱስም “የዘላለም አባታችን” ሊሆንልን ይችላል። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሁሉ ስለ አምላክ ብቻ ሳይሆን ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ጭምር ዕውቀት ማግኘት አለባቸው። የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎቱን የሚገልጹትን ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ማንበብህና ማጥናትህ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሰጭ እውቀት እንድታገኝ ረድቶሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። 1 ዮሐንስ 2:17፤ 1:7፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ 3:16፤ 17:3፤ 19:5፤ ሉቃስ 23:43፤ ዘፍጥረት 1:28፤ 1 ቆሮንቶስ 15:24-28፤ ራእይ 20:1-3, 6-10፤ 21:3, 4፤ ኢሳይያስ 9:6
◆ የአርማጌዶን ተራፊዎችና ልጆቻቸው ምን አስደሳች መብት ይኖራቸዋል?
◆ ከአርማጌዶን ተራፊዎችና ከልጆቻቸው ሌላ ገነትን የሚያገኙ እነማን ናቸው? ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር የሚሆነውስ በምን መንገድ ነው?
◆ በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ሁኔታው ምን ይሆናል? ኢየሱስስ ያኔ ምን ያደርጋል?
◆ ሰይጣን ከጥልቁ የሚፈታው ለምንድን ነው? እርሱና እርሱን የሚከተሉ ሁሉስ በመጨረሻው ምን ይሆናሉ?
◆ ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?