የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 42—ሉቃስ
ጸሐፊው:- ሉቃስ
የተጻፈበት ቦታ:- ቂሣርያ
ተጽፎ ያለቀው:- ከ56–58 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ3 ከክ.ል.በፊት እስከ 33 ከክ. ል. በኋላ
የሉቃስን ወንጌል የጻፈው፣ ንቁ አእምሮ ያለው ደግ ሰው ነው፤ እነዚህ ግሩም ባሕርያት የአምላክ መንፈስ ከሚሰጠው አመራር ጋር ተጣምረው ጸሐፊው ትክክለኛና ሕያው የሆነ ዘገባ እንዲያቀርብ አስችለውታል። በመግቢያው ላይ “እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ” ሲል ተናግሯል። ጸሐፊው በዝርዝርና በጥንቃቄ ያሰፈረው ይህ ዘገባ አባባሉ እውነት መሆኑን በሚገባ ያረጋግጣል።—ሉቃስ 1:3
2 በዚህ ወንጌል ውስጥ የሉቃስ ስም አንድም ቦታ ላይ ባይጠቀስም ጸሐፊው እሱ መሆኑን የጥንት ጸሐፊዎች ይስማማሉ። በሙራቶሪያን ቁርጥራጭ (170 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ላይ ወንጌሉን የጻፈው ሉቃስ እንደሆነ ከመጠቀሱም ሌላ እንደ ኢራንየስና የእስክንድርያው ክሌመንት ያሉ የሁለተኛው መቶ ዘመን ጸሐፊዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። በወንጌሉ ውስጥም ጸሐፊው ሉቃስ መሆኑን የሚጠቁሙ ጠንካራ ማስረጃዎች ይገኛሉ። ጳውሎስ፣ በቈላስይስ 4:14 ላይ “የተወደደው ሐኪሙ ሉቃስ” ብሎ የጠራው ሲሆን የወንጌሉ አጻጻፍም ቢሆን እንደ ዶክተር ያለ ምሑር እንዳዘጋጀው ያስታውቃል። ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈበት ቋንቋ ላቅ ያለ ደረጃ ያለው ከመሆኑም በላይ ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው ቃላት አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳ የማይተካከሏቸው ብዛት ያላቸው የተለያዩ ቃላትን ተጠቅሟል፤ ይህም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ርዕሰ ጉዳይ ጥንቃቄ በተሞላበትና ሰፋ ባለ መንገድ ለማስፈር አስችሎታል። አንዳንዶች፣ ሉቃስ ስለ አባካኙ ልጅ ያሰፈረው ዘገባ እስከ ዛሬ ድረስ ከተጻፉት አጫጭር ታሪኮች ሁሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት እንደሆነ ይናገራሉ።
3 ሉቃስ፣ ከ300 የሚበልጡ የሕክምና ስያሜዎችን ወይም ከሕክምና ጋር የተያያዘ ፍቺ የሰጣቸውን ቃላት ተጠቅሟል፤ ሌሎች የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች እነዚህን ቃላት (ለዚያውም ከተጠቀሙባቸው ነው) በዚህ መንገድ አልተገለገሉባቸውም።a ለምሳሌ ያህል፣ ሉቃስ ስለ ለምጽ በሽታ ሲናገር እንደ ሌሎቹ ጸሐፊዎች ሁልጊዜ ተመሳሳይ መግለጫ አልተጠቀምም። ለሌሎቹ ጸሐፊዎች ለምጽ፣ ለምጽ ነው፤ ሐኪሙ ሉቃስ ግን የለምጽ በሽታ የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ያውቅ ስለነበር “ለምጽ የወረሰው ሰው” የሚል መግለጫ ተጠቅሟል። ስለ አልዓዛር ሲናገርም “መላ ሰውነቱ በቊስል የተወረረ” እንደነበር ገልጿል። የጴጥሮስ አማች “ኀይለኛ ትኵሳት” ይዟት እንደነበር የገለጸ ሌላ የወንጌል ጸሐፊ የለም። (5:12፤ 16:20፤ 4:38) ሌሎቹ ሦስት የወንጌል ጸሐፊዎች ጴጥሮስ፣ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ እንደቆረጠው ቢነግሩንም ይህንን ሰው ኢየሱስ እንደፈወሰው የጠቀሰው ሉቃስ ብቻ ነው። (22:51) “የድካም መንፈስ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አካለ ስንኩል ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ከመጕበጧ የተነሣ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር” የሚል መግለጫ የሚሰጠው ዶክተር የሆነ ሰው ነው። ሳምራዊው፣ ለተጎዳው ሰው ስላደረገለት የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ሲገልጽ “ቍስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት” በማለት ዝርዝር ሁኔታውን ሊገልጽ የሚችለው ‘የተወደደው ሐኪም ሉቃስ’ ብቻ ነው።—13:11፤ 10:34
4 ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው መቼ ነው? በሐዋርያት ሥራ 1:1 ላይ የሚገኘው “ቀደም ባለው መጽሐፌ” የሚለው ሐሳብ እንደሚጠቁመው መጽሐፉን የጻፈው ሰው (ሉቃስ) ከዚያ በፊት ሌላ መጽሐፍ ማለትም ወንጌሉን ጽፏል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጠናቀቀው በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሆነ ይገመታል፤ በዚህ ጊዜ ሉቃስ፣ ለቄሣር ይግባኝ ለማለት በሮም ሆኖ ጉዳዩን ይጠባበቅ ከነበረው ከጳውሎስ ጋር ነበር። በመሆኑም ሉቃስ ይህን የወንጌል ዘገባ የጻፈው፣ ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ሲያጠናቅቅ ከፊልጵስዩስ አብሮት ከተመለሰ በኋላ ማለትም ከ56-58 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፤ ጳውሎስ ለቄሣር ይግባኝ ለማለት ወደ ሮም ከመወሰዱ በፊት በቂሣርያ ለሁለት ዓመታት እስር ቤት ቆይቷል። ሉቃስ በዚህ ወቅት በፓለስቲና ስለነበር የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት በተመለከተ ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ለመመርመር’ ጥሩ አጋጣሚ ነበረው። በመሆኑም የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው ከማርቆስ ወንጌል ቀድሞ ይመስላል።
5 እርግጥ ነው፣ ሉቃስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ስላልነበረና ምናልባትም አማኝ የሆነው ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ስለሚሆን በወንጌሉ ውስጥ ያሰፈራቸው ክንውኖች በሙሉ ሲፈጸሙ አልተመለከተም። ይሁን እንጂ ጳውሎስ በሚስዮናዊነት ሲያገለግል የቅርብ ወዳጁ ነበር። (2 ጢሞ. 4:11፤ ፊል. 24) በመሆኑም በሉቃስ 22:19, 20 እና በ1 ቆሮንቶስ 11:23-25 ላይ ስለ ጌታ እራት የሚገልጸውን የሉቃስንና የጳውሎስን ዘገባ በማወዳደር፣ ሉቃስ ለጻፈው መጽሐፍ ሐሳብ ያገኘው ከጳውሎስ እንደነበረ መመልከት ይቻላል። ሉቃስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የማቴዎስን ዘገባም አመሳክሮ ሊሆን ይችላል። ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ለመመርመር’ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች የተመለከቱ በርካታ ሰዎችን ለምሳሌ በሕይወት የነበሩትን ደቀ መዛሙርት እንዲሁም የኢየሱስን እናት ማርያምን በግል ቀርቦ ሊጠይቅ ይችል ነበር። አስተማማኝ የሆነ ዝርዝር ዘገባ ለማሰባሰብ ሲል ያልፈነቀለው ድንጋይ እንደማይኖር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
6 አራቱን የወንጌል ዘገባዎች ስንመረምር፣ ጸሐፊዎቹ አንዳቸው የሌላውን ትረካ እንዳልገለበጡ እንዲሁም ወንጌሎቻቸውን የጻፉበት ዓላማ ለዚህ በጣም አስፈላጊ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በርካታ ምሥክሮች እንዲኖሩ ለማድረግ ሲሉ እንዳልሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ሉቃስ ዘገባውን ያሰፈረው ለየት ባለ መንገድ ነው። በአጠቃላይ እሱ ከጻፈው ወንጌል ውስጥ 59 በመቶ የሚሆነው በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ አይገኝም። በሌሎች የወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ያልተጠቀሱ ቢያንስ ስድስት የሚያህሉ ተአምራትንና ከእነዚህ በእጥፍ የሚበልጡ ምሳሌዎችን መዝግቧል፤ ከወንጌሉ አንድ ሦስተኛውን በትረካ መልክ ያቀረበው ሲሆን ሁለት ሦስተኛ በሚሆነው ላይ ደግሞ ሌሎች የተናገሩትን በቀጥታ አስቀምጦታል። ከአራቱም ወንጌሎች ረጅሙ የሉቃስ ወንጌል ነው። ማቴዎስ ወንጌሉን በዋነኝነት የጻፈው ለአይሁዳውያን ሲሆን ማርቆስ ደግሞ አይሁዳውያን ላልሆኑ አንባቢዎች በተለይም ለሮማውያን ነበር። የሉቃስ ወንጌል ግን የተጻፈው ‘ለክቡር ቴዎፍሎስ’ ሲሆን በእሱ አማካኝነት ለሌሎችም ማለትም ለአይሁዶችና አይሁዳዊ ላልሆኑ ሰዎች እንዲደርስ ታስቦ ነው። (ሉቃስ 1:3, 4) ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው በዋነኝነት ለአይሁዳውያን በመሆኑ የኢየሱስን የዘር ሐረግ የዘረዘረው እስከ አብርሃም ድረስ ብቻ ሲሆን ሉቃስ ግን ወንጌሉ ሁሉንም ሰው የሚማርክ እንዲሆን ሲል የኢየሱስን የዘር ሐረግ እስከ ‘እግዚአብሔር ልጅ፣ እስከ አዳም’ ድረስ አስፍሮታል። በተለይም በኢየሱስ በኩል ‘አሕዛብ መገለጥ እንደሚሰጣቸው’ እንዲሁም ‘የሰው ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን እንደሚያይ’ ስምዖን የተናገረውን ትንቢት ትኩረት ሰጥቶ አስፍሮታል።—3:38፤ 2:29-32፤ 3:6
7 ወንጌሉ በአጠቃላይ እንደሚያሳየው ሉቃስ የተዋጣለት ተራኪ ከመሆኑም በላይ ዘገባው በሚገባ የተደራጀና ትክክለኛ ነው። በሉቃስ ጽሑፎች ላይ የተንጸባረቀው ትክክለኛነትና ታማኝነት የጽሑፉን እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። በአንድ ወቅት አንድ የሕግ ሰው እንዲህ ብለው ነበር:- “ስለ ፍቅር የተጻፉ ልብ ወለድ መጻሕፍት፣ አፈ ታሪኮችና የሐሰት ማስረጃዎች የሚያወሱት ታሪክ በጣም ሩቅ በሆነ ሥፍራ እንዲሁም በውል በማይታወቅ ዘመን ላይ የተፈጸመ እንደሆነ ይገልጻሉ፤ ይህ ደግሞ እኛ የሕግ ሰዎች ጥሩ አድርጎ ሐሳብን መግለጽን በተመለከተ የምንማረውን የመጀመሪያውን ደንብ ይኸውም ‘አንድ ሰው የሚሰጠው ቃል፣ ጊዜውንና ቦታውን የሚገልጽ መሆን አለበት’ የሚለውን መመሪያ ይጥሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ግን የተጠቀሱት ክንውኖች የተፈጸሙበትን ጊዜና ቦታ በትክክል ይገልጹልናል።”b እኚህ ሰው ሉቃስ 3:1, 2ን ለዚህ እንደ ማስረጃ አድርገው ጠቅሰዋል:- “ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።” እዚህ ዘገባ ላይ ጊዜን ወይም ቦታን በሚመለከት ሳይጠቀስ የቀረ ነገር የለም፤ ይልቁንም ሉቃስ ዮሐንስና ኢየሱስ አገልግሎት የጀመሩበትን ጊዜ ለይተን ማወቅ እንድንችል ከሰባት የማያንሱ የሕዝብ ባለ ሥልጣናትን ጠቅሶልናል።
8 በተጨማሪም ሉቃስ በምዕራፍ 2:1, 2 ላይ “በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር” ብሎ ሲጽፍ ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ የሚጠቁሙ ሁለት ፍንጮችን ሰጥቶናል። ዮሴፍና ማርያም ለመመዝገብ ወደ ቤተ ልሔም የሄዱት በዚህ ጊዜ ሲሆን ኢየሱስም የተወለደው እዚያው እያሉ ነበር።c “ሉቃስ እውነተኛ ታሪክ ጸሐፊ መሆኑን ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች አንዱ ምንጊዜም ቢሆን ፍጹም ትክክለኛ የሆነ መረጃ የሚያቀርብ መሆኑ ነው” በማለት ከተናገሩት ተንታኝ ጋር ከመስማማት ሌላ ምን እንላለን?d ሉቃስ “ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ [እንደመረመረ]” መግለጹ ትክክል መሆኑን አምነን ለመቀበል እንገደዳለን።
9 ሉቃስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዴት በትክክል ፍጻሜያቸውን እንዳገኙም ጠቁሟል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ በመንፈስ አነሳሽነት የሰጠውንም ምሥክርነት ጠቅሷል። (24:27, 44) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ነገሮች የተናገራቸውን ትንቢቶች በትክክል መዝግቧል፤ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በሚያስደንቅ ሁኔታ በዝርዝር ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ቅጥር ተሠርቶ ከተከበበች በኋላ አሰቃቂ የሆነ እልቂት ደርሶባታል። (ሉቃስ 19:43, 44፤ 21:20-24፤ ማቴ. 24:2) ከሮማውያን ሠራዊት ጋር የነበረውና የተፈጸመውን ክንውን በዓይኑ የተመለከተው ታሪክ ጸሐፊው ፍላቭየስ ጆሴፈስ እንደገለጸው ሮማውያን ከተማዋን የሚከቡበት እንጨት ለማግኘት ሲሉ ወደ ገጠሩ ክፍል ዘልቀው እስከ 16 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙ ዛፎችን መንጥረው ነበር፤ ከዚህም በላይ ወታደሮቹ በከተማዋ ዙሪያ 7.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ቅጥር እንደሠሩ፣ ብዙ ሴቶችና ሕፃናት በረሃብ እንዳለቁና ከ1,000,000 በላይ አይሁዳውያን ሕይወታቸውን እንዳጡ እንዲሁም 97,000 የሚያህሉ በምርኮ እንደተወሰዱ ጆሴፈስ ጽፏል። እስከ ዛሬም ድረስ በሮም ከተማ የሚገኘው የቲቶ ቅስት፣ ሮማውያን ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በጦርነት የማረኳቸውን ነገሮች ይዘው የድል ሰልፍ ሲያደርጉ ያሳያል።e ሉቃስ በመንፈስ አነሳሽነት የመዘገባቸው ሌሎቹ ትንቢቶችም እንደዚሁ በትክክል እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
30 “የሉቃስ ወንጌል” መጻተኛ ሆነን የምንኖርበት ዓለም የሚሰነዝርብንን ጥቃት ለመቋቋም እንድንችል በአምላክ ቃል ይበልጥ እንድንተማመንና እምነታችን እንዲጠናከር ይረዳናል። ሉቃስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ ፍጻሜ እንዳገኙ የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን ጠቅሷል። ኢየሱስ ከኢሳይያስ መጽሐፍ በቀጥታ በመጥቀስ ተልእኮውን መግለጹ የተካተተ ሲሆን ሉቃስም ይህንን ጥቅስ ለመላው መጽሐፉ ጭብጥ አድርጎ የተጠቀመበት ይመስላል። (ሉቃስ 4:17-19፤ ኢሳ. 61:1, 2) ይህ ኢየሱስ ከነቢያት መጻሕፍት ከጠቀሰባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነው። ዲያብሎስ ያቀረበለትን ሦስት ፈተናዎች በተቃወመበት ጊዜ እንዳደረገው ከሕግም ይጠቅስ ነበር፤ እንዲሁም ባላጋራዎቹን “ሰዎች ክርስቶስን እንዴት የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ከመዝሙራት ጠቅሷል። የሉቃስ ወንጌል ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ሌሎች ብዙ ጥቅሶችንም ይዟል።—ሉቃስ 4:4, 8, 12፤ 20:41-44፤ ዘዳ. 8:3፤ 6:13, 16፤ መዝ. 110:1
31 ኢየሱስ በዘካርያስ 9:9 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በዚያ የነበሩት ብዙ ሰዎች መዝሙር 118:26 በእሱ ላይ እንደተፈጸመ በመግለጽ በደስታ ተቀብለውታል። (ሉቃስ 19:35-38) ኢየሱስ ነቀፋ በሚያስከትል መንገድ እንደሚገደልና በኋላም ትንሣኤ እንደሚያገኝ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በትንቢት የተነገሩት ስድስት ነጥቦች በሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ በሁለት ቁጥሮች ተጠቃልለው ተቀምጠዋል። (ሉቃስ 18:32, 33፤ መዝ. 22:7፤ ኢሳ. 50:6፤ 53:5-7፤ ዮናስ 1:17) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም የጠቅላላውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቀሜታ ለደቀ መዛሙርቱ ጠበቅ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “‘ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል” ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው’ አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:44, 45) እንደ መጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እኛም ሉቃስና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ሌሎች ሰዎች በትክክል ያብራሩትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ፍጻሜ በትኩረት መከታተላችን ተጨማሪ እውቀት እንድናገኝና እምነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል።
32 የሉቃስ ወንጌል ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ አንባቢዎቹ በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። መልአኩ፣ ማርያም የምትወልደው ልጅ ‘በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም እንደሚነግሥና ለመንግሥቱም ፍጻሜ እንደማይኖረው’ ከተናገረበት ከመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል አንስቶ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንደሚገባ ወይም እንደሚሾማቸው እስከገለጸባቸው የመደምደሚያ ምዕራፎች ድረስ ሉቃስ የመንግሥቱን ተስፋ ጎላ አድርጎ ጠቅሷል። (1:33፤ 22:28, 29) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዳገለገለ እንዲሁም 12 ሐዋርያቱና በኋላ ላይ ደግሞ 70 ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ ሥራ እንዲሠሩ እንደላካቸው ተናግሯል። (4:43፤ 9:1, 2፤ 10:1, 8, 9) “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” እንዲሁም “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” የሚለው የኢየሱስ ቀጥተኛ ንግግር ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ልባችን ሳይከፋፈል ለአምላክ የማደርን አስፈላጊነት ያጎላል።—9:60, 62
33 ሉቃስ ስለ ጸሎትም አበክሮ ገልጿል። በዚህ ረገድ የሉቃስ ወንጌል ጎላ ብሎ ይታያል። ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በርካታ ሰዎች ይጸልዩ እንደነበር፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ወላጆች ልጅ ለማግኘት ያቀረቡት ጸሎት መልስ እንዳገኘ እንዲሁም ነቢይቱ ሐና ሌት ተቀን ትጸልይ እንደነበር ይናገራል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሲጠመቅ እንደጸለየ፣ 12 ሐዋርያቱን ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ እንዳደረና በተአምራዊ መንገድ በተለወጠበት ጊዜ ስላቀረበው ጸሎት ተገልጿል። ኢየሱስ፣ አንድ ዳኛ እስኪፈርድላት ድረስ ትነዘንዘው ስለነበረች መበለት ምሳሌ በመናገር ደቀ መዛሙርቱ “ሳይታክቱ ሁልጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው” አሳስቧል። ደቀ መዛሙርቱ እንዴት መጸለይ እንደሚችሉ እንዲያስተምራቸው ለኢየሱስ ያቀረቡትን ጥያቄና ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሲጸልይ መልአክ መጥቶ እንዳበረታው የጠቀሰው ሉቃስ ብቻ ነው፤ ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ሊሞት ሲል ባቀረበው ጸሎት ላይ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ!” እንዳለ የዘገበው ሉቃስ ብቻ ነው። (1:10, 13፤ 2:37፤ 3:21፤ 6:12፤ 9:28, 29፤ 18:1-8፤ 11:1፤ 22:39-46፤ 23:46) ሉቃስ ወንጌሉን በጻፈበት ጊዜ ከነበረው ባልተለየ መንገድ ዛሬም ጸሎት፣ መለኮታዊውን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ብርታት እንዲያገኙ የሚረዳ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዝግጅት ነው።
34 ንቁና አስተዋይ አእምሮ ያለው ሉቃስ በተባ ብዕሩ አማካኝነት ለኢየሱስ ትምህርት ሕይወት ሰጥቶታል። ኢየሱስ ለደካሞች፣ ለተጨቆኑና መንፈሳቸው ለተሰበረ ሰዎች ያሳየውን ፍቅር፣ ደግነት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ደንታቢስ የሆነ፣ በደንብ ላይ ያተኮረ፣ ጠባብና ግብዝ ሃይማኖት ጋር በማነፃፀር ልዩነቱን ቁልጭ አድርጎ ገልጿል። (4:18፤ 18:9) ኢየሱስ ለድሆች፣ ለታሠሩ፣ ማየት ለተሳናቸው እንዲሁም ለተጨቆኑ ሰዎች ያላሰለሰ ማበረታቻና እርዳታ በመስጠት ‘ፈለጉን ለመከተል’ ለሚጥሩ ሁሉ ግሩም ምሳሌ ትቷል።—1 ጴጥ. 2:21
35 ፍጹም የሆነውና ድንቅ ሥራዎችን ያከናወነው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳሳየ ሁሉ እኛም አገልግሎታችንን በፍቅር፣ አዎን ‘ከአምላካችን በጎ ምሕረት የተነሣ’ ለማከናወን መጣር ይገባናል። (ሉቃስ 1:78) ይህንንም ለማድረግ “የሉቃስ ወንጌል” በጣም ጠቃሚ ነው። ‘የተወደደው ሐኪም’ ሉቃስ ይህንን ትክክለኛ፣ የሚያንጽና የሚያበረታታ እንዲሁም ‘የእግዚአብሔር ማዳን’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ስለሚገኘው መዳን የሚገልጽ ዘገባ እንዲጽፍ ይሖዋ በመንፈሱ ስላነሳሳው እጅግ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል።—ቈላ. 4:14፤ ሉቃስ 3:6
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ሜዲካል ላንጉጅ ኦቭ ሉክ፣ 1954 ደብልዩ ኬ ሆበርት፣ ገጽ xi-xxviii
b ኤ ሎውየር ኤግዛምንስ ዘ ባይብል፣ 1943 አይ ኤች ሊንተን፣ ገጽ 38
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 766-767
d ሞደርን ዲስከቨሪ ኤንድ ዘ ባይብል፣ 1955 ኤ ሬንደል ሾርት ገጽ 211
e ዘ ጂዊሽ ዎር፣ V, 491-515, 523 (xii, 1-4)፤ VI, 420 (ix, 3)፤ በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 751-752 ተመልከት።